ሰውና የ“ከ− እስከ” ጉዞው

ወደ መጣሁባት ምድር፣

እስክመለስባት በክብር፤

ሰውን ከማስደሰት በቀር፣

አይወጣኝም ክፉ ነገር።

(ተወዳጇ ድምፃዊት ብዙነሽ በቀለ)

መጽሐፉ የሰውን ልጅ የ“ከ— እስከ” ጉዞ በግልጽ ሲያስቀምጥ “አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ” በማለት ነው። ይህ ማለት ግን እርስ በርስህ ተላለቅ፤ በወንድምህ ላይ ዝመት፣ ዘገር ነቅንቅ” ∙ ∙ ∙ ማለት አይደለም፤ ፈፅሞም እንደሱ ማለት አይደለም።

ዛሬ ስለ ሰው ልጅ ጉዞ፣ እየሄደበት ስላለው መንገድ፣ እየረገጠው ስላለው ∙ ∙ ∙ እንነጋገር ዘንድ ምርጫችን ያደረግነው በወቅታዊው የዓለማችን ሁኔታ ሲሆን” በተለይም ሰሞኑን በእስራኤልና ሀማስ ጦርነት ንፁሃን ላይ የወረደው ያልተጠበቀ ውርጅብኝ ነው። ስለ እስራኤልና ሀማስ/ጋዛ ጉዳይ እናወራለን ማለት ግን አይደለም። የምናወራው ጠቅለል አድርገን “ሰው” ስለተባለው ፍጡር ነው። አዎ “ሰው” ስለተባለው ∙ ∙ ∙። በፈጣሪ አምሳል ስለተፈጠረው ሰው። (“እግዚአብሔርም አለ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌያችን እንፍጠር፣ የባህር ዓሳዎችንና የሰማይ ወፎችን፣ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፣ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትን ሁሉ ይግዛ፡፡ እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፣ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው” ዘፍ 1፡2627፡፡)

መቼም ከላይ የጠቀስነው የብዙነሽ ዜማ ከመጽሐፍ ቅዱስ አይቀድምምና ዜማው መጽሐፍ ቅዱስን መነሻው እንዳደረገ፤ በምንጭነት እንደተጠቀመው፣ “ዋቢዬ”ባይለውም ዋቢው ስለመሆኑ በሙሉ ድምፅ መስማማት ይቻላል። በመሆኑም ሁለቱን በመሳነት ማስኬድ ይቻላል ማለት ይሆናል። እንዲሁም፣ ካስፈለገ “ክብር ለሚገባው ክብር እንስጥ” (ይህ አገላለፅ መሰረቱ መጽሐፍ ቅዱስ (ሮሜ 13፡7) መሆኑን ልብ ይሏል) የምትባልና በአንድ ወቅት የአንድ ኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያ መርህ የነበረችውን፤ እንዲሁም የእጅጋየሁ ሽባባው(ጂጂን)፦

የሰው ልጅ ክቡር

ሰው መሆን ክቡር

ሰው ሞቷል – ሰው ሊያድን፣

ሰውን ሲያከብር

በደግነት፣ በፍቅር፣ በክብር ተጠርቶ፣

በክብር ይሄዳል፣ ሰው ሊኖር – ሰው ሞቶ፤

ጨምሮ እየተነጋገርንበት ስላለው ጉዳይ የኋላ ደጀን ማስከተል ይቻላል። (ጋዜጣ ሆነ እንጂ፣ ጥቁር ሰሌዳ ላይ ቢሆን ኖሮ “የብዙዬንና የጂጂን ግጥሞች አንድነትና ልዩነት ፈልግ”ብሎ የክፍል ሥራ መስጠት ይቻል ነበር።)

ልክ እየተግባባንበት እንዳለው ቋንቋ ሁሉ (የ“ሪፖርተር” አምደኛ የሆኑት ታከለ ታደሰ (ዶ/ር) “የኢትዮጵያ ቁልፍ ችግር” በሚል ርእስ ባሰፈሩት ጥናት አከል ሙያዊ ጽሑፍ እንዳስቀመጡት ከሆነ የኢትዮጵያ ቁልፉ ችግር ቋንቋ ከማህበረሰብ ጋር ያለውን ግንኙነት የሚመለከተው፣ የማህበራዊ ሥነልሳን (Sociolin­guistics) ነው – መናናቅ፣ አንዱ አንዱን ዝቅ አድርጎ ማየት፣ የንግግር ብልግና እና ሌሎች በርካቶች)፣ የሰውን ልጅ “መወለድ”፣ “ማደግ” እና “መሞት” የተረዳው “ወደ መጣሁበት ምድር” ስንኝ ሰው ከአፈር መምጣቱን ሲያስረግጥ (“አፈር”ና “ምድር” የተለያዩ ናቸው ካልተባለ በስተቀር)፣ ለ“አፈር ነህና”ም እጁን ሰጥቶ እናገኘዋለን። “እስክመለስባት”ም በቀጥታ የተወሰደ ሆኖ የምናገኘው ሲሆን፤ ልዩነቱ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልፅ ያልተቀመጠው፤ ነገር ግን በስንኙ ውስጥ “በክብር” ተብሎ የተገለፀው የሰው ልጅ የ“ከ- እስከ”የሕይወት ሙሉ ጉዞ ነው።

በታላቁ መጽሐፍ “ትመለሳለህ” ሆኖ በትእዛዛዊ ቃል ይቀመጥ እንጂ “መመለስ”ከ“ጉዞ” ጋር አንድ አካልና አንድ አምሳል ናቸው። አሁንም ልዩነት አላቸው ከተባለ የባህርይው ሆኖ መጽሐፉ በጥቅል ያስቀመጠውን (በአንድምታ አይተረጎምም ማለታችን አይደለም) የብዙዬ ዜማ “በክብር” ማለቱ ነው። አዎ፣ እንደ ብዙነሽ ዜማ የሰው ልጅ ወደ መጣበት የመመለሱ ጉዳይ አይቀሬ ከሆነ፤ የመመለሱ ጉዳይ በነውር ታጥሮ፣ በነውር ሰክሮ፣ በሀጢያት ተጨማልቆ፣ ከፈሪሀ ፈጣሪ ርቆ ∙ ∙ ∙ ሳይሆን፤ መሆን ያለበት ከእነዚህ ሁሉ ፅድት ብሎ፣ እንዳማረበት በክብር ነው።

ብዙዬ እንደ ዋዛ “ክብር” ያለችውን መሰረታዊ ጉዳይ በተመለከተ ሊነሱ የሚገባቸው ጥያቄዎች ቢኖሩ “ይህ ክብር እንዴት ይገኛል፣ ከወዴት ይገኛል፤ በቀላሉስ ይገኛልን???” የሚሉትና የመሳሰሉት ሲሆኑ፣ ለምላሻቸውም ወደ የትም ከመሄድ በፊት እዚሁ ብዙነሽ በቀለ ዜማ ላይ በመብሰልሰል (ሜዲቴት በማድረግ) ምላሹን ማግኘት የሚቻል ሆኖ፤ የተገኘውን ምላሽ ለማጠናከር፣ ማደንደንና ማወፈር ሲባል ከሌሎች ምንጮች ተጨማሪ መረጃዎችን መፈለግ ይቻላል።

እዚህ ጋ በክብር ወደ’ዚህ ምድር መጥታ፣ በክብር ተመልሳ ወደ መጣችበት ከሄደችው፣ ከብዙዬ ዜማ “በክብር” ለመመለስ የሚያስፈልገው መሰረታዊ ጉዳይ በዋናነት አንድ ሲሆን፤ እሱም፦

ሰውን ከማስደሰት በቀር፣

አይወጣኝም ክፉ ነገር።

የሚለው ነው (ወይም ይሆናል)።

“ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ” (መዝ 19፥1) (እዚህ ጋ ሁለንታ (universe) የሚለውን እሳቤ ማሰላሰል ይገባል።)፤ ጆን ፓይፐር እንደ ጻፉትና አማረ ታቦር የተባሉ ሰው እንደ ተረጎሙት “ይህ የተፈጠረ ሁለንታ ምክንያቱ ለክብር ነው። የሰው ልጆች ልብ ውስጣዊ ምኞትና የሰማይ የምድር ውስጣዊ ምንነት በሚከተለው ሐረግ ሊጠቀለል ይችላል። ሁለንታ የተፈጠረው ይህንን ለማሳየት ነው፤ የእኛም ህልውና ይህንኑ ለማየትና ለመጠማት ነው። ከዚህ ያነሰው ረብ የሌለው ይሆናል። ዓለም ሥርዓት የለሽና ተግባረ ቢስ የሆነችውም በዚህ ሳቢያ ነው። የእግዚአብሔርን ክብር በሌላ ለውጠነዋል (ሮሜ 1፥23)። እዚህ ላይ “ዓለም ሥርዓት የለሽና ተግባረ ቢስ የሆነችውም በዚህ ሳቢያ ነው።” የሚለውን ከስሩ አስምረንበት ብናልፍ የሚያመልጠን ነገር የለምና እናድርገው።

(ካስፈለገም፣ ኢሳይያስ 43፥6-7፣ ሮሜ 9፥23፣ ሮሜ 5፥2፣ ዮሐንስ 17፥24 …ወዘተርፈ በመመልከት ከጸሐፊውም ሆነ ከተርጓሚው፤ እንዲሁም ከራሳችን ጋር መግባባት ባይቻል እንኳን በጉዳዩ ላይ መብሰልሰል ይቻላል።) ይህንን ስንል “ከማንም በላይ ክብር ሊሰጠው የሚገባ እግዚአብሔር ነው” የሚለውን ዘንግተን እንዳልሆነ ሊታወቅልን ይገባል።

አሁንም ከዚሁ ከብዙዬ ስንኞች ከተገኘው መልስ ተነስቶ ሊነሳ የሚችል አቢይ ጥያቄ ሊኖር የሚችል ሲሆን፣ እሱም “ሰውን ማስደሰት እንዴት ይቻላል፣ ክፉ ነገርንስ ከአፍ ሳያወጡ እንዴት መኖር ይቻላል???” የሚለው ይሆናል። ለተሟላም ባይሆን ለከፊል ምላሹ ሙሉ የብዙዬን ዜማ ማዳመጡ (“መስማት”አልተባለም) ተገቢ መሆኑን እየጠቆምን መቻል አለመቻሉን እንመልከት።

እርግጥ ነው፣ “ክፉ ነገር ከአፍ ሳይወጣ መኖር ይቻላል ወይ? የሚለው ተወደደም ተጠላ ከዲያቢሎስ በስተቀር ክፉ ነገር ከአፍ ይወጣ ዘንድ የሚፈቅድ አንድም አካል እስከ ዛሬ አልተገኘም። ይልቁንም – ባፍ ይጠፉ በለፈለፉ፤ አፍና ቅብቅብ ሁል ጊዜ አያበላም፤ ካፍ የወጣ አፋፍ ../”እና ሌሎችም ስነቃላዊ እሴቶቻችን የሚነግሩን ይህንን የብዙዬን “አይወጣኝም ክፉ ነገርን ነው። (እዚህ ላይ እየተነጋገርንብት ያለው ጉዳይ ከዝምታ ጋር እንደማይገናኝ ልብ ማለት ይገባል።)

ርእሳችን “ሰውና የ‘ከ— እስከ’ ጉዞው” (ከልደት እስከ ሞት) ሲሆን፣ ርእሰ ጉዳያችንም እንደ ረጅም ልቦለድ (ለምሳሌ፣ ፍቅር እስከ መቃብር) ከዚሁ ማእቀፍ ውስጥ ሊወጣ የሚችል አይደለም። በመሆኑም ከበደ ሚካኤል፦

ጽድቅና ኩነኔ ቢኖርም ባይኖርም፣

ከክፋት ደግነት ሳይሻል አይቀርም።

እንዳሉትም ሆነ፣ ፈሪሀ ፈጣሪ ያደረባት ብዙዬ “አይወጣኝም ክፉ ነገር” እንዳለችው ፅድቅ ኖረም አልኖርም፤ ሃይማኖት ኖረንም አልኖረንም ∙ ∙ ∙ ሰውን ከሰው የሚያኖረው ደግነት እንጂ ክፋት አይደለም። “ቅንነት ለራስ ነው” ይሉ አባባል የሚዘወተረው ለሌሎች ቅን በሆንን ቁጥር ለእኛም ቅን የሚሆኑ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አለመሄዱን ታሳቢ ያደረገ ሰብአዊ አገላለፅ ነው።

አንዳንድ ሰዎች እንደሚሉት፣ እኛም ባቅማችን እንደምናብሰለስለው፣ ዘመኑ ከእነዚህ፣ ከላይ ስንላቸው እዚህ ከደረስናቸው ሁሉ የተለየ፣ ከሁሉም የተጣላና የሰው ልጅ የአውሬ ጠባይን ያህል እንኳን እያጣ የመጣበት መሆኑ ነው። የሥነ ልቡና ጉዳይ ዘልቆ የገባቸው ሰዎች ሲሉ እንደሚሰማው የዱር አውሬ የራሱ ቤተሰብ የሆነን የዱር አውሬ (ለምሳሌ ነብር ነብር)ን አያሰቃይም፣ ለጠላት አሳልፎ አይሰጥም፤ ባጭሩ፣ ነብር ነብርን አይገድልም። ተባብሮ፣ ተረባርቦ፣ ተጋግዞ ∙ ∙ ∙ እራሱንና ቤተሰቡን ከጠላት ይከላከላል እንጂ እርስ በእርሱ በጭካኔ አይጠፋፋም። በአሁኑ ዘመን ይህ እየታየ ያለው በሰው ልጅ ዘንድ ብቻ ነው።

በዛሬዋ ዓለማችን እዚህም እዛም እየታየና እየተሰማ ያለው የድምፃዊት ብዙነሽ በቀለ፦

ወደ መጣሁባት ምድር፣

እስክመለስባት በክብር፤

ሰውን ከማስደሰት በቀር፣

አይወጣኝም ክፉ ነገር።

ሳይሆን፤ በተቃራኒው ግደል፣ ዝረፍ፣ አቃጥል፣ አውድም፣ አዋርድ፣ ክብር ለሚገባው ክብር አትስጥ፣ ወደ መጣህበት በክብር መመለስም ሆነ አለመመለስን ማሰብ ያንተ ሥራ አይደለም፤ እንደዚህ የሚሉትንም አትመናቸው፤ በገጀራ (አንገቱን) በለው ∙ ∙ ∙ ወዘተ ወዘተ ነው።

ብዙነሽ “አይወጣኝም ክፉ ነገር” ትበል እንጂ፣ በአሁኒቱ ዓለማችን አየሩ በሙሉ የተጨናነቀው በጥላቻ ንግግር ነው። የሀሰት ትርክት እንደ ሰው በአካል ቆሞ ሲሄድ እየታየ ነው።

የዛሬዋ ዓለማችን በሀሰት ትርክት (ታሪክ ነገራ) ከዳር እስከ ዳር የተጥለቀለቀችበት፤ አንዱ ባንዱ ሲዝት ጀንበር የምትጠልቅበት፤ አንዱ አንዱን ሊገድል ገጀራ የሚስልበት ወዘተርፈ ሲሆን፤ ለዚህም የሰሞኑና ምንም ሳይታሰብ ድንገት የንፁሐን እስራኤላዊያንን ሕይወት የቀጠፈው የጋዛው ሀማስ ሰይፍ ነው። ከእስራኤል እየተሰጠ ያለው አፀፋም ቢሆን የንፁሐን አንገት ላይ ከማረፍ ወደ ኋላ አላለም።

ዘመናችን ወደ መጣንበት በክብር ለመመለስ የምንመኝበት ሊሆን ቀርቶ ከየት እንደ መጣን እንኳን የማናውቅበት ድንዛዜ ውስጥ ያለንበት ነው።

ዘመናችን “አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ” የሚለውን ከነጭራሹ የሚያውቅ ሁሉ አይመስልም። እራሱ ዘመኑ በእኛ ምክንያት “አብዷል”። “አይፈረድበትም” የሚሉ ወገኖች “ትክክል ናቸው” እስኪባል ድረስ አብዷል፤ ከራማው ተገፏል ማለት ይቻላል። ሶሪያዊያን ቢጠየቁ ከዚህ ውጪ ምን ሊመልሱ እንደሚችሉ ለመናገር ያስቸግራል። ሊቢያዊያንም ቢሆኑ ከሶሪያዊያን ምን እንደሚለያቸው ለመናገር አንደበት ያላቸው አይመስሉም፡፡ ደቡብ ሱዳን – ተመሳሳይ።

ጋዛና አካባቢው ላይ ሰሞኑን እየፈሰሰ ያለው ደምና እየተከሰከሰ ያለው አጥንት እየተፈፀመ ያለው “አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህን” በራሱ፤ ወይም፣ መኖሩንም በማያውቁ ሰዎች አንጎል እና እጅ ነው። በአፍጋኒስታንም እንደዛው።

ወደ መጣሁባት ምድር፣

እስክመለስባት በክብር፤

ሰውን ከማስደሰት በቀር፣

አይወጣኝም ክፉ ነገር።

በማለት፣ ከአንደበቷ እንኳን ክፉ እንዳይወጣ የመጠንቀቋን ያህል ዛሬ ሰው አውሬ እማያደርገው ተግባር መፈፀም ላይ ሲተጋ ይታያል። የሰው ልጅ ከአፈር እንደ መፈጠሩ ሁሉ በክብር ተመልሶ ወደ አፈር ያለመሄዱ ጉዳይ አሻሚ ባልሆነ መልኩ እየታየ ይገኛል።

በተለያዩ ሃይማኖቶች ተከታዮች ዘንድ “የመጨረሻው ዘመን” መምጣት እየተቃረበ እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲነገር ይሰማል። በተለይ በፈረንጆቹ አካባቢ በ“ዘ ኢንድ ኦፍ …”፤ “ኢንድ ታይም ፕሮፌሲ” እና በመሳሰሉ ርእሶች የተሰየሙ ድርሳናት ለአደባባይ እየበቁ ነው።

ዓለም ስጋት በስጋት ከሆነች ቆየች። መጽሐፉ (ለምሳሌ ዘፀአ.20፥ 12 (1 ኔፊ 17፥55) “አባትና እናትህን አክብር” ይበል እንጂ ያለው ሁኔታ የተገላቢጦሽ ይመስላል። ቃሉ (ዘህልቁ ምዕ∙2) እየተፈፀመ ያለ ያህል እስኪመስል ድረስ መጨራረስ የትጉሀን ተግባር እየሆነ ነው።

አዲስ የዓለም ሥርዓት (NWO) እየተባለ ከበሮ መመታት፣ በገና መጎሰም ከተጀመረ ቆየ። እንደ አንዳንዶች “የዋህ” አተያይ ከሆነ ይህ ለዓለምና ህዝቦቿ መርዶ እንጂ ብስራት ይዞ የሚመጣ ጉዳይ አደለም። መፍትሄው ወደ አውሬ ባህርይነት መመለስ ነው ባይ ናቸው። መፍትሄው ሁሉም የብዙዬን “ወደ መጣሁበት ምድር” በጋራ ማዜም ይገባዋል ነው የሚባለው።

በመጨረሻም፣ ሰውን በአምሳሉ የፈጠረው ፈጣሪ እንዲወለድ፣ ጥሮ ግሮ በወዙ፣ በላቡ እንዲኖር፣ ወንድሙን እንደ ራሱ እንዲወድ፣ ተፈጥሮን ያለ ምንም ገደብ እንዲጠቀም፣ ታላላቆቹን እንዲያከብር፣ እንዲማር፣ እንዲመራመር፣ ጭንቅላቱን ለተሻለ ነገ እንዲጠቀም፤ የፍጥረታት ሁሉ ገዥ እንዲሆን፤ በመጨረሻም “አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ” ባለው መሰረት እንዲሆንና ነፍሱ በገነት እንድትኖር እንጂ፤ እንዲህ እንደሚታየው እርስ በርሱ እንዲተላለቅ አልነበረም። “የማን ቤት ፈርሶ …” እንዳለው ባለ ቀረርቶ ዓለምን ያውሬ መውለጃ ትሆን ዘንድ እንዲያመቻች አይደለም። የሰው ልጅ የ “ከ- እስከ” ጉዞ ክብ ነው የሚባለውም ለዚሁ ነው፤ ሁሉ ነገራችን ክብ። ዞሮ ክቡን ለመግጠም ግን መከራ። ሠላም!!!

 ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 3/2016

Recommended For You