
አዲስ አበባ:- የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሀገርን ብሄራዊ ደኅንነት ለማስጠበቅ፤ በዜጎች ላይ ሊደርሱ የሚችሉ ጥቃቶችን አስቀድሞ ለመከላከል እና ለመቀነስ ያስችላል ያለውን አዋጅ ለዝርዝር ዕይታ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መራ፡፡
ምክር ቤቱ ትናንት በዋለው ሦስተኛ ዓመት የሥራ ዘመኑ አንደኛ መደበኛ ስብሰባው የቀረበለትን፤ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርቶች የደኅንነት ማረጋገጫና ቁጥጥር አዋጅ መርምሮ ነው ለዝርዝር እይታ የመራው፡፡
የአዋጁን ሃሳብ ለምክር ቤት አባላት ያቀረቡት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ በልጅጌ እንደገለጹት፤ ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርቶች ዕድገትና መራቀቅ ጋር ተያይዘው የሚመጡ አሉታዊ ተጽዕኖዎች በሀገራዊ የኢንፎርሜሽን ሀብቶች ደኅንነት መከላከል በማስፈለጉ አዋጁ እንዲወጣ ምክንያት ሆኗል፡፡
በዜጎች ላይ ሊደርሱ የሚችሉ ጥቃቶችን አስቀድሞ መከላከልና መቀነስ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱም ለአዋጁ ድንጋጌ ምክንያት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
አዋጁ ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገባ የሚከለከሉ እና በገደብ የሚገቡ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርቶችን ለመለየት፣ የደኅንነት ማረጋገጫ ፈቃድ አሰጣጥን ሥርዓት ለመወሰንና በምርቶቹ ላይ ክትትል እና ቁጥጥር ለማድረግ የሚያስችል ግልጽ፣ ወጥ እና ፍትሐዊ አሠራር ይዘረጋል፡፡
በፍጥነት እያደገ የመጣው ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ሰዎች መረጃ የሚያገኙበት፣ የሚማሩበት፣ የሚሠሩበት፣ የሚጓጓዙበት የሚገበያዩበት፣ የሚዝናኑበትና የተለያዩ ማኀበራዊ አገልግሎት የሚያገኙበት ከፍተኛ ለውጦችን ማምጣቱም ተገልጿል።
እያደገ ከመጣው የኢንተርኔት መሠረተ ልማት አቅርቦት ጋር ተዳምሮ ሰዎች ከቴክኖሎጂ ጋር ያላቸው ቁርኝት በከፍተኛ ደረጃ በመጨመሩም የዜጎችን የሕይወት ጫና ማቅለሉም ተጠቁሟል፡፡ በመሆኑም የሀገርን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርቶች ደኅንነት ማረጋገጫ ቁጥጥር ሥርዓት የሀገሪቱን ደኅንነት በሚያስጠብቅ መልኩ በግልፅ፣ ወጥና ፍትሐዊ በሆነ እንዲሁም ሕግን መሰረት ባደረገ መልኩ ለመምራት አዋጅ ተዘጋጅቷል ብለዋል።
ቴክኖሎጂዎቹ በሀገር ደኅንነት ላይ ሊኖራቸው የሚችለውን አሉታዊ ተጽእኖ አስመልክቶ በቂ ግንዛቤ ለመፍጠር፣ መብትና ግዴታቸውን በግልጽ ለማስቀመጥ፣ ጥቅል የአሠራር ሥርዓቶችን ለመዘርጋት፣ ስጋት ለሚፈጥሩ ድርጊቶች ተገቢ እና ተመጣጣኝ እርምጃ ለመውሰድ እንዲሁም የሀገርን ብሄራዊ ደኅንነት ለማስጠበቅ እንደሚያስችልም ተናግረዋል፡፡
ምክር ቤቱ በትናንት ውሎው የተለያዩ የብድር ስምምነቶችን አጽድቋል፡፡ በኢትዮጵያ እና የዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር መካከል ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም ማስፈጸሚያ በተመሳሳይም ለሰው ሀብት ልማት ኦፕሬሽን ማስፈጸሚያ የተደረገውን የብድር ስምምነት ለማድረግ የቀረበውን አዋጅ መርምሮ አጽድቋል፡፡
በኢትዮጵያና በጣሊያን መንግሥት መካከልም ለኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን የቡና እሴት ሰንሰለትን ማሻሻያ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ፣ ለኢንዱስትሪ ዘርፍ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ እና ለውሃ እና ኢነርጂ ዘርፍ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር የተደረጉ የብድር ስምምነቶችንም አጽድቋል፡፡
የምክር ቤት አባላቱ በውይይታቸው ለሰው ሀብት ልማት ኦፕሬሽን ማስፈጸሚያ የጸደቀው መሰረታዊ አገልግሎቶችን ጤናና ትምህርትን እንዲያማክል አሳስበዋል፡፡ በተለይም የመምህራን የብቃት እና ጥራት አሁን በተማሪዎች ውጤት ማነስ ላይ ለሚታየው ችግር ሚና ስላላቸው ብድሩ በባለሙያዎቹ ብቃት ጉዳይ ትኩረት ሊያደርግ እንደሚገባ አንስተዋል፡፡
ከተገኘው የ350 ሚሊዮን ዶላር ዕርዳታ እና የ50 ሚሊዮን ዶላር ብድር ውስጥ 135 ሚሊዮን ዶላሩ የአሠራር ሥርዓትን ማስተካከል ላይ በማተኮር የጤናና የመምህራን የአሠራር ብቃት ላይ እንደሚያተኩር ከገንዘብ ሚኒስቴር የተወከሉ ኃላፊ አቶ ኮከብ ምስራቅ ጠቁመዋል፡፡
የምክር ቤት አባላቱ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም ማስፈጸሚያ የተገኘው ብድር በተገቢው መንገድ እንዲመራ፣ የተጨማሪ ኃይል ፍላጎትን ለመመለስና የኃይል መቆራረጥን ለማስቀረት ትኩረት እንዲደረግ አሳስበዋል፡፡
ዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን ጥቅምት 2 ቀን 2016 ዓ.ም