ከተንጣለለው የቋራ አድማስ ስር ማልዳ የወጣችው የታሪክ ጀምበር ብሩህ የጥበብ ወጋጋን እየፈነጠቀች፤ የኪነ ጥበቡን መንደር በብርሃን አድምቃዋለች። ጥበብና ታሪክን በጀግንነት አስተሳስራ የያዘችው ገመድም ከማርጀትና ከመበጠስ ይልቅ ዘመናትን ተሻግራ እያደር መጥበቅና መድመቅን መርጣለች። ትላንትና ሞተ ሲባል የተቀበረው አንድ ለናቱ ዛሬ በጥበብ ቤት እንደገና ተወለደ። በኪነ ጥበብ እየተኮተኮተ ያደገው የጀግናው ታሪክ ዛሬ ላይ ጎልምሶ እንደ ጀግናውም ጀግኗል። የጠቢባኑን ልብ አሸፍቶ ብዕራቸውን ማረከው። የብዕር ምርኮኞች አደረጋቸው።
ትላንት አንዲት ፍሬ የቀረች ባውላላ፤
እንዲያው እንደ ዋዛ ከአፈር ተጥላ፤
እሷም አንዲት ፍሬ ከተራራው በቅላ፣
ሁለት አራት እጥፍ አፈራች ዘለላ።
ሥጋም አፈር ሆነ ሊጎመራ ፍሬ፤
ስሩ ከጥበብ ላይ ቢጣበቅ ካገሬ፤
ዜማው ላንድ እናቱ የጀግናው ዝማሬ፤
አሸተ አፈራ ከትላንቱ ዛሬ።
እንቡጥ ፍሬን ያደልሽ ተናገሪ ቋራ፤
ከመቅደላ አፋፍ ቆሞ የተጣራ፤
ወልደሽው የለም ወይ ያን ንስር አሞራ፤
አንቺ ተናገሪ ለኛም እንዲበራ።
ለሀገር ሲሉ ሞተው ዳግም በጥበብ ስለተወለዱት ስለ ቋራው አንበሳ በታቀፈችው መቅደላ እውነቱን ትነግረን ዘንድ በስንኞቻችን፤ እራሷን ቋራን ተማጽነን መንገዳችንን እንቀጥል። ታዲያ በዚሁ መንገዳችን፤ ኪነ ጥበብ ሀገራዊ ጀግኖችን አይረሴ በሆነ ምስል ቀርጾ የሚያኖር ቢሆንም ነገር ግን ከሁሉም በተለየ መልኩ የተቀረጸ አንድ ግዙፍ ምስል መኖሩን እንመለከታለን። አንድ አምፖል የማይታየውን ውስጣዊ ኃይል ወደሚታይ ብርሃን ቀይሮ እንደሚያበራ፤ ጥበብም የሞተውን ታሪክ ወልዳ ለሚመጣና ለሚሄደው ሁሉ ይሆን ዘንድ በብርሃን አምሳል ቀርጻ ከመንገዱ በላይ ካለው ማማ ላይ ሰቅላዋለች። በኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ ውስጥ የሚወሱ ስመጥር ባለታሪኮች አሉ ይኖራሉም፤ ነገር ግን ጥበብ እንደ ዳዊት የምትደግመውን የአጼ ቴዎድሮስን ስም የሚገዳደር ጀግና ፈልጎ ማግኘቱ የማይሆን ነው። ምክንያቱም በኪነ ጥበብ መንደር የዚህን ያህል የናኘ ስምና መሳጭ ታሪክ አለመኖሩ ገሀድ ነው። ከተራ ሽፍታነት አንስቶ እስከ ሀገር መሪነት ከዚያም እስከ ሞት ያበቃቸው ታሪክ፤ አንድም የሚጣል ሳይኖረው ለጥበብ የተመረጠ ብስል ፍሬ ሆኖ ተገኝቷል። ከመጽሐፍት ድርሰት እስከ መድረክ ቲያትር፣ ከግጥም መድብሎች እስከ ሙዚቃ ሥራዎች፣ ከቴሌቪዥን መስኮት እስከ ሥዕል ሸራዎች ድረስ ባሉት የጥበብ ሰዎች፤ ከዚህ ፍሬ ቀምሶ ያላጣጣመ የለም ለማለት ይቻላል።
የሀያሲያኑና የደራሲያኑን፣ የሙዚቀኛውንና የሰዓሊያኑን ቀልብ የገዙበት ትልቁ ሚስጥር አንደኛው ከዚሁ ጣፋጭ ፍሬ የተገኘ ነው። ነገር ግን በዚሁ ብቻ ነው ብለን የምናበቃው አይደለም። የቋራው አንበሳ… አንድ ለናቱ… ቆራጡ ካሳ… አጼ ቴዎድሮስ በኪነ ጥበቡ ዓለምና በፀሐፊያኑ ዘንድ የዚህን ያህል ያመሰግነናቸው ትልቁ ሚስጥር ምን ይሆን? ስለጉዳዩ ብዙዎች ጥናትና ምርምራቸውን በማካሄድ የነገሩን ጫፍ ለመያዝ በአሰሳና ዳሰሳ ቧጠዋል። አንዳንዶችም ባወቁትና በተረዱት የእውቀታቸው ልክ የተለያዩ መላ ምቶችን ሲሰነዝሩም ተደምጧል። ታዲያ አጼ ቴዎድሮስ የኪነ ጥበቡ ዓለም የሃሳብ መፍለቂያ ያደረጋቸውን ሚስጥር ለማወቅ የሚረዳውን ሚስጥራዊ የእውነት ቁልፍ መገኛውስ እነማን ዘንድ ይሆን? የሚስጥሩን ቁልፍ ፍለጋ የወጡትን ዳና ተከትለን ብዕራቸውን አንስተው ወደከተቡቱ የጥበብ ሰዎች መንደር በመዝለቅ ሥራዎቻቸውን መመልከቱ መልካም ነው። እያንዳንዱን የኪነ ጥበብ በር በማንኳኳት፤ በተቻለው አቅም ሁሉ ልዩ ልዩ የጥበብ ማህደሮችን እያገላበጡ ከዚሁ ምኩራብ ላይ ጥቂት መቆየቱም አይከፋም።
በኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ ውስጥ አጼ ቴዎድሮስ ከአንዲት ፍሬ በበቀሉ በሦስት የታሪክ ሀረጎች ተተክለዋል። ሦስቱም የታሪክ ምዕራፎች በአንዲት ግንድ ላይ ያረፉ በመሆናቸው ውበትን አጎናጸፋቸው እንጂ ፈጽሞ አልደበቃቸውም። ይሄም የጀግናው ምርኮኛ በሆኑት በታሪክ ቀያሽ መሐንዲሶቻቸው የተዋቀረ የእውነት ድልድይ ነው። በታሪክና ሥራቸው ቀልቡን በመግዛት በቁጥጥራቸው ስር ያደረጉት የመጀመሪያው የብዕር ምርኮኛ በዚያው በቤተ መንግሥታቸው ውስጥ የነበረው ደብተራ ዘነበ ነበር። ደብተራ ዘነበ የአጼውን የዕለት ውሎ ከማህደር ላይ እያሰፈረ በመዋዕለ ዜና ፀሐፊነት የሚያገለግል ቢሆንም፤ እያደር ግን ከሥራነት አልፎ በብዕራዊ ተመስጦ በነገሩ ውስጥ ልቡ መፍሰሱ አልቀረም ነበር። ብዙ ነገሮች የሚጀምሩትም ከዚሁ ምዕራፍ ነው። በርካታ ብዕረኞችን የታሪኩ ምርኮኛ አድርጎ እያክለፈለፈ በመውሰድ ከመንደሩ የጣላቸው ጉዳይ መነሻው የዚሁ ደብተራ ጽሑፎች ናቸው። ተማርኮ ብዙ ምርኮኞችን በማፍራት፤ በጥበብ ደጅ አስጠንቶ የኪነ ጥበብ ጅረት ወደ አጼ ቴዎድሮስ መንግሥት የሚፈስበትን ቦይ በመቆፈር መሠረቱን ጥሏል። ከጥበብ ቤት የብዙዎች ታሪክ እየደበዘዘ በሄደበት ወቅት እንኳን ይሄኛው ግን እየሞቀና እየደራ፤ እያደር እንደ ወይን ጣፋጭ እየሆነ እንዲመጣ ሆኗል። ዘመን የጊዜ ፈረሱን ሽምጥ እየጋለበ ከታሪኩ በራቀ ቁጥር፤ ጥበብ ግን በተቃራኒው ወደ ታሪኩ መጠጋቷ ሌላኛው አስገራሚ ጉዳይ ነው። የጥበብ ልጆች በየዘመናቱ ብቅ እያሉ ከብዕር የተሰራውን ኪነ ጥበባዊ አካፋና ዶማቸውን እያነሱ የጅረቱን መፍሰሻ ቦይ፤ መንገዱን አስፍተው እንደ ዓባይ ወንዝ የማይነጥፍና በግርማ ሞገስ የሚንፎለፎል አድርገውታል።
ሁለተኛው የአጼ ቴዎድሮስ የታሪክ ስንግ ማህደር ከደራሲያኑ የብዕር ጠብታ የተወሰደች ናት። ከሀገራችን ደራሲያን እስከ ውጭው ዓለም በተለይ ደግሞ የእንግሊዝ ፀሐፊያን የኚህ ጀግና ታሪክ ምርኮኞች ሆነዋል። እንዲያውም ከሀገራችን ደራሲዎች ቀድመው እጅ የነሱት እነርሱ ናቸው። መጽሐፍቱንና ቅርሳ ቅርሱን ለመስረቅ ላይ ታች ሲሉ፤ ልባቸውን ከዚሁ ጥለውት ሳይሄዱ አልቀረም። ከዚህ በኋላም እስከ 1950ዎቹ ድረስ የነበሩት የሀገራችን ደራሲያን ሲግተለተሉ ወደዚሁ ገብተዋል። ሦስተኛው የታሪክ ማህደርም መነሻውን ከሁለተኛው በማድረግ ካለፉት ሁለት ምዕራፎች በተለየ መልኩ ከ1950ዎቹ በኋላ በእጅጉ ደማቅና አብረቅራቂ ሆኖ ቀርቧል። በኪነ ጥበብ የተለኮሰው ታሪክ ሙቀትና ግለቱ እያየለ የመጣው ከዚህ ጀምሮ ነበር። በጥበብ ገበሬው በሰኔ የተዘራው የጀግናው ታሪክ እንደ ጥቅምቱ አዝመራ ከማሳው ተንዠርግጎ እያሸተ መጣ። እዚህ ጋር ልናውቀው የሚገባ አንድ ነገር ቢኖር፤ የተዘራው የታሪክ ዘር በጊዜ ሂደት ፍሬው እያማረ መጣ እንጂ ከመጀመሪያው የታሪክ ጎተራ የተጨመረም ሆነ የተቀነሰ ወይንም የተቀየጠ አንዳችም ነገር አለመኖሩን ነው።
የአጼ ቴዎድሮስን ታሪክ በጥበባዊ ብዕር ሰቅለው በጠብታዋ ካደመቁት የምን ጊዜም ታላቅ የሀገራችን ደራሲያን መሃከል አንደኛው አቤ ጎበኛ ነበር። “አንድ ለናቱ” በተሰኘው ባለ ብዙ ገጽ በሆነው ግዙፍ መጽሐፉ የቴዎድሮስን ዳግመ ውልደት አብስሮበታል። በመጽሐፉ የተካተቱት የጀግናው ታሪክ ልብን በጀግንነት እያሸፈቱ ሀገራዊ ፍቅርን በደም ስር የሚያዘዋውሩ ቢሆኑም በሌላኛው የስሜት ጫፍ ደግሞ ልብን በሀዘን እየሰበሩና ዓይንን በእንባ እያጠቡ በቁጭት የሚያብከነክኑ ናቸው። በጊዜው የሚረዳውን አጥቶ በአንድ ለእናቱ ፍቅር ለብቻው ቆሞ ለብቻው የሞትን ጽዋ የተጎነጨ አሳዛኝ ጀግና አድርጎ አስፍሮታል። በዚሁ የጀግንነት ማዕበል ውስጥ ቁጭ ብሎ የወጀቡን ኃይል ከውስጣዊ ስሜቱ ጋር አዋህዶ የጀግናውን እውነተኛ ታሪክ በማስገር አካል አልብሶ በቲያትር መድረክ ላይ ያቆመው ሁለተኛው ጉምቱ ብዕረኛ ደግሞ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ነው። በአቤ ጉበኛ “አንድ ለናቱ” መጽሐፍ እያደከደከ አድጎ በብርታት የቆመው ኃያል ታሪክ በፀጋዬ ገ/መድህን “አፄ ቴዎድሮስ” ቲያትር ነብስ ዘርቶ አካልና ሥጋን ለብሶ ቆመ። የአጼ ቴዎድሮስ ታሪክ የመድረክ ጉዞ በዚህ አላበቃም በሌላኛው የጥበብ ልጅ፤ በብርሃኑ ዘሪሁን “የቴዎድሮስ ዕንባ” በተሰኘው ቲያትር ሌላ የታሪክ ሰበዝ መዞ ቀጥሏል። ከጀብዱው መሃል ጠብ ያለውን የስሜት ዕንባ ተጋርቶ ከልቡ አንብቶበታል። ቴዎድሮስ በጥበብ ሰዎች ልብ ውስጥ ብቻም ሳይሆን ከልጅ እስከ አዋቂ፤ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ባለው ሁሉ ልብ ውስጥ በብርሃን ምስል እንደገና ታዩ። አጼ ቴዎድሮስ የብሔራዊ ጀግና ቁንጮ ሆኑ።
በዘመኑ የአዲስ ዘመን ጋዜጣና ልዩ ልዩ መጽሔቶች ላይ አዘጋጅ የነበረው ደራሲና ጋዜጠኛ በዓሉ ግርማ የእነዚህ ሁሉ ልባዊ የታሪክ ስሜቶች ምስክር ሆኖ በመቅረብ መሃላውን በብዕሩ አድርጓል። ስለ እውነት ኖሮ እውነትን በመናገር በዓሉ ግርማን ማንስ ይስተካከለዋል… እውነተኛው የቴዎድሮስ ታሪክ ከነምስሉ የተገለጠው በእነዚህ ሦስት ደራሲያን ነው ሲል የሚስጥር መክፈቻ ቁልፉን መገኛ በብዕሩ እየጠቆመ ለማሳየት ሞክሯል። የአጼ ቴዎድሮስ ጀግንነት በደራሲያኑ ምናብ የተሰራ እንጂ ፈጽሞ የዚህን አይነት ሰው አልነበሩም እያሉ ለሚሞግቱ አንዳንድ ሰዎች ምላሽ ይሆን ዘንድም ምስክርነቱን እንዲህ ሲል በቃል አጸናው “አፄ ቴዎድሮስ ከመቶ ዓመት በኋላ ተወለዱ”። በዚያን ጊዜ አንዲት ፍሬ የታሪክ ዘር የነበረችው ያቺ ጎስቋላና እንቡጥ ታሪክ ከብዙ ትውልድ በኋላ አሽታ በመመልከቱ፤ ያኔ ሞተው አሁን ተወለዱ የሚል ሃሳብ ባዘለች ሰፋ ያለች ዳሰሳዊ ጽሑፉ ውስጥ ሁሉንም ዘርዝሮ ተናግሮታል።
ስለ አጼ ቴዎድሮስ ያልተናገረ ማን አለ?…የገጣሚው ግጥም፣ የደራሲው ድርሰት፣ የሰዓሊው ብሩሽ ያለ አጼ ቴዎድሮስ ታሪክ መች ይደምቅና፤ ጥበብስ ደስታዋ መቼ ሙሉ ሊሆን…ብቻ ግን ለሁሉም ስንግ የሃሳብ ስንቅ ነው። ከሙዚቃው መንደርም እንደ ችቦ በርቶ በብርሃን አጥለቅልቆታል። ከእነዚህም የቴዎድሮስ ካሳሁን ወይንም ቴዲ አፍሮ “የቋራው አንበሳ” የተሰኘው ሙዚቃ የካሳን ጀግንነት የስሜቱን ንዝረት ገልጦ ያሳየ ሆኗል። እንዲሁም ደግሞ ጌትነት እንየው በሙዚቃዊ ቲያትር ከመድረክ ላይ አቁሟቸዋል። ገሪማ ተፈሪ በ”አባ ታጠቅ ካሳ የቋራው አንበሳ” መጽሐፍ፣ ደጃዝማች ግርማቸው ተ/ሐዋርያት በ”ቴዎድሮስ ታሪካዊ ድራማ” እንዲሁም ተክለ ፃዲቅ መኩሪያና ጳውሎስ ኞኞ ሁሉም ስለ ቴዎድሮስ ብዕራቸውን አንስተዋል። እውነቱን ለመናገር፤ እነማን ስለ ቴዎድሮስ ጻፉ? ከማለት ይልቅ ያልጻፉቱ እነማን ናቸው? ብሎ መጠየቁ ቀላል ነው። በዚህ ግዙፍ ታሪክ የሀገራችን ፀሐፊያን ብቻም ሳይሆኑ ታላላቅ የውጭ ሀገር ፀሐፊያንም ተለክፈውበታል። ለአብነት ያህልም ሄነሪ በላንክ እና ሪቻርድ ፓንክረስት ተጠቃሾች ናቸው። ቴዎድሮስ መቼ ሞቱ? ቴዎድሮስ እኮ አልሞቱም! ተወለዱ እንጂ… ኃያላን ቢሞቱም ዳግም በጥበብ ይወለዳሉ።
አጼ ቴዎድሮስ እያደር በትውልዱ ዘንድ ጣፋጭ እየሆኑ ለመጡበትና ታሪካቸው ከኪነ ጥበቡ ጎጆ በታች ነግሶ ለመታየታቸው ምክንያት ታሪኩ በራሱ ትራጄዲና በጥበብ መድረክ ላይ የተሰናዳ የሚመስል ገሀድ መሆኑ ነው። በእያንዳንዱ ገቢር ውስጥ የሚገኙት የታሪክ ክስተትና ድርጊቶች ኪነ ጥበባዊ ለዛን የተላበሱ በመሆናቸው በእጅጉ ለጥበብ የቀረቡ ናቸው። ከታሪክ ፍሰቱ አንስቶ በውስጡ የሚገኙት ክዋኔዎች ዓይንና ቀልብን የሚስቡ መሳጭ ታሪኮች ናቸው። ታሪኩ በመጽሐፍትና ቲያትሮች ውስጥ የምንመለከተውን የልብ አንጠልጣይነት ባህሪን የያዘ ከመሆኑም በተጨማሪ በድርጊቶች የተሞላ ውጣ ውረዶች የታጨቁበት ነውና የማንንም ዓይንና ጆሮ የመሳብ አቅም አላቸው። ከእነዚህም ድርጊቶች አንደኛው ይህ ነው። እንግሊዞቹ አንዱን ቴዎድሮስን ለመማረክ በግዙፍ የጦር ሠራዊት ከደጃቸው መድረሳቸውን ባወቁ ጊዜ “እጅህን ስጥ አለኝ ፈረንጅ….” ከሚለው የጀግንነት ፉከራ ስር የነበረውን የመሳሪያ አፈሙዝ በአፋቸው በመደገን ጥይቱን እንደ ውሃ ጠጡት። ይሄ እብደትና ለማመን የሚከብድ ጀብዱ ቢመስልም፤ እውነታው ግን እውነት መሆኑ ብቻ ነው። ቴዎድሮስ ከነበራቸው ወጣ ያለ የቆራጥነት መንፈስና ሀገር ወዳድነት የተነሳ፤ እምቢ ለሀገሬ ሲሉ የጎረሱት ጥይት የጥበብ ሰዎችን ዓይንና ልብ እየገዛ፤ ወይ ፍንክች ወይ ውልፍት እንዳይሉ አድርጎ ስሜታቸውን ከብዕር ጋር ቋጠረው። ከቋራ አድማስ፤ በመቅደላ ጀንበር ጥበብ ከተራራው ስር ፈለቀች። ብዕረኞችም ከዚሁ ምንጭ እየተጠመቁ በምርኮ እጅ ነሱ።
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 1 ቀን 2016 ዓ.ም