በተለያዩ የምግብ ሸቀጦች ላይ በአናት በአናቱ እየተስተዋለ ያለው የዋጋ ጭማሪ ኅብረተሰቡን እያማረረ ይገኛል። ይህ መፍትሔ ያጣ የዋጋ ጭማሪ በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የማኅበረሰብ ክፍሎች ከመፈተኑ ባለፈ አጠቃላይ የኑሮ ውድነቱን እያባባሰው ነው።
በአሁኑ ወቅት በዋጋ ንረታቸው ሸማቹን እያማረሩ ከሚገኙ ምርቶች መካከል የግብርና ምርት የሆነው ቀይ ሽንኩርት በዋናነት ይጠቀሳል። ዋጋው እየናረ የመጣው የሽንኩርት ምርት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በአሁኑ ወቅት ዋጋው ከሸማቹ የመግዛት አቅም በላይ ሆኗል።
የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ አበራሽ ጂማ እየናረ የመጣው የቀይ ሽንኩርት ዋጋ በእጅጉ አስመርሯቸዋል። ወይዘሮ አበራሽ ነዋሪነታቸው በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ጀሞ አካባቢ ነው። እሳቸው እንደሚሉት፤ የሸቀጣሸቀጦችና ግብርና ምርቶች ዋጋ በየዕለቱ ጭማሬ እየተስተዋለበት ነው። አትክልትና ፍራፍሬ በተለይም ቀይ ሽንኩርትና ቲማቲም ካለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ወዲህ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ጭማሪ እያሳዩ ናቸው።
‹‹ምንም እንኳን አትክልትና ፍራፍሬ በተለይም ሽንኩርትና ቲማቲም የክረምት ወቅት የማይወድላቸው ቢሆኑም፣ የዘንድሮው የተለየ ነው›› የሚሉት ወይዘሮ አበራሽ፤ ካለፈው ከዘመን መለወጫ ጀምሮ በተለይም ሽንኩርት ዋጋው በቀን በቀን እየጨመረ ነው፤ በአሁኑ ወቅት የአንድ ኪሎ ቀይ ሽንኩርት ዋጋ እስከ 140 ብር ደርሷል›› ሲሉ ነው ሁኔታውን በም ሬት የተናገሩት።
እሳቸው እንደሚሉት፤ ባለፈው የበዓል ወቅት አንድ ኪሎ ሽንኩርት 60 እና 70 ብር ሲሸጥ ነበር። አሁን ግን አንድ ኪሎ ሽንኩርት 140 ብር ድረስ እየተሸጠ ነው። ሽንኩርት እጅግ በጣም ተወደደ እንጂ ሌሎች የምግብ ሸቀጦችም ቢሆኑ ዋጋቸው በየዕለቱ እየጨመረ ነው። በአሁኑ ወቅት የቀይ ሽንኩርት ዋጋ መጨመሩን ቀጥሏል፤ ይህም የኑሮ ውድነቱን ይበልጥ አባብሶታል ይላሉ።
ሌላዋ የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሪት ጽጌ በቀለ ‹‹በሀገሪቱ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ ላይ እየተስተዋለ ያለው የኑሮ ውድነት ሽንኩርትና ቲማቲም ብለን የምንተወው አይደለም፤ ሁሉም ነገር ተወዷል። ያልተወደደ ነገር የለም›› ስትል ትገልጻለች። ዝቅተኛ ገቢ ያለው ሰው መኖር እያቃተው መሆኑን ወይዘሪት ጽጌ ጠቅሳ፣ ሁሉም ነገር በየዕለቱ እየጨመረ ገበያው ከሸማቹ አቅም በላይ መሆኑን ታብራራለች። ለዚህም የተለያዩ ምክንያቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ገልጻ፣ በተለይ በሀገር ውስጥ ምርቶች ላይ እየታየ ያለው የዋጋ ንረት ከአቅም በላይ እንደሆነ አመላክታለች።
የሽንኩርት ዋጋም ከሸማቹ አቅም በላይ ከሆነ ቆይቷል ስትል ገልጻ፣ ቲማቲም፣ ድንች፣ ካሮትና ሌሎች ምርቶችም በተመሳሳይ መወደዳቸውን ነው የጠቀሰችው። የእነዚህ ምርቶች መወደድ አጠቃላይ ባለው የኑሮ ውድነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳረፉን ገልጻ፣ መንግሥት መፍትሔ ቢሰጠን መልካም ነው ትላለች።
መንግሥት በእሁድ ገበያና በተለያዩ የሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት አማካኝነት ገበያውን ለማረጋጋት እያደረገ ያለው ጥረት በበጎ ጎኑ እንደሚወሰድ የጠቀሰችው ወይዘሪት ጽጌ፤ ይህ ብቻ በቂ እንዳልሆነም ተናግራለች። ይህ መፍትሔ በየዕለቱ እየናረ ለመጣው የዋጋ ውድነት ዘላቂ መፍትሔ መሆን እንዳልቻለ ነው የገለጸቸው።
ከሌሎች የገበያ ቦታዎች አንጻር የእሁድ ገበያ የተሻለ አማራጭ መሆኑን ጠቅሳ፣ በእነዚህ ገበያዎች በተለይ በአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ከመደበኛው ገበያ የዋጋ ቅናሽ እንደሚታይ ጠቁማለች። መደበኛው ገበያ በኪሎ ከ15 እስከ 20 ብር ድረስ ቅናሽ አለው ያለችው ወይዘሪት ጽጌ፤ ማኅበረሰቡ እነዚህን የገበያ አማራጮች ተጠቅሞ በአቅሙ እየሸመተ መሆኑን አመላክታለች።
‹‹ይህ እርምጃ የኑሮ ውድነቱን ዘላቂ በሆነ መንገድ ለመፍታት በቂ አይደለም። ጠንካራ ሥራ መሠራት አለበት›› ስትል አስገንዝባ፣ በተለይም መንግሥት በበዓላት ወቅት ገበያ ለማረጋጋት የሚሠራውን ሥራ ከበዓል ውጪ ባሉ ወቅቶችም አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁማለች። ምክንያታዊ ያልሆኑ የዋጋ ጭማሪዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ ቁጥጥርና ክትትል እንዲደረግም ጠይቃለች።
ይህን በየዕለቱ ዋጋው እየጨመረ የሸማቹን አቅም እየተፈታተነ ያለውን የኑሮ ውድነት በተለይም የሽንኩርት ዋጋን በተመለከተ ያነጋገርናቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰውነት አየለ እንደሚሉት፤ ንግድ ቢሮው በከተማ ያለውን የንግድ ሥራ ዘመናዊ፣ ፍትሐዊና በውድድር ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ማድረግ የሚያስችል ሥራ እየሠራ ይገኛል። በተለይም ከመሠረታዊ የምግብ ሸቀጦች አቅርቦት ጋር በተያያዘ ከተማ ውስጥ የሚስተዋለው የምርት አቅርቦት እጥረት ለመፍታት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ነው።
ከእነዚህም መካከል ከተማ አስተዳደሩ በከተማዋ መግቢያና መውጫ በሮች አካባቢ ትላልቅ የገበያ ማዕከላትን ገንብቶ ወደ ሥራ አስገብቷል፤ እየገነባም ይገኛል ያሉት ዳይሬክተሩ፣ በተለያዩ አካባቢዎች የሚካሄዱ የእሁድ ገበያዎችንና የሸማቾች የኅብረት ሥራ ማኅበራትን እያጠናከረ መሆኑን ይገልጻሉ።
ከተማ አስተዳደሩ እነዚህን የገበያ ማዕከላት በመጠቀም በተለያዩ ክልሎች ከሚገኙ አርሶ አደር ማኅበራት ጋር የገበያ ትስስር በመፍጠር የምርት አቅርቦት መጠኑን ለመጨመር እየሠራ እንደሆነ ጠቅሰው፤ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ፍጥነት በየዕለቱ የዋጋ ጭማሪ እያሳየ ባለው የሽንኩርት ምርት ላይም እንዲሁ ገበያውን ለማረጋገት እየሠራ እንደሆነ አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት በሽንኩርት ምርት ላይ ከፍተኛ የሆነ የምርት አቅርቦት እጥረት ይታያል ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ይህን ተከትሎም ከፍተኛ ፍላጎት ይታያል ይላሉ። ከበዓል ጋር በተያያዘ የሽንኩርት ምርት በከፍተኛ መጠን ወደ ከተማዋ ሲገባ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ሰውነት፤ በወቅቱም የነበረው የሸቀጦች ዋጋ የተሻለና የኅብረተሰቡን የመግዛት አቅም ባገናዘበ መልኩ ሲፈጸም እንደነበር ገልጸዋል።
ለዚህም ቢሮው ከተለያዩ አርሶ አደሮች ማኅበራት ጋር ትስስር በመፍጠር ከገበያ ማዕከላቱ በተጨማሪ የተለያዩ ኤግዚቢሽኖችን በመፍጠር አምራቹና ሸማቹ በቀጥታ ተገናኝተው ግብይት መፈጸም የሚችሉበትን ምቹ ሁኔታ ፈጥሮ መሥራቱን አስታውሰዋል። በዚህም ሽንኩርትን ጨምሮ የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የሰብል ምርቶችና እንስሳትና የእንስሳት ተዋጽኦዎች በተሻለ መጠን ቀርበው በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ ሲቀርቡ እንደነበር ተናግረዋል።
ከተማ አስተዳደሩ አሁንም በተመሳሳይ ሁኔታ ገበያውን ለማረጋጋት የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን የገለጹት አቶ ሰውነት፤ ባሉት ሰባት የሚደርሱ ትላልቅ የገበያ ማዕከላት፣ 172 በሚደርሱ የእሁድ ገበያዎችና 152 በሚጠጉ የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት በኩል አስፈላጊ የሆኑ የግብርና ምርቶችና የኢንዱስትሪ ምርቶች ለሸማቹ እያቀረበ መሆኑን ይጠቅሳሉ።
ይሁንና አሁን ላይ የሽንኩርት ምርት በተለይም በመደበኛ ገበያ ውስጥ በከፍተኛ መጠን ዋጋው እየናረ ያለበት ሁኔታ እንደሚታይ ገልጸው፣ ለዚህም ለችግሩ በርካታ መነሻ ምክንያቶች ስለመኖራቸው አቶ ሰውነት አስረድተዋል። ለበዓሉ ከፍተኛ መጠን ያለው የሽንኩርት ምርት መቅረቡ አንዱ ምክንያት መሆኑን ጠቅሰው፣ ከዚህ በተጨማሪም የክረምቱ ወቅት መርዘሙ ለሽንኩርት ምርት እጥረት ዋነኛ ምክንያት መሆኑን አስታውቀዋል።
ሽንኩርት ከፍተኛ የሆነ የዝናብ መጠን ካለመፈለጉ ጋር ተያይዞ በነበረው የአየር መዛባት ምክንያት የሽንኩርት ምርት በሚፈለገው መጠን ተመርቶ ወደ ከተማዋ መግባት አለመቻሉን ጠቅሰዋል። ሽንኩርት ወደ ከተማዋ የሚገባው በሀገሪቱ ከሚገኙ የተለያዩ ሽንኩርት አምራች አካባቢዎች መሆኑን የጠቀሱት አቶ ሰውነት፤ ቢሮው ሽንኩርት ከሚመረትባቸው በአማራ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች ከሚገኙ የአርሶ አደር ማኅበራት ጋር ትስስር በመፍጠር ባሉት የገበያ ማዕከላት እያቀረበ ይገኛል ብለዋል።
ከተማ አስተዳደሩ አራት ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ ለሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት መመደቡን አስታውሰው፣ ማኅበራቱ የፋይናንስ ችግር ሳይገጥማቸው ምርቱን ወደ ገበያው እያቀረቡ መሆናቸውን አቶ ሰውነት ይገልጻሉ። ከተማ አስተዳደሩ በገነባቸው ትላልቅ የገበያ ማዕከላት፣ በእሁድ ገበያ እና በሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት አንድ ኪሎ ሽንኩርት ከ70 ብር ጀምሮ እየተሸጠ መሆኑንም አመልክተዋል፤ በመደበኛ ገበያው ግን የሽንኩርት ዋጋ በከፍተኛ መጠን የዋጋ ጭማሪ እየታየበት መሆኑን ተናግረዋል። ለዚህም ከፍተኛ የሆነ የምርት አቅርቦት እጥረት በመከሰቱና አቅርቦቱ ካለው ፍላጎት ጋር ሊጣጣም አለመቻሉ አሁን እየታየ ላለው የዋጋ ንረት አንዱና ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ይገልጻሉ። ዓለምአቀፋዊ ሁኔታውም ሌላው ምክንያት እንደሆነ የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፤ ከማዳበሪያ ዋጋ መጨመር ጋር ተያይዞ አርሶ አደሩ የሚያነሳቸው ችግሮች ስለመኖራቸውም ተናግረዋል።
እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍም ቢሮው እየሠራ መሆኑን አስታውቀው፤ በዋነኛነት የገበያ ትስስሮችን በመፍጠርና የገበያ ማዕከላትን በማስፋት ችግሮቹን ለማቃለል እየተሠራ ነው ብለዋል። ለአብነትም ይህ ዘገባ እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ የጥራት ደረጃው የተለያየ ቢሆንም በእሁድ ገበያዎች፣ በትላልቅ የገበያ ማዕከላትና በሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ሽንኩርት በኪሎ ከ70 ብር እስከ 90 ብር ድረስ እየተሸጠ ስለመሆኑ መታዘብ እንደቻሉ አመላክተዋል። እነዚህ የገበያ ማዕከላትም በመደበኛ ገበያው ላይ ያለውን የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ በማረጋጋት ትልቅ ድርሻ አላቸውም ብለዋል።
ከክረምቱ መጠንከርና ዓለምአቀፋዊ ከሆኑ ጫናዎች በተጨማሪ የሠላምና ጸጥታ ችግርም ለምርቶች ዋጋ መናር የጎላ ድርሻ አለው ያሉት አቶ ሰውነት፤ ነፃ የሆነ የምርትና የሰዎች እንቅስቃሴ በተሟላ መንገድ ከሌለ የሚፈለገውን ምርት ወደ ከተማ ማስገባት አይቻልም ብለዋል። በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚኖሩ ግጭቶችና የሠላም እጦቶች በማምረቱ ሥራና በምርቶች እንቅስቃሴ ላይ ጫና ማሳደራቸው እንደማይቀር አስታውቀዋል።
ሽንኩርትን ጨምሮ ሌሎች የአትክልት ልማቶች ማዳበሪያ እንደሚያስፈልጋቸው ጠቅሰው፣ የማዳበሪያ ዋጋ ከፍተኛ የሆነ ጭማሪ ማሳየቱም ሌላው ምክንያት መሆኑን ያመላክታሉ። ይህ ሁሉ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ከመጣው የሕዝብ ቁጥር ጋር ተዳምሮ ከፍተኛ የሆነ የምርት ፍላጎት መፈጠሩም ሌላው የዋጋ መናሩ ምክንያት መሆኑን አቶ ሰውነት ይገልጸሉ።
እነዚህ ምክንያቶች በምርት ዋጋ ላይ ጭማሪ እንዲከሰት ምክንያት ሊሆኑ እንደሚችሉ ይጠበቃል ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ይህ ሁሉ ባለበት ሁኔታ የቀድሞውን ዓይነት ዋጋ መጠበቅ እንደማይቻልም ተናግረዋል። እየታየ ያለው ጭማሪ ምክንያታዊ ያልሆነና ተገቢነት የሌለው በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ባለው የማኅበረሰብ ክፍል ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል እንዳይሆን ቢሮው ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነም አመላክተዋል።
ከተማ አስተዳደሩ ያስገነባቸው የገበያ ማዕከላት ገበያውን በማረጋጋት በኩል ከፍተኛ አስተዋጽዖ እያበረከቱ እንደሆነ ቢሮው ግምገማ አለው የሚሉት አቶ ሰውነት፤ በዋነኛነት በኦሮሚያ፣ በአማራና በደቡብ ክልሎች ከሚገኙ አምራች አርሶ አደሮች ጋር ሽንኩርትን ጨምሮ የተለያዩ ምርቶች ወደ ከተማዋ እየገቡ ነው ብለዋል።
የሚቀርበውን የምርት መጠን በመጨመር ከጥራት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን ማቃለል የሚያስችሉ ትብብርና ድጋፎች እየተደረጉ መሆናቸውንም አስታውቀዋል። በተለይም በእሁድ ገበያዎች የሚቀርቡ ምርቶች ከመደበኛው ገበያ ከ15 እስከ 20 በመቶ ቅናሽ እንዲኖራቸው በማድረግ ቢሮው ምርቶችን ለሸማቹ በተመጣጣኝ ዋጋ የማቅረብና ገበያውን የማረጋጋት ሥራ እየሠራ መሆኑን አስረድተዋል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን መስከረም 30/2016