ያኔ ለብዙ ኢትዮጵያውያን “ማነው?”ያስባላቸውና በድምጹ፣ በእንቅስቃሴውና በሙዚቃ ቪዲዮቹ ጥራት የተደነቁበት፣ የአፋን ኦሮሞ ድምጻዊው ቀመር ዩሱፍ የሙዚቃ ቪዲዮ ከወጣ 17 ዓመታትን ተሻገረ። በሙዚቃ ቪዲዮው ላይ “ሄሎ”፣ “ኦሮሚያ”፣ “ነነዌ” እና ሌሎችም ተወዳጅ ሙዚቃዎቹ ተካተዋል፡፡
አፋን ኦሮሞ ቋንቋን በሚችሉም ሆኑ ለቋንቋው እንግዳ በሆኑ ሰዎች ተወዳጅ የአፋን ኦሮሞ ድምጻዊ የሆነው ቀመር ዩሱፍ ውልደቱ በምሥራቅ ሐረርጌ፣ ደደር ነው፡፡ እሱ ሲወለድ በአካባቢው ሆስፒታል ይሉት ነገር አልተለመደም ነበርና እናቱ ከተከታታይ ሴት ልጆች በኋላ “ወንድ ልጅ ከነቃጭሉ ተወለደ” ተብሎ መንደርተኛውን እልል ያስባለው ቀመር ይችን ምድር የተቀላቀለው በመኖሪያ ቤታቸው ነው፡፡ ታዲያ በግብርና ሥራ ይተዳደሩ የነበሩትንና ሳይማሩ ትምህርት ቤት ያስገቡትን ወላጆቹን “የልደት ቀኔ መቼ ነው?” እያለ ለሚያነሳው ተደጋጋሚ ጥያቄ “ዝናብ ዘንቦ ኃይለኛ ጎርፍ ነበር∙∙∙” በማለት የሚሰጡት መልስ ቀኑን ለማወቅ በቂ አይደለም፡፡
በዚህ የተነሳ በትክክል የልደት ቀኑን አያውቀውም። ስለዚህ የወሰደው አማራጭ የትውልድ ቀኑን እንዳይረሳው ጃንዋሪ አንድን የልደት ቀኑ በማድረግ ወሩና ቀኑ 01/01 ሆኖ የማይረሳው ቀን እንዲሆን ማድረግ ነበር፡፡ ቀልድ ይችልበታል፣ ታዲያ ይሄ ቀልድ እራስ ላይ መቀለድንም ያካትታል። የሁሉም ውጭ የኖረ ኢትዮጵያዊ ልደት “”ጃንዋሪ አንድ” እንደሆነው፣ የኔም የልደት ቀን ጃንዋሪ አንድ ነው ይላል፡፡ ለምን ሲባል አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ዋሽቶ ስለሚሞላ እንዳይረሳ 01/01 እንዲመጣለት ጃንዋሪ አንድን ምርጫው ያደርጋል፡፡
ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል ሲማር በጉብዝናው የተነሳ በአንድ ዓመት ከአንድ ክፍል ወደ ሌላ እየተሸጋገረ (ደብል እየመታ) ትምህርቱን ተከታትሏል፡፡ ይህ የክፍል ዝላይ ከሰባተኛ ክፍል ጀምሮ “አይቻልም” ተብሎ ቢቀርም የእሱ ጉብዝና ግን አልተለየውም፡፡ በትምህርት ቤቱ የፈጠራ ሥራዎችን እየሞከረና ጎበዝ በርታ እደግ እየተባለ፣ በርካቶች ነገውን ለማየት እየናፈቁ ትምህርቱን ተከታትሏል። የባህል መድኃኒት መቀመምም ይሞክር ነበር፡፡ በትምህርቱ አብዛኛውን ጊዜ አንደኛ ካልሆነ ሁለተኛ ይወጣ ነበር፡፡ ታዲያ እናቱ፣ እህትና ወንድሞቹ፤ እንዲሁም ሌሎች፣ ቤት ውስጥ የሚገኙ ዘመዶቹ አስራ ምናምነኛ እየወጡ ሁሌ እሱ አንደኛ ቢወጣ ለምን ለልጄ ሁሉ አንድ ብቻ ይሰጡታል ብለው ተክዘው ነበር፡፡
ግን ምን ዋጋ አለው ዘጠነኛ ክፍልን ጨርሶ ወደ አስር ሲዘዋወር፤ በሚኖርበት አካባቢ በአንድ በኩል የሶማሊያ ወረራ፤ ወዲህ ሲባል ቀይ ሽብር ተብሎ በርካቶች ሲገደሉ፤ አለፍ ሲሉም ለወታደርነት እየተመለመሉ እንደወጡ መቅረታቸው “ነጋችንስ?” ብለው ቢያስፈራቸው ከጓደኞቹ ጋር ስደትን ምርጫው አደረገ፡፡ ጦርነትን ሽሽት በእግር በካራማራ፣ በጅጅጋ እያለ በጀመረው ስደት በርካቶች አብረውት ጉዞ የጀመሩት ከመንገድ ቢቀሩም እሱ ግን በጣሊያን አልፎ መዳረሻው ካናዳ ሆኗል፡፡ የስደትን መጥፎነት ሲያስታውስም “ስደተኛ ተብዬ የስደተኞች ካምፕ ነዋሪ ስሆን ካለሁበት ወደ ኋላ መለሰኝ” ይላል፡፡
የቀይ ሽብር ዘመቻንና የኢትዮ ሶማሊያ ጦርነትን ሽሽት ከሀገር የወጣ ‘ቢጭኑት አህያ ቢጋልቡት ፈረስ’ ሊሆን ተሰደደ፡፡ ይሄ ጉዞው በሰው ሀገር አለፍቃድ ተገኝቷልና እስር ቤትና የስደተኞች መኖሪያ ካምፕ አኑሮታል፡፡ ሙዚቃና ቀመር የተግባቡት ስደተኞች ካምፕ ውስጥ ነው፡፡ በስደት እስርን፣ የሚበላው ማጣትን አስተናግዷል፡፡ ስደተኞች ካምፕ ካገኛቸው መሰሎቹ ጋር እንደነገሩ በተሰራች ክራር ዛፍ ስር ቁጭ ብለው ሀገራቸውን፣ የናፈቃቸውን ሰው እያስታወሱ ማዜም የእለት ተእለት ተግባራቸው ነበር፡፡ በዛም የሱ ድምጽ በተፈጥሮ የተቸረው ነውና መንፈስን የሚያድስ በመሆኑ ከሌሎቹ ይልቅ እሱ እንዲዘፍን ምርጫቸው ሆነ፡፡ ያም ቢሆን ለሱ ሙዚቃ ስሜት መግለጫ፣ ጊዜ ማሳለፊያ እንጂ እንጀራዬ፣ እንዲሁም መታወቂያዬ ይሆናል ብሎ አያስብም ነበር፡፡
በስደት ጣልያን ደርሶ፣ በህጋዊ መንገድ ተመዝግቦ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አማካኝነት ካናዳ የመሄድ አጋጣሚ ተፈጠረለት፡፡ ሲሰደድ የዘጠነኛ ክፍል ትምህርቱን እንደጨረሰ ነበርና በካናዳ ትምህርቱን ካቋረጠበት ቀጠለ፡፡
በስደተኞች ካምፕ ቆይታው ጊታር ለመጫወት ሞክሯል፡፡ ይሄ በካምፕ የተጀመረ የሙዚቃ ትውውቅ ወደ ካናዳ አቅንቶ ሙዚቃን ሲጫወት የሚያውቁት ተማሪዎች በትምህርት ቤት መድረክ ላይ እንዲዘፍን ጠይቀውት አዜመ፡፡ የአድማጭ ማበረታቻ ሞራል ሆኖትም ሙዚቃን ለመቀጠል ተበረታታ፡፡
በሂደት የተቀላቀላት ሙዚቃ መታወቂያው፣ ብሎም መከበሪያው ሆናለች፡፡ እሱም ዋጋ ከፍሎላታል። በዚህም ተበድሮ አልበም እስከማውጣት ደርሷል፡፡ በዚህም ከሱ በላይ አበዳሪው የአልበሙን መውጣት በጉጉት ጠብቋል፡፡ ብሩ እንዲመለስ የጓጓው አበዳሪ አልበሙን በዝግጅቶች ላይ አዙሮ ሸጧል፡፡ ቀመር ከማራኪ ድምጹ፣ መድረክ ላይ ከሚያደርገው ሳቢ እንቅስቃሴ፣ ጥልቀት ካላቸው የዘፈን መልእክቶቹ በተጨማሪ ሌላው መለያው ዘናጭነቱ ነው፡፡ በተለይ የመድረክ ሥራዎቹና የቪዲዮ ክሊፖቹ ላይ ከላይ እስከታች ላለባበሱ ተጨንቆ ታዳሚን አክብሮ መገኘት መታወቂያው ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል ብዙ ጊዜ የሚለብሳቸው ልብሶች ከገበያ የተገዙ ሳይሆን በሱ ዲዛይን፣ ለሱ ተብለው የሚሰሩ ናቸው፡፡
ከአንዴም ሦስቴ መድረክ ላይ ጊታር ሰብሯል። በምእራባዊያን ሙዚቀኞች ዘንድ ተጫውተው ሲጨርሱ ጊታርን እራስ ላይ መስበር የተለመደ ነው። ታዲያ ይሄን በተደጋጋሚ የታዘበው ቀመር እኛስ ብንሰብር ምን ይለናል? ሲል አንድ ቀን መድረክ ላይ እየተጫወተ ጊታሩን እላዩ ላይ ሰበረው፡፡ ታዲያ መስበር እራሱ ልምድ ይጠይቅ ነበርና አለልምድ ጊታሩን ቢሰብረው አዙሮት ወደቀ፡፡ ደግነቱ ለየት ያሉ ዳንሶችን መደነስ መለያው ነበርና አዙሮት ወድቆ መሬት ቢንደፋደፍም ታዳሚዎች አዲስ ዳንስ ስለመሰላቸው ከመጨነቅ ይልቅ ተደስተዋል፡፡
በካናዳ እያለ ማናጀሩ የነበረ ሰው “አንድን ሙዚቀኛ ሙዚቀኛ ብለን የምንጠራው ከሙዚቃ መሳሪያ ውጭ መዝፈን ሲችልና የሚዘፍንበትን ቋንቋ የማያውቅ ሰው ዘፈኑን መስማት ሲጀምር ነው ሙዚቀኛ መሆኑን ማወቅ የምንችለው” እንዳለው ያስታውሳል፡፡ ቋንቋውን የሚያውቅ ሰው ግጥሙን ሊሰማ ይችላል ወይም የድሮ ትዝታው ተቀስቅሶበት ሊሰማ ይችላል፡፡ ቋንቋውን የማይችል ሰው ሙዚቃውን ሲወደው ሙዚቃው ብቻውን ስቦት ስለሆነ የሙዚቃን የዓለም ቋንቋነት ያስረዳል ይላል። የቀመር ዘፈኖች የኦሮምኛ ቋንቋ በሚችሉም ሆነ ቋንቋውን በማይችሉ ሰዎች ዘንድ ተወዳጅ ናቸው። የዚህ ሚስጥሩ ምንድነው ተብሎ ሲጠየቅ ሙዚቃ የዓለም ቋንቋ ነው፡፡ እንደዘፋኝ እኛ ይሄ ይወደዳል ያ አይወደድም ብለን አናውቅም፤ ሁሉጊዜም ኃላፊነት (ሪስክ) እንወስዳለን፡፡ አንዳንዴ ቆንጆ ሙዚቃ ብለን የሰራነውን ሥራ ቋንቋውንም የሚችል ሰው ላይወደው ይችላል፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ቋንቋውንም በማይችለው ዘንድ ይወደዳልና ይህ ስለሆነ ማለት አይቻልም የሚለው መልሱ ነው፡፡
“ነነዌ” የተሰኘው ሥራው እሱም የሚወደው፤ በሕብረተሰቡ ዘንድም የበለጠ ተቀባይነት አግኝቷል ብሎ የሚያስበው ሥራው ነው፡፡ ዘፈኑ ለበርካታ ጊዜ ሩቅ ቦታ ሲፈልጋት የቆየችው ልጅ ጎረቤቱ መሆኗን ሲገነዘብ እንኳን መጣሽልኝ፣ ነይልኝ የኔ ቆንጆ፣ ከዛሬ ጀምሮ ያ ሁሉ ድካምና ፍለጋ ወጥቶልኛል፣ አረፍኩ የሚልበትን ነው፡፡ “ኦሮሚያ” የተሰኘው ዘፈኑ ለብዙ ጊዜ ተለይቶት ስለቆየው አፈሩ፣ ጓደኞቹ ሕዝቡ፣ ወንዙን፣ ሳር ቅጠሉን ሲያስታውስ ያዜመው ነው። እሱም ለዚህ ይመስላል እንደቀመር ሆኜ ነው የሰራሁት፤ ዘፈኑንም እንደዘፈን ሳይሆን እንደራሴ ነው የማየው ይላል፡፡
ቀመር ከሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ በርካታ ቋንቋዎችን ይችላል፡፡ አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ሶማሊኛ፣ እንግሊዘኛ፣ ጣልያንኛ፣ አረብኛና ፖሊሽ ከሚችላቸው ቋንቋዎች መካከል ናቸው፡፡ እነዚህን ቋንቋዎች ቻልኩ ብሎ የቋንቋ ጉዞውን አልገታም፤ አሁንም ባገኘው አጋጣሚ አዳዲስ ቋንቋዎችን ለመማር ብሎም ቋንቋዎቹን ለማዳበር ይጥራል፡፡ በካናዳ ቆይታው የተለያዩ ኮርሶችን ተምሯል፤ ከትምህርት ባሻገርም የተለያዩ ሥራዎች ላይ ተሳትፏል፡፡ ከመደበኛ ሥራው ጎን ለጎን ለማህበረሰቡ በሚሰጡ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ላይም ተሳታፊ ነበር፡፡
ሙዚቃን አሁን የመጨረሻ ሥራ ሰርቼ ለተተኪዎች ለመተው መንገድ ላይ ነኝ ይላል። የገበሬ ልጅ ነኝ፤ ምግቡን ያላረጋገጠ ማህበረሰብ በሌላ ነገር ሊሳካላት አይችልም። ለዚህም ግብርናውን ማዘመን ያሻል ይላል፡፡ በዜግነት ካናዳዊ በትውልድ ኢትዮጵያዊ የሆነው ቀመር ካናዳ በዓመት ሦስት ወር ብቻ ቢመረትም በዚህ አጭር ጊዜ ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች እንደሚተርፉ ያነሳል፡፡ የራሱን አስተዋጽኦ ለማበርከት ወደ ግብርናው እንደገባም ይናገራል፡፡
ሄሎ፣ ነነዌ፣ ኦሮሚያ፣ የተካተቱበት የሙዚቃ ክሊፕ ከወጣ 17 ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ መኖሪያውን ካደረገበት ካናዳ ወደ ሀገሩ ከተመለሰ 15 ዓመት ተቆጠረ፡፡ ወደ ሀገሩ የተመለሰው ከካናዳ የ24 ዓመት ቆይታ በኋላ ነው፡፡ ኑሮ ቢመቸውም፣ በወረቀት ካናዳዊ ቢባልም የተለየ ቴክኖሎጂ ባየ ቁጥር፣ የተሻለ የመሰለውን ነገር በሙሉ ባየ ቁጥር ለሀገሬ ብሎ ያስብ ነበርና ጠቅልሎ ወደ ሀገሩ ገብቷል፡፡
ይኖርበት በነበረው ካናዳ የአየር ጸባዩ የሚፈቅደው ሶስት ወር ለማምረት ብቻ ቢሆንም በእነዚህ ወራት አምርተው፣ ከራሳቸውም አልፈው ለሌሎች ሀገራት ይተርፋሉ፡፡ በዚህ በትውልድ ሀገሩ ደግሞ የአየር ንብረቱ 13 ወር ለማምረት ቢፈቅድም በአግባቡ ባለመሰራቱ ምክንያት ከሌሎች ሀገራት እርዳታ ይመጣል፡፡ ይሄ ስላናደደኝ ፊቴን ወደ ግብርና አዙሬ ገበሬ ሆኛለሁ ይላል፡፡ “ለኢትዮጵያ ምግብ መለመን ሊያሳፍር ይገባል” የሚለው ድምጻዊው የተለያዩ ሀገራት በመሄድ የእርሻ ተሞክሮን ይቀስማል፡፡
ከበርካታ ዓመታት የስደት ኑሮ በኋላ ወደ ሀገሩ ያጠራቀመውን ጥሪትና በትምህርት፣ እንዲሁም በልምድ የቀሰመውን ይዞ፣ እራሱ ተጠቅሞ ሀገሩን ሊጠቅም ወደ ሀገሩ ገብቷል፡፡
ከድምጻዊነቱ ባሻገር አግሮ ኢንዱስትሪ እና ሪልስቴት የተሰማራባቸው የሥራ ዘርፎች ናቸው፡፡ ከሁሉም በላይ ግን እርሻ ያስደስተኛል ይላል፡፡ ከብዙ መድረኮች ላይ እንደበፊቱ ሙዚቃን ባያቀርብም ግን በቋሚነት የሙዚቃ ሥራውን የሚያቀርብበት ሥፍራ ማሳው ነው፡፡ እርሻ ቦታው ላይ ቱታውን ለብሶ ሥራ ላይ ሲሰማራ ነብሴ ሀሴት ታደርጋለች ይላል። እጽዋቱም ሙዚቃ ሲሰሙ ይለመልማሉ ባይ ነው። በተለይ የእርሻ ሥራው በኦሮሚያ ክልል ስለሚገኝ “ኦሮሚያ”፣ “ኦሮሚያ” በሚለው ዘፈኑ መሬቱንም እጽዋቱንም እያለማ ይዘፍናል፡፡
ዘመናዊ ገበሬ ሆኖ ቢቻለው ሌሎች እንዲከተሉት ለማድረግ አቅዶ እየሰራ ነው፡፡ ኢትዮጵያን የመሰለች ሀገር ተርባ ስንዴ መለመን ውርደት ነው፡፡ ወደ ግብርናው ሲገባ ሃሳቡ ለራሱ ከሚያመርተው አልፎ ለተቀሩት ልምዱን ማካፈል ነው፡፡ አዋሽ መልካሳ፣ መቂ፣ ወንጂ፣ ፍራፍሬና አትክልት ቦሎቄ፣ ስንዴ፣ ጤፍና መሰሎቻቸውን ዘመናዊ በሆነ መንገድ በስፋት ያመርታል፡፡ ከእርሻው ጎን ለጎን የመጨረሻ አልበሜን እሰራለሁ ቢልም ይሄ ቃል አሁንም ከቃል ዘሎ ተግባራዊ ሊሆን አልቻለም፡፡
የአምስት ልጆች አባት የሆነው ቀመር፤ ከመጀመሪያ ትዳሩ ሦስት ወንድ ልጆችን አፍርቷል፡፡ ከአትሌት እጅጋየሁ ዲባባ ጋር ከመሰረተው ትዳሩ የአንድ ሴት ልጅና ወንድ ልጅ አባት ሆኗል፡፡ በተደጋጋሚ ልጅ አባቱን መብለጥ አለበት ይላል፡፡ ይሄን አረዳዱን ከሱ የተሻሉ ልጆች ለመፍጠር፣ እንዲሁም በሙዚቃውም ከእሱ በፊት ከነበሩት የተለየ ነገር ለመጨመር ሰርቷል” አሁን ያሉት ሙዚቀኞችም ከሱ የተሻለ መሆን እንዳለባቸው ያምናል፡፡
“አርቲስቶችን ሁሉ እወዳለሁ” የሚለው ቀመር “ዶክተር አሊ ቢራን ግን እኛን እዚህ ያበቃን፣ በልጅነታችንም አርአያ ያደረግነው ስለሆነ ለእሱ ያለኝ ስሜት ከሌሎች ያይላል” ይላል፡፡ ከሙዚቃ መሳሪያ ጊታር፣ ማሲንቆ፣ ኪቦርድ ይጫወታል። ሆኖም ከጊታር ጋር ያለው ቁርኝት ይለያል፡፡ የብቻ ጊዜ ሲያሳልፍም ሆነ ዜማ ለመፍጠር ሲያንጎራጉር፤ እንዲሁም መድረክ ላይ ጊታር ይጫወታል፡፡ “የምትፈራው ነገር?” ሲባል፤ መልሱ “የመጀመሪያ ነገር ፈጣሪን ነው የምፈራው” የሚል ነው፡፡ ከዛ ግን ድህነትን እፈራለሁ፤ ድህነትን ደግሞ መፍራትም አለብን፤ ለዛም መሥራት አለብን ይላል፡፡
አልበሙ የተናፈቀው ቀመር በቅርቡ ኢሬቻ በአዲስ አበባ መከበር በመጀመሩ፣ ስለበዓሉ አከባበር የዘፈነበት ነጠላ ዘፈንና ከእርሻው ሥራ በተጓዳኝ በሚሰራቸው የመድረክ ሥራዎቹ ከአድማጭ ጋር ይገናኛል፡፡ ግን ደግሞ በርካታ አድናቂዎቹ የሱን ሙሉ አልበም በጉጉት እየጠበቁ ይገኛሉ፡፡ ቃል የተገባው የቀመር አልበም በዚህ ዓመት ከአድማጭ ጋር እንደሚገናኝ ተስፋ እናደርጋለን፡፡
ቤዛ እሸቱ
አዲስ ዘመን መስከረም 27 ቀን 2016 ዓ.ም