ፋጡማ ዓሊ ስለነገ ብዙ ታልማለች። የአንድ ልጇ ዓለም፣ የባለቤቷ ነገ የተሰራው በዛሬው ማንነቷ ነው። ይህ ህልሟ ዕውን እንዲሆን አታስበው የለም። ጠንክራ ብትሰራ፣ ጉልበቷን ብትከፍል ያቀደችውን አታጣም። ነገ ለእሷ የዛሬው ላብ ድካሟ ነው። ይህ ድካም ዋጋ የሚያገኘው ልቧ ሲቆርጥ፣ እግሯ ርቆ ሲሄድ መሆኑ አልጠፋትም።
ፋጡማ ይህ እውነት ከገባት ወዲህ ባለችበት መቆየት አላሻትም። ቀዬዋን ርቃ ባህር ተሻግራ ለመሄድ ወስናለች። አዎ! ትዳሯ እንዲሰፋ ቤት ጎጆዋ እንዲቀና ያላት ምርጫ ይህ ሆኗል። ለነገው መልካም ሕይወት ዛሬን ዋጋ መክፈል።
አሁን ፋጡማ ዓሊ አንድ ልጇን ስማ፣ ባለቤቷን ተሰናብታ ዓረብ ሀገር ተጉዛለች። የዓረብ ሀገር ሥራ እንደ ሀገር ቤት አይደለም። የበዛ ዋጋ የሚከፍሉበት፣ ጉልበት ከሕይወት የሚገብሩበት ነው። ወይዘሮዋ ይህ ሁሉ አልጠፋትም። ልጇን ለማሳደግ በእሾህ መንገድ መራመድ ካለባት ታደርገዋለች።
ትንሹ ዑስማን ከፍ ብሎ ቁምነገር እስኪደርስ የሰው ሀገር ልፋቷ አይቆምም። ፋጡማ የሰራችበትን ይዛ ሀገሯ ስትመለስ ጎጆ ትዳሯ ይሞላል፣ ቤቷን ሰርታ ልጇን ወግ ታደርሳለች፣ አክባሪ ባሏን ታኮራለች። ይህን ሕይወት በሀይቅ በተሁለደሬ እንዳሰበችው ይሞላል።
ትንሹ ዑስማን
አሁን ዑስማን የአጸደ ሕጻናት ተማሪ ነው ። ይህ ዕድሜ ለነገው የዩኒቨርሲቲ ትምህርት መንደርደሪያ ይሆናል። ይህን ስታስብ ፋጡማ ደስ ይላታል። ዛሬን እንዲበረታ እጇ አይታጠፍም። የሚሻውን ጠይቃ፣ የጎደለውን ትሞላለች።
እነሆ ! ዓረብ ሀገርና ፋጡማ ከተገናኙ ከሁለት ዓመት በላይ ተቆጥሯል። ፋጤ ዘወትር ባሏ ይናፍቃታል፣ ሀገር ቀዬው ትዝ ይላታል። አንድ ልጇ በዓይኗ እየዞረ ይፈትናታል። ዓላማ ይዛለችና ለዚህ ስሜት አትሸነፍም፣ በሥራ አትለግምም ‹‹አቤት ወዴት›› ብላ ትታዘዛለች። ለቤት ጓዳዋ ሙላት ለልጇ ፍላጎት ትሮጣለች። በምትልከው ገንዘብ የምትሻውን ቤት የመሥራት ሃሳብ አላት። ይህ እንዲሆን ባለቤቷ ከጎኗ ነው።
አንዳንዴ ፋጤ ስለወደፊት ኑሮዋ ከቤተሰብ ማውጋቷ አይቀርም። ወንድሟ በስልክ ባገኛት ጊዜ ጠንክራ እንድትሰራ ይመክራታል። ባለቤቷ ልጇን አይታ እንድትመለስ ይጠይቃታል። የእሷ ሃሳብ ግን ከአንድ ረግቷል። ጨከን ብላ ነገዋን መሥራት አለባት። በእሷ ነገ ውስጥ የልጇ፣ የባለቤቷ ሕይወት አለ። ይህን ቀን በብርታቷ ማንጋት፣ ማየትን ትሻለች።
የስልክ ጥሪው…
አንድ ቀን ፋጡማ ከቤተሰቦቿ የደረሳት የስልክ ጥሪ ለውሳኔ አበቃት። ሁሉም እየደጋገሙ ልጇ መናፈቁን ይነግሯት ይዘዋል። እስከዛሬ ይህን ቃል ስትሰማው ቆይታለች። የልጇ ናፍቆት በተነገራት ቁጥር ሆዷ ይባባል፣ ዓይኗ ያነባል። እንዲህ በሆነች ጊዜ መልሳ ለመጠንከር አትዘገይም። አሁን ግን ይህ ስሜት ከእሷ ርቋል። የዘመዶቿን ቃል ሰምታ የልጇን ዓይን ማየት ጓጉታለች።
ፋጡማ ፈጥና አሰሪዋቿን ፈቃድ ጠየቀች። ለሁለት ወር ሀገሯ ቆይታ እንድትመለስ ይሁንታ ተሰጣት ። ጓዟን ሸክፋ ጉዞ ስትጀምር ትንሹ ዑስማን ይበልጥ ናፈቃት። ዓይኖቹን እያየች አንገቱ ስር ገብታ እስክትስመው ቸኮለች።
አዲስ አበባ ስትደርስ እህቷ ተቀበለቻት። ጥቂት ቆይቶ ልጇና ባለቤቷ በቅርብ መኖራቸውን አወቀች። እሷ እንዳሰበችው ትንሹ ዑስማን ትምህርት ቤት አልዋለም።ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ገብቶ መታከም ጀምሯል። ፋጤ የሰማችውን ማመን አልቻለችም። በድንገጤ ልቧ እየመታ የሆነውን ጠየቀች።
ልጇ ከታመመ አንድ ዓመት ከአራት ወር እንደሆነው ተነገራት። ፋጤ አባትና ልጅ ካሉበት ፈጥና ደረሰች። ባለቤቷ ተጎሳቁሏል። ትንሹ ዑስማን እንዳሰበችው አላደገም። ዕንባ አነቃት ፣ ላብ አጠመቃት። ልጇን እየሳመች፣ ፀጉሩን እያሻሸች ስለ ሕመሙ ጠየቀች ። ችግሩ ከአንገቱ የወጣች ትንሽ ዕባጭ ስለመሆኗ ቀለል አድርገው ነገሯት ።
ፋጡማ በእጇ ያለውን ገንዘብ መንዝራ ልጇን ለማሳከም ተነሳች። ይሄኔ ባለቤቷ ቀስ እያለ ያረጋጋት ያዘ። የልጃቸው ሕመም እንደተነገራት ሆኖ ቀላል አልነበረም። የባሏን የመጨረሻ ቃል በጭንቀት ጠበቀች። የሰማችውን አምኖ መቀበል ተሳናት ። አንድ ልጇ የደም ካንሰር በሚሉት ሕመም ስለመያዙ ሰማች።
ፋጡማ ከዚህ ቃል በኋላ ራሷን በዱላ እንደመቷት አቅሏን ሳተች። ካንሰር ከባድና የማይድን ሕመም መሆኑን ደጋግማ ሰምታለች። ዙሪያው ጨለመባት፣ የት እንዳለች ጠፋት፣ ወዴት እንደምትሄድ ግራ ገባት። በውሰጧ ያለው ሃሳብ አንድ ልጇ እንደማይድን ሹክ እያላት ነው። ልቧ ፈራ ፣ ክፉኛ ተጨነቀች።
ውሎ አድሮ ፋጡማ ለሰዎች ምክር ጆሮ ሰጠች። የዑስማን ዓይነት ሕመም ያላቸው ልጆች በርካታ መሆናቸው ተነገራት። ችግሩ ቀድሞ ከተለየ ሕክምናው እንዳለ ባወቀች ጊዜ ተስፋዋ ለመለመ። ተረጋግታ ጥቂት ቀናት ከልጇ አሳለፈች። አባት ዑስማንን ይዞ ሕክምናውን ሲቀጥል እሷ ሀገሯ ደርሳ መምጣት አሰበች።
የነበረው እንዳልነበረ
ፋጡማ ከሀገር ቤት ስትወጣ ብዙ ውጥን ይዛ ነው ለባሏ በምትልከው ገንዘብ ቤት እንደሚሰራ ታውቃለች። ከትናንት በተሻለ ነገን ለመድረስ በዓረብ ሀገር ጉልበት መክፈሏ ግድ ሆኗል። ይህን እያሰበች ወሎ ሀይቅ የገባችው ፋጤ ከመኪና ወርዳ ወደ ሰፈሯ አቀናች።
ፋጤ ከቤቷ ስትደርስ፣ በዕልልታ የተቀበላት፣ በደስታ አቅፎ የሳማት የለም። ጓዳ ሳሎኗ ‹‹ኦና›› ሆኗል። የትናንት ጥሪቷ ደብዛው የለም። ንብረቷ ተበትኗል። የጓሮ ሰብሏ ጠፍቷል። ላሞቹ አይታዩም። የእርሻ በሬዋ ተሸጧል። ይህን ስታይ ሆድ ባሳት፣ ባዶነት ተሰማት።
ፋጡማ እንደከፋት ዙሪያ ገባውን ቃኘች። ስትለፋለት የነበረው ቤት አልተሰራም። እንዲህ የሆነው በልጇ መታመም ነው። አምርራ አለቀሰች። ሁኔታዋን ያዩ ከቤቷ ገብታ እንድታርፍ አግባቧት። እሷ ሕይወት አልባውን ጎጆ አልመረጠችም። ሁሉን ትታ ከወንድሟ ዘንድ ከረመች።
ፋጡማ ተመልሳ ሳትሄድ አባትና ልጅ ከአዲስ አበባ ተመለሱ። ዑስማን ቀጠሮ ተሰጥቶት መድኃኒት ታዞለታል። አባወራው መንደሩ ሲገባ ሚስቱን ከቤት አላገኘም። በሁኔታዋ ቢከፋም አላዘነባትም። ካለችበት ሄዶ ከቤቱ መለሳት።
ፋጡማ እንደ አዲስ ባለትዳር ጎጆዋን ቀለሰች። ባዶ ጓዳዋን ልትሞላም የእጇን ሰነዘረች። ያለ ሰው የከረመው ቤት ጸድቶ፣ ተጠርጎ እንደምንም አንሰራራ። ከእናቷ ማጀት የመጣው እህል ተጋግሮ ቤተሰቡ ለገበታ በቃ። አሁን በነፋጡማ ቤት ስለነገ ማሰብ ቀርቷል። የሁሉም ዓይን ከዑስማን ውሎ ተስፋ እየጠበቀ ነው።
ከአስራ አምስት ቀን በኋላ ዑስማን ለቀጠሮው አዲስ አበባ ተመለሰ። ይሄኔ ፋጡማ ተመልሶ መሄዱን ትታ ባሏን መደገፍ፣ ልጇን ማገዝ ፈለገች። ይህ ፍላጎቷ ከአባወራዋ አነጋገራት። እሱ ወደ እርሻው እንዲመለስ ነገረችው። ባል ይህን ቢያደርግ፣ የጎደለ ማሳውን ቢመልስ ፈቃዱ ነው። እንደ ሀሳቧ ለመሆን ግን ጥርጣሬ ገባው። ከእሱ በላይ ለዑስማን የሚደርስ የሚያውቅለት እንደሌለ ቢሰማው ኃላፊነቱን ለመስጠት ‹‹እምቢኝ›› አለ። ፋጡማ ባሏ ያለፈበትን የመከራ መንገድ ልትጓዝበት አልዘገየችም።
ሁለቱም ስለአንድዬ ልጃቸው ዋጋ ሊከፍሉ ተሸቀዳደሙ። ባልና ሚስት ስለ አንድዬ ልጃቸው መከሩ። ኋላ ኋላ አባወራው ተሸነፈ። ለአሁኑ ልጁን እናት ተቀብላ እንድታሳክም ተወስኖ በምርቃት ተለያዩ።
አሁን ፋጤ ከእጇ የቀረውን ስምንት ሺህ ብር ለበሬ መግዣ ሰጥታለች። አባወራው ከሌሎች አቀናጅቶ እርሻውን ጀምሯል። በብድር የተገዙት በጎች ከሜዳ ይውላሉ። ሕይወት በአዲስ ሊጀመር መውተርተር ተይዟል። ዑስማን ቀጠሮ ባለው ጊዜ አዲስ አበባ እየቆየ መመለስ ግድ እያለው ነው። እንዲህ መሆኑ ለቤተሰቡ ኑሮን አላቀለለም።
ከዓመታት በፊት የአባወራው ፈተና
አባወራው ባለቤቱ ዓረብ ሀገር ሄዳለች። ሁለቱም ስለነገ ብዙ ወጥነዋል። ከምንም በላይ የአንድ ልጃቸው ሕይወት ያሳስባቸዋል። የዑስማን አባት የልጁን መታመም ያወቀው በአጋጣሚ ነበር። ዑስማን ከትምህርት ውሎ ሲገባ ድካሙን ያያል። ርቦት ይሆናል ብሎ ምግብ ይሰጠዋል። ልጁ የእህል ዘር ማየት አይሻም። አንዳንዴ ለመብላት ልቡ ቢፈቅድ ካፉ ሲደርስ አይጥመውም። እሱን ትቶ መረር ፣ ጎምዛዛውን ይፈልጋል። በየምክንያት ሰበቡ መበሳጨት ልማዱ ነው።
ዑስማን ከቤት በወጣ ጊዜ መንገድ ይርቀዋል። ከእኩዮቹ እኩል አይራመድም። ከኋላ ቀርቶ አዝግሞ ይገባል። ውሃ ሲጠጣ ጥሙን አይቆርጥም። ይህ ስሜቱ ከደስታ አርቆታል። አባት ችግሩ ሲገባው ሆስፒታል መውሰዱ አልቀረም። የሐኪም ውጤት ችግሩ ታይፎይድና ወባ መሆኑን ጠቁሟል።
ሁሌም የሚሰጠው መድኃኒት ለውጥ አላመጣም። ‹‹ተሽሎታል›› ሲባል ያገረሸዋል። ‹‹ዳነ›› ሲባል ካልጋ ይውላል። አባት ሁኔታው እያሳሰበው ነው። አሁንም ዝም አላለም። ደሴ ከሚገኝ የግል ሆስፒታል ወስዶ አስመረመረው። በጊዜው የተገኘው ውጤት የዑስማን ችግር የደም ማነስ መሆኑን አመለከተ። ከሆስፒታሉ ለቀናት ተኝቶ የሌላ ሰው ደም እንዲሰጠው ሆነ። እናት ፋጡማ ከሰው ሀገር ላቧ ያላትን እየላከች ነው። እሷ አዲስ ቤት መስራቷን እንጂ ልጇ መታመሙን አታውቅም። አባት ስለልጁ ጤና እየዋተተ ነው። ድካሙ አልያዘለትም። ዑስማን ልጁ በጎ አልሆነም። አልተሻለውም።
ውሎ አድሮ ከሐኪሞች ምክር ተገኘ። የዑስማን ሕመም ከባድ በመሆኑ አዲስ አበባ እንዲወስደው ተነገረው። አባወራው ከደሴ አልፎ አያውቅም። አዲስ አበባ ‹‹የኔ›› የሚለው፣ መጠጊያ ዘመድ የለውም። እንዲያም ሆኖ ምርጫ አልነበረም። ትንሹ ልጁ ይድን ዘንድ ጉዞውን ከታሰበው መንገድ ጀመረ።
ግራ መጋባት- በአዲስ አበባ
አባትና ልጅ አዲስ አበባ ካደረሳቸው መኪና ሲወርዱ መገኛቸው ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሆነ። የያዙት ማስረጃ አግዟቸው ዑስማን አልጋ ይዞ እንዲታከም ተፈቀደለት። ሁለት ወራትን ያስቆጠረው ሕክምና ያለዘመድ ጉብኝት በብቸኝነት አለፈ።
ሂደቱ እንዳበቃ ዑስማን ከሆስፒታል ወጥቶ በክትትል መታከም ነበረበት። ይህ እውነት የተነገረው አባወራ ልጁን ይዞ ለመውጣት ተቸገረ። ባለበት ቦታ ‹‹እከሌ›› ብሎ የሚጠራው ሰው የለም። አባት በትካዜ አንገቱን ደፋ። ዑስማንን ይዞ ይሄድ፣ ይደርስበት መንገድ ጠፋው። በብቸኝነት ግራ ተጋባ።
ችግሩን ያስተዋሉ ባይተዋርነቱን ያወቁ ዕንባውን ሊያብሱለት አልዘገዩም። ዑስማንን የመሰሉ የካንሰር ሕሙማን የሚያርፉባቸው ማዕከላት ስለመኖራቸው ጠቆሙት። አባወራው ልጁን ይዞ ወደተባለው ሥፍራ አመራ። በዚህ ሥፍራ እግሩ ከደረሰ ወዲህ የት ልግባ ብሎ አልተጨነቀም። ጥቂት የማይባል የመከራ ዓመታትን ግን መግፋት ያዘ።
ቀጠሮው ሳብ ሲል ሀገር ቤት ሊሄድ እግሩ ይቀናል። ጊዜው ሲደርስ ደግሞ ከማዕከሉ ይመለሳል። አባወራው የነጻ ሕክምናው እስኪገኝ ስለልጁ ጤና ያልሞከረው የለም። የፋጡማ ገንዘብ ሳይበቃው የአባቱን በሬ ሸጧል። ሀብት ንብረቱን ጨርሶ ጥሪቱን አሟጧል።
እናት ፋጡማ ለልጇ
ፋጡማ ዓሊ ዛሬን ወንዱ ኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ ማዕከል ውስጥ ትገኛለች። አንደበተ ሸጋ ነች። ያሳለፈችውን ስትናገር ለአፍታ አትሰለችም። ቃሏ ይጣፍጣል። ከገጽታዋ የሚታየው ጥንካሬ ግን ከዚህ የዘለለ ነው። ያለፉ የማይመስሉ መከራዎች፣ የተሸነፉ የማይመስሉ የመከራ ቀናትን ድል ነስታለች። ፋጤ በሥፍራው ለመገኘቷ ሚስጥሩ የልጇ ዑስማን ጤንነት ነው። በዚህ ተቋም ብዙ አግኝታለች። ምስጋናዋ የበዛ፣ አክብሮቷ የተለየ ነው።
ዑስማን ለእሷና ለባለቤቷ አንድ ልጃቸው ነው። ገና ከሰባት ዓመቱ ጀምሮ በተገኘበት የደም ካንሰር ብዙ ዋጋ ከፍሏል። ይህ ክፍያ ግን የእሱ ብቻ አይደለም። እናቱ ስለእሱ ያልሆነችው የለም። ኑሯቸው ግብርና ነውና ሕይወታቸው ከገጠር ነው። እንዲያም ሆኖ ፋጤ ዝም አላለችም። ቤት ጓዳዋን ዘግታ፣ ዓለም ትዳሯን ትታ ስለ ዑስማን ታግላለች። አዲስ አበባ እያመላለሰች ጤናውን ልትመልስ ተስፋ ጥላለች።
ፋጤ አዲስ አበባ ስትመጣ ከቤት የሚቀረው አባወራ ሴት የምትሞላው ሙያ ይቸግረዋል። ቆሞ ለመሄድ፣ በልቶ ለማደር የሚያግዘው የለም። ይሄኔ ቂጣ እስከ መጋገር ይደርሳል። ፋጤም ብትሆን ባሏ ከሌለ ጎዶሎዋ ይበዛል። የወንዱ ሥራ ይቸግራታል።
እህል ሲታጨድና ሲወቃ ብቻዋን ናት። ባልና ሚስት በአንድ የሚሰሩት ሁሉ በእሷ ትከሻ ብቻ መውደቁ ብርቅ አይደለም። ይህ ሁሉ ዋጋ ስለ አንዱ ልጅ ዑስማን ሲባል ነው። በእሱ ጥንዶቹ ነገን አሻግረው ያያሉ። መዳኑን ተስፋ አድርገው መልካም ቀንን ይመኛሉ።፡
ሌሎች ስለእነሱ
የባልና ሚስቱን ብርታት ያዩ ሁሉ ገረሜታቸው የተለየ ነው። ሁሌም የሚከፍሉት ዋጋ የበዛ ሲመስላቸው ያልተገባውን ይመክሯቸዋል። እሱን ትተው ሌላ እንዲወልዱ፣ በእሱ ተስፋ እንዳይጥሉ ይነግሯቸዋል። አንዳንዶች ደግሞ የእነሱን አዲስ አበባ መመላስ ከምቾት ቆጥረው ብዙ ይላቸዋል። ሌሎች ጠጋ ብለው እንደሱ ዓይነት ልጅ ቢኖራቸው ትተውት እንደሚመጡ እየነገሩ ውስጣቸውን ያደሙታል። እነሱ ግን ሁሌም ስለ ዑስማን ያላቸው አቋም የፀና ነው። ዛሬን አድነውት ነገን በተስፋ ማየት።
ዑስማን ዛሬ
ዛሬ ዑስማን የአስራ ሰባት ዓመት ወጣት ሆኗል። ከታመመ አስር ዓመታት ቢያስቆጥርም አሁን በደሙ የደም ካንሰር አይታይም። ከጊዜ በኋላ ያጋጠመው የነርቭ ሕመም ግን ጤናውን እየፈተነው ነው። እንዲያም ሆኖ ከትምህርቱ አልቦዘነም። ያቋረጠውን ትምህርት ቀጥሎ ስድስተኛ ክፍል ደርሷል። አንባቢና ፀሐፊ ነው። ዶክተር የመሆን ህልሙ ብሩህ ሆኖ ይታየዋል።
ጎበዝና የደረጃ ተማሪ የሆነው ዑስማን አንዳንዴ መቼ ነው የምድነው ሲል ራሱን ይጠይቃል። መርሳትና መበሳጨት ቢታይበትም ባህርይው አያስቸግርም። ፋጤ ትናንት ከልጇ ጋር የነበሩ መሰል ልጆች ዛሬ በሕይወት እንደሌሉ ታውቃለች። የዛኔ በመጀመሪያ ሕመሙ የታየበት የእሷ ልጅ ነበር። ይህን ስታስብ ዑስማንን ‹‹ጌጤ ወርቄ፣ ተስፋ አስትንፋሴ ›› ትለዋለች። እንደብረት የጠነከረችው፣ እንደ እዮብ የጸናችው ብርቱዋ እናት ፋጡማ ዓሊ።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን መስከረም 26/2016