ዘንድሮ እንደሚጠናቀቅ የሚጠበቀው የኮልፌ ጠቅላላ ሆስፒታል ግንባታ ፕሮጀክት

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህብረተሰቡን መሠረታዊ ችግሮች የሚቀርፉና ሰው ተኮር ፕሮጀክቶችን እየገነባ ለአገልግሎት ክፍት እያደረገ ይገኛል። ፕሮጀክቶቹ የመዲናዋን ውበት የሚጠብቁ፣ ለኑሮ፣ ለመዝናኛ፣ ለአገልግሎት ምቹ እንዲሆኑ ተደርገው የሚገነቡም ናቸው።

ከተማ አስተዳደሩ ፕሮጀክቶቹን እያስገነባ ያለው የግዙፍ ፕሮጀክቶች ጽሕፈት በማቋቋም እንዲሁም በከተማዋ ኮንስትራክሽን ቢሮ በኩል ነው። ሜጋ ፕሮጀክቶች ጽሕፈት ቤቱ ከሚያስገነባቸው ፕሮጀክቶች መካከልም አቃቂ አካባቢ የሚገነባው የሴቶች ተሐድሶ እና የክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል እና የኢንዱስትሪ ክላስተር፣ አይሲቲ አካባቢ የሚገነባው የሥራ አመራር አካዳሚ፣ በመዲናዋ መውጫ በሮች ተገንብተው ወደ ሥራ የገቡና እየተገነቡ የሚገኙ የግብርና ምርቶች የገበያ ማዕከላት ይገኙበታል።

ግንባታቸው በጥሩ አፈጻጸም ላይ የሚገኙት መገናኛ ሾላ አካባቢ የሚገነባው የየካ ፓርኪንግ ሁለት እና እዚያው መገናኛ አካባቢ እየተገነባ የሚገኘው የተለያዩ የትራንስፖርት ተቋማት መሥሪያ ቤቶች ህንጻ ግንባታ ሌሎች ከተማ አስተዳደሩ እያስገነባቸው የሚገኙ መሠረተ ልማቶች መካከል ተጠቃሾች ናቸው።

በከተማዋ እምብርት በርካታ አገልግሎቶችን እንዲሰጥ ታስቦ ግንባታው እየተጠናቀቀ ያለው የዓድዋ ሙዚየም ግንባታ፣ ግንባታው ተጠናቆ ወደ ሥራ የገባው የጎተራ ጎፋ ማዞሪያ ሣር ቤት መንገድ ማሳለጫ እንዲሁም አብዛኛው ግንባታው ተጠናቆ ወደ ሥራ የገባው የቃሊቲ ቱሉ ዲምቱ መንገድ ግንባታም እንዲሁ በከተማ አስተዳደሩ የተገነቡ ፕሮጀክቶች ናቸው።

ከተማ አስተዳደሩ የከተማዋን የተጠራቀሙ የመሠረተ ልማት ችግሮች ለመፍታት የሚያካሂደውን ግንባታ ቀጥሏል። በዚህም የህብረተሰቡን የጤና አገልግሎት ለማስፋት የሚያግዙ የሆስፒታል ማስፋፊያዎችን ከማድረግ በተጓዳኝ በከተማዋ ማስፋፊያ አካባቢዎች አዳዲስ ሆስፒታሎችን እየገነባም ይገኛል። ሆስፒታሎቹ የሚገነቡት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ጀሞ አካባቢ እና በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ቤቴል አካባቢ ነው።

የሆስፒታሎቹ መገንባት ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥሩ እየጨመረ ለመጣው በማስፋፊያ አካባቢ ለሚኖረው የመዲናዋ ሕዝብ የጤና አገልግሎት ፍላጎትን ለመመለስ ፋይዳቸው ከፍተኛ እንደሆነ ይታመናል። በእነዚህ አካባቢዎች የመዲናዋ ሕዝብ የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት በሚያደርገው ጥረት ከፍተኛ እንግልት ሲደርስበት ኖሯል። ወረፋ ጥበቃው፣ የሆስፒታሎች ርቀት፣ አልጋ ለማግኘት ያለው ፈተናና የመሳሰሉት የከተማዋን ሕዝብ በእጅጉ ሲገዳደሩት የቆዩ ችግሮች መሆናቸው ሲነገር ይደመጣል።

የከተማ አስተዳደሩም ይህንን በመመልከት ሆስፒታል በሌለባቸው የከተማዋ ክፍለ ከተሞች የአዳዲስ አጠቃላይ ሆስፒታሎች ግንባታ በአዲስ አበባ ዲዛይንና ግንባታ ሥራዎች ቢሮ በኩል እያካሄደ ይገኛል። የዛሬው መሠረተ ልማት አምዳችን በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ እየተገነባ የሚገኘውን ሆስፒታል የግንባታ ሂደት ያስቀጥላል፡፡

የአዲስ አበባ ዲዛይንና ግንባታ ሥራዎች ቢሮ የኮንትራት አስተዳደር ባለሙያ ወይዘሮ ፈትሃ ነስሩ እንዳብራሩት፤ የኮልፌ ጠቅላላ ሆስፒታል የከተማ አስተዳደሩ ትኩረት ሰጥቶ ከሚያስገነባቸው ፕሮጀክቶች አንዱ ነው። በከተማዋ የጤና አገልግሎት ፍላጎት ከፍተኛ በመሆኑ እና ሆስፒታሎች በየክፍለ ከተሞቹ ባለመኖራቸው የተነሳም ህብረተሰቡ ራቅ ወዳሉ አካባቢዎች በመሄድ አገልግሎቱን ለማግኘት ሲገደድ ቆይቷል። በአካባቢው የመንግሥት ሆስፒታል የሌለ በመሆኑ የአካባቢው ማህበረሰብ የሆስፒታል አገልግሎት እያገኘ ያለው ረጅም ርቀት በመሄድ እና ከፍተኛ ወጪ በማውጣት መሆኑን ወይዘሮ ፈትሃ ተናግረዋል። የሆስፒታሉ ግንባታ መጠናቀቅ ህብረተሰቡ በጉጉት እየተጠባበቀ እንደሚገኝም ነው ያመለከቱት።

በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሰባት ቤቴል አካባቢ የሚገነባው ይህ አጠቃላይ ሆስፒታል ግንባታው መንግሥታዊ በሆነው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን (ኢኮስኮ) የግንባታ ሥራ ተቋራጭነት እየተካሄደ መሆኑን የኮንትራት አስተዳደር ባለሙያዋ ጠቅሰው፣ ተቋራጩ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የሚገነባውን ሆስፒታል ጨምሮ ሌሎች ሰፊ ሀገር አቀፍ መሠረተ ልማቶችን እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። ከተማ አስተዳደሩ በጀት በሌለበት ሁኔታ ላይ ሆኖ የጤና መሠረተ ልማቱ ለህብረተሰቡ አስፈላጊ መሆኑን በማመን ከፍተኛ በጀት ይዞ በልዩ ትኩረት የሚያስገነባው መሆኑንም ይናገራሉ።

የኮልፌ ጠቅላላ ሆስፒታል ግንባታ ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር የአካባቢው ማህበረሰብ የሆስፒታል አገልግሎት ለማግኘት በሚያደርገው ጥረት የሚደርስበትን እንግልት ያቃልላል የሚል እምነት እንደተጣለበትም ይገልጻሉ።

እሳቸው እንዳሉት፤ የዚህ ሆስፒታል ግንባታ አብዛኛዎቹ የስትራክቸር ሥራዎች ተጠናቅቀዋል፤ በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ የግንባታው አፈጻጸም 55 ነጥብ 24 በመቶ ላይ ይገኛል።

ሆስፒታሉ በ33 ሺ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ ሲሆን፣ ከዚህም ውስጥ 11 ሺ 300 ካሬ ሜትሩ ሕንፃዎች ያረፉበት ቦታ ነው። አጠቃላይ በጀቱም ከሶስት ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ብር በላይ ነው።

እሳቸው እንዳሉት፤ የሆስፒታሉ ግንባታ በፈጠረው የሥራ እድልም (በቋሚና እና ኮንትራት ቅጥር ከ70 በላይ እንዲሁም በጊዜያዊ የሥራ እድል ከ500 በላይ ሰዎች )ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ግንባታው ለሆስፒታል አስፈላጊ የሆኑ እንደ ጋራዥ፣ መጋዘን፣ የተሟላ የመኪና መቆሚያ፣ የውሃ እና የመብራት አገልግሎት መስጫ፣ የቆሻሻ ማስወገጃ፣ የተሟላ መታጠቢያና መጸዳጃ ቤት፣ የኤክስ-ሬይ(x-ray)፣ እና ለሕክምና አስፈላጊ የሆኑ ክፍሎች ይኖሩታል።

የኮልፌ ቀራንዮ ጠቅላላ ሆስፒታል የሎት አንድ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር በዕውቀት መራ በበኩላቸው እንደገለፁት፤ የግንባታ ፕሮጀክቱ 14 ሕንጻዎች ያሉት ሲሆን፣ ግንባታውም በሎት ተከፋፍሎ እየተካሄደ ይገኛል። በሆስፒታሉ ሎት አንድ፤ ሕንፃ አንድ፣ ሁለት፣ ሶስት፣ አራት፣ ስድስት፣ ሰባት፣ ዘጠኝ፣ አስር፣ አስራ ሁለትና ሕንፃ አስራ አራት ይገኙበታል። በሎት ሁለት ሥር ደግሞ ሕንፃ አምስት፣ አስራ አንድ፣ አስራ ሶስት እና ሕንፃ ስምንት የሚባሉ በሎኮች ይገኙበታል። ሎት አንድ 323 አልጋዎች፤ ሎት ሁለት አጠቃላይ 100 አልጋዎች በጠቅላላው 423 ያህል አልጋዎች ይኖሩታል።

ግንባታው በግንባታ ቴክኖሎጂዎች በተዘጋጀ የአርማታ ሙሌት የሚያከናወን ነው። በመሆኑም የኮንክሪት ሙሌት ሳይት ላይ የሚዘጋጅ ሳይሆን ተዘጋጅቶ በሚቀርብ አርማታ በፓምፕ የሚሞላ ነው። የሥራ ተቋራጩ በቂ ልምድ ያለው እና ብዙ የመንግሥት እና የግል ፕሮጀክቶችን በወቅቱ አጠናቆ ያስረከበ ተቋራጭ መሆኑንም ገልጸዋል። የሆስፒታሉ ግንባታ እ.ኤ.አ ሐምሌ 2 ቀን 2021 የተጀመረ መሆኑን ጠቅሰው፣ ግንባታውን በተያዘው 2016 በጀት ዓመት ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

የሆስፒታሉ ግንባታ የአእምሮ ሕክምና፣ የእናቶች እና የሕፃናት ሕክምና፣ የካንሰር ሕክምና መስጫ እና ማዋለጃ፣ የድንገተኛ ክፍል፣ ላብራቶሪ ፣ አክስ-ሬይ/ X-ray/፣ የጨረር ሕክምና (Nuclear medicine)፣ የሥነ-ልቦና ሕክምና መስጫ፣ የቀዶ ጥገና ሕክምና መስጫ፣ ማቀዝቀዣ ክፍል፣ ቤተመጻሕፍት፣ ካፍቴሪያ እና መሰብሰቢያ አዳራሽ የያዘ ነው።

የአእምሮ ሕሙማን፣ የእናቶች እና ሕጻናት፣ የኤክስ- ሬይ እና የተለያዩ ምርመራዎች እንዲሁም የካንሰር ሕክምናን ጨምሮ ህብረተሰቡ የተቸገረባቸውንና ለአላስፈላጊ ወጪ የሚዳረግባቸውን ሕክምናዎች አቅፎ የሚይዝ ሆስፒታል እንዲሆን ተደርጎ እየተገነባ ይገኛል። ከአንዳንድ ትላልቅ ሆስፒታሎችም በበለጠ በተሟላ ሁኔታ አገልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ የሚገነባ ትልቅ ሆስፒታል ነው ብለዋል።

የግንባታ ሂደቱ እንደተጀመረ በቁፋሮ ሂደቱ ላይ ባጋጠመው ጠንካራ አለት እንዲሁም ፤ አንዳንድ የዲዛይን ጉዳዮች የተወሰነ መዘግየት መታየቱን ጠቅሰው፣ አሁን ግንባታው በተሻለ ደረጃ ላይ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

የሎት አንድ ግንባታ በሕንፃ ሁለት እና ሕንፃ ሶስት፦ ለአእምሮ ጤና ክሊኒክ፤ ለኦብስቴሪክና ጂኒዮሎጂ ሕክምና፤ ለውስጥ ደዌ ሕክምና አገልግሎት የሚውሉ ከምድር በታች ወለሎች፣ በመጀመሪያ ወለል እና በሁለተኛ ወለል በአጠቃላይ 66 አልጋዎች ይኖሩታል።

ሕንፃ አራት፦ ግራውንድ ወለል ጨምሮ በጠቅላላው አራት ወለሎች ሲኖሩት የእናቶች ሕክምናን ጨምሮ ለተለያየ አገልግሎት የሚውሉ አጠቃላይ 71 አልጋዎች የማስተናገድ አቅም ያለው ነው። ሕንፃ ስድስት እና ሕንፃ ሰባት፦ በግራውንድ ወለሉ ስድስት ክፍሎቸ ይኖሩታል። የመጀመሪያ ወለል፣ ሁለተኛ ወለል እና ሶስተኛ ወለልን ጨምሮ ለተለያዩ የሕከምና አገልግሎቶች የሚያገለግሉ 81 አልጋዎች የማስተናገድ አቅም አለው።

ሕንፃ ዘጠኝ እና ሕንፃ 12፦ ሕንጻዎቹ በተመሳሳይ ግራውንድ ወለልን ጨምሮ በጠቅላላው አራት ወለሎች ሲኖሯቸው፣ በግራወንድ ወለሉ ላይ የፔዲያትሪክ እና የሳይካትሪክ ድንገተኛ አገልግሎቶች የሚሰጡባቸውን ክፍሎች ጨምሮ በመጀመሪያ ወለል፣ በሁለተኛ ወለል እና በሶስተኛ ወለል ላይ ለሌሎች የሕክምና አገልግሎቶች የሚውሉ በጠቅላላው 51 አልጋዎችን ይይዛል።

ሕንፃ 10፦ የሕንጻው የመጀመሪያው ቤዝመንት ለላብራቶሪ አገልግሎት የሚውል ሲሆን፣ የግራውንድ ወለሉ መጋዘን እና የምግብ ማዘጋጃ ቤትን ጨምሮ ለካፍቴሪያ አገልግሎት የሚውል ግንባታ ተካተውበታል። የዚህ ሕንፃ የመጀመሪያው ወለል ደግሞ የማገገሚያ፣ የቅድመ ኦፕሬሽን ክፍልንና የስቴራላይዜሽን ክፍሎች አሉት።

ሕንፃ 14፦ ከምድር በታች በሁለተኛው (ሰከንድ ቤዝመንት) ወለሉ ላይ ዘጠኝ የሕሙማን አልጋዎችና ሁለት የፕሮሲጀር ክፍሎች ይኖሩታል። ከምድር በታች የመጀመሪያው (ፈርስት ቤዝመንት) ወለል ሕክምናቸውን ጨርሰው ለሚወጡ ታማሚዎች የሚሆኑ 20 የምርመራ ክፍሎች አሉት። በምድር (ግራውንድ) ወለሉ ላይም ለድንገተኛ እና የወጪ ታካሚዎች የሚያገለገሉ 17 የምርመራ ክፍሎች እንዲሁም ለውጭ ታማሚዎች የሚውል መድኃኒት ቤትን ያካተተ ነው።

በሕንጻ 14 የመጀመሪያው ወለል ለጥርስ ሕክምና ክሊኒክ፣ ለላቦራቶሪ እና ለኦርቶዴንቲክስ፣ ለፕሮስቶዶንቲክስ፣ ለኤክስ-ሬይ ክፍሎች እንዲሁም ሁለት ለምርመራ ክፍሎች፣ ለስቴራላይዜሽን ክፍሎች እና ለመድኃኒት ቤቶች የሚውሉ ግንባታዎች ተካተውበታል። አራት ለጂንኮሎጂ (Gnnecology) የሚውሉ ክፍሎች፣ ሁለት የአልትራሳውንድ ክፍሎች እና ስድስት የምርመራ ክፍሎችንም የያዘ ግንባታ ነው።

የሄሞዲያለሲስ ክፍሎቹም ለሶሻል አገልግሎቶች መስጫ የሚውሉ ስምንት አልጋዎችም እንዲኖሩት ተደርጎ እየተገነባ ይገኛል። በዚሁ ሕንጻ 14 ሁለተኛ ወለል ላይ የዴይ ኬር፣ ከሁለት እስከ አምስት ዓመት እድሜ ያላቸው ሕፃናት መዋያ ክፍሎች፣ የአስተዳደር ቢሮዎችንና የስብሰባ አዳራሾችን ያካተተ መሆኑም አብራርተዋል።

ኢንጂነር በዕውቀት እንዳብራሩት፤ ግንባታው በአንድ ጊዜ 130 መኪናዎችን ማስተናገድ የሚችል የመኪና ማቆሚያ ይኖሩታል። በቀን ለ500 ሕሙማን አገልግሎት መስጠትም ይችላል። በሎት ሁለት ግንባታው የሕንፃ አምስት፣ አስራ አንድ፣ አስራ ሶስት እና ሕንፃ ስምንት ግንባታ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።

ሕንፃ አምስት፦ በጠቅላላ 68 አልጋዎች ያሉት ሲሆን በግራውንድ ወለል ላይ የራዲዮኒውክላር እና ራዲዮ ፋርማርሲ ክፍሎች ይኖሩታል። በመጀመሪያው ወለሉም የሰርጂካል አይሲዩ ሰባት የአልጋ ክፍሎች ይኖሩታል። በሁለተኛው ወለል ላይ ፔዲያትሪክስ አምስት የአልጋ ክፍሎች፣ የአይሶሌሽን ክፍሎች አሉት። እንዲሁም በሶስተኛ ወለሉ የውስጥ ሕክምና ስድስት የአልጋ ክፍሎች፣ የአይሶሌሽን እና ፕሮሲጀር ክፍሎች አሉት። ሕንፃ 11፣ 13 እና 8 አጠቃላይ 32 አልጋዎች አሉት።

 በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን መስከረም 26/2016

Recommended For You