ድሮ ድሮ ውሸት በኢትዮጵያ ውጉዝ ከመ አሪዎስ ነበር አሉ የሚባለው። በጥንታዊቷ ኢትዮጵያ ዋሽቶ መኖር እንኳን ሊደረግ የሚታሰብ አልነበረም። ጥንት አንድ ሰው ዋሸ ማለት ከሰውም ከፈጣሪውም ተጣላ ማለት ሲሆን፣ ተመልሶ ለመታመን የሕይወት ዘመኑ እንኳን አይበቃውም ሲባል ነበር የሚሰማው። ተጽፎ የሚገኘውም ይሄው እንጂ ሌላ አይደለም።
በድሮዋ ኢትዮጵያ ለእውነት የሚሰጠው ስፍራ ከሁሉም በላይ የላቀ ነው። ስለ እውነት ሲባል ይሞታል እንጂ እውነት ለውሸት ቀብድ መያዣ አትደረግም። የፍትህ ሥርዓቱ መሰረቱ እውነት ነው፤ የአስተዳደር ሥርዓቱ ሞተሩ እውነትና እውነት እንጂ ሌላ ሆኖ አያውቅም። በመሆኑም፤ በአደባባይ የፍትህ ሥርዓት አሰጣጥ (የ“በላ ልበልሃ″ ፍርድ ሂደት) የሚጀመረው፣
በላ ልበልሃ
የአፄ ሥርዓቱን፣
የመሰረቱን፤
አልናገርም ሀሰቱን፣
ሁሌ እውነት እውነቱን፤ (“እውነቱን ተናግሮ የመሸበት ማደር″ ይሏል ይህ ነው)
በሚለው ነበር። በዛሬይቱ ኢትዮጵያ (በድፍን ዓለም ጭምር) ይሄ የ“ፋራ″ና ያለመሰልጠን ነው።
የዛሬን አያድርገውና፣ በጥንታዊቷ ኢትዮጵያ (እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ) በኢትዮጵያዊያን ልብና ህሊና ውስጥ ፈሪሀ እግዚአብሔር ጠፍቶ አያውቅም ነበር። በውሸት መማል፤ በሀሰት መመስከር፤ አድሏዊነት፣ ሙሰኝነት … በኢትዮጵዊያን ዘንድ ጥዩፍ ብቻ ሳይሆኑ ሀጢያትም ነበሩ። (“ነበሩ”ስንል በፀፀት ነው።)
በድሮው የሀገራችን ዘመናት ሀሰት ከሰው በታች ያደርጋል። ሀሰተኛ መሆን ቃል አባይነት ነውና “ልጅህን ለልጄ” የሚለው ሰው እንኳ የለም። እንደ አንዳንድ የጽሑፍ መረጃዎች ከሆነ፣ “ዋሾ” መሆን ያስንቃል፤ “ውሸታም” ከመባል መሞት ይሻላል። በኢትዮጵያ ዘመንና እውነት ይህንን ይመስሉ ነበር።
ያ ዘመን ለእውነት ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጥ ትውልድ የነበረበት ዘመን ሲሆን፣ በአሻራነትም “አንገት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ” የሚለው ለትውልድ ተሸጋግሮ መገኘቱ ነውና የአሁኑ ዘመን ቢያሳፍር የሚፈረድበት አይደለም።
“እውነት ለዘለዓለም አያረጅም፣ አይደክምም፣ አይቀያይርም፣ አይሸነፍም፣ ህያው ነው፣ እርሱም እየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱን እንኑረው፣ እንማረው፣ እንመነው፣ እናስተምረው፣ እናከብረው፣ እናስብው፣ እንተንብየው፣ እናንብበው፣ መድረካችን ይፈወስ፣ ልብና ህሊናችን ይመለስ፣ አንደበታችን ይቀደስ። አሜን” ይላል አንድ ከወደ ማህበራዊ ድረ-ገፅ አካባቢ አግኝቼ ማስታወሻዬ ላይ ያሰፈርኩት ጽሑፍ። እንዳለ እንቀበለውና እንለፈው።
በታላቁ መጽሐፍ የተገለፀው “እውነት፣ እውነት፣ እላችኋለሁ …” የብዙኃን የእውነት እና እምነት መሰረት ነው። በትውልዶች ያልተመረዘና ያልተከለሰ የፈጣሪ መርህ ነው። በሌሎችም ሃይማኖቶች የተለየ አይደለም፡፡ በመሆኑም ባለበት ይፀና ዘንድ “ፈቅደን” እንለፈው።
ርእሳችን ሁለት ከበድና ጠጠር ያሉ ጽንሰ ሃሳቦችን ይዟል። “ከበድና ጠጠር” ስንል ጽንሰ ሃሳቦቹ የሰው ልጅ ማሰብ፣ መጠየቅ፣ መመራመር፣ መፈላሰፍ ∙∙∙ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ያለ እረፍት የደከመባቸውና ማጠቃለያ፤ ወይም፣ ድምዳሜ ላይ ያልደረሰባቸው በመሆኑ ነው።
ብዙዎች እንደሚስማሙት ስለ አንድ ዘመን ለመነጋገር ወይም ለማጥናት በቅድሚያ የዘመኑን መንፈስ (በዚህ ጉዳይ ላይ ሰፋ አድርጎና ጠለቅ ብሎ የሄደ ሰው፣ እኔ እማውቀው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ቴዎድሮስ ገብሬ ሲሆን፣ ስራዎቹን (ለምሳሌ፣ “የዘመን መንፈስ በተመረጡ የአማርኛ ሌበ ወለዶች ውስጥ”፤ እንዲሁም “በይነዲሲፕሊናዊ ሥነጽሑፍ”ን ማየት ጠቃሚ ነው) መረዳት የግድ ይሆናል። “የዘመን መንፈስ″ (መሰረቱ ከወደ ጀርመን ስለሆነው “Zeitgeist″ ማለታችን ነው) አንድ ራሱን የቻለ ጽንሰ ሃሳብ እና የጥናት መስክ ሲሆን፣ በተለይ ታሪክን፣ ትውልድን፣ ጥበብን፣ ማኅበረሰብን ወዘተ በአግባቡ ለመረዳትና የታሪክ ትርክትን በተገቢው ሀዲድ ለማስኬድ በጣም ጠቃሚና ሚዛናዊ የሆነ አተያይ ነው።
የቴድሮስ ገብሬን ብያኔ ስንመለከተው ደግሞ “የዘመን መንፈስ የሚለው ጽንሰ ሃሳብ በዋናነት ነገሮችን ራሳቸውን ሳይሆን ነገሮች በሰው ልቡና ላይ የሚያሳድሩትን ተጽእኖ ይመለከታል፡፡ ለዘመን መንፈስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ አይደለም አቢይ ጉዳዩ፤ አብዮት አይደለም ግዱ፤ ጅሃደ ወይም የመስቀል ጦርነቱ አይደለም ትኩረቱ፡፡ ትኩረቱ እነዚህ ክስተቶች በማህበሩ ልቡና ውስጥ የሚፈጥሩት ወረራ ወይም በባሕል ላይ የሚጥሉት ድባብ ነው፡፡ በብዙዎቹ ሃያስያንና የማኅበረሰብ አጥኝዎች እምነት ደግሞ ሥነጽሑፍ ለዚህ አይነቱ ዝንቅ መንፈስ የተመቸ ማደሪያ ነው፡፡”
ወደ “እውነት” (Truth) እንምጣ።
እውነትን በተመለከተም ያለው እሰጥ አገባ እንዲህ በቀላሉ “ይሄ ነው” ተብሎ ሊገለፅ የሚችል አይደለም። በሃይማኖት በኩል ያለውን ባለበት ትተን ወደ ዓለማዊውና ፍልስፍናው ስንመጣ የምናገኘው የሃሳብ ዥንጉርጉርነት አንድ ሁለት ተብሎ የሚቆጠር አይደለም። ውስብስብ ነው።
በተለይ ፈላስፎች ትክት እስኪላቸው ድረስ ተከራክረውበታል፤ አላቆሙም። ከአገላለፆች ሁሉ ከፍ ብሎ የሚነገርለትን፣ አልበርት አነስታይንን (“እውነት አንፃራዊ ነው”) ጨምሮ የዓለም ሳይንቲስቶች ሁሉ ተራቀውበታል።
እውነትን በተለያዩ አይነቶች (types) ከፍለው የሚተነትኑ ያሉ ሲሆን፣ አንዱም እውነት ግልፅ ያልሆነና ውስብስብ ጽንሰ ሃሳብ መሆኑን የሚገልፀውና እውነትን በአራት (ተጨባጭ/objective፣ ህሊናዊ/subjective፣ የጋራ እምነት/normative፣ እና አዎንታዊ/positive truth) ከፋፍሎ የሚመለከተው Lynch, M.P (2010) ሲሆን፣ እንደዚሁ ተመራማሪ አተያይ “ተጨባጭ እውነት“ ማለት እምነት ከእውነት (እውነታ) ጋር በትይዩነት መቆም ሲችል ነው። ለምሳሌ አንድ ሰው መጽሐፍ ያነባል እንበል። በንባቡ ሂደት ከቃላት ጋር ይነጋገራል፤ አወቃቀራቸውን ያያል፣ መልእክታቸውን ይወስዳል፣ ፕሮሰስ ያደርጋል፣ ይመራመራል፣ አንድምታቸውን ይገነዘባል ∙∙∙፤ እንደ ጸሐፊው ድምዳሜ ይህ ተጨባጭ እውነት ነው። ተጨባጭ እውነት ለአድሏዊነትና ስሜት አይገዛም፤ ወይም በእነዚህ ኃይሎች አይደፈቅም።
እንደ ሊንች ትንታኔ አንድን ነገር እንደ ፈለግነው የምናደርገው ከሆነ፣ ወደ ፈለግነው የምናመጣው ከሆነና ሰዎች እኛ እንዲረዱት በፈለግነው መንገድ እንዲረዱት ካደረግነው (ልናደርገው የምንችል ከሆነ) ያ ተጨባጭ ያልሆነ ህሊናዊ) እውነት ነው። ይህንንም “We make the truth, we forge it as we see it or as we want people to see it.” በማለት ያስቀምጠዋል።
ተመራማሪው “Normative truth“ን በተመለከተ የተለያዩ ማሳያዎችን ያስቀመጡ ሲሆን፣ በአጠቃላይ ግን ይህ አይነቱ እውነት ሙሉ ለሙሉ በእኛ ስሜት ላይ የተመሰረተና ስሜታችን በፈቀደው፣ ባመነውና በወደደው ልክ እውነት ነው ብለን የምንቀበው የእውነት አይነት ነው። ይህ እውነት ወይ ግለሰብ የሰራው፣ የፈጠረው፤ አለያም የአንድ አካባቢ ማህበረሰብ “እውነት” ነው ብሎ የተቀበለው (በአብዛኛው መካሪና አስተማሪ የሆነ) የእውነት አይነት ነው። ለምሳሌ መግደል መጥፎ ነው፤ መንገድ ስታቋርጥ ግራና ቀኝ ተመልከት ∙∙∙ እና የመሳሰሉት ከዚህ የእውነት ምድብ ስር ናቸው። በአብዛኛው ይህ አይነቱ እውነት የአንድን አካባቢ ማኅበረሰብ እምነት፣ ሥርዓተ-ፆታ፣ ሃይማኖት፣ ባህል፣ የአኗኗር ዘይቤ ∙∙∙ መነሻ ያደረገ ይሆናል።
በፍልስፍና እምነት ሁላችንም አምነን እስከተቀበልነው ድረስ ሀሰት የሆነው ሁሉ እውነት፤ እውነት የሆነው ሁሉ ሀሰት ነው (በ“Truth and Falsehood“ ላይ የተጠበቡ፣ የእንግሊዙን ታላቅ ፈላስፋ በርትራንድ ራስልን ጨምሮ፣ ሥራዎች ስንመረምር የምናገኘው በዚሁ ሃሳብ ዙሪያ የሚሽከረከሩ ሆነው ነው)። ይሁን እንጂ ለጊዜው እውነት የመሰለ ሁሉ በእውነቱ መዝለቅ ሳይቻለው ይቀርና መሀል መንገድ እንኳን ሳይደርስ ይወድቃል፤ ወይም ራሱ ራሱን ሀሰት መሆኑን ያጋልጣል። ለዚህ በምሳሌነት የሚጠቀሱ በርካቶች ቢሆኑም፣ “መሬት ዝርግ ናት” የሚለውን የኖረ እምነትና እውነት በ“አይደለም፣ ክብ ናት” የቀየረው ጋሊሊዮ፤ እንደ የዘርአያዕቆብ ዘመነኛና የ17ኛው ክ/ዘ ፈላስፋ ዴካርት (René Descartes’s philosophy) ደግሞ cogito ergo sum (I think, therefore I am)፤ አስባለሁ፣ ስለዚህ አለሁ በሚለው አገላለፁ (1637 የታተመ ስራው) የራሱን እውነት ይዞ የመጣ ሲሆን፤ እነሆ እስካሁንም የጋሊሊዮም ተቀባይነትን አግኝቶ፤ የዴካርትም በሃሳብ የበላይነቱ ከበርካታ ዘመነኞቹ ጎልቶ ሊወጣ ችሏል።
“እውነት” በየፈርጁ መታየትና መመዘኑ ደግሞ ልዩ የእውነት ገፅታ ነው። ከፖለቲካው (Truth in Politics) እንጀምር።
እውነት በፖለቲካው ዘርፍ ልዩ ይዞታን የሚላበስ ሲሆን፤ ለምሳሌ፣ የኒኮሎ ማኪያቬሊ (በተለይ “ከማንኛውም መሪ የኮት የውስጥ ኪስ ውስጥ አትጠፋም” በምትባለው “The Prince″) ውስጥ፤
Politics was never about morality; rather, those who gain the most power are those who are able to adapt to the current political situation. (በግርድፉ፣ “ፖለቲካ ፈፅሞ የግብረገብ (ስነምግባር ጉዳይ አይደለም፤ ይልቁንም፣ ስልጣን የተቆጣጠሩ ኃይሎች የፖለቲካውን ሁኔታ በሚመቻቸው መልኩ የሚዘውሩበት ነው።”) በማለት የገለፀው ከብዙዎች የተለየ በመሆኑ ይህ አገላለፁ ልክ እንደ ብቻው (የእሱ ብቻ) እውነት ተቆጥሮ በብዙዎች ተደጋግሞ ሲጠቀስና ሲብራራ ይታያል።
በሥነጽሑፉ ዓለምም እንደዚሁ የሥነጽሑፍን ኃያልነት በመገንዘብ የየራሳቸውን እውነት (Truth in Literature) የሚያስተላልፉ ሰዎች መኖራቸው ይነገራል። እውቅና ስመ ጥሩው እንግሊዛዊው ደራሲ ጆርጅ ኦርዌል፣ በተለይም በ“Animal Farm″ እና ማእከላዊ ጭብጡን በእውነት፣ ፕሮፓጋንዳና ሳንሱር ላይ ባደረገው፣ በ“Nineteen Eighty Four″ (1949) ሥራዎቹ የሚያሳየን ይህንኑ እንደሆነ ነው የዲክስቴን (Dickstein, M. Animal Farm: history as fable.) ጥናት የሚተነትነው። በሀገራችን “የእንስሳት እድር” ተብሎ በተተረጎመውና በዓለማችን እጅግ በከፍተኛ ደረጃ ተነባቢነትን ባገኘው “Animal Farm” ውስጥ የእነ ስታሊን የጠቅላይነት አገዛዝ (Stalinist totalitarianism) ሁነኛ ስፍራን ይዞ የሚገኝ ሲሆን፣ ይህም በመጽሐፉ ውስጥ ያለው እውነት በእንግሊዝ መንግሥት እንደ ሀሰት ፕሮፓጋንዳ በመቆጠሩ እንዳይታተም ሁሉ ታግዶ የነበረ ዘመን ተሻጋሪ፣ አብዝቶም ተጠቃሽ መጽሐፍ ነው።
ይህንን ወደ ሀገራችን እናምጣው ብንል የበዓሉ ግርማ “ኦሮማይ″ ለደራሲው “እውነት“ ሲሆን፤ ለደርግ መንግሥት ደግሞ “ሀሰት″ ሆነና ደራሲውን አስበላው። ልዩነቱ የእንግሊዝ መንግሥት ኦርዌልን አለመግደሉ ነው።
እውነትን ከታሪክ አኳያም (Truth in History) ከላይ በመጣንባቸው መንገዶች ማየትና ዓለማችን (የሀገራችንን ዝም ነው) ምን ያህል በተዛባ የታሪክ ነገራ (ትርክት)፤ እንደተጥለቀለቀች መገንዘብ፤ እውነትን በነጭ የመሰረዝና ሀሰትን በደማቁ ከስሩ የማስመር ተግባራት ሁሉ በስፋትና በተደጋጋሚነት እየተፈፀሙ እንደሆነ መረዳት ይቻላል።
ሌላው፣ ዘመንና እውነት የሚገለፁበትና በፈረንጆቹ 2016 (https://en.oxforddictionaries.com/word-of-the-year/word-of-the-year-2016 ይጎብኙ) የዓመቱ ምርጥ (ተዝወታሪ) ቃል የሆነው “ድህረ-እውነት” ነው። “post-truth” ማለት የሀሰት ፕሮፓጋንዳ በተጨባጭ እውነት (Objective truth) ላይ የበላይነቱን ይዞ፣ ማኅበረሰብ ላይ ተፅእኖ በመፍጠር የህዝብን አመለካከት በመበረዝ የሀሰት ትርክትን በመንዛት አንድ የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ እንዲደርሱ የማድረጊያ ህሊና ቢስ ስልት ነው። በምርጫ ወቅት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚጠቀሙባቸው የቅስቀሳና ምረጡኝ ስልቶችም (post-truth rhetoric) ከዚሁ የሚመደቡ በአብዛኛው በሀሰት፣ ጥላቻና የጥላቻ ንግግር፣ ዘረኝነት፣ ብልግና ላይ የተመሰረቱ (ለዚህ በምሳሌነት የትራምፕ የምረጡኝ ዘመቻ ይጠቀሳል) ናቸው።
ጥናቶቹ እንዳረጋገጡት፣ ይህ “ድህረ-እውነት” የእውነት አይነት፣ ከሀሰት ፕሮፓጋንዳም ሆነ የተዛባ (የሀሰት) ትርክ በላይ የከፋ በመሆኑ፣ ከጊዜያዊ ጥቅም ያለፈ ለማንም ምንም የማያስገኝ የስግብግቦች ፖለቲካ አካሄድና አሰራር ሲሆን፤ በሂደትም ራሳቸውን ጠልፎ የሚጥል አደገኛ የ“እውነት” ባዮቹ የክህደት “እውነት” ነው።
ሌላው የ“ዘመንና እውነት” ማሳያዎች ማኅበራዊ ሚዲያወለድ የሆኑ እውነቶች መኖራቸው ሲሆን፣ እሱም ሆን ተብሎ፣ ታስቦበትና ታቅዶ የሚሰራጭ የሀሰት ትርክት ነው። የአልኮት እና ጌንትዝኮው (Allcott, H, Gentzkow, M. Social Media and Fake News in the 2016 Election. In: Journal of Economic Perspectives.) ጥናት እንደሚያረጋግጠው The Denver Guardian፣ WTOE 5 News እና የመሳሰሉት ስራቸው ይሄ ብቻ ሲሆን፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች “ሼር” እና “ላይክ” በማድረግ ሲያታኩሱና ሲያጋድሉ የሚውሉት እነዚህ ተቋማት የሚፈበርኩትን የሀሰት ወሬ ነው። ዘመኑ በተጨባጭ ይህንን ነው የሚመስለው።
በተለይ በአደጉት ሀገራት፣ በተለይ በተለይ በአሜሪካ ስር እየሰደደ የመጣውን (አሁን አሁን ለእኛም እየተረፈ ነው)፣ የሴራ ንድፈ ሃሳብ (ኮንስፒራሲ ቲየሪ)ን መጠነ ሰፊ አውዳሚነትና ከእውነቱ እጅጉን የራቀ አሰራር እየተነጋገርንበት ካለው ዘመንም ሆነ ትውልድ ጋር አሰናስሎ በማየት ዘመኑ ምን ያህል ለሰው ልጅ አስቸጋሪ እንደሆነና እየሆነም እንደመጣ መረዳት ይቻላል።
ለዚህ አንድ ምሳሌ ወስደን እንመልከት። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ወደ ሥልጣን መምጣት ተከትሎ “ዐቢይ አማራ ነው/አይደለም ኦሮሞ ነው። ዐቢይ ኦሮሞ ነው/አይደለም አማራ ነው” የሚሉ፣ ሀገርንና ሕዝብን ምንም የማይጠቅሙ መጠላለፎች ብቅ ብለው አጀንዳ ሆነውብን ስንነታረክ ነበር። ሀገርና ሕዝብ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚፈልገው በሳል አመራርን ሆኖ እያለ ለግል የፖለቲካ ሽኩቻ ሲባል ብቻ አጀንዳ እየተሰጠን ስንወዛገብ ነበር። ይህ አንዱ የሴራ ፖለቲካ አካል ነው። ሌሎችም ብዙ ብዙ አሉ።
ማጠቃለያ
አንዳንዶች እንደሚያምኑበት “ግማሽ እውነት ከውሸት የበለጠ አደገኛ ነው፡፡” አንዳንዶች ደግሞ እንደሚያስተምሩት “እውነት”ም ሆነ “ውሸት” ብሎ ነገር የለም፤ ዝም ብሎ መኖር ነው። “ዘመንን ከመከተል ሌላ ምን አማራጭ አለ?” የሚሉ ደግሞ አሉ። “ዘመኑ ውሸታም ከሆነ ዋሽ። ዘመኑ እምነትና እውነትን ፈላጊ ከሆነ ደግሞ አንገትህን ለእምነትና እውነት ስጥ” ነው የእነዚህኞቹ ጥብቅ መርህ።
እንደ ብፁእ አቡነ ማቲያስ ከሆነ ዘመኑ የሥነምግባር ውድቀት የሚታይበት ነው።
ብፁእነታቸው የ2007 ዓ∙ም የትንሳኤ በዓልን አስመልክተው ለምእመናን የ“እንኳን አደረሳችሁ” መልእክት ሲያስተላልፉ እንደተናገሩት፤ “ዓለማችን በመልካም ሥነምግባር ከመበልፀግ ይልቅ በዘቀጠና ለአእምሮ በሚዘገንን ነውረ ኃጢያት ክፉኛ እየተናወጠች ትገኛለች። (ይህ) የሥነ ምግባር ውድቀት ሊመጣ የቻለው የሥነምግባር ትምህርቱ በፈሪሀ እግዚአሔብር ያልተቃኘ ከመሆኑ የተነሳ እንደሆነ ሊሰመርበት ይገባል።”
ለፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ዘመኑ “ከእውነት የተጣላ” የበዛበት ዘመን ነው። በመሆኑም “የፌስቡክ መንጋ” እውነትን እየሰረዘ ሀሰትን እየተካ ይገኛል። “በሬ ወለደ”ውን ሲነዛ ውሎ ሲነዛ ያድራል። ይነቅላል እንጂ አይተክልም። የዚህ ሁሉ ድምር ደግሞ ሀገርና ሕዝብን ዋጋ እያስከፈለ ይገኛል።
እንደ ፕሮፌሰር መስፍን አተያይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጨዋ ነው። ችግሩ ያለው “ለሆዱ ያደረው፣ በሆዱ ተሰንጎ የተያዘው ∙∙∙” ክፍል ጋ ነው። እሱ ነው ሕዝብን ከሕዝብ እያጣላ፣ እያጋደለ ∙∙∙ የሚገኘው እንጂ ሕዝቡ ጋ ምንም ችግር የለም። ሕዝቡ ጋ እውነት አለ።
ይህ የፕሮፌሰር አስተያየት ወይዘሮ የትነበርሽ ንጉሴ ይመሩት የነበረ የሰላምና እርቅ ኮሚሽን ተቋም የተደገፈ ሆኖ ነው የሚገኘው። ተቋሙ በ85 የሀገሪቱ ከተሞች ተዘዋውሮ ባነጋገረበት ወቅት ከሕዝቡ ያገኘው መልስ “እኛ ጋ ችግር የለም። የሚያጋደሉን ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው። እነሱን እዛው ሀይ በሉልን” የሚል ነበር። (ጉዳዩ በወቅቱ በኢቴቪ ፕሮግራም ተሰርቶበት ነበር።)
ዘመንና እውነት በዚህ ደረጃ የተፋጠጡበት፤ “እውነቱን ተናግሮ እመሸበት ማደር”ተረት የሆነበት ነው።
በመጨረሻው መጨረሻው “እውነትን መናገር ሰውን ነፃ ለማውጣት ከፈጣሪ መንፈስ ጋር መተባበር ነው፡፡ ውሽት ሰውን ያለ አግባብ ለመቆጣጠር የሚደረግ የስጋ ሥራ ነው፡፡ ውሸት ከራስ ወዳድነት የሚመጣ የሐጢያት ባህሪ ነው፡፡” በማለት ሃሳባቸውን (መንፈሳዊ ቃሉን) ያካፈሉንን በማመስገን፤ የተሻለ ነገን እንመኛለን።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን መስከረም 26/2016