‹‹የኢሬቻ በዓል አካታችነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ መጥቷል››- አቶ አለማየሁ ኃይሌ በኦሮሞ ባህል ማዕከል የባህልና ታሪክ ዘርፍ ዳይሬክተር

የቀድሞው ሸዋ ክፍለ አገር፣ ኤጀሬ ወረዳ፣ አዲስ ዓለም ከተማ የትውልድ ስፍራቸው ነው። ከአንደኛ እስከ ዘጠነኛ ክፍል ያለውን ትምህርታቸውን የተከታተሉትም በዚሁ በአዲስ ዓለም ከተማ በአሁኑ መጠሪያው ኤጄሬ ጨንገሬ ትምህርት ቤት ነው። ከ9ኛ በኋላ ግን ከትውልድ አካባቢያቸው በቅርብ ርቀት ላይ ወደምትገኘው አዲስ አበባ በመምጣት እስከ 12ኛ ክፍል ያለውን ትምህርት በምስራቅ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሩ።

የዛሬው የዘመን እንግዳችን ከአንደኛ እስከ ዘጠነኛ ባሉ ክፍሎች ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ የሚታወቁ ሲሆን፤ ከየደረሱበት የክፍል ደረጃ ሁሉ የአንደኛነትን ቦታ ሳይለቁ እስከ ዘጠነኛ ድረስ መዝቀል የቻሉ ናቸው። በተለይም የ6ኛ እና የ8ኛ ከፍል ሚኒስትሪ ውጤታቸው ከመቶ 99 ነጥብ በመሆኑ በወላጆቻቸውም ሆነ በመምህራን ዘንድ ተወዳጅነት ያተረፉበት ጊዜ ነበር።

እንግዳችን አቶ አለማየሁ ኃይሌ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በከፍተኛ ደረጃ አጠናቀው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቴክኖሎጂ ሳይንስ የተማሩ ሲሆን፣ በተማሩበት ዘርፍም ለአምስት ዓመት ያህል ማገልገል ችለዋል። ከአምስት ዓመት የሥራ አገልግሎት በኋላ ለትምህርት ወደ ውጭ ሀገር የማቅናት እድል አግኝተዋል።

በመሆኑም እንግዳችን ከዛሬ ሶስት አስርት ዓመታት በፊት በሌላ የትምህርት ዘርፍ በዩክሬን ተከታትለው በሶሽዮ ፖለቲካል ሳይንስ መመረቅ ችለዋል። እንደተመረቁም የመጀመሪያውን የሳይንስ ትምህርታቸው ሙሉ በሙሉ ወደማኅበራዊ ሳይንስ በመቀየር የሥራ ዓለሙን እንደገና ለመቀላቀል በታማኝነት ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል።

እንግዳችን ማኅበራዊ ሳይንሱ ውስጣቸው ገብቶ ስለነበር የኦሮሞን እንዲሁም የኢትዮጵያንም ባሕል ማጥናቱን ተያያዙት። ምንም እንኳ ራሱን የቻለ መጽሐፍ ባያሳትሙለትም የኢትዮጵያን ባህል ከኦሮሞ ጋር አያይዘው አጥንተዋል። የኦሮሞን ባህል በተመለከተ ግን ወደ ሰባት ያህል መጻሕፍት ለንባብ አብቅተዋል። ከሰባቱ አንዱ ደግሞ በሶስት ቋንቋዎች የተተረጎመ ጭምር ነው። በመረጃ አሰባሰብ ላይ ጓደኞቻቸውም የተሳተፉበት ሥራ ነው።

አዲስ ዘመን ከእኚህ ከአራት አስርት ዓመታት በላይ የካበተ የሥራ ልምድ ካላቸው እንግዳችን ጋር ቆይታ ማድረግን ወድዷል። እንግዳችን አቶ አለማየሁ ኃይሌ፣ በኦሮሞ ባህልና ቱሪዝም የኦሮሞ ባህል ማዕከል የባህልና ታሪክ ዘርፍ ዳይሬክተር ሲሆኑ በተለይም በኦሮሞ ባህል ታሪክ ላይ ሰፊ ጥናትና በዘርፉም በተለያየ ርዕሰ ጉዳይ ላይ በመመስረት መጻሕፍትን ለአንባቢያን እነሆ ብለዋል። ከእርሳቸው ጋር የኢሬቻን በዓል በማስመልከት ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አጠናቅረን አቅርበነዋል። መልካም ንባብ።

አዲስ ዘመን፡- ሶቬዬት ኅብረት ዩክሬን ለትምህርት በሔዱ ጊዜ ወደኢትዮጵያ የተመለሱት ትምርትዎን እንዳጠናቀቁ ነው?

አቶ አለማየሁ፡– አዎ! ወቅቱ የደርግ ዘመን ስለነበር ብዙዎቹ ተማሪዎች ወደሀገራቸው መመለስን እምብዛም አይፈልጉም ነበር። እኔ ግን በዚያ ሀገር በፍጹም የመቅረት ፍላጎቱ አልነበረኝም። እውነት ለመናገር ሀገሬን እወዳታለሁ። ስለዚህም ትምህርቴን እንዳጠናቀቅሁ ወደኢትዮጵያ ልመለስ ችያለሁ።

በወቅቱ ‹‹እናታችሁ ትጠራችኋለች፤ ልጆቼ ድረሱልኝ እያለች›› የሚል መልዕክት ያዘለ አንድ የኦሮሚኛ ዘፋኝ ያቀነቅን የነበረው ሙዚቃ ውስጤ ይመላለስ ነበር። ይህ የመዝሙር ያህል ውስጥን የሚኮረኩር ሙዚቃ እንኳን ሀገር አስከድቶ ሊያስቀር ቀርቶ ልብን የሚያባባ በመሆኑ መቅረት ይሉት ነገር የማይታሰብ እንደነበር አስታውሳለሁ።

በመሆኑም ወደሀገሬ የተመለስኩት ያለአንዳች ማቅማማት ነው። በተለይም ‹‹እናታችሁ ትጠራችኋለች›› የሚለው የዘፈኑ ስንኝ ከአዕምሮዬ ያልጠፋ በመሆኑ ትምህርቴን ጨርሼ ያጠፋሁት ጊዜ የለም። እውነት ለመናገር በወቅቱ ሲሰማኝ የነበረው የምትጠራኝ ወላጅ እናቴ እንደሆነች ነበር። ከዚህ የተነሳ ወደ ሀገሬ ኢትዮጵያ የመጣሁትም በታላቅ ጉጉት ነው። መጥቼም ሀገሬን በታማኝነት ማገልገሉን ተያያዝኩት።

አዲስ ዘመን፡- በተለይ የኦሮሞ ባህልና ታሪክን በመጻፍ ለተደራሲያን ማድረስ ችለዋል፤ የመጀመሪያ ስራዎም የሆነው እስከ 16ኛ መቶ ክፍለ ዘመን ያለው የኦሮሞ ታሪክ ምን እንደሚመስል የሚያሳይ ነው፤ ጅማሬውን በዚህ መልኩ ለመጻፍ የተነሳሱበት ዋና ምክንያትና ስለሌሎቹም መጻሕፍዎ ይንገሩን?

አቶ አለማየሁ፡– በእርግጥ መጀመሪያ የጻፍኩት የኦሮሞ ታሪክ እስከ 16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የሚል ነው፤ ሁለተኛው ሥራ ደግሞ የኦሮሞ ታሪክ እስከ 20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የሚል ነው። የኦሮሞ ታሪክ እስከ 16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የሚለው የጻፍኩበት ዋናው ምክንያት አንዳንዶች ኦሮሞ ከ16ኛ መቶ ክፍለ ዘመን በፊት በኢትዮጵያ እንደሌለ የሚናገሩ ስለነበሩ ነው። የእነርሱ አባባል እንዲህ እንዲህ ነው በሚል የማሳመን (Justify) የሚያደርግ ሳይሆን ሐሰት (Falsify) ስለመሆኑ የሚገልጽ ሥራ መሥራት ስለፈልኩ ነው።

የኦሮሞ ሕዝብ የኩሽ ሕዝብ ነው። የኦሮሞ ሕዝብ በኢትዮጵያም በአፍሪካም ውስጥ ያለ ሕዝብ ነው እንጂ አንዳንዶች እንደሚሉት ከሌላ ዓለም የመጣ አይደለም። ይህ አባባላቸው ምናልባት ያለመረዳትና ታሪክ ያለማወቅ ሊሆን ስለሚችል ግንዛቤው እንዲኖር በማሰብ ጭምር ነው ስራዬን መስራት የቻልኩት። እዚሁ ኢትዮጵያ እንዲሁም ምስራቅ አፍሪካ ያለ ሕዝብ ስለመሆኑ በመረጃ የተደገፈ ታሪክ ለንባብ ማብቃት ችያለሁ።

ከዚህ ሌላ የገዳ ሥርዓትን በመጽሐፍ አሳትሜያለሁ። ይህ መጽሐፍ የተጻፈው በሶስት ቋንቋ ማለትም በኦሮሚኛ፣ በአማርኛ እና በእንግሊዝኛ ነው። በተጨማሪም የአዲስ አበባ (ፊንፊኔ) አመሰራረት እና የኦሮሞ ታሪክን የሚገልጽ መጽሐፍም ለንባብ አብቅቻለሁ። እንዲሁም የጨፌ ገዳ ሥርዓት በገላን ከተማ የሚል እና የኦሮሞ ወርጂዎች ታሪክ ከኦሮሞ ጋር ያላቸው ታሪካዊ አንድነትን የሚገልጽም እንዲሁ ከጻፍኳቸው ውስጥ የሚካተቱ ሥራዎቼ ናቸው። ከእነዚህ በተጨማሪ ለሕትመት በዝግጅት ላይ የሚገኝ ‹‹የገዳ ሥርዓት እና የኦሮሞ ወታደራዊ አወቃቀር›› በሚል ርዕስ የተጻፈ መጽሐፍ ነው። ይህም መጽሐፍ በዚህ ዓመት ለንባብ ይበቃል ብዬ አስባለሁ። ይህን ጨምሮ ወደ ስምንት መጽሐፍት አሉኝ ማለት ይቻላል።

አዲስ ዘመን፡- ዋና ርዕሳችን ወደሆነው የኢሬቻ በዓል እንምጣ፤ በመጀመሪያ ኢሬቻ ምንድን? መከበር የተጀመረውስ መቼ ነው?

አቶ አለማየሁ፡- በገዳ ሥርዓት ውስጥ በርካታ ተቋማት (Institutions) አሉ። ኢሬቻ ደግሞ በገዳ ሥርዓት ውስጥ ካሉት አንኳር ማኅበራዊ ተቋማት (Institutions) መካከል አንዱ እና ትልቁ ነው። ኢሬቻ የጋራ የምስጋና ቀን ነው። ኦሮሞ በጋራ ወደአደባባይ ወጥቶ አምላኩ እግዚአብሔርን የሚያመሰግንበት በዓል ነው። ፈጣሪ አምላክ ከዝናባማው፣ ከጭጋጋማውና ከጨለማው ወቅት ወደ ብራው ወቅት ስላሸጋገረ ምስጋና የሚቀርብበት ነው። ወቅቱ የኦሮሞ ሕዝብ ተሰባስቦ ምስጋና የሚያቅርብበት እንዲሁም ስለበደለው ነገር እርቅ የሚጠይቅበት እና እጅ የሚነሳበት በዓል ነው።

ኦሮሞ በባህሉ ውስጥ ባሉት የክረምቱ ወራት የዘራው በቅሎ የሚያፈራበት፣ ያረባው ውጤታማ የሚሆንበት ወቅት በመሆኑ በዚያ ጊዜ ዝናብ ሊበዛ ይችላል፤ እንደዛ ከሆነ እግዚአብሔርን የሚጠይቀው ዝናቡን አቁምልን ብሎ ሳይሆን እርቅን አውርድልን በሚል ነው። ምንም እንኳ ወቅቱ ብራ የሚሆንበት ጊዜ ቢሆንም ከዚያም በኋላ ከመጠን በላይ የሆነ ዝናብ ሲጥል የተዘራውን ያበላሻል፤ ከብቱን መውጫ ያሳጣል፤ መሻገሪያ ድልድዮችን ይሰብራልና ይህ እንዳይሆን ‹‹አምላክ ሆይ ታገሰን›› ሲል ኦሮሞ ፈጣሪውን የሚለምንበት በዓል ነው። ከዚህም የተነሳ ኢሬቻ በጋራ በመሆን ፈጣሪ የሚመሰገንበትና ምልጃ የሚጠየቅበት ቀን ነው ማለት ይቻላል።

በኢሬቻ በዓል ላይ የሚከወነው ሥርዓት ከሃይማኖታዊው ይልቅ ሚዛኑ የሚደፋው ባህላዊው ላይ ነው። ይህን ያልኩበት ምክንያት ከአለባበስ ጀምሮ በቡድን በቡድን በመሆን የሚደረገው ባህላዊ ዘፈን ሁሉ ስላለበት ጭምር ነው። በበዓሉ ላይ የተለያየ ኃይማኖት ተከታይ ስለሚታደምበት ባህላዊ ገጽታው ላቅ ብሎ ይስተዋላል። ከዚህ የተነሳ የምስጋናም የባህልም ቀን ነው ማለት ይቻላል።

መቼ ነው የተጀመረው ላልሽው በጥንት ዘመን የነበሩ ከኩሽ አባቶቻችንና እናቶቻችን ጊዜ ጀምሮ የነበረ ክዋኔ ነው። አንድ ምሳሌ ላንሳልሽ፤ በኦሮሞ ዘንድ ‹ወድቃ በተነሳችው ዘር አምላክ› የሚባል ጽንሰ ሃሳብ አለ። አንዲት ፍሬ መሬት ላይ ወድቃ ስትነሳ ብዙ ፍሬ እንደምታፈራው ሁሉ የሰው ልጅም እንዲሁ ነው። ምክንያቱም የሰው ልጅም ከእግዚአብሔር የተሰጠው ፍሬ እናት ከወንድ ተቀብላ በማኅጸኗ ይዛ ሰው ወደምድር ይመጣል። ልክ ወድቃ በተነሳች ዘር አይነት እሳቤ እግዚአብሔር አምላክ የሰውን ዘር በዚህ መልክ እየቀጠለ ያለበት ምስጢር ነው። ከዚህ ምስጢር የተነሳ ኦሮሞ ‹ወድቃ በተነሳች ፍሬ አምላክ› ይላል። የሰው ልጅም የሚገኘው በዚህ የትውልድ መቀጠል ምስጢር ውስጥ ነውና። ይህ ፍልስፍና የኦሮሞ ብቻ ሳይሆን የኩሽ ሕዝቦች ፍልስፍናም ጭምር ነው።

በጥቅሉ ግን ኢሬቻ የተጀመረው በዚህ ጊዜ ነው የሚል ድምዳሜ መስጠት ባይቻልም ለረጅም ጊዜ የቆየና ከጥንትም ጀምሮ ያለ ባህላዊ ክዋኔ እና ኃይማኖታዊ አተገባበር የሚታይበት በዓል ነው ማለት ይቻላል። በዚያን ወቅት ሁሉም ሕዝብና ጎሳ በየወንዝ ዳር፣ በየተራራ እና በየአካባቢው ኢሬቻንም እምነቱንም ያካሂዳል። የኦሮሞም ኢሬቻ የወጣው ከዚሁ ውስጥ ነው። ይህ ማለት ከብዙ ሺ ዘመናት በፊት ነው። እንዲያውም በገዳ አቆጣጠር መሰረት ኢሬቻ አንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን አካባቢ ጀምሮ እንደሚከወን ይነገራል። ከዚህ የተነሳ ኢሬቻ ቀደም ብሎም እንደነበር መረዳት ይቻላል።

አዲስ ዘመን፡- ኢሬቻ ከገዳ ሥርዓት ጋር ያለው መስተጋብር ምን ይመስላል?

አቶ አለማየሁ፡– እንደጠቀስኩት ኢሬቻ ገዳ ውስጥ ያለ አንድ ተቋም ነው። ገዳ ደግሞ ሥርዓት ነው። ኢሬቻ ደግሞ በገዳ ውስጥ ያለ ማኅበራዊ እና በጋራ ፈጣሪ የሚመሰገንበት ክዋኔ ነው። ይህ ክዋኔ በዓመት ሁለት ጊዜ የሚካሔድ ነው። ይኸውም በመልካና በኢሬቻ ቱሉ የሚካሄድ ማለት ነው። ማለትም በተራራ (ቱሉ) ላይ የሚካሄድ ኢሬቻ እና በጅረት (መልካ) አካባቢ የሚካሔድ የጋራ የምስጋና ቀን ማለት ነው። በተራራ (ቱሉ) ላይ የሚከናወነው በመጋቢት መጨረሻ ወር ነው። በዚያን ወቅት ፈጣሪ አምላክንን ‹ታረቀን!› የሚባልበት ጊዜ ነው። ‹በጋው በቅቷል፤ ከዚህ የተነሳ ሰውም ከብቱም እየተጎዳ ነውና ዝናብ ስጠን፤ እርዳን!› የሚባልበት ወር ነው።

መስከረም ወር መገባደጃ ላይ የሚካሄደው ምስጋና ደግሞ ከከባዱ ክረምት የወጣንበት ጊዜ በመሆኑ ‹ምስጋና ይገባሃል› ተብሎ አበባ ተይዞ ምስጋና የሚቀርብበት ወቅት ነው። በዚህ ወቅት የጨለማውን ወቅት አሳልፎ ፍሬ የሚያብብበት ጊዜ በማድረሱ ‹‹አምላካችን ታርቆናልና ምስጋና ይድረሰው›› በሚል የሚከበር በዓል ነው።

በገዳ ሥርዓት ውስጥ እንዳልኩሽ በርካታ ተቋማት አሉ። ልክ በመንግስት ስርዓት ውስጥ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ተቋማት እንዳሉ ሁሉ በገዳ ስርዓት ውስጥ ያለው የዚያ አይነት ነው ማለት ይቻላል። በገዳ ሥርዓት ውስጥ ያሉ ተቋማት ሁሉ የሚያገለግሉት ማኅበረሰቡን ነው። አስቀድሜ እንደጠቀስኩት ከዚያ ውስጥ አንዱ ኢሬቻ ነው። ከዚህ ሌላ የቃሉ ተቋም፤ የጋብቻ ተቋም እና ሌሎች ተቋማትም አሉ።

አዲስ ዘመን፡- ኢሬቻ በሰዎች መካከል ሰላም እንዲኖር ትልቁን ሚና የሚጫወት እንደሆነ ይነገራል፤ ከዚህ አንጻር ኢሬቻ ለሀገራችን ሰላም የሚጫወተው ምንድን ነው ይላሉ?

አቶ አለማየሁ፡- እንደሚታወቀው ኢሬቻ የጋራ ነው። የጋራ ኢሬቻ በሚካሄድበት ጊዜ በድቅድሚያ በአካባቢው የተቀያየመ ሰው ካለ እንዲታረቅ ይደረጋል። በአባ ገዳዎች፣ በአገር ሽማግሌዎች፣ በአረጋውያን ሴቶች ምክር ይሰጣል። ቁርሾ እና ቂም ይዞ ወደፈጣሪ የሚደረግ ነገር የለም። በመጀመሪያ ፈጣሪን ይቅርታ ከመጠየቃችን በፊት አጠገባችን ያለውን ሰው ይቅርታ መጠየቅና መታረቅን የግድ የሚል ሥርዓት ነው።

ከዚህ የተነሳ በመጀመሪያ የሚካሔደው የእርቅ ሥነሥርዓት ነው። ወደፈጣሪ መቅረብ እንዲያስችል በመታረቅ እጅ ለእጅ መያያዝ ያስፈልጋል። ምክንያቱም በኢሬቻ በዓል ላይ የሚካሄደው እንዳልኩሽ የጋራ ምስጋና እና የጋራ ጸሎት ነው። በዚያን ሰዓት የሚካሄደውም ልመና፣ ‹ፈጣሪ ሆይ ታረቀን› የሚል ነው። ስለዚህ ቂም እና ቁርሾ ይዞ ወደፈጣሪ መቅረብ ስለማይቻል መታረቅ ነው።

ይህ አካሔድ ደግሞ አብሮ ለመኖር በጋራ የሚካሄድ እሴት በመሆኑ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ነው። ከዚህ የተነሳ ለመታረቅና በአካባቢው ካለ ሰው ሁሉ ጋር ለመስማማት የኢሬቻ በዓል ትልቅ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን የሚወጣ እሴት ነው። በመሆኑም ጥል እንደማይፈልግ ይልቁኑ የተጣለ ካለ የሚታረቅበት መድረክ መሆኑ አንድ ማሳያ ነው ማለት ይቻላል። ከዚህ የተነሳ ኢሬቻ ማኅበራዊ ፋይዳው የጎላ ነው። ሰላምንና አንድነትን ለመፍጠር የራሱን ላቅ ያለ ሚና መጫወት የሚችል ነው።

አዲስ ዘመን፡- የኢሬቻ በዓል ሲከበር የራሱ የሆኑ ፋይዳዎች እንዳሉት ይታወቃል፤ በተለይ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው የሚገለጸው እንዴት ነው?

አቶ አለማየሁ፡- በሁለቱም ዘርፍ የየራሱ ጥቅም አለው። ማኅበራዊውን ስንመለከት በጋራ የመኖር ዓላማ የሰነቀ ስለሆነ አብሮነትን የበለጠ የሚያጎለብት ነው። ወንድማማችነትንና እህትማማችነትንም ያጠናክራል።

በተለይ ሕዝብን በማቀራረቡ ረገድ ሚናው የጎላ ነው። በበዓሉ የሚታደሙት የተለያዩ እምነት ተከታዮች ናቸው። የሚመጡትም የኢሬቻ በዓል አከባበርን በቅርብ ለማየትም አብሮ ለማክበር እንደመሆኑ የመቀራረቡ ሁኔታ ይፈጠራል። አብዛኞቹ ጥንታዊ የኦሮሞ ባህል አከባበር ምን ይመስላል፤ ሥርዓቱስ እንዴት ይከወናል የሚለውን ለማየት እንደመምጣታቸው ከብዙዎች ጋር ኅብረትና ወንድማማችነትን ፈጥረው ይመለሳሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ በበዓሉ ስፍራ በመገኘት በጋራ በመሆን ፈጣሪውን ለማመስገን፣ ማንነቱንና ኦሮሞነቱን ለመግለጽ በሚደረገው ሁነት ትስስሩን ይበልጥ የሚያጠናክር ይሆናልና ማኅበራዊ ፋይዳው ከፍ ያለ ይሆናል። ከዚህ ባለፈም በቅርበት የመተዋወቅና የመጠያየቁ ነገርም የሚሰፋበት መድረክ እንደመሆኑ ቅርርቦሹ የሚጎለብትበት ነው። ወዳጅነት እና ፍቅርም የሚጠናከርበት ስፍራ ነው። ከዚህ የተነሳ ማኅበራዊ ጠቀሜታው ላቅ ያለ ነው ማለት ይቻላል።

ከዚህ አኳያ ዕለቱን የብሔራዊ ማንነት ቀን ነው ብሎ መውሰድም ይቻላል። ምክያቱም በዓሉ በኢትዮጵያም ሆነ ከኢትዮጵያ ውጭ ማንነት በስፋት የሚገለጽበት ዕለት እንደመሆኑ ልዩ የሚያደርገው ነው። ከኢትዮጵያ ውጭ በተለያየ እንደ አሜሪካና ሌሎች አገራት የኦሮሞ ልጆች ኢሬቻን ያከብራሉ። በዚያን ጊዜ የሚሰበከው ሰላም ነው። በዕለቱ የሚነገረውም የሚዘፈነውም ሰላምን የተመለከቱ እና ምስጋናን ስለሚገልጹ ጉዳዮች ነው።

ኢኮኖሚያዊ ጥቅሙ ደግሞ የመጀመሪያው ወደ ኢሬቻ በዓል ሲኬድ አለባበሱ በራሱ የበዓሉ መገለጫ ቢሆንም ከኢኮኖሚ አኳያ የሚሰጠው ፋይዳ ላቅ ያለ ነው። ምክንቱም የተለያየ ባህል መገለጫ የሆኑ አልባሳት የሚለበስበትም ክብረ በዓል እንደመሆኑ ሁሉም እንደየፍላጎቱ ያንን የባህል ልብስ ይገዛል። በዚህ ጊዜ ያንን የባህል ልብስ ለገበያ የሚያቀርቡ አካላት ደግሞ ይኖራሉ። ከዚህ አንጻር ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ይኖረዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን ሽያጩ በአገር ውስጥ የበዓሉ ታዳሚያን ብቻ የሚወሰን ሳይሆን ከውጭ አገር የሚመጡ ቱሪስቶችም በመኖራቸው እነርሱም የሚገበያዩበት እንደመሆኑ ለቱሪዝም ገበያውም ሚናው የጎላ ይሆናል። የኢሬቻ በዓል በሚካሄዱባቸው ከተሞች ሁሉ የግብይት ሥርዓቱና ሰንሰለቱ ከፍ ያለ ይሆናል። በየከተሞቹ ያሉ ሆቴሎችም ገበያቸው ከፍ ያለ የሚሆንበት ወቅት እንደመሆኑ የየከተሞቹ ገቢም የሚጨምርበት ጊዜ ይሆናል። ከዚህ የተነሳ ኢሬቻ በሀገር ውስጥ በሚደረገው ግብይት ላቅ ያለ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያለው ከመሆኑ በተጨማሪ ኢኮኖሚውን ለሚያመነጨው ለቱሪዝም ዘርፉ ትልቅ ሚና የሚጫወት ነው።

አዲስ ዘመን፡- የኢሬቻ በዓል አካታችነቱ የሚገለጸው እንዴት ነው?

አቶ አለማየሁ፡- በጣም የሚያስገርመው አካታችነቱ ከጊዜ ወደጊዜ እየጎለበተ ነው። ከቀድሞው ደቡብ ኢትዮጵያ፣ በኋላ ላይ ራሳቸውን ችለው ከወጡ ክልሎች የኢሬቻን በዓል ለመታደም ይመጣሉ። ለአብነት መጥቀስ ካስፈለገ ከንባታ፣ ሀድያ፣ ሲዳማ እና ሌሎቹም በበዓሉ ለመታደም ከሚመጡት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። ኢሬቻ ከእነርሱ ጋር የሚተሳሰርበት መገለጫም አለ። ምናልባትም በቋንቋ ካልሆነ በስተቀር በብዙ መንገድ ከኦሮሞ ጋር የመመሳሰል እሴት አለ፤ የእነርሱም የኦሮሞም ሽማግሌዎች ሲናገሩ እንደሚደመጠው ከሆነ ሕዝቡ አንድ እንደሆነና መነሻቸው ተመሳሳይ መሆናቸውን ማጤን ይቻላል።

ልክ ኦሮሞዎች በሲዳማ ፊቼ ጫምባላ ላይ እንደምንገኝ ሁሉ ሲዳማዎችም በኢሬቻ በዓል ላይ ለመገኘት ይመጣሉ። ስልጤውም ጉራጌውም ሌሎቹም የሚመጡ በመሆናቸው አካታችነቱ ላቅ ያለ ነው። በዚህ ብቻ የሚወሰን ሳይሆን ከአማራም ከትግራይም ከሱማሌም ክልል በመምጣት በዓሉን ይታደማሉ። የኢሬቻ በዓል ልክ በአውሮፓና በመሰል አህጉራት እንደሚካሄደው አይነት ካርኒቫል በኢትዮጵያ ሆኗል ማለት የሚያስችል ነው።

በዓሉን ለመታደም አዋሳኝ አገራት ያሉ የኦሮሚኛ ቋንቋ ተናጋሪዎችም ይመጣሉ። ለምሳሌ ከኬንያ የሚመጡት በየዓመቱ ነው። የእነርሱን ማንነት የሚገልጽ ነገር በበዓሉ ላይ ስለሚያዩም ደስተኞች ናቸው።

አዲስ ዘመን፡- ብዙዎች እንደሚሉት የኢሬቻ በዓል ፈጣሪ ለሰው ልጆች ሰላምና ደኅንነትን እንዲሰጥ የሚለመንበትም ጭምር ነው፤ከዚህ አንጻር እንደሀገር ያለው ፋይዳ ምንድን ነው ?

አቶ አለማየሁ፡- በኢሬቻ በዓል ላይ ግን አባ ገዳዎች የሚያደርጉት ንግግር እና ምረቃት አለ። አንድ የፖለቲካ አመራር ከሚናገረው አሊያም አንድ ታዋቂ ዶክተር ለበሽታ ፈዋሽ የሆነውን መድሃኒት ከሚናገረው በላይ የኦሮሞ ሕዝብ በአባ ገዳ የሚናገረውን ነገር ያዳምጣል። የትኛውንም በአባ ገዳ የሚነገርን ጉዳይ በአግባቡ የሚያዳምጥ ነው። ይህ የማዳመጥ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የተነገረውንም ነገር በአግባቡ ከመፈጸም ጋር የሚያያዝ ነው። ታዳሚው ከሰላም ጋር ተያይዞ በባህላዊ መሪው የሚነገረውን ነጥብ አስተውሎ የሚተገብር ስለመሆኑ ጥርጥር የለውም።

ከዚህ አኳያ እኔ ልል የምችለው የፖለቲካ መሪዎች የተያዘው ታላቅ መርሀግብር ስኬታማ ይሆን ዘንድ አባ ገዳዎችን ቢጠቀሙ መልካም ነው እላለሁ። ሰላም ለማምጣት አባገዳዎች፣ የጎሳ መሪዎች፣ አያንቱዎችና ቃሉዎች በሕዝቡ ውስጥ ትልቁን ሥራ መሥራት አለባቸው። ምክንያቱም እኛ መልካም የሆኑ እና ለሰላም ምቹ የሆኑ እሴቶች ያሉን ነን። እነዚህ ትልቅ ተሰሚነት ያላቸው ናቸው። ይህ የኢሬቻ አይነቱ ታላቅ እሴት በሌሎቹም አካባዎች ያለ እሴት እንደመሆኑ እንደዚህ አይነቶችን በማቀፍ የተያዘውን ትልቅ እቅድ ስኬታማ ማድረግ አለባቸው።

ስለዚህም በየቦታው ያለውን እንዲህ አይነቱን መልካም እሴት በመጠቀም የተጎዳው እንዲካስ፣ የበደለውም እንዲክስ ማድረግ ይቻላል። የተከፋውንም ማስታረቅ ይቻላል። አንዱ ለሌላው የሚያስብ፣ የሚጠነቀቅ፣ የሚሳሳ እንዲሆን በማድረግ የተሳሳተውን ነገር መመለስ ይቻላል።

ይህንን መልካም ነገር አድራጊ የሆኑት ሁሉ እውነት ብቻ ይዘውና እሱን ብቻ መሰረት አድርገው እንዲሰሩ ለአባገዳዎችም ሆነ ለሌሎች ግንዛቤ መስጠት መልካም ነው። ምክንያቱም እንዳልኩሽ ሕዝቡ አባገዳዎችን ይቀበላል። አባገዳዎች የሚሉትን ሰምቶ በስምምነት ተቀብሎ ካበቃ በኋላ በጎን ሌላ ነገር የሚሰራ ከሆነ ደግሞ ከክህደት የሚቆጠር ነው።

ሰላም መፍጠር ማለት የአንድ ወገን እጣ ፈንታ ብቻ አይደለም፤ ሰላም መፍጠር በበዳይም በተበዳይ መካከል የሚደረግ ቃል ኪዳን እንደመሆኑ የሁለቱን ማለት የበዳይንም የተበዳይንም ስምምነት ግድ የሚል ነው። ብሔራዊ እርቅንም ብሔራዊ ሰላምንም ማካሄድ የሚቻለው በዚህ አይነት መንገድ ነው።

እርቅ በአንድ አካባቢ ብቻ ተፈጥሮ መወሰን ያለበት አይደለም፤ እርቅ ሲባል እንዳልኩሽ ብሄራዊ እርቅ መሆን አለበትና ሌላም ቦታ በተመሳሳይ ያንን የእርስ በእርስ ሰላም ለማውረድ ለዚህ ሥራ ዝግጁ መሆንን የሚጠየቅ ነው። በሁሉም የሀገራችን ክፍል ውይይት ተካሂዶ እና መግባባት ተፈጥሮ ሰላም እንዲወርድ ከሁላችንም ዘንድ የሚጠበቅ መልካምነት እንዳለ መጤን አለበት። በሌላው አካባቢም ሆነ በእኛ አካባቢ የሰላም አቅጣጫ እንዲያዝ አባገዳዎች በኢሬቻ በዓል ላይ የሚያስተላልፉት መልዕክት ትልቅ ዋጋ አለው። እሱ ብቻ ሳይሆን ሕዝቡ ለመታረቅ እንዲዘጋጅ፣ የተጣላም ቢኖር የአባገዳዎችን እና የሀገር ሽማግሌዎችን እንዲሁም የእናቶችን ተማጽዕኖ ወደጎን ሳይል ልቡን ለእርቅ እና ለሰላም ክፍት እንዲያደርግም የሚጠበቅበት ነው።

ሰላም ለሰው ልጅ ሁሉ ወሳኝ እንደመሆኑ ከዚህ ሰላም ላለመጉደል በፈጣሪ ፊት ለሰላም ራስን ዝግጁ ማድረግ ጊዜ የማይሰጠው ተግባር ነው። ለዚህ ታላቅ ለሆነው የሰላም አጀንዳ በኢሬቻ በዓል ላይ የሚታደሙትን ሁሉ አባገዳዎች ዝግጁ ማድረግ የሚጠበቅባቸው እንደመሆኑ ምክራቸውንም በዚያው አጋጣሚ ማስተላለፍ አለባቸው።

አዲስ ዘመን፡- እርስዎ የኦሮሞ ባህል እና ታሪክ ተመራማሪ እንደመሆንዎ በቀጣይ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ሥራው ስኬታማ እንዲሆን ለሕዝቡ የሚያስተላልፉት መልዕክት ምንድን ነው?

አቶ አለማየሁ፡- ይህ የኢሬቻ ቀን አጋጣሚ ሆኖ የእርቅ፣ ምልጃ እና የሰላም ቀን ነው። እርቅ መውረድ ያለበት ከፈጣሪ ጋር ብቻ ሳይሆን በቅድሚያ እርስ በእርስ መተራረም እና እርቅ ማውረድ ነው። ኢሬቻ ይህን ማድረግ እንደሚገባ የሚያስቀምጥ ነው።

ይህ በመሆኑ ሕዝባችን ከተቀያየመ እርቅን ያውርድ፤ ቂም እና ቁርሾ ይዞ ረጅም መንገድ መጓዝ አይችልምና ያንን ከጫንቃው ላይ አውርዶ ይጣል። ሁሉም ለሰላም መረጋገጥ ራሱን አዘጋጅቶ ለሕዝባችን እና ለሀገራችን ሰላም መስፈን የበኩሉን ሚና መጫወት አለበት።

በምድራችን የፈሰሰው የሰው ደም አለ፤ ያ ደም ደግሞ ወደፈጣሪ መጮሁ አይቀርም። ከዚህ የበለጠ የከፋ ነገር እንዳይኖር እና አንዱ ሌላውን የማይገድልበት ጊዜ እንዲሆን ሁሉ የኅብረተሰብ ክፍል ለእርቅና ሰላም መምጣት ራሱን ዝግጁ ማድረግ አለበት እላለሁ። አገራችን ለዜጎቿ የምትበቃ ናት፤ ከዚህ የተነሳ መገፋፋቱ ቀርቶ ወደ ሰላሙ እንምጣ። ለዚህ ደግሞ ለምክክሩና ለውይይቱ ራሳችንን ከወዲሁ እናዘጋጅ። ሰላም ሊመጣ የሚችለው በውይይት ውስጥ ነው። በደልን በመቁጠር ለብቻ በመገለል ሰላምን ማምጣት አያስችልም። ባለን መልካም እሴት ተነሳስተን የሀገር ሽማግሌዎች የሚሉንን ሰምተን ለተዘጋጀው የውይይት መድረክ ተሳትፏችንን በንቃት እናሳይ። ወደሰላም እንድንመጣ ዓይነልቦናችንን ያብራልን እላለሁ።

ፊታችንን ወደተዘረጋው የሰላም ተማጽዕኖ በማዞር የመተላለቅን ሂደት እንግታ፤ ደም መፋሰሱ እንዲቆም እንበርታ፤ እርስበእርስ መገዳደሉ ይቅር። ልጆቻችንን በሰላም ወደትምህርት ቤት ሄደው ይመለሱ፣ ማሳዎቻችን በዘር ይሸፈኑ። ከብቶቻችን በመስኩ ላይ ቦርቀው ይመለሱ። አስተማሪው ትውልድን ያለስጋት ይቅረጽ። ተመራማሪዎቻችን ወደምርመምር ይመለሱ። ሀገራችን ሰላም ትሁን። ሰላም ካለ ሁሉ ይኖራልና የማስተላልፈው መልዕክት ይህንን ነው።

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡኝ ሰፊ ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ?

አቶ አለማየሁ፡- እኔም አመሰግናለሁ።

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን መስከረም 26/2016

Recommended For You