የኢትዮጵያ የሕክምና ግብዓት ፍላጎት ከ83 በመቶ በላይ በኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት በኩል እንደሚቀርብና 92 በመቶ የሚሆነው መድኃኒት ደግሞ ከውጭ ሀገራት እንደሚመጣ መረጃዎች ያሳያሉ። የተቀረው ስምንት በመቶ የሚሆነው መድኃኒት ከሀገር ውስጥ መድኃኒት አምራቾች የሚገዛ መሆኑንም ከኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት የተገኘ መረጃ ያመለክታል። ይህም በመድኃኒት እና በሕክምና ግብዓቶች በኩል እጥረትና የዋጋ አለመረጋጋት በስፋት እንዳለ ይጠቁማል።
አቶ ዮሴፍ አርጋው በሂዩማን ዌል ፋርማሲውቲካል ኢትዮጵያ ሊሚትድ የሥራ አስኪያጁ ረዳት ሆነው ይሰራሉ። እርሳቸው እንደሚሉት፣ ኩባንያው በመድኃኒት ዘርፍ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ በማፍሰስ በአማራ ክልል ቱለፋ ከተማ እ.ኤ.አ በ2017 ተቋቁሟል። ኩባንያው ለሕይወት አድን፤ ለሚጥል ሕመም እና ሌሎችንም መድኃኒቶች ያመርታል። በአሁኑ ጊዜ 77 ዓይነት መድኃኒቶችን የማምረት ፈቃድና አቅም አለው። ይሁንና በጥሬ ዕቃ ግብዓት ችግር ምክንያት ሁሉንም መድኃኒቶች ማምረት አቅቶታል። በአሁኑ ጊዜ እያመረተ የሚገኘውም ሃያ አምስቱን ብቻ ነው። የውጭ ምንዛሬ እጥረቱም ፈተና ሆኖበታል። ለዚህም ከኢትዮጵያ ፋርማሲዩቲካል አገልግሎት ጋር በጋራ እየሰራ ይገኛል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ ብሎም የዘርፉ ተዋናዮች ለሚገጥማቸው ፈተና መፍትሔ ለማስቀመጥ ‹‹ግንኙነትን መፍጠር፤ የአቅርቦትን ድልድይ በጋራ ለመገንባት›› በሚል መሪ ቃል ሦስተኛው ዓለም አቀፍ የፋርማሲውቲካል አቅራቢዎች ጉባኤ በቅርቡ መካሄዱ ይታወሳል። የመድኃኒት አቅርቦት ሰንሰለቱ ምቹ፣ ጠንካራና ጽኑ ግንኙነት የሚታይበት እንዲሆን እየተሰራ መሆኑንም የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት አስታወቋል።
በዚሁ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ጥራታቸውና ፈዋሽነታቸው የተረጋገጡ መድኃኒቶችን ለ75 ዓመታት ሲያቀርብ እንደቆየ አስታውሰዋል። ከዚህ አንፃር የዜጎችን ጤና ለመጠበቅ የመድኃኒት አቅርቦት ሰንሰለቱ ምቹ፣ ጠንካራና ጽኑ ግንኙነት ያለው ሊሆን እንደሚገባ ጠቁመዋል። የአቅርቦት ሰንሰለቱ የተሳለጠ እንዲሆን ዓለም አቀፍ የመድኃኒት አቅራቢዎች ኮንፈረንስ እና ሌሎች የውይይት መድረኮች ጉልህ ሚና እንዳላቸውም አስምረዋል።
የአንድን ሀገር የብልጽግና ጉዞ እውን ከሚያደርጉ ጉዳዮች መካከል የጤና አገልግሎት ሥርዓቱን ማዘመን አንዱ መሆኑንም ጠቁመው፤ ዓለም አቀፍ የመድኃኒት አቅራቢዎች ኮንፈረንስም የውጭ ኢንቨስተሮችን ወደ ሀገር ውስጥ በመሳብ የሀገር ውስጥ አምራቾችና አቅራቢዎችን አቀራርቦ የመድኃኒት አቅርቦት ሥርዓቱ የተሳለጠ እንዲሆን እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው፣ በዘመናዊ የአቅርቦት ሰንሰለት መስተጋብር ውስጥ ገዢ እና ሻጭ ያላቸው ግንኙነት በመርህ ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት ብለዋል። የግንኙነቱ መሠረት እንዳይዋዥቅና የጸና እንዲሆን በግዢ ውስጥ፤ ከቁሳቁሶች ልውውጥ በሻገር በመርህ ላይ ያተኮረ እና ዘላቂ መሆን ይኖርበታል ሲሉም ገልጸዋል።
የአገልግሎቱ የግዢ አስተዳደር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ንጉሴም የሀገር ውስጥ መድኃኒት አምራቾች የሚጠቀሙትን ጥሬ እቃ ከውጭ ለማስገባት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እንደሚያስፈልጋቸው ጠቁመዋል። አገልግሎቱም ወደ ሀገር ውስጥ መድኃኒት ለማስገባት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እንደሚፈልግም ጠቅሰዋል። አገልግሎቱ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የሀገር ውስጥ መድኃኒት አምራቾችን የውጭ ምንዛሬ ችግር የሚፈታ መመሪያ ማዘጋጀቱንም ተናግረዋል።
አቶ ዳንኤል ዋቅቶላ የኢትዮጵያ የመድኃኒት እና የሕክምና መገልገያ አምራቾች ማህበር ፕሬዚዳንትና የክሌጀስትሮ መድኃኒት ፋብሪካ መሥራች እና ባለቤት ናቸው። እንደ እርሳቸው ማብራሪያ ከአምስት ዓመት በፊት የዓለም የጤና ድርጅት ያወጣውን ደረጃ የሚያሟሉ ፋብሪካዎች በሀገር ውስጥ አልነበሩም። አሁን ላይ ግን አምስት ደርሰዋል። ይህም ትልቅ ስኬት ነው። መድኃኒትና ለሕክምና አገልግሎት የሚውሉ ግብዓቶችን ማምረት ከፍተኛ እውቀት፣ ቴክኖሎጂ እና ገንዘብን ይጠይቃል። ይህንን ወደ ሀገር ውስጥ ለማምጣት ከፍተኛ ጥረትና ትብብር ይጠይቃል። በመንግሥት በኩል ፖሊሲዎች ተቀርጸዋል። ተግባራዊ ከማድረግ አንፃር ግን ወደኋላ የመቅረት ነገር ይታያል።
አቶ ዮሴፍ አርጋው በበኩላቸው ከ95 ከመቶ በላይ ጥሬ ዕቃዎች የሚገቡት ከውጭ መሆኑን ጠቁመው፣ የዶላር እጥረት ቢያጋጥም ከእናት ኩባንያ ድጋፍ በማግኘት በፍራንኮ ቫሉታ (ሕጋዊ ከሆነ ምንጭ የሚገኝ የውጭ ምንዛሬ) በማስገባት እና በመቀየር ሥራው እየሄደ ይገኛል። የትራንስፖርት ዋጋ ጭማሪ፣የዶላር ዋጋ በየጊዜው መጨመር፤ የዓለም አቀፍ ገበያው ላይ የሚያደርሰው አስተዋጽኦም ቀላል የሚባል አይደለም። በዚህም ብዙዎች ድርጅቶቻቸውን ዘግተዋል። አገልግሎቱ የሚያወጣውን ጨረታ በማሸነፍ ከሚገኘው 55 በመቶ ዶላር ጥሬ እቃ አምጥቶ በገበያ ላይ ለመቀጠል ጥረት እየተደረገ ነው።
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ የገንዘብ ሚኒስቴር፣ ጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት አዲስ መመሪያ በማውረዳቸው ችግሮች በተወሰነ መልኩ ቀለዋል። ጨረታውን ለሚያሸንፍ አካል 55 በመቶን ከመንግሥት ማግኘት የሚቻልበት አሠራር መዘርጋቱም መንግሥትን ያስመሰግነዋል። ይሁን እንጂ አብዛኛው ጥሬ ዕቃ ከውጭ የሚገባ መሆኑን በማጤን፤ ሌሎችም መዋለ ነዋያቸውን በማፍሰስ ወደ ሀገር እንዲመጡ ሲጋበዝ፤ ፈዋሽ የሆኑ መድኃኒቶች በሀገር ውስጥ እንዲመረቱ ቢደረግ፣ መድኃኒት ከሚያመርቱ ድርጅቶች በተጨማሪም ጥሬ ዕቃውን ማምረት የሚችሉ ድርጅቶች ወደ ሀገር ውስጥ ቢገቡ ችግሮችን በሚገባ ያቃልላሉ።
የአገልግሎቱ የግዢ አስተዳደር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ንጉሴ እንደሚናገሩት፣ የሀገር ውስጥ አምራቾች ሀገር ውስጥ ያምርቱ እንጂ ጥሬ ዕቃዎቹ ከውጭ የሚመጡ በመሆናቸው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ይገጥማል። የጥሬ ዕቃውን ለማምጣት የሚወጣውን ዶላር ለማስታረቅ ከአምራቾች፣ ከማህበራት፣ ከግዢ ኤጀንሲ ከጤና ሚኒስቴር እና ከፋይናንስ ሚኒስቴር ጋር በጋራ በመሆን ለመድኃኒት አቅራቢዎች የጥሬ ዕቃ ችግራቸውን የሚፈታ መመሪያ ተዘጋጅቷል። ስለዚህ እንደሚያመጡት እሴት እስከ 55 በመቶ የዶላር አቅርቦት በጤና ሚኒስቴር በኩል እንዲመቻች ተደርጓል። ይህ በመሆኑ በቀጣይ ዓመታት ትልቅ እመርታ የሚያሳይ እና ብዙ መድኃኒቶች በሀገር ውስጥ እንዲመረቱ ይረዳል።
የመድኃኒት እና የሕክምና መገልገያ አምራቾች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ዳንኤል በበኩላቸው፣ በአሁን ወቅት ለአገልግሎቱ እስከ 40 በመቶ የሚደርስ መድኃኒት ድርጅቱ እያቀረበ ነው። ይህም ለድርጅቱ ትልቅ አቅም አለው። ትንሽ ማስተካከያ ከተደረገ ደግሞ ወደ ውጭ የመላክ አቅም ይኖራል። ለዚህም የሚረዳ ምቹ ሁኔታ እና የሰው ኃይል እንዲሁም የመጓጓዣ አማራጮች አሉ።
አቶ ዳንኤል እንደሚገልጹት የውጭ ምንዛሬው እጥረት ከተቀረፈ ራስን ለመቻል ትልቅ ዕድል ይፈጥራል። ምሥራቅ አፍሪካ ውስጥ የሌሉ የመድኃኒት ፋብሪካዎች በሀገሪቱ እየተገነቡ ነው። ይህ ትልቅ አቅም ሲሆን ራስን ለመቻል ጠንክሮ መሥራት ይገባል።
የሕክምና እና የመድኃኒት ምርት ላይ ከሚታዩ ችግሮች የግንዛቤ እጥረት፣ የትብብር እና የቅንጅት ማነስ እንዲሁም ውሳኔዎችን በፍጥነት ያለመወሰን ችግር ይስተዋላል። በመሆኑም ፖሊሲዎች ወደ ተግባር እንዲውሉ ለማድረግ ከመንግሥት ጋር በጋራ መሥራት ይጠይቃል።
ሽሮፕ እና መሰል ምርቶች በጭራሽ ከውጭ ሀገር መምጣት የለባቸውም። ይልቁንም ከአስር ዓመት በኋለ ሀገሪቱ ከ60 እስከ 70 በመቶ በመድኃኒት ምርት እና በአቅርቦት ራሷን እንድትችል ተስፋ ማድረግ ያስፈልጋል። ምንም እንኳን አሁን ያለው የመድኃኒት እጥረት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ቢደርስም በመንግሥት በኩል የሚታየው ቁርጠኝነት ይበል የሚያሰኝ ነው።
በየጊዜው የሚጨምሩ መድኃኒቶችም ይሁን የሕክምና ግብዓት ዋጋ ለመቀነስ ጥሬ ዕቃዎች፣ በሀገር ውስጥ ወደ ማምረት ሂደት መግባት ይኖርበታል። ኢትዮጵያ ዘመናዊ መድኃኒት ማምረት ከጀመሩ ሀገራት አንዷ ነች። ሀገር ውስጥ የሚመረቱ እንደ ፓራሲታሞል እና የጸረ ተህዋስያን መድኃኒት በማምረት ልምድ አላት። አሁንም በመድኃኒት ምርት በስፋት መቀጠል ይኖርባታል።
አቶ ዮሴፍ እንደሚሉት፣ ከዚህ ቀደም ከነበረው ጋር ሲነጻጸር አሁን ላይ የሚያበረታቱ ብዙ ነገሮች አሉ። ለምሳሌ እስከ አምስት ዓመት ድረስ ከግብር ነጻ (እፎይታ) መኖሩ እና ከውጭ የሚገቡ ጥሬ ዕቃዎች ከታክስ ነጻ እንዲሆኑ መደረጋቸውም ዘርፉን ለማበረታታት ከሚደረጉት መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን እንደሚሉት፣ የሀገር ውስጥ ምርት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣት ከውጭ ሀገር የሚገባውን ይቀንሰዋል። የሀገር ውስጥ አምራቾች ቁጥር ለመጨመር ፖሊሲዎቹ እና አበረታች ነገሮች አሉት። ለአብነትም ጥሩ የኢንቨስትመንት ትኩረት እንዳለው ለማሳየት የኢትዮጵያ ፋርማሲውቲካል ኢንዱስትሪ ውስጥ ዝግጁ የሆነ የፋርማ ኢንዱስትሪ ፓርክ አለ። ከታክስ ጋር በተያያዘም ተያያዥ አበረታች አማራጮች አሉ።
ሌላው የሚነሰው ችግር የአቅርቦት ችግር ሲሆን የንግድ ሰንሰለቱን የጠበቀ አለመሆን በመድኃኒቶች ላይ የዋጋ መውጣት እና መውረድ (መዋዠቅ) እንዲፈጠር ማድረጉ ነው። በጥራት ላይ ግን የሚታይ ችግር የለም። ጥሬ ዕቃን በተመለከተ ግን በአሁን ወቅት መንግሥት ለሚገዛቸው መድኃኒት እስከ 55 በመቶ የውጭ ምንዛሬ እንዲገዛ የገንዘብ ሚኒስቴር አዲስ መመሪያ ማውጣቱ ኢንዱስትሪዎች እንዲነቃቁ እንደሚያግዝ የማህበራቱ ፕሬዚዳንት አቶ ዳንኤል ይገልፃሉ።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት ግንኙነት ለማጠናከር እና ለማጎልበት በተሠሩ ሥራዎች ምንም እንኳን ዓለም አቀፋዊ እና ሀገራዊ ችግሮችን በአቅርቦት ሥርዓቱ ላይ መስተጓጎል የፈጠሩ መሆናቸውን ያስታወሱት ዶክተር ሊያ፤ የገጠሙ ተግዳሮቶችን ያህል የአቅርቦት መቆራረጥ እንዳይፈጠር ማድረግ እንደሚገባ ጉባኤው በተካሄደበት ወቅት አስረድተዋል።
እየሩስ ተስፋዬ
አዲስ ዘመን መስከረም 26/2016