ተስፋ የተጣለበት የድንጋይ ከሰል ማዕድን ልማት

“የድንጋይ ከሰል” የኃይል ምንጭ አማራጭ በመሆን በኢንዱስትሪዎች ውስጥ በእጅጉ ከሚፈለጉ ማዕድናት መካከል አንዱ ነው፡፡ ከኢንዱስትሪዎቹ ቀደም ሲልም የሰው ልጅ ከሚጠቀምባቸው ጥንታዊ የኃይል አማራጮች አንዱም ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜም ይህ ማዕድን የተለያየ ግዙፍ ኢንዱስትሪዎች በኃይል አማራጭነት በእጅጉ ይፈልጉታል።

የድንጋይ ከሰል ከኢንዱስትሪ ልማት ጀምሮ ለልዩ ልዩ ጉዳዮች የኃይል ምንጭ ሆኖ ማገልገሉ ተፈላጊነቱ የበለጠ እየጨመረ እንዲመጣ አስችሎታል፡፡ ቤቶችን ለማሞቅ፣ በኢንዱስትሪ ውስጥ ምድጃዎችን ለማሞቅ እና ኤሌክትሪክ ለማመንጨት የሚያገለግል ሲሆን፣ ማዕድኑን አልምቶ ለውጭ ገበያ በመላክ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማግኘትም ይቻላል፡፡

በማዕድኑ ላይ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎችን ዋቢ ያደረጉ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ ለሰው ልጅ ጠቀሜታ ያላቸው ብዙ ዓይነት ንጥረ ነገሮች ከድንጋይ ከሰል ማግኘትም ይቻላል፡፡ ሰልፈር፣ ቫናዲየም፣ ዚንክ እና መሰል ማዕድናትን የያዘ ማዕድን መሆኑ ይገለጻል፡፡

በዘርፉ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች የድንጋይ ከሰል ዘላቂና አስተማማኝ የኃይል ምንጭ መሆኑን ይገልፃሉ። ባለሙያዎቹ በተፈጥሮ ይዘቱ ኃይል የማውጣት አቅሙ የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት እንደሚረዳና ተመራጭ እንደሚያደርገው ያመለክታሉ። የድንጋይ ከሰል እንደ ጋዝ ወይም ፈሳሽ ወደ ተለያዩ ቅርጾች ሊቀየር ይችላል። ይህም የድንጋይ ከሰሉ የበለጠ ንፁህ እና ውጤታማ በሆነ መልኩ ማቃጠል እንዲችል እንደሚረዳ ነው እነዚሁ ባለሙያዎች የሚናገሩት። የግሪንሀውስ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስ እንደ ባዮማስ ካሉ ታዳሽ የኃይል ምንጮች ጋር መጠቀም የሚያስችል አማራጭ እንደሚሰጥም የዘርፉ ተመራማሪዎች ያብራራሉ።

በዓለም ላይ የተለያዩ የድንጋይ ከሰል አይነቶች ቢኖሩም፣ ሁሉም በሚባል ደረጃ አስፈላጊ ግፊትና የሙቀት መጠን መነሻ አላቸው፤ የጥራት ደረጃቸው ግን በተለያዩ ምክንያቶች ከፍ ወይም ዝቅ ያለ ሊል ይችላል። ሁሉም የድንጋይ ከሰል ከፍተኛ የሙቀት አቅም ያለው ኃይል ማመንጨት የሚችሉ በመሆናቸው፣ ይህም ሁኔታ የድንጋይ ከሰል በዓለም ላይ አንዱ ኃይል ማመንጫ እንዲሆን እንዳስቻሉት መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት በርካታ የድንጋይ ከሰል ዓይነቶች ጥቅም ላይ ይውላሉ። ከእነዚህም መካከል የካርቦን ይዘታቸው ከፍተኛ የሆነ በተለየ መልኩ ከፍተኛ የካሎሪ እሴት ያላቸው የድንጋይ ከሰል ዓይነቶች ኤሌክትሪክ ለማመንጨት ተመራጭ ናቸው፡፡ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2021 ኢንተርናሽናል ኢነርጂ ኤጀንሲ ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው፤ የድንጋይ ከሰል በኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት አቅሙ በዓለም 37 በመቶ ድርሻ ያለው ከፍተኛው የኤሌክትሪክ ኃይል አመንጪ አማራጭ ነው።

መረጃዎች እንደሚያመላክቱት፤ በዓለም ላይ ከ3ነጥብ6 ሺህ በላይ የድንጋይ ከሰል ተፋሰሶች አሉ። በዓለም ላይ ትልቁ የድንጋይ ከሰል ክምችት በአሜሪካ የሚገኝ ሲሆን፤ አሜሪካ ከፍተኛውን የዓለም የድንጋይ ከሰል ክምችት ማለትም 23 በመቶውን ድርሻ ትይዛለች። 13 በመቶ በመያዝ ሩሲያ የሁለተኛነት ደረጃ የያዘች ሲሆን፤ ቻይና 11 በመቶ የድንጋይ ከሰል ክምችት ያላት ሦስተኛዋ ሀገር ሆና ትከተላለች፡፡

ኢትዮጵያ ከቢሊዮኖች ቶን በላይ የድንጋይ ከሰል ክምችት እንዳላት መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይሁን እንጂ ለበርካታ ዓመታት ይህን የማዕድን ሀብት መጠቀም አልቻለችም፤ እስከ 2014ዓ.ም ድረስም የድንጋይ ከሰልን ለኢንዱስትሪዎች የኤሌክትሪክ ኃይል ግብዓትነት ከውጭ ሀገር በውድ ዋጋ እያስገባች ስትጠቀም መቆየቷ ይታወሳል። በዚሁ ዓመትም ከ300 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ በማድረግ የድንጋይ ከሰል ከውጭ አስገብታለች፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የድንጋይ ከሰል በማምረት ለኢንዱስትሪዎች የኃይል አማራጭነት ለማዋል ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ ይሁንና ይህ የድንጋይ ከሰል ምርት ግን ከጥራት ጋር በተያያዘ ተፈላጊነቱ እስከዚህም ነው ሲባል ቆይቷል፡፡ ባለፉት ዓመታት ሀገር ውስጥ ያለው ድንጋይ ከሰል ጥራት የጎደለው፣ የእርጥበት መጠኑ ከፍተኛ የሆነ እና የኤሌክትሪክ ኃይል ለሚፈልጉ ፋብሪካዎች የማይሆን ነው እየተባለ ከውጭ ሀገራት ከቱርክ፣ ከቻይና፣ ከደቡብ አፍሪካ እና ከመሳሳሉ ሀገራት የድንጋይ ከሰል እንዲገባ ሲደረግ ቆይቷል፡፡

ይሁንና የድንጋይ ከሰል ከውጭ ከሚገባው ይልቅ በሀገር ውስጥ የሚመረተው ምርትን የማቃጠል አቅሙ ከፍተኛ መሆኑን በጥናት እንደተረጋገጠ የማዕድን ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡ ስለሆነም መንግሥት ከውጭ የሚገባውን የድንጋይ ከሰል ምርት በማስቀረት በሀገር ውስጥ የመተካት ሥራ በመሥራት በሀገር ውስጥ ለማምረት የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎች በማስጀመር ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ እንደ ሀገር የድንጋይ ከሰል ክምችት ያለባቸው መገኛ ቦታ ተብለው የተለዩ አካባቢዎች የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች፣ የኦሮሚያ፣ የአማራ እና የቤኒሻንጉል ጉምዝ ይጠቀሳሉ። በቅርቡ ሕልውናውን ያጣው የቀድሞው የደቡብ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የድንጋይ ከሰል ማዕድን እንዳላቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

የድንጋይ ከሰል ምርት ከሚታወቁት አካባቢዎች አንዱ የሆነው የአማራ ክልል ነው፡፡ በክልሉ በጭልጋ ዞን ምስራቅና ምዕራብ ደንቢያ ወረዳዎች ከፍተኛ የሆነ የድንጋይ ከሰል ክምችት ስለመኖሩ አንድ መረጃ ይጠቁማል፡፡ የድንጋይ ከሰል ክምችቱን አስመልክቶ ከአራት ዓመታት በፊት የጎንደር ዩኒቨርሲቲና ሌሎች የዘርፉ ባለሙያዎች ባደረጉት ጥናት 19 ሚሊዮን ቶን የማዕድን ሃብት እንዳለ በጥናቱ መረጋገጡን የክልሉ የማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ መረጃ ይጠቁማል፡፡

በክልሉ የድንጋይ ከሰል ሃብትን ፈጥኖ ወደ ልማቱ በማስገባት ለማዕድኑ ግዢ በየዓመቱ የሚወጣውን ወጪ በማስቀረት ረገድ በትኩረት እየተሰራ ነው። የድንጋይ ከሰል ለማልማት የሚያስችሉ የአሰራር መመሪያዎችና ደንቦችን ከማዘጋጀት ጀምሮ በየደረጃው መዋቅሮችን በመዘርጋት ለአልሚ ባለሀብቶች ፈጣን አገልግሎት እየተሰጠ እንደሚገኝ ተመላክቷል፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታትም አቅምና ፍላጎት ያላቸውን ባለሃብቶች በዘርፉ ለማሰማራት በተደረገው ጥረት በወቅቱ ፍላጎታቸውን ላሳዩ አራት ባለሃብቶች በዘርፉ መሰማራት የሚያስችላቸውን ፈቃድ ለመስጠት የሚያስችል ሥራ በሂደት ላይ እንደነበር ተጠቁሟል፡፡

በሀገሪቱ የድንጋይ ከሰል የሚመረትበት ሌላው ክልል የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ነው፡፡ የክልሉ ዳውሮ ፣ ኮንታ እንዲሁም ከፋ ዞኖች በድንጋይ ከሰል ምርታቸው ይታወቃሉ፡፡

የክልሉ ማዕድንና ኢነርጂ ልማት ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የማዕድን ዘርፍ ኃላፊ አቶ መንገሻ መዳልቾ በክልሉ ያለውን የድንጋይ ከሰል ክምችትና እየተካሄደ ያለውን ልማት አስመልክቶ በቅርቡ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳሉት፤ በክልሉ ያለውን የድንጋይ ከሰል ማዕድን ክምችት ለማወቅ ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ አሁን ላይ ማዕድኑ እየወጣ ያለው በገጸ ምድር እና በከፊል ገጸ ምድር ላይ ያለውን ማዕድን በመጠቀም ነው፡፡

በክልሉ 15 አነስተኛ ደረጃ አምራቾች እና ሦስት በከፍተኛ ደረጃ አምራቾች በአጠቃላይ 18 አምራቾች ፈቃድ ወስደው የድንጋይ ከሰል ወደ ማምረት ሥራ ተገብቶ እየተሰራ መሆኑን ኃላፊው ጠቅሰው፣ ከክልሉ በ2015 በጀት ዓመት 748 ሺ24 ቶን ያህል የድንጋይ ከሰል ለማምረት ታቅዶ፤ 209ሺ398 ቶን ለማምረት ተችሏል ይላሉ፡፡

ከእቅዱ አንጻር አፈጻጸሙ ውስን ነው የሚሉት ኃላፊው፤ ለዚህም በርካታ ችግሮች መኖራቸውን ነው በምክንያትነት የሚጠቅሱት፡፡ ከገቢም አንጻር 30 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማስገባት ታቅዶ፤ 29 ነጥብ3 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘት መቻሉን ይናገራሉ፡፡ በድንጋይ ከሰል ምርት ብቻ ለ600 ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ፣ ለ525 ዜጎች ቋሚና ጊዚያው የሥራ እድል መፍጠር መቻሉንም ጠቅሰዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ በ2016 በጀት ዓመት የድንጋይ ከሰል ምርት ሥራውን አጠናክሮ ለማስቀጠል ታቅዷል። በበጀት ዓመቱ 500ሺ ቶን የድንጋይ ከሰል ለማምረት የሚያስችል እቅድ ተዘጋጅቷል፡፡

ከጥራት ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የድንጋይ ከሰል ምርትን መስፈርቱ (ስታንዳርዱን) የጠበቀ ለማድረግ ከምርት ሂደት አንጻርም ዝቅ ሊል እንደሚችል የጠቆሙት ኃላፊው፤ ለዚህም መፍትሔ ለማፈላለግ እየተሰራ ነው ይላሉ፡፡ የድንጋይ ከሰል ፕሮሰሲንግ ማሽን በዳውሮ ዞን በኢትዮ ማይኒንግ ኮርፖሬሽን የመትከል ሂደት እያለቀ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ ይሄ እየታየ እንደሚሰፋም ተናግረዋል፡፡

የማዕድን ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽንና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አወቀ ተስፋው በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ከግማሽ ቢሊዮን ቶን በላይ የድንጋይ ከሰል ክምችት አላት፡፡ የድንጋይ ከሰል በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ በጂማ፣ በዳውሮ፣ በኮንታ፣ በወላይታ ሶዶ፣ በከማሼ፣ በአርጆ፣ በጭልጋ አካባቢዎችና በሌሎችም አካባቢዎች ይገኛል፡፡

“ከውጭ የሚመጣውን የድንጋይ ከሰል በሀገር ውስጥ ምርት ሙሉ ለሙሉ ለመተካት የሚያስችል ሥራ እየተሰራ ነው” የሚሉት የኮሙኒኬሽንና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው፤ የድንጋይ ከሰል በሀገር ውስጥ ለማምረት ፈቃድ ወስደው የተሰማሩ ኩባንያዎች መኖራቸውን ይገልጻሉ፡፡ ከፌዴራል መንግሥት ስምንት ኩባንያዎች የድንጋይ ከሰል ለማምረት የሚያስችላቸው ፈቃድ መውሰዳቸውንም ያመለክታሉ። ክልሎችም የድንጋይ ከሰል ለማምረት ለሚፈልጉ አካላት ፍቃድ መስጠት የሚችሉበት አግባብ መኖሩን ተናግረዋል፡፡ በክልሎች ፈቃድ ወስደው በዘርፉ የተሰማሩ ማህበራትና ኩባንያዎች እንዳሉም አመላክተዋል፡፡

ከውጭ የሚገባውን የድንጋይ ከሰል ምርት በሀገር ውስጥ የመተካት ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉን ነው ኃላፊው የሚገልጹት፡፡ እሳቸው እንዳሉት፤ በ2015 በጀት ዓመት በሀገር ውስጥ 1ነጥብ2 ሚሊዮን ቶን የድንጋይ ከሰል ምርት ማምረት ተችሏል፡፡ በዚህ ከ7 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማዳን ተችሏል፡፡ የ2016 በጀት ዓመት ሁለት ሚሊዮን ቶን የድንጋይ ከሰል በሀገር ውስጥ ለማምረት ታቅዷል፡፡

በሀገር ውስጥ ድንጋይ ከሰል በማምረት ዙሪያ ተግዳሮቶች እንዳሉም ጠቅሰው፣ የድንጋይ ከሰል በሚመረትባቸው ቦታዎች የአለመረጋጋትና የጸጥታ ችግሮች ማጋጠማቸውንም ተናግረዋል፡፡ ይህም በማምረት ሥራ ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎች በእቅዳቸው መሠረት ወደ ሥራ ያለመግባት ተግዳሮት ሆኖባቸው መቆየቱን ይናገራሉ፡፡

ይህንን ችግር ለመፍታት አሁን ላይ ምርቱ በሚመረትባቸው አካባቢዎች ላይ የጸጥታ አካላት ተሰማርተው ከህብረተሰቡ ጋር እየሰሩ ነው የሚሉት ኃላፊው፤ ኩባንያዎችም ወደ ሥራ እንዲገቡ የመደገፍና የመከታተል ሥራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ነው የገለጹት፡ ፡

እሳቸው እንደሚሉት፤ በቀጣይም ከውጭ የሚገባውን የድንጋይ ከሰል ምርት ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት እየተሰራ ነው። የድንጋይ ከሰል በሀገር ውስጥ ለማምረት ፈቃድ የወሰዱ ትልልቅ ኩባንያዎች ወደ ምርት እንዲገቡ ድጋፍ እየተደረገ ነው። ሌሎች ኩባንያዎችም ወደ ዘርፉ እንዲገቡ የሚያደርግ ሥራም እየተሰራ ነው። በሌላ በኩል ከዚህም አልፍ ብሎ የድንጋይ ከሰል ወደ ውጭ ለመላክ እቅድ ተይዞ እየተሰራ ይገኛል፡፡

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የዛሬው ዋንኛ ርእሳችን የሆነውን የድንጋይ ከሰልን ጨምሮ ኢትዮጵያ እንደ ወርቅ፣ ፖታሽ፣ የብረት ማዕድን፣ የከበረ ድንጋይ፣ ሊቲየም፣ የኢንዱስትሪ ማዕድናት ያሉ የተለያዩ የማዕድን ሃብቶች አላት። የማዕድን ዘርፍ ለጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት አንድ በመቶ ድርሻ እና 14 በመቶ ኤክስፖርት መጠን እንዳለውም ይገመታል። ይህ ዘርፍ የሚፈለገውን ያህል ባይሆንም ለብዙ ሰዎች የሥራ እድልም የፈጠረ ነው።

መንግሥት የማዕድን ዘርፉን ለማሳደግና ተጨማሪ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ የሚያስችል ስትራቴጂክ ዕቅድ ነድፎ እየሰራ መሆኑንም በተደጋጋሚ ሲገልጽ ይደመጣል። በተጨማሪም የማዕድን ልማት ሥራው አካባቢያዊ እና ማህበራዊ ጥቅሞችን የሚያስጠብቅ ብሎም ዘላቂነት ለማረጋገጥ ያለመ ነው። የማዕድን ዘርፉ ዋና ዋና ተግዳሮቶችን እየተጋፈጠም ይገኛል፡፡ የመሠረተ ልማት፣ የሰለጠነ የሰው ኃይል፣ የቴክኖሎጂ እና የቁጥጥር ማዕቀፍ ጉድለቶች ከተግዳሮቶቹ መካከል ይጠቀሳሉ። የአካባቢ መራቆት፣ ግጭት እና ሕገወጥ ንግድም ሌሎች ዘርፉን የሚፈትኑ ችግሮች ናቸው።

መንግሥት የዘርፉን ፋይዳ በማጤን በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው የአስር ዓመት መሪ እቅድ አምስት ምሰሶዎች ካላቸው ውስጥ ማዕድንን አካቶት እየሰራ ይገኛል፡፡ መንግሥት ተኪ ምርቶችን በማምረት የውጭ ምንዛሬ ለማዳን እያከናወናቸው ከሚገኙ ተግባሮች መካከል የድንጋይ ከሰል ምርትን በሀገር ውስጥ ለማምረት እየተከናወነ ያለው ተግባር ይጠቀሳል። በአሁኑ ወቅትም ከውጭ የሚመጣውን የድንጋይ ከሰል በሀገር ውስጥ ምርት መተካት እየተቻለ መሆኑን የማዕድን ሚኒስቴር መረጃ ይጠቁማል፡፡

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን  መስከረም 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You