ተመካክረን ውስጣችንን እናጽዳ

ሰፈር የደረሰችው አርፍዳ ነው፤ እንደዋዛ የእጅ ቦርሳዋን ጠረጴዛው ላይ ጣል አድርጋ የሁለቱን ጓደኞቿን ጉንጮች አንዳንድ ጊዜ ብቻ በጎንጯ አነካክታ ሶፋው ላይ ዘፍ አለች፡፡…ወደ ኋላዋ ደገፍ ብላ በረጅሙ ከተነፈሰች በኋላ ‹‹እኔ ደግሞ አቦሉ ያመለጠኝ መስሎኝ ነበር›› ስትል በዝግታ ተናገረች።

እውነት ለመናገር ማርታ ታደሰ፣ የጓጓችው አቦል ለመጠጣት ብቻ አልነበረም፤ ምንም እንኳ ዛሬ ቅዝዝ ብትልም ቡናው እየተጠጣ የሚነሳው የተለያየ ርዕስ የያዘ ወሬ ጭምር እንጂ።በእርግጥ ዛሬ ብዙም የማውራት እቅድ ያላት አትመስልም፡፡፡

‹‹አይ ማርቲ! ያንቺን መምጣት እየጠበቅን እንጂ አቦሉማ እስካሁን አይቆይሽም ነበር›› አለቻት ጓደኛዋ ሮማን ባልቻ፣ በማንደጃው ላይ ያለው ከሰል አመዱን ለማላቀቅ ያህል በመቆንጠጫው ነካ ነካ እያደረገች።‹‹እኔማ እኮ ቶሎ የምትመጪ መስሎኝ ቡናውን መቁላት ጀምርኩ፤ ትንሽ አዘግይቼው ቢሆን ይሸትሽ ነበር።የሆነው ሆኖ መቆየትሽ በሰላም ነው?›› ስትል ሮማን ጠየቀቻት፡፡

ቀድማ የተገኘችው ጓደኛዋ ዘነበች ደስታም ‹‹ዛሬ ስራ በዛ እንዴ? ስትል የሮማንን ጥያቄ አጠናከረች።ማርታ የቆየችበትን እውነተኛ ምክንያት ለጓደኞቿ መግለጽ አልፈለገችም፤ በእርግጥ ብትነግራቸው የእርሷን ያህል የሚጨነቁላት እንደሆነ ታውቃለች።ይሁንና የእርሷ ጭንቀት አንሶ እነርሱንም ማስጨነቅ በፍጹም አትፈልግም፤ ይህን እያሰላሰለች ሳለ መልስ መስጠት እንደሚጠበቅባት ዘንግታው ኖሮ …‹‹አሃ!… ዛሬ ደግሞ ከየት የመጣ ዝምታ ነው በይ!›› ስትል ሮማን ለመጀመሪያው ጥያቄዋ መልስ ሳታገኝ ሌላ ጥያቄ ደገመች፡፡

‹‹ውይ…የዛሬው የታክሲ ሰልፍ ደግሞ አይጣል ነው፤ ታክሲ ጥበቃ ሰልፍ ላይ ከአርባ ደቂቃ በላይ አልቆምኩም ብላችሁ ነው!?›› ስትል ቀድሞ የመጣላትን ሰበብ ተነፈሰች።በእርግጥ ቀለሟ ለአዲስ ዓመት እናቷን ለመጠየቅ አስባ አልተሳካላትም።ከዛ በፊትም መሄድ ፈልጋ የነበረ ቢሆንም ያለው የጸጥታ ሁኔታ አሳሳቢ በመሆኑ እናቷን ለመጠየቅ አልታደለችም።ዛሬ ያሳሰባት ግን በለመደችው የስልክ ቁጥር ላይ ከቀናት በፊትም ሆነ ዛሬ ደጋግማ ብትደውልም ከአገልግሎት መስጫ ከልል ውጭ በመሆኑ ነው፡፡

ምንም እንኳ የተቀዳላትን ቡና ያለፋታ ጠጥታ ስኒውን ከዘነበች ቀድማ ብትመልስም ከእርሷና ከዘነበች ፊት የተቀመጠውን የቡና ቁርስ ግን ዘነበች በተደጋጋሚ ስትቆርስለት ማርታ ግን በተደጋጋሚ ስልኳን ትጠቀጥቅ ነበር።‹‹ማርቲ!..፣ደህና ነሽ?…አልታወቀሽም እንጂ እያጉተመተምሽ እኮ ነው›› አለቻት ሁኔታዋን በትኩረት ትከታተል የነበረችው ሮማን፡፡

በዚህ መሃል የማርታ ስልክ አቃጨለ፤ የማታውቀው ቁጥር ነው፤ ፈራ ተባ እያለች አነሳችው። ‹‹ከወዲያኛው ጫፍ ተለቅ ያሉ ሰው አይነት ድምጽ ‹‹ሃ..ሎ…›› ሲል ተሰማት።ባለማንሳት በዝምታዋ ልትጸና ወሰነች።ነገር ግን ያለ ፈቃዷ እጇ ሳይታዘዝ አረንጓዴውን ነክቶት ኖሮ ‹‹ሄሎ..አቤት!…›› የሚል ድምጽ ከውስጧ ሲወጣ ታወቃት።‹‹ማርታ ነሽ የኔ ልጅ…›› ሲሉ በድምጻቸው የእናቷ ጎረቤት መሆናቸውን አወቀች።አሁንም በደመነፍስ አዎንታዋን ገልጻላቸው በእርሳቸው ስልክ ከቀን ጀምሮ ስትሞክርላቸው እንደነበር ነገረቻቸውና የእናቷን ደህንነት ጠየቀቻቸው። ‹‹እርሷ ምን ትሆናለች ብለሽ ነው፤ ደህና ናት የኔ ልጅ። የእኔ ስልክ ባትሪዋ አልቆ ኖሮ ነው የተቸገርሽው።በይ ይኸው እናትሽን አናግሪያት…›› ሲሏት እውነት አለመሰላትም።‹‹የልጄን ድምጽ ሳልሰማ ሰነበትኩ ስላለችኝ ነው በሌላ ሰው ስልክ ለምኜ መደወሌ…›› ቢሏትም የሰማቻቸው ‹‹አናግሪያት›› የምትለዋን ቃል ብቻ ነውና ጆሮዋን አቁማ ከወዲያኛው ጫፍ ትጠባበቅ የነበረው የእናቷን ድምጽ ነበር፡፡

አሁን ሁሉም ሰላም ሆኗል፤ ማርታ የእናቷን ድምጽ በመስማቷ ለበሽታው ትክክለኛ መድኃኒት አግኝቶ እንደተፈወሰ ሰው ፊቷ ሁሉ በራ።ለጭንቀቷ እፎይታ በማግኘቷም ለጓደኞቿ ሲያሳስባት የነበረውን ነገረቻቸው።

ዘነበች፣ በተራዋ ጭንቀቱ የተጋባባት ይመስል ‹‹ግን እስከ መቼ ነው በዚህ አይነት መንገድ የምንቀጥለው›› ስትል ፊቷን ክስክስ አደረገች።‹‹አንድ የማይገባኝ ነገር ቢኖር ልጅ ወላጁን፤ ወገን ወገኑን የሚጠይቀው እንዴት ነው? አሁን እኮ ዘመድ ለመጠየቅ ወደ ምዕራቡም ሆነ ወደ ሰሜኑ የአገራችን ክፍል ላቅና ብትይ ከመንቀሳቀስሽ በፊት ደጋግመሽ ማሰብ ይጠበቅብሻል።እንደ አጋጣሚ ሆኖ ደግሞ የክፍለ ሀገር ልጆች ነን።ከወገንሽ ጋር አትቆራረጪም።አያድርስና ከዘመዶቻችን አንዳቸው እክል ቢያጋጥማቸው ለመሄድ ያለው ስጋት ከባድ ነው።መቼም ምንም እንኳ ሮሚ የሸገር ልጅ ብትሆኚም ክፍለ አገር ያሉ ዘመዶችሽን ለመጠየቅ በደስታም በሐዘኑም መድረስሽ አይቀርም›› አለች፡፡

ምንም እንኳ ዘነበች አሁን ላይ ስላለው ሁኔታ እና እሱን ተከትሎ ስለተፈጠረው ስጋት ቅዝዝ ባለ መንፈስ ሆና እያወራች ቢሆንም በማርታ ፊት ላይ እየታየ ያለው መረጋጋት አልደበዘዘም፤ ብቻ የእናቷን ድምጽ በመስማቷ ደስ ብሏታል።‹‹ሰው ቤተሰቡንም ሆነ ዘመዱን ጥየቃ በመኪና መሄድን ፈርቷል።ከመኪና ውጭ ያለው አማራጭ ደግሞ አውሮፕላን ነው።ነገር ግን እሱም ቢሆን የሚያደርሰው ዋና ከተማ የሚባሉት ድረስ እንጂ በየዞኑ፣ ወረዳውና ቀበሌው ድረስ አያስገባ!…›› ስትል ዘነበች፣ ሁለተኛውን ቡና ቀድታ ሲኒውን እያቀበለች ያለችው ሮማን ደግሞ፤ ‹‹ዘኒ!… አሁን እንዳልሽው አውሮፕላኑ ቀበሌሽ ድረስ ኸረ እንዲያው ሰፈርሽ መግባት ቢችል ዋጋውን አስበሽዋል? ትችያለሽ!? እንደ እኔ ከባድ ነው።

እንዲያው ግን…. አፍ አውጥቶ አይናገር እንጂ አሁን አሁን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትርፍ በትርፍ ሳይሆን ይቀር ብለሽ ነው። በቀደም ዕለት ከክፍለ ሀገር የመጡ ዘመዶቼን ልሸኛቸው አየር መንገድ ስሔድ ገና ረፋድ ላይ ወደዚያች ከተማ በቀን ለስድስተኛ ዙር ተሳፋሪዎች ወደ አውሮፕላኑ እየገቡ መሆናቸውን ሰማሁ።ለወትሮው እኮ እኔ እስከማውቀው ድረስ ወደዚያች ከተማ አውሮፕላኑ የሚበረው ረፋድ ላይ አምስት ሰዓት፤ ከሰዓት በኋላ ደግሞ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ብቻ ነበር።ታዲያ በዚህ ዘመን እንደ አየር መንገዳችን ማን የታደለ አለ?! “ትርፍ በትርፍ ሆኛለሁ” ብሎ ሚዲያውን ጠርቶ መግለጫ አለመስጠቱ እሱ ሆኖ ነው እንጂ ትርፉንማ እያጋበሰው ነው›› አለች፡፡

የእናቷን ድምጽ መስማቷ አቅምም ደስታም የፈጠረላት ማርታ፣ መጨረሻ አካባቢ ሮማን ያወራችውን በመስማቷ ‹‹በአየር መንገዳችንማ እንድትመጪብኝ አልፈቅድልሽም ሮሚ፤ መኩሪያችንንና መንቀባረሪያችንን ጫፉን መንካት አትችይም። በከፍታው ላይ ከአህጉር አህጉር ሰንደቅ ዓላማችንን ከፍ አድርጎ የሚያሳየውን ተቋም መንካት የአይናችንን ብሌን እንደመንካት ነው የሚቆጠረው።ደግሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ምን አሳጣኝ ብሎ ነው ከአገር ውስጥ የተቃረመችውን ገንዘብ ‹ትርፋማ ሆኛለሁ› ብሎ መግለጫ የሚሰጠው!? ተቋሙ እኮ በየቀኑ በሚያስብል ደረጃ አንዴ ከአህጉራችን ሌላ ጊዜ ደግሞ ከዓለም አቀፍ የታላቅነቱን ምስክርነት የሚያረጋግጥለትን ማስረጃ የሚቀበለው፡፡

ወይኔ…!? ምናለ በአገራችን ያሉ ተቋማት ሁሉ እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ አስተማማኝ ቢሆኑ!?…›› እያለች ልትቀጥል ሲዳዳት፤ ‹‹እንዴ ማርቲ!?…እኔ መች ታላቅ ተቋም አይደለም አልኩሽ? እኔ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ አንቺ አለኝ ከምትይው በላይ ክብርም ኩራትም እንዳለኝ መዘንጋት የለብሽም›› ብላ አጋምሳ ያስቀመጠችውን ቡና ለመጨረስ ስኒውን አንስታ ወደአፏ ስታስጠጋው ቡናው ቅዝቅዝ በማለቱ መልሳ አስቀመጠችውና ረከቦቱን ባለበት ትታ ወደሶፋው መጥታ ተቀላቀለቻቸው፡፡

ዘነበች፣ የራሷን እና የማርታን ስኒ ደራርባ ካነሳች በኋላ ሳትነጣጥላቸው እንደዚያው ረከቦቱ ላይ አስቀምጣ ወደነበረችበት ተመለሰች።ቀጥላም ‹‹ጓደኞቼ! ኢትዮጵያ አየር መንገድ ባይኖር እኮ የበለጠ ከዘመዶቻችን ጋር ለመገናኘት ይቸግረን ነበር።የእሱ መኖር ነው በቀላሉ ዘመዶቻችንን ለበዓል እንኳ እንድንጠይቅ ያስቻለን።የሆኖ ሆኖ ዋናው ሰላም ነውና ሀገራችንን ሰላም ያድርግልን።ሰላሙ ሲመለስ እንደለመድነው በአውቶቡስ ሽር ብትን ብለን የፈለግነው ቦታ ደርሰን መመለስ እንችላለን፡፡

ግን በዚህ መሃል የታዘብኳቸው አሉ።ሰላም ሲባል የሚያማቸውና የሚያንቀጠቅጣቸው።በለው፤ ግደለው፤ ግፋው ማለት የሚቀናቸው።‹ብጥብጡና ኹከቱ በጣም ተመችቶኛል፤ በዚሁ ይቀጥል› ላለማለታቸው በእርግጥ ማሳያ የለኝም እንጂ ሕዝቡ እንዳይተማመን የሚያደርጉ፤ አንዱ ሌላውን በጎሪጥ እንዲያይ የሚጥሩ መኖራቸው የአደባባይ ምስጢር ከሆነ ሰንብቷል። ሲሆን ሲሆን ዘመቻ መክፈትና የማያዳግም እርምጃ መውሰድ እነርሱ ላይ ነበር›› ስትል በቁጭት መንፈስ ተናገረች።

‹‹ዘኒ! አስር ቦታ ሆኖ አንዱንም ለመስማት ግራ ገብቶሽ ካልሆነ በስተቀር በአደባባይ አይደለም እንዴ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ላይ ‹በለው! ግፋ! በርታ! ውቃው!› እያሉ ምኞታቸውን በቁም ሲቃዡ የሚውሉ።በእርግጥ ምኞት ብቻ ሆኖባቸው ቢቀር መልካም ነበር፤ አንዳንዶች ባለማወቅ በቁማቸው ሲቃዡ የሚውሉትን ቅዠት ሲሰሙና በስሜት ሲናጡ ይስተዋላሉ፡፡

ሰውም ክፉ ምክራቸውን ባይሰማ ይበጅ ነበር። አገር አፍራሽ ጥሪያቸውን አልሰማም ቢል ያዋጣ ነበር።ሁሌ ከጉዳታችንና ከውድቀታችን የምንማረው ነገር አላበቃ ማለቱ ያስገርመኛል›› ስትል ነገ ሊከሰት የሚችለውን አሻግራ በማሰብ ስለነበር፤ ቅድም ስትገባ የነበራት ስሜት መልሶ ሊቆጣጠራት ሲዳዳው ተሰማትና ዝም አለች።

ማርታ ‹‹መፍትሔው ምንድን ነው!?›› ስትል በልቧ አሰበች። ወደአዕምሯዋ የመጣው ነገር ግን ይህ ከሰሞኑን አጀንዳ ልየታ ነው…ተሳታፊ ልየታ… የተባለው የምክክር ኮሚሽኑ ስራ ነበርና ‹‹እኔ የምለው ጓደኞቼ…ይህ እነ ፕሮፌሰር መስፍን ያሉበት የምክክር መድረክ በዚህ ዓመት እንዲያው የሆነ መላ ያመጣልን ይሆን!?›› ስትል የሮማንን እና የዘነበችን አይን እያየች ጠየቀቻቸው፡፡

ዘነበች፣ ቀበል አድርጋ ‹‹በነገራችን ላይ ውይይት እና ምክክር የሚለው ቃል ይለያያል፤ ማለቴ ማወያያት እና ምክክር ማድረግ ለየቅል ናቸው፡፡…›› ብላ ልዩነታቸውን በብያኔ አስደግፋ ልታብራራ ስትል፤ ሮማን ቀበል አድርጋ ‹‹ያው ናቸው ባክሽ፤ መከረም ዘከረም ያው እርቅ ለማምጣት አይደል!? የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው አሉ…›› ብላ እሷም ገና ሐሳቧን ስትጨርስ፤ ማርታ፣ መፍትሔው የተገኘ ያህል ፈጥና ‹‹መመካከርም ሆነ መወያየት በጣም መልካም የሆነ ነገር ነው፤ ለሰላም ሲባል ደግሞ አስገድዶም ለሰላም እጅ ማስጠት እንኳ ቢሆን ትርፋማ እንሆናለን እንጂ ማንም ኪሳራ ውስጥ አይገባም›› አለች።

ከአፏ እየነጠቋት አላስወራ ያሏትን ሁለቱንም ጓደኞቿን በየተራ እያየች የቆየችው ዘነበች፣ ሁለቱም የየበኩላቸውን ተናግረው ጋብ ማለታቸውን አስተውላ ‹‹ለማንኛውም ይህ ዛሬ ያነሳነው ርዕሰ ጉዳይ እንዲሁ በዋዛ የሚታለፍ ጉዳይ አይደለም፤ በትክክለኛው መንገድ አስተውለን ካልተንቀሳቀስን በነገው ትውልድ ማለትም በልጆቻችን እጣ ፈንታ ላይ ጭምር እንደመቀለድ የሚቆጠር ይሆናል።የሆነው ሆኖ መመካከር እኮ መልካም ነገር ነው።

ለምን ይሆን ኮሚሽኑ የያዘውን እቅድ ለማጣጣል ታች ላይ የሚሉ የሚበዙት!?…፡ ማለት… የሚካሄደው አገራዊ ምክክር ሁሉንም ህዝብ የሚያሳትፍ ነው። በመንግሥት እና በሕዝብ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል፣ መተማመን የሰፈነበትና አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት ለመፍጠር በሚያስችል አግባብ ነው የሚከናወነው። ታዲያ ችግሩ ምኑ ላይ ነው?›› ስትል እንዳያቋርጧት በመፍራት እና ጊዜውም ለአይን ያዝ ማድረግ በመጀመሩ አጠር አድርጋ ሐሳቧን ጥያቄም ስጋትም ያዘለ አድርጋ ገለጸችላቸው፡፡

አከታትላም፣ “እስስቷን ሳያት ነው የምበረግገው አለ አለ ዘፋኙ” አለችና “እኔም ልክ ዘፋኙ እንዳለው ምክክሩ ስኬታማ እንዳይሆን ለማድረግ ይጥራሉ ብዬ የማስበው እስስቶች ከተቀላቀሉ ነው ባይ ነኝ።ቀና ልብ ያለውና ተበድያለሁ ባይ ለዚህ ምክክር ይሁንታውን የሚነፍግ አይመስለኝም።የእውነት ቅር ተሰኝቶ ከሆነ፣ የምርም ተበድሎ ከሆነ በይቅርታ መካስን የሚጠላ እና አሻፈረኝ የሚል አለ ብዬ አላስብም።

ከፍቶ የሚመጣ ብሶት ቢኖር፤ የነፈረና የቆሰለ ውስጠት ባይጠፋም ተመካክረን ውስጣችንን እናጽዳ በሚል ለመጣ አጀንዳ ጀርባውን የሚሰጥ ይኖራል ብዬ አልገምትም።ጀርባውን ከሰጠማ በቀላሉ መታከም ሲችል ቁስሉ እንደመረቀዘ ሊቀር ይችላል።ስለዚህ እኔን የሚያሳስበኝ ወገን ከወገኑ ጋር፣ ብሔር ከብሔሩ ጎሳውም ከጎሳው ጋር እንዳይስማማ እና እርስ በእርሱ ጥርጣሬ ውስጥ እንዲወድቅ የምታደርገው የእስስቷ ጉዳይ ነው፡፡”

ጓደኛሞቹ ለተጨማሪ ወሬ ጊዜ ስላልነበራቸው ሁሉም ሐሳባቸውን ወደመምሸቱ ላይ አድርገው ማርታ እና ዘነበች የእጅ ቦርሳቸውን ብድግ ብድግ አድርገው ቆሙ።ሮማን፣ ‹‹እስኪ መልካሙን ያምጣልን…›› ስትል፣ ‹‹ዋናው ነገር ከመልካም ነገር ጋር መተባበር ነው›› አለች ማርታ።‹‹ሌላውንም የመልካም ነገር ተባባሪ ማድረግ ወደ አሸናፊነት የመጠጋት ያህል የሚቆጠር ነው›› አለችና ልትሸኛቸው ከተል ያለቻቸውን ሮማንን እንዳትወጣ ገፋ አድርጋት ልክ እንደማርታ ሁሉ ጉንጯን ከጉንጯ ጋር አነካክታ እስከመገንጠያው ድረስ ለመሄድ ከማርታ ጋር ተያይዘው ወጡ።

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን  መስከረም 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You