“እያንዳንዱ ሠራተኛችን የራሱ የሆነ የፖለቲካ ዕይታ፣ ሃይማኖትና ብሔር ሊኖረው ቢችልም፤ ከነዚህ ሁሉ ነፃና ገለልተኛ ሆኖ ሙያዊ በሆነ መንገድ ሥራዎችን ይሠራል”ዶክተር እንዳለ ኃይሌ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ዋና እንባ ጠባቂ

የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በሁለት አዋጆች (በማቋቋሚያ አዋጅ 1142/2011 እና በመረጃ ነፃነት አዋጅ 590/2000) መሰረት ስልጣንና ኃላፊነት ተሰጥቶት የተቋቋመ የዴሞክራሲ ተቋም ነው፡፡ በእነዚህ አዋጆች መሰረትም በአጠቃላይ በመልካም አስተዳደር ስራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ፣ እንደ ሀገር በመንግስታዊ ተቋማት ውስጥ የመልካም አስተዳደር ሥርዓት እንዲሰፍን ማስቻል ተቀዳሚ ሥራው ነው፡፡

በተያያዘም ከመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ እና ከመልካም አስተዳደር አንፃር ልዩ ልዩ ጥናቶችን በማድረግ ለመንግስት ምክረ-ሃሳብ ይሰጣል፡፡ እኛም በዛሬው የተጠየቅ ዓምዳችን የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ይሄን ኃላፊነቱን ከመወጣት አንጻር የ2015 በጀት ዓመት እቅድና ክንውኑን መነሻ በማድረግ በሌሎች ተቋማዊ እንቅስቃሴዎቹ ዙሪያ ከተቋሙ ዋና እንባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ኃይሌ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ተቋሙ ከተሰጠው ተልዕኮ አኳያ በ2015 በጀት ዓመት በያዘው እቅድ መሰረት ምን ያህል በውጤታማነት የሚጠቅሳቸው ስራዎችን ሰርቷል?

ዶክተር እንዳለ፡– የኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በአዋጅ የተሰጡትን ስልጣንና ተግባራት መሰረት በማድረግ 13 ግቦችን ለይቶ ስራዎችን ሰርቷል። ከነዚህ ውስጥ በዋናነት ተቋሙ የተቋቋመለት አንዱ ስራ፣ በመንግስት አስፈፃሚ አካላት የደረሱ የአስተዳደር በደሎችን መርምሮ የመፍትሄ ሀሳብ መስጠት ነው፡፡

በዚህ ረገድ በተቋማችን በ2015 የበጀት ዓመት በእቅድ ደረጃ የተያዘው አምስት ሺህ 800 አቤቱታዎችን ለመቀበል ነበር፡፡ ነገር ግን ሰባት ሺህ 416 አቤቱታዎችን ተቀብለናል። ይህ ቁጥር በመዝገብ ጀረጃ የተቀበልነው ሲሆን፤ በግለሰብ ደረጃ 277 ሺህ 698 ዜጎች ለተቋማችን አቤቱታቸውን አቅርበዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ ደግሞ ከ100 ሺህ በላይ አቤቱታዎች የቤት ፈረሳን የሚመለከቱ ናቸው፡፡

በአጠቃላይ ከቀረቡት አቤቱታዎች መካከል በተቋማችን ስልጣንና ኃላፊነት ሊፈቱ የሚችሉ አንድ ሺህ 844 አቤቱታዎች ተቀባይነት ያገኙ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥም በበጀት ዓመቱ ለአንድ ሺህ 601 አቤቱታዎች እልባት ተሰጥቷል፡፡ የተቀሩት አቤቱታዎች ምርመራቸው ባለመጠናቀቁ ለ2016 በጀት ዓመት የተላለፉ ሲሆን፤ አንዳንድ መዝገቦች በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ተፈፃሚ የሚሆኑና በሂደት ላይ ያሉ ናቸው፡፡

ለተቋማችን የሚቀርቡ አንዳንድ አቤቱታዎች ምርመራ ሳያስፈልጋቸው አቤቱታ ከቀረበባቸው ተቋማት ጋር በመነጋገር የሚፈቱበት ሁኔታ አለ፡፡ ይህንን early resolution ብለን እንጠራዋለን፡፡ ሌሎች አቤቱታዎችንም በደል መፈፀሙን ካረጋገጥን በኋላ ምርመራ አድርገን የመፍትሄ ሃሳብ እንሰጥባቸዋለን፡፡

በበጀት ዓመቱም እልባት የሰጠንባቸው ጉዳዮች በዋናነት ከስራ ጋር የሚያያዙ አቤቱታዎች፣ የጡረታ ማስከበር አቤቱታ፣ ከመሬት ጋር የተያያዙ የይዞታ አቤቱታዎች፣ የአገልግሎት አሰጣጥ አቤቱታዎች እና የመረጃ ነፃነትን የተመለከቱ አቤቱታዎች ናቸው፡፡

ተቋማችን ባደረገው ምርመራ እና በሰጠው የመፍትሄ ሃሳብ አንድ ሺህ 332 ሰዎች ወደ ስራ ገበታቸው እንዲመለሱ፤ ያልተከፈላቸው የወር ደሞዝ እንዲከፈላቸው እና የደረጃ እድገት የሚገባቸው ሰራተኞችም እድገት እንዲሰጣቸው ተደርጓል፡፡

ከካሳና ምትክ ጋር ተያይዞ አቤቱታ ያቀረቡ 32 ግለሰቦች ካሳ እና ከ250 እስከ 500 ካሬ ሜትር ምትክ ቦታ እንዲሰጣቸው አድርገናል፡፡ ከጡረታ ጋር በተያያዘ 28 ሰዎች የጡረታ መብታቸው እንዲከበርላቸው አድርገናል፡፡ ሁለት መቶ አቤቱታ አቅራቢዎች ከህግ ውጪ የተከለከሉትን ልዩ ልዩ መንግስታዊ አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡

በበጀት ዓመቱ በአጠቃላይ የመፍትሄ ሃሳብ የተሰጠባቸው ጉዳዮች እስከ ሰኔ ወር ድረስ 60 ነጥብ ሶስት በመቶ የሚሆነው የመፍትሄ ሃሳብ ተፈፃሚ ሆኗል፡፡ የተቀሩትም የተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ስላላቸው በዚያ መሰረት ተፈፃሚ ይሆናሉ፡፡

ሌላው እንደተቋም በአዋጅ የተሰጡን ስራዎች፣ የምርመራ ስራዎችን ማከናወን፣ የቁጥጥር ስራዎችን ተግባራዊ ማድረግ እና ልዩ ልዩ ጥናቶችን መስራት ነው፡፡ በተጨማሪም ስልታዊ ምርመራዎችንም እናካሂዳለን፡፡

ከዚህ በመነሳት የአስተዳደር በደልን ከመከላከል አንፃር በበጀት ዓመቱ 52 ጉዳዮች ላይ የቁጥጥር ስራ ለመስራት አቅደን የነበረ ሲሆን፤ 46 ጉዳዮች ላይ ቁጥጥሩን ተግባራዊ ማድረግ ችለናል፡፡ ይህንን በተቋም ደረጃ 153 ተቋማት ላይ መደበኛ ቁጥጥር ለማድረግ አቅደን 164 ተቋማት ላይ በ46 ጉዳዮች ዙሪያ ቁጥጥር አድርገናል፡፡

አቤቱታ አቅራቢዎች ቅሬታ ከሚያቀርቡባቸው ጉዳዮች በመነሳት፤ ቅሬታ የሚበዛባቸውን ጉዳዮችና ተቋማት በመለየት የምርመራ ስራ እናከናውናለን። ባለፉት ዓመታት ከመንግስት የግዢ አገልግሎት ጋር በተያያዘ ምን ያህል ግልፀኝነት የሰፈነበት ነው የሚለውን መሰረት በማድረግ ምርመራ አካሂደናል፡፡

ምክንያቱም አብዛኛው የመንግስት ተቋማት ግዢ የሚካሄደው በዚህ ተቋም አማካኝነት ነው። ይህ ተቋም ነጋዴዎችን በምን አይነት አግባብ ነው የሚለየው፣ ምን አይነት የግዢ ስርዓት ይከተላል፣ ከደንበኞች ምን አይነት ቅሬታ ይቀርባል የሚለውን መሰረት አድርገን ቁጥጥር አካሂደናል፡፡

በተመሳሳይ፣ አሁን ካለው የኑሮ ሁኔታ አንፃር መንግስት ከፍተኛ ድጎማ እያደረገ የሚቀርቡ በርካታ የፍጆታ እቃዎች አሉ፡፡ እነዚህ በድጎማ የሚቀርቡ የፍጆታ እቃዎች በአግባቡ ለተጠቃሚ ሕብረተሰብ እየቀረቡ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን በሚኒስቴር፣ በንግድ ቢሮ፣ በክፍለ ከተማ እና በወረዳ ደረጃ ምን ያህል እየተቆጣጠረ ይገኛል የሚለውን የቁጥጥር ስራ አድርገናል፡፡

ከሀገራዊ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች በነበረው ጦርነት ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎች አሉ፡፡ እነዚህ የተፈናቀሉ ዜጎችን ሰብዓዊ እርዳታ ከማቅረብ አንፃርና መልሶ ከማቋቋም ረገድ ምን እየተሰራ እንደሆነ ቁጥጥር አካሂደናል። በሌላ በኩል በኦሮሚያ፣ ሶማሊያና በደቡብ ክልል የተለያዩ ዞኖች ድርቅ የተከሰተባቸው አካባቢዎች አሉ። በእነዚህ አካባቢዎች የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትና መልሶ ከማቋቋም ረገድ ምን ስራዎች ተሰርተዋል በሚል የቁጥጥር ስራዎችን ሰርተናል።

ሌላኛው፣ ለተቋማችን የተሰጠው ስልጣን ልዩ ትኩረት የሚያስፈልጋቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ማለትም ሴቶች፣ ህፃናት፣ አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች በዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች የተሰጣቸው እና ኢትዮጵያም ተግባራዊ ለማድረግ የፈረመቻቸው መብቶች አሉ። እነዚህ መብቶች በሕገ መንግስቱም ተካተው የሚገኙ ናቸው፡፡

የተለያዩ ተቋማትም እንደየስራ ባህሪያቸው የሚያወጧቸው የስራ መመሪያዎች ይገኛሉ፡፡ እነዚህ መመሪያዎች ምን ያህል በአግባቡ እነዚህን የሕብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ አድርገዋል የሚለውን እንመረምራለን። ለአብነትም፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጀት በሚመድብበት ወቅት እነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ አድርጓል ወይ? መንገድ ትራንስፖርት እንዲሁም ስራና ከተማ ልማት፣ እቅድ በሚያቅዱበትና በጀት በሚመድቡበት ወቅት እነዚህን የማህበረሰብ ክፍሎች ምን ያህል ታሳቢ ያደርጋሉ? በአጠቃላይ ለነዚህ የማሕበረሰብ ክፍሎች የተሰጡ መብቶችስ ምን ያህል ተፈፃሚ ናቸው የሚለውን የመከታተልና የመቆጣጣር ኃላፊነት ለተቋማችን ተሰጥቶታል፡፡

በዚህ ረገድ በበጀት ዓመቱ በአንድ መቶ 28 ተቋማት ላይ በ49 ጉዳዮች ዙሪያ ቁጥጥር እናደርጋለን ብለን አቅደን የነበረ ሲሆን፤ በ36 ጉዳዮች ዙሪያ አንድ መቶ 57 ተቋማት ላይ ቁጥጥር አድርገናል፡፡ ልዩ ትኩረት ከሚሹ የሕብረተሰብ ክፍሎች አንፃር አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ የትምህርት ተቋማት ምን ያህል ተደራሽነት እንዳላቸው ቁጥጥር አድርገናል፡፡ በዚህም የተገነዘብነው ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ጀምሮ የክፍል ደረጃቸው እየጨመረ በሚሄድበት ቁጥር ትምህርት የማቋረጥ ምጣኔው እየጨመረ እንደሚሄድ ነው።

ለዚህ ዋና ምክንያቱ ደግሞ ትምህርት ቤቶቹ ለነዚህ የማሕበረሰብ ክፍሎች ድጋፍ ማድረግ የሚችሉበት ብቁ የሰው ኃይል የላቸውም፡፡ የትምህርት ቤቶቹ መሰረተ ልማቶችም ለነዚህ ተማሪዎች ምቹ ሆነው አልተሰሩም። ከዚህ በተጨማሪም አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች በአግባቡ ስለማይስተናገዱና በሌሎች ተማሪዎች መገለል ስለሚደርስባቸው ለማቋረጥ ይገደዳሉ፡፡

በከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም ከሌሎቹ የተሻሉ ናቸው በሚባሉት በሀዋሳ እና በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲዎች ላይ ባደረግነው ቁጥጥር እንዳየነው፤ ሁለቱም ዩኒቨርሲቲዎች ላይ ለአይነ ስውራን የሚሆን ምቹ መንገድ የላቸውም። የመማሪያ ክፍሎቹም ቢሆኑ አካል ጉዳተኞችን ማዕከል ያደረጉ አይደሉም። የሚደረግላቸው ልዩ ድጋፍ አናሳ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲ ከደረሱ በኋላ በርካቶች ለማቋረጥ ይወስናሉ፡፡

የመረጃ ነፃነት አዋጅ ተግባራዊ እንዲሆን ለተቋማችን ሶስት መሰረታዊ ኃላፊነቶች ተሰጥተውታል። እነዚህም አንደኛ ግንዛቤ ማሳደግ፤ በተለይም በአዋጁ መረጃ እንዲሰጡ በየተቋማቱ ኃላፊነት የተሰጣቸው ለሕዝብ ግንኙነት ሰራተኞች እንደመሆኑ መጠን ለነሱ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ ይሰራል፡፡ ሁለተኛ አዋጅ ቁጥር 590/2000ን ተግባራዊ ለማድረግ የሚረዱ የሕግ ማዕቀፎች እናዘጋጃለን፡፡ ሶስተኛ የመረጃ ነፃነትን ተግባራዊ ከማድረግ አንፃር ተቋማት ምን እየሰሩ ነው የሚለውን የቁጥጥር ስራ እንሰራለን፡፡

በዚህም የመረጃ ነፃነት መብት አዋጁ በሚፈቅደው ልክ ተግባራዊ እየተደረገ እንዳልሆነ ባደረግነው ቁጥጥር ስራ ለማወቅ ችለናል፡፡ የመንግስት አስፈፃሚ አካላት በእጃቸው ያለውን መረጃ የመገናኛ ብዙሃንን ጨምሮ ለሚጠይቋቸው ዜጎች መስጠት እንዳለባቸው አዋጁ ያስገድዳል፡፡ ነገር ግን ይህንን ባለማድረጋቸው ከበርካታ የመገናኛ ብዙሃን ቅሬታ ያቀርባሉ፡፡

ከዚህ አኳያ በበጀት ዓመቱ የመረጃ ነፃነት የሚመለከቱ 141 አቤቱታዎች ለተቋማችን ቀርበዋል። እነዚህ አቤቱታዎች የመገናኛ ብዙሃንን ጨምሮ ለተለያዩ የምርምር ስራዎች መረጃ ጠይቀው በተከለከሉ ግለሰቦች የቀረቡ ጥያቄዎች ናቸው፡፡

የመረጃ ነፃነት አዋጁ የመገናኛ ብዙሃን መረጃ በጠየቁ በ10 ቀናት ውስጥ፤ እንዲሁም ማንኛውም ዜጋ በ30 ቀን ውስጥ የጠየቁትን መረጃ የማግኘት መብት እንዳላቸው ያስቀምጣል። ሆኖም ለመገናኛ ብዙሃን የተቀመጠው የአስር ቀን ገደብ መረጃን በወቅቱ ወደ ማሕበረሰቡ እንዳያደርሱ የሚያደርግ ነው፡፡ ይህንን መሰረት አድርገን አዋጁ በራሱ ክፍተት እንዳለበት በመመርመር እንዲሻሻል ሃሳብ አቅርበናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- እነዚህን ሥራዎች በማከናወን ሂደት ምን ያህል ተደራሽ ሆነናል ብላችሁ ታምናላችሁ?

ዶክተር እንዳለ፡– በሀገራችን ያለው የሰላም ሁኔታ ሁሉም ቦታ ተደራሽ ለመሆን እንዳንችል ተግዳሮት ሆኖብን ቆይቷል፡፡ ኃላፊነት ለመውሰድም ሆነ ስምሪት ለመስጠት አዳጋች ሁኔታዎች ነበሩ። ለአብነትም ኦሮሚያ ክልልን መጥቀስ እንችላለን፡፡ ስራዎቻችንን እየሰራን ያለነው ማዕከላዊ ኦሮሚያ ላይ ትኩረት አድርገን ነው፡፡

ላለፉት አራት ዓመታት ወደ ምዕራብ ወለጋ በመሄድ ስራችንን መስራት አልቻልንም፡፡ በአካባቢው ያለው የሰላም ሁኔታ አስተማማኝ ስላልሆነ ባለሙያዎቻችንን ወደ ቦታው መላክ አልቻልንም። ባለፉት ዓመታት ስራችንን እንዳንሰራ ተግዳሮት ከሆኑብን ችግሮች መካከልም ይሄ በዋናነት የሚጠቀስ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ተቋሙ የተፈተነባቸውን ጉዳዮች ካነሱ አይቀር ተቋሙ በአዋጅ የተሰጡትን ኃላፊነቶች ውጤታማ በሆነ መልኩ ተግባራዊ እንዳያደርግ እያጋጠሙት ያሉ ተግዳሮቶች ምንድናቸው?

ዶክተር እንዳለ፡– ተቋሙ በአዋጅ የተሰጠውን ስልጣንና ተግባር በአግባቡ ትግባራዊ እንዳያደርግ በርካታ ተግዳሮቶች ይገጥሙታል፡፡ ከነዚህ መካከልም በሀገሪቱ ያለው የዴሞክራሲ ባህል ደካማ መሆን ተጠቃሽ ነው፡፡ እንደ እንባ ጠባቂ ተቋም ያሉ ተቋማት ስራቸውን በአግባቡ ለማከናወን እና ውጤታማ እንዲሆኑ መንግስታዊ ተቋማት የዴሞክራሲ እሴቶችን ተግባራዊ ማድረግ አለባቸው። የዴሞክራሲ ባህላችንም ማደግ አለበት። አሁን ባለንበት የሀገራችን የፖለቲከ ሁኔታ የዴሞክራሲ ባህላችን ደካማ ነው። የዜጎችን መብት አክብረው የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት የሚሰጡ መንግስታዊ ድርጅቶችም አነስተኛ ናቸው፡፡

ምክንያቱም “መንግስት በግልጸኝነትና በተጠያቂነት መርሆች መሰረት ስራውን እየሰራ ነው ወይ? የትኛው የመንግስት ስራ አስፈፃሚ አካል ስራውን በአግባቡ ባለመስራቱ ከስልጣኑ እንዲነሳ ተደረገ? የመንግስት ስራ አስፈጸሚ አካላት ስራቸውን በግልጸኝነት ያከናውናሉ ወይ? ማህበረሰቡንስ ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ያስተናግዳሉ?” የሚሉት ጉዳዮች ሁሉ በዴሞክራሲ ስርዓት ማደግ ጋር የተገናኙ ናቸው።

ሌላኛው ለተቋሙ ተግዳሮት የሆነበት ጉዳይ፤ ከመንግስት ለስራ ማስኬጃ የሚመደብለት በጀት አነስተኛ መሆን ነው፡፡ ለተቋሙ ሰራተኞች የሚከፈለው የደመወዝ ክፍያ ዝቅተኛ መሆንም ሰራተኛው ረጅም ጊዜ በተቋሙ እንዳይቆይ አድርጎታል፡፡ የስራ ልምድ ለማግኘት ብቻ የሚቀጠሩ ከቆይታ በኋላ ድርጅቱን የሚለቁ ሰራተኞች በርካታ ናቸው፡፡ ይህ በመሆኑ ተቋሙ በርካታ ልምድ ያላቸው ሰራተኞችን ለማቆየት አልቻለም፡፡

ሌላውና ትልቁ ችግር ደግሞ፣ ተቋሙ የሚሰጣቸው የመፍትሄ ሀሳቦች የሚተገበሩት በመንግስት አስፈፃሚ አካላት በጎ ፍቃደኝነት ላይ የተመሰረቱ መሆናቸው ነው፡፡ የተቋሙ ስራ የመፍትሄ ሃሳብ መስጠት ነው፤ ይህ የመፍትሄ ሃሳብ ግን የሕግ አስገዳጅነት ባህሪ የለውም። የሕግ አስገዳጅነት ባህሪ የለውም ስንል ግን ተጠያቂ አያደርግም ማለት አይደለም፡፡ ተጠያቂ የምናደርግባቸው የተለያዩ መንገዶች አሉ፡፡

የሌሎች ሃገራትን ልምድ ስንመለከት እንደ እንባ ጠባቂ ተቋም ያሉ የዴሞክራሲ አካላት የሚሰጧችው የመፍትሄ ሃሳቦች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተግባራዊ ይደረጋሉ። በሀገራችን ግን ተፈፃሚነቱ ቅድመ ሁኔታ የበዛበትና አስፈፃሚ አካላት ተባባሪ የማይሆኑበት ሁኔታ ስላለ ችግር ሆኖብናል፡፡ እነዚህን መሰል ጉዳዮች ናቸው በበጀት ዓመቱ ውስጥ ስራዎቻችንን ለመስራት በዋና ዋና ተግዳሮት ሆነው የሚገልጹት፡፡

አዲስ ዘመን፡- ተቋሙ በችግርነት ካነሷቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የአስፈጻሚ አካላት ተባባሪነትን ይመለከታል፡፡ በዚህ ረገድ ተቋማችሁ ስራውን በተሳካ መልኩ እንዲሰራ የመንግስት አስፈፃሚ አካላት እገዛ ምን ሊሆን ይገባዋል?

ዶክተር እንዳለ፡– በአዋጃችንም ሆነ በዓለም አቀፍ መርሆች የሚያስቀምጡት፤ የመንግስት አስፈፃሚ አካላት፣ የዴሞክራሲ ተቋማት በተለይም ከሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የሚሰጡትን የመፍትሄ ሀሳቦች የመተባበር ኃላፊነት አለባቸው፡፡

የመተባበር ኃላፊነት አለባቸው ሲባል፤ ሕገመንግስቱም ላይ በግልፅ እንደተቀመጠው የመንግስት ተቋማት በግፀኝነትና በተጠያቂነት መርህ መሰረት መስራት አለባቸው፡፡ እነዚህ መንግስታዊ ተቋማት ስራቸውን የሚሰሩት ከሕዝብ በሚሰበሰብ ግብር ነው። ስለዚህ ለግብር ከፋዩ ሕብረተሰብ የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት በአግባቡ የመስጠት ግዴታ አለባቸው፡፡

አንዳንድ ተቋማት ይህንን ግዴታቸውን በመዘንጋት በእነሱ ፍቃድ ላይ የተመሰረተ አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ይመስላቸዋል፡፡ ከዚህ አኳያ በ2016 በጀት ዓመት መንግስት ትኩረት ሊያደርግባቸው ይገባል ብለን የለየነው፤ የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽንን መሰረት አድርገው የተዋቀሩ የሲቪል ሰርቪስ ቢሮዎች አሉ፡፡ በእነዚህም የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያ ፕሮግራምን የበለጠ ማጠናከር ይኖርበታል፡፡

ለአብነት፣ አብዛኛው የመንግስት ተቋማት በተለይ ገቢ ከሚያመነጩ ስራዎች ጋር የተያያዙ ተቋማት ከፍተኛ የሆነ ብልሹ አሰራር እንደሚስተዋልባቸው በቁጥጥር የለየናቸው ተቋማት አሉ፡፡ የመንግስት ተቋማት ከሕዝብ በሚሰበሰብ ታክስ የሚተዳደሩ እንደመሆናቸው መጠን የሕብረተሰቡን ፍላጎት መሰረት ያደረገ አገልግሎት መስጠት አለባቸው። ይህንን ሳያደርጉ ቀርተው ወደ ተቋማችን የሚመጡ አስተዳደራዊ በደሎችን መርምረን ተቋማቱ የመፍትሄ ሃሳብ የማሰጠት ኃላፊነት አለብን፡፡ ስለዚህ ይህንን በመፈፀም ረገድ የመንግስት አስፈፃሚ አካላት ኃላፊነትም ግዴታም ያለባቸው መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡

አዲስ ዘመን፡- በዚህ መልኩ በሥራ አስፈጻሚው ተጽዕኖ ያለ ከመሆኑ አንጻር በተቋማት ምላሽ የማይሰጥባቸውን ጉዳዮች ለይቶ ምላሽ በማይሰጡ የመንግስት ተቋማት ላይ ክስ ከመመስረትና ጉዳዩን ለሚመለከተው አካልም ሆነ ለሕዝብ ከማሳወቅ አንፃር ምን የተሰሩ ስራዎች አሉ?

ዶክተር እንዳለ፡– የሚሰጣቸውን የመፍትሄ ኃሳቦች የማይፈፅሙ አካላት ካሉ አንደኛው መንገድ ክስ መመስረት ነው፡፡ ሌላኛው፣ ደግሞ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኤርፖርት እናቀርባለን፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በመገናኛ ብዙሃን የማጋለጥ ስራ እንሰራለን፡፡

በዚህም በ2015 በጀት ዓመት የተሰጣቸውን የመፍትሄ ሀሳብ ተግባራዊ ባላደረጉ ሶስት የመንግስት አስፈፃሚ አካላት ላይ በልዩ ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበናል። እነዚህ ተቋማትም፤ የፌደራል ጉምሩክ ኮሚሽን፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ናቸው፡፡

ለምሳሌ፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አባላት የሰባት ዓመታት አገልግሎት ካጠናቀቁ በኋላ መልቀቂያ የማግኘት መብት አላቸው። ይህ የፖሊስ አባላት መብት ነው። ይህንን ደንብ በመተላለፍ መልቀቂያ የሚከለክሉ ተቋማት አሉ፤ በተለይም የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፡፡ ስለዚህ እነዚህ ተቋማት ከእኛም አቅም በላይ ስለሆኑ እና በተደጋጋሚ በአካልም ውይይት አካሂደን፣ በርካታ የደብዳቤ ምልልሶችንም አድርገን ለማስተካከል ፍቃደኛ ስላልሆኑ በልዩ ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ልከናል፡፡

ከፌደራል ጉምሩክ ኮሚሽን ጋር በተያያዘ፤ ማንኛውም ሰው ወደ ሀገር ውስጥ በሚገባበት ወቅት የግል መገልገያ እቃዎችን ይዞ የመግባት መብት አለው። ነገር ግን ይህ መብት በእቃው አይነት አልተለየም፤ በዓመት ምን ያህል ጊዜ ማስገባት እንደሚቻል አልተገለፀም፤ መግባት የሚችለው የእቃ መጠንም በቁጥር አልተቀመጠም፡፡

ይህንን ክፍተት እንዲያስተካክል ለኮሚሽኑ አሳውቀን መመሪያ አዘጋጅቷል፡፡ ይህንን ማድረጉ የሚበረታታ ነው። ነገር ግን ይህ መመሪያ ከመዘጋጀቱ በፊት ከ300 በላይ አቤቱታዎች ወደ ተቋማችን መጥተዋል፡፡ ይህ መመሪያ ግን በነዚህ ሰዎች ላይ ተግባራዊ አይሆንም ተገዢም አያደርጋቸውም፡፡ ስለዚህ የተወረሰባቸው ንብረት እንዲመለስላቸው ብለን የመፍትሄ ሀሳብ ብንሰጥም አልፈፀመም፡፡ በዚህ ምክንያት ተቋማችን ተጠሪነቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመሆኑ በልዩ ሪፖርት አስተላልፈናል።

ከዚህ ባለፈ፣ ተቋማችን ሰባት የክልል ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶች አሉት፡፡ በእነሱ አማካኝነት 11 ጉዳዮች ላይ ክስ እንዲመሰረትባቸው ወደ ፍርድ ቤት ልከናል። ሁለት ጉዳዮች ላይ በመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት የማጋለጥ ስራ ሰርተናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ተቋሙ በሥራ ሂደት የሚገጥሙት ፈተናዎችንም ሆነ ከአስፈጻሚ አካላት ጭምር የሚመጡበትን ጫናዎች ተቋቁሞ የመስራት ሁኔታው ምን ይመስላል?

ዶክተር እንዳለ፡– ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት ባለው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ የዴሞክራሲ ተቋማት እንደልባቸው የሚሰሩበት አውድ የለም፡፡ ፖለቲካዊ ጫና፣ የበጀት ጫና እና በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ተንቀሳቅሶ መስራት አለመቻልን የመሳሰሉ ጫናዎች አሉ፡፡ እነዚህ ጫናዎች ተቋሙ መስራት በሚፈልገው ልክ እንዳይሰራ እንቅፋት ሆነውበታል። ቢሆንም ተቋማችን እነዚህን ጫናዎች ተቋቁሞ ያቀዳቸውን እቅዶ 85 በመቶ ለማሳካት ችሏል፡፡

ሌላው መታወቅ ያለበት ተቋማችን የተለያዩ ጫናዎች ቢኖሩበትም፣ ነፃና እና ገለልተኛ ሆኖ ከመስራት አንፃር ከየትኛውም የመንግስት ወገን ጣልቃ ገብነት የለበትም። እያንዳንዱ ሰራተኛም የራሱ የሆነ የፖለቲካ እይታ፣ ሀይማኖትና ብሄር ሊኖረው ቢችልም፤ ከነዚህ ሁሉ ነፃና ገለልተኛ ሆኖ ሙያዊ በሆነ መንገድ ስራዎችን ይሰራል። የመንግስት አስፈፃሚ አካላት በስራችን ጣልቃ የመግባት ሁኔታም አነስተኛ ነው፤ ይህ መሆኑ ለኛ ትልቅ እድል ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ተቋሙ በአዋጅ የተሰጠው ስልጣንና ተግባር ላይ የተደረገው ማሻሻያ በስራችሁ ላይ የፈጠረው ለውጥ አለው?

ዶክተር እንዳለ፡– በ2011 ዓ.ም በፊት ከነበረው ስልጣንና ተግባር ላይ ማሻሻያ ተደርጓል፡፡ ከዚህ በፊት ተቋሙን የሚመሩ አመራሮችን መርጦ በቦታው ላይ ያስቀምጥ የነበረው ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ነው፡፡ የተቋሙ ሰራተኞች አብዛኞቹ የፖለቲካ ፓርቲ አባል የነበሩ ሲሆን ሁለት ኃላፊዎች የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የነበሩ ናቸው። አዋጁ ከተሻሻለ በኋላ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የነበሩ ከአባልነታቸው እንዲለቁ ተደርጓል፡፡ በተቋሙ ውስጥ የነበሩ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ አባል የነበሩ ሰራተኞች ከአዋጁ መሻሻል በኋላ ከአባልነታቸው እንዲለቁ ተደርጓል፡፡

በአዋጁ በግልፅ እንደተቀመጠው የተቋሙ አመራር የየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆን እንደሌለበትና ነፃና ገለልተኛ ሆኖ መስራት እንዳለበት አስቀምጧል፡፡ በ2011 ዓ.ም የተሻሻለው ይህ አዋጅ ተቋሙ ነፃና ገለልተኛ ሆኖ መስራት የሚያስችለውን አቅም ሰጥቶታል፡፡ በቀጣይም ተቋሙ ተጨማሪ አቅም እንዲኖረው እና ተደራሽነቱን ለማስፋት እንዲያስችል ተጨማሪ ማሻሻዎች እንዲደረጉበት ጠይቀን ምላሽ በመጠበቅ ላይ እንገኛለን፡፡

እስካሁን ስንሰራ የነበረው በመንግስት አስፈፃሚ አካላት የሚፈፀሙ አስተዳደራዊ በደሎች ላይ ብቻ ነው፡፡ በቀጣይ አዋጁ ሲሻሻል በመንግስት ተቋማት ላይ ብቻ ሳንወሰን በትላልቅ የግል ተቋማት ላይ የሚቀርቡ አቤቱታዎችንም ማስተናገድ እንድንችል ያግዘናል፡፡

ምክንያቱም፣ ባለው ሁኔታ በተመረጡ ትላልቅ የግል ተቋማት ላይ የሚቀርቡ አቤቱታዎች አሉ። ለምሳሌ፤ አበባ እርሻ ላይ ከደመወዝ ጋር ተያይዞ፤ እንዱስትሪ ፓርኮችም ከጉልበት ብዝበዛ ጋር በተያያዘ የሚቀርቡ ቅሬታዎች አሉ። ኣዋጁ ሲሻሻል ይህንን ማስተናገድ የምንችልበት ስልጣንና ኃላፊነት ይሰጠናል ብለን እንገምታለን፡፡

አዲስ ዘመን፡- ተቋሙ ካለፉት ካለፈው ሂደት (ከድክመቱም፣ ከጥንካሬውም) ተምሮ በቀጣይ ተልዕኮውን የሚመጥን ሥራን ከመስራት አኳያ ምን አስቧል?

ዶክተር እንዳለ፡– ከባለፉት ዓመታት ልምዶቻችን አንዳንድ ሀገራዊና ወቅታዊ ጉዳዮች ትኩረት የሚፈልጉ መሆናቸውን ተምረናል፡፡ ስለዚህ እነዚህን የእቅዳችን አካል አድርገን እንዲሰራ አድርገናል፡፡ ከዚህ በፊት እርምጃ የምንወስደው ክስተቶቹ ሲከሰቱ ብቻ ነበር። ለአብነት፤ በአንድ አካባቢ ላይ መፈናቀል ይኖራል። ከመፈናቀላቸው በፊት መንግስት የሕግ የበላይነትን ማስከበር ያልቻለው ለምንድነው፣ ከተፈናቀሉ በኋላስ መንግስት ለነዚህ ተፈናቃዮች ምን አደረገ የሚለውን የምናየው ጉዳዩ ከተከሰተ በኋላ ነበር፡፡

ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ግን የሚከሰቱ ወቅታዊና ሀገራዊ ጉዳዮች በማለት ለይተን ከሁለት እስከ ሶስት የሚደርሱ ጉዳዮችን ማየት እንዳለብን የእቅዳችን አካል አድርገናል፡፡ ይህንን የእቅዳችን አካል አድርገናል ስንል ለዚህ ታሳቢ የሚሆን በጀትም እንመድባለን ማለት ነው፡፡

ለምሳሌ፣ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮችን የሚመለከቱ ተቋማት፤ መንግስት የሚሰራቸውን መልካም ስራዎች ለሕብረተሰቡ የማሳወቅ ስራ ይሰራሉ፡፡ የዴሞክራሲ ተቋማት ደግሞ መንግስት፣ በእቅድ የሚይዛቸው ጉዳዮች፣ የሚሰጣቸው ውሳኔዎች፣ በሚያወጣቸው መመሪያዎች ደንቦችና አዋጆች ክፍተቶች ካሉ ያንን የመተቸት ስልጣንና ኃላፊነት አለባቸው፡፡ እኛም በድፍረት መንግስትን በመተቸት መንግስትም እጁን ሰብሰብ እንዲያደርግ እና ውሳኔዎችን ዳግም ማየት እንዲችል የተደረገበት ሁኔታ አለ፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ከባለፉት ዓመታት የወሰድናቸው ተሞክሮዎች ናቸው፡፡

በቀጣይም እነዚህን ልምዶች ከማስቀጠል ባሻገር ተቋሙ በአዋጅ የተሰጠውን፤ አስፈፃሚ አካላት የሚያወጧቸው ህጎችና ደንቦች በህገ መንግስቱ ላይ ከተቀመጡ የዜጎች መብቶችን ጋር የማይቃረኑ መሆናቸውን የመመርመር ኃላፊነት በተጠናከረ መልኩ ለመወጣት ራሱን የቻለ ክፍል በማቋቋም ሰፊ ስራ ለመስራት አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡

ከዚህ ቀደም ከዚህ ጋር በተገናኘ በጉምሩክ ኮሚሽን ላይ ምርመራ አድርገናል፡፡ አንድ የጉምሩክ ኃላፊ አንድን የጉምሩክ ሰራተኛ በሙስና ከጠረጠረ ወዲያው ያለ ምንም ማስጠንቀቂያ ከስራ እስከ ማባረር የሚደርስ ስልጣን ይሰጠዋል፡፡ ይህ ተገቢ አይደለም፡፡ ዜጎች የመደመጥ መብት አላቸው፡፡ እነዚህን የመሳሰሉ ጉዳዮችን እንመረምራለን፡፡

የዜጎችን መብት የሚጣረሱ በርካታ የሚወጡ ህጎች አሉ፡፡ ለአብነትም በዚህ ዓመት የምርመራ ስራ ያካሄድንበትን ለመምህራን በሚሰጥ ቤት ላይ የወጣ ሕግን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለመምህራን ቤት የሚያቀርብ መሆኑ ይታወቃል፤ ነገር ግን በዚህ ሕግ መሰረት ቤት የሚሰጣቸው መምህራን ቤቱን የሚወርሱበት ሁኔታ የለም፡፡ ቤቱን የሚጠቀሙም በሕይወት እስካሉ ብቻ ነው። ይህ የዜጎችን ንብረት የማፍራት መብት መገደብ ነው። ስለዚህ ይህንን እና መሰል ሌሎች ጉዳዮችን የሚመለከት የተደራጀ ክፍል የምናቋቁም ይሆናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ እናመሰግናለን።

ዶክተር እንዳለ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

በለጥሻቸው ልዑልሰገድ

አዲስ ዘመን መስከረም 23/2016

Recommended For You