
የግብርና ሥራ ብዙ ድካምና ልፋት ይጠይቃል:: አርሶ አደሩ ማሳውን አርሶና አለስልሶ በተለይ በዘር ከመሸፈን አንስቶ ምርቱን ወደ ጎተራ እስከሚያስገባ ድረስ ባሉት ጊዜያት በርካታ ፈተናዎች ሊገጥሙት ይችላሉ:: ምን ቡቃያው ቢያምር፣ የሰብሉ ቁመና ቢያጓጓ፣ አዝመራው ተሰብስቦ ጎተራ ካልገባ እፎይ አይባልም:: ሀይለኛ ዝናብ፣ በረዶ፣ ጎርፍ፣ አንበጣና የመሳሰሉት ተባዮች ፈተና የሚሆኑባቸው ጊዜያት ያጋጥማሉ::
በተለይ በሰብል ላይ የሚከሰቱ ተባዮች ዓመቱን ሙሉ የተደከመበትን አዝመራ ከንቱ ሊያስቀሩት ይችላሉ:: እንደ ተምች፣ አንበጣ፣ ግሪሳ ወፍ ያሉት ጸረ ሰብል ተባዮች ሰብሉን ከቡቃያው አንስቶ በእሸትነቱ በማውደም አርሶ አደሩን መና የሚያስቀሩባቸው ሁኔታዎች በርካታ ናቸው::
ጸረ ሰብል ተባዮቹ በተመሳሳይ ወቅት ወይም በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ መነሻ ምክንያቶች ሊከሰቱ ይችላሉ:: ይህን የሚያውቀው አርሶ አደር የጸረ ሰብል ተባዮቹን እንቅስቃሴ በንቃት በመከታተል በሰብል ላይ ብዙ ጉዳት ከማድረሳቸው በፊት አስቀድሞ በቁጥጥር ስር ለማዋል ርብርብ ያደርጋል::
አርሶ አደሮች ተባዩ ከአቅማቸው በላይ ሊሆን ሲችል ባህላዊ ዘዴዎችን በመጠቀም አቅማቸው በፈቀደው መጠን ለመከላከል ጥረት የማድረግ ልምድ አላቸው:: ተባዮቹን ለመቆጣጠር ከዚህም ባለፈ እንደ መከላከያ ሰራዊትና የመሳሰሉትን የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በማስተባበር ጭምር በዘመቻ ይሰራል::
እነዚህን ተባዮች በመከላከል ረገድ በአርሶ አደሩ የሚሰሩ ሥራዎች እንዳሉ ሁሉ በግብርና ሚኒስቴር በኩልም የተለያዩ ሥራዎች ይከናወናሉ:: ተባዮቹ አንዳንዴ ድንበር ተሻጋሪ በመሆናቸውም በምስራቅ አፍሪካ ደረጃ ተባዮቹን ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባሮችም ይሰራሉ::
በግብርና ሚኒስቴር መስሪያ ቤት በኩል በሰብል ጥበቃ ሥራ ተባይ በመከላከልና አሰሳ ዙሪያ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ይሰራሉ:: ተባይ ሳይከሰትም ሆነ ከተከሰተ በኋላ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ለመከላከልና ለማጥፋት የሚያስችሉ ሥራዎችም እንዲሁ ይከናወናሉ::
የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ እስካሁን ድረስ ያለው የበልግም ሆነ የክረምት ወቅቱ በጣም ርጥበት አዘል መሆን ተባዮቹ እንዲስፋፉ ሰፊ እድል ይፈጥራል:: ከዚህ ውስጥ አንዱ ወቅቱ ለተምች መከሰት ምቹ ሁኔታው እንደሚፈጠር ቀድሞም የታወቀበት ስለነበር ቅድመ ዝግጅቶች በማድረግ ተምቹን በኬሚካልና በሰው ኃይል የመከላከል ሥራ ተሰርቷል::
ሌላው በመኸር ወቅት የመከሰት አጋጣሚው ብዙ እንደሆነ የሚታወቀው የግሪሳ ወፍ ነው:: ይህንንም ቀደም ሲል በባህላዊም ሆነ በዘመናዊ መንገድ የመከላከል ሥራ ተሰርቷል:: ከዚህ በተጨማሪም እንዲዚህ አይነት ጸረ ሰብል ተባዮች የመከላከል ሥራን ለመስራት አውሮፕላኖች ጭምር በመጠቀም የመከላከልና መቆጣጠር ሥራዎች እንደሚከናወኑ መረጃው ያመላክታል::
በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተው የግሪሳ ወፍ ቀደም ብሎ ሊከሰት የሚችልበት አጋጣሚ ከፍተኛ እንደነበር በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከተለዩት ውስጥ አንዱ ነው:: በተለይ በዚህ ወቅት እንደሚከሰት የሚጠበቀው የግሪሳ ወፍ በሰብል ላይ ጉዳት ከማድረሱ በፊት ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን ነው የግብርና ሚኒስቴር የእጽዋት ጥበቃ መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ በላይነህ ንጉሴ የሚናገሩት::
እሳቸው እንደሚሉት፤ የግሪሳ ወፍ በየዓመቱ የሚከሰት ተዛማች ተባይ ነው:: ከሦስት ሳምንት በፊት በሦስት ክልሎች (በቀድሞው ደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አካባቢዎች፣ በአማራ እና በኦሮሚያ) የግሪሳ ወፍ ተከስቷል:: በተለይ ስንዴ እና ጤፍ አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች ላይ በብዛት ገዝፎ ታይቷል::
የወፉን ሥርጭት ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው የሚሉት አቶ በላይነህ፤ አሁን ግሪሳ የተከሰተባቸው ቦታዎች ላይ በአውሮፕላን የኬሚካል ርጭት እየተካሄደ መሆኑን ይገልጻሉ:: የግሪሳ ወፉ በሰብሎች ላይ ጉዳት ከማድረሱ በፊት ርብርብ በማድረግ የመከላከል ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ይናገራሉ::
እሳቸው እንዳሉት፤ በቀድሞው የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በሚገኝ አንድ ወረዳ ተከሰቶ ለመቆጣጠር ተችሏል:: በኦሮሚያ ክልልም እንዲሁ በስምጥ ሸለቆ (ዝዋይና መቂ) አካባቢ ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሰሩ ናቸው:: በአማራ ክልልም ባለሙያዎች የተከሰተባቸውን ቦታዎችና አካባቢዎች የመለየት ሥራዎች እየተሰሩ ሲሆን፣ ቦታዎቹ ከተለዩ በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ መከላከል ሥራ ይገባል::
ወፉ ቀድሞ እንደሚከሰት ይታወቅ ስለነበር የመከላከል ሥራውም ቀደም ብሎም ሲሰራ ነበር ያሉት አቶ በላይነህ፣ ቀድሞ መከላከል ሲባል ተባዮቹ ተዛማች ስለሆኑ እንደ ተከሰቱ (እንደመጡ) የመከላከል ሥራ እንደሚካሄድ ይናገራሉ:: እሳቸው እንዳሉት፤ ከሶስት ሳምንት በፊት የኬሚካል ርጭቱ ተጀምሯል፤ በምስራቅ ሐረርጌ ዞን በተለይ ባቢሌ ወረዳ አምስት ሚሊዮን የሚገመቱ የግሪሳ ወፎችን የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራ ተሰርቷል:: በሌሎችም ቦታዎች ላይ የሚደረገው የመከላከል ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል:: እነዚህ ወፎች ተዛማች እንደመሆናቸው መጠን እንደተከሰቱ በፍጥነት የመከላከሉ ሥራ ይካሄዳል::
የግሪሳ ወፎቹ አመጣጥ ከታንዛንያ ጀምሮ ኬንያ እያለ ከዚያ ወደ ኢትዮጵያ ይገባሉ የሚሉት አቶ በላይነህ፤ ተዛማች እንደመሆናቸው መጠን እንደ ክስተቱ መጠን እየታየ የመከላከል ሥራው እንደሚሰራ ይናገራሉ:: ወፎቹን መቀነስ እንጂ ሁሉንም ጥርግርግ አድርጎ ማጥፋት አይቻልም ያሉት አቶ በላይነህ አርሶ አደሩ በባህላዊ መንገድም በመጠቀም፣ ማማዎች እየሰራ ሰብሎች ላይ ጉዳት ከመድረሱ በፊት እየተከላከለ እንደሆነም ይገልጻሉ::
‹‹ይህ ሲባል ግን በሰብሎች ላይ ምንም አይነት ጥቃት አልደረሰም ማለት አይደለም ሲሉም ጠቅሰው፣ ጥቃቱ ሊደርስ ይችላል፤ ነገር ግን ከፍተኛ አይሆንም›› ብለዋል:: ይህም አርሶ አደሩ ሰብሉን በንቃት እየጠበቀ መሆኑንና በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በኩልም የሚደረገው የመከላከል ጥረት በሰብል ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዳይደርስ አድርጓል ብለዋል::
ከወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር ተያይዞ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ እንደተፈለገ ተገብቶ የመከላከል ሥራው የማይሰራባቸው ሁኔታዎች እንዳሉ የገለጹት አቶ በላይነህ፤ በእነዚህ ቦታዎች ላይ ከሕዝቡ ጋር በመተባበር የመከላከል ሥራው እንደሚሰራ ይናገራሉ::
አቶ በላይነህ እንደሚሉት፤ የግሪሳ ወፍ የዝናቡ ሁኔታ ምቹ ሲሆን በስፋት ይራባል:: እንዲህ እንዲራቡ የሚያደርጋቸው በዝናብ ወቅት ከሰብል ይልቅ ሳር ስለሚያገኙ ነው፤ ሳሩን እየተመገቡ መራባት ይጀምራሉ:: እነዚህ ቦታዎች ምናልባትም ሰው የማይደርስባቸው ወይም የማያያቸው ለወፎቹ ምቹ የሆኑ ቦታዎች ሊሆኑ ይቻላል:: የአየር ሁኔታውም እንዲሁ ምቹ ከሆነላቸው የመራባት ሁኔታቸው ይጨምራል::
በሌላ በኩል የግሪሳ ወፎችን በመከላከል ረገድ ሁሉም አገራት እኩል ትኩረት አይሰጡም ያሉት አቶ በላይነህ፤ አንደኛው አገር ትኩረት ሰጥቶ የመከላከል ሥራውን ሲሰራ፤ ሌላኛው ብዙም ትኩረት የማይሰጥበት ሁኔታ ያጋጥማል ይላሉ:: በዚህ የተነሳ የግሪሳ ወፉ ከአንዱ አገር ወደ ሌላው አገር የሚያደርገው መዛመት ሊበራከት የሚችልበት ሁኔታ መኖሩን ያመለክታሉ::
ተዛማች ተባዮችን መከላከልና መቆጣጠር ላይ የአገራት ቅንጅት በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዚህም ሲባል የበረሃ አንበጣ መከላከል ድርጅት ተቋቁሞ ተዛማች ተባዮችን የምስራቅ አፍሪካ አገራት በቅንጅት እየተከላከሉ መሆናቸውን ይጠቁማሉ:: ይህም በቀጣይ የወፉ ስርጭት እየቀነሰ ይመጣል የሚል ግምት እንደሚያሳድር አመላክተዋል::
አቶ በላይነህ፤ የወፎቹ ባህላዊ መራቢያ የሚባሉ ቦታዎች እንዳሉም ያመለክታሉ:: እነዚህን እየተከታተሉ የወፎችን ጎጆዎች እያፈረሱ፣ እንቁላሎቻቸውን በመሰባበር እና መሰል መራቢያ መንገዶችን በማጥፋት አርሶ አደሩ የሚሰራ ከሆነ የወፉ መጠን እየቀነሰ ይመጣል ይላሉ::
አቶ በላይነህ እንዳብራሩት፣ እነዚህ የግሪሳ ወፎች ከማደሪያ ቦታቸው 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ድረስ በመጓጓዝ ሰብሎችን ማጥቃት ይችላሉ:: ጥቃቱን በሚፈጸሙበት ጊዜ ሰብሎቹ ለወፎቹ ምግብነት ምቹ የሚሆኑበት ጊዜም ይወስናል:: ተዘርቶ እስከ ወር ድረስ ያለውን የስንዴ ቡቃያ ሊመገቡ የሚችሉበት ሁኔታ አለ:: በተለይ ሰብሉ ጮርቃ (ለጋ) በሚሆንበት ጊዜ የመመገብ ፍላጎታቸው ይጨምራል፤ ጠንከር ሲልም ይመገቡታል:: እንዲሁም በእግራቸው ፈርፍረው ሊያጠፉትም ይችላሉ:: ጥፋታቸው በመብላት ብቻ የሚወሰን ሳይሆን በእግራቸውም ጭረው በመበተን ጥፋት ሊፈጸሙ ይችላሉ::
አእዋፍቱ ለእነሱ ምግብነት ምቹ የሆነው የሰብል አይነት ሁሉ ያጠፋሉ የሚሉት አቶ በላይነህ፤ በተለይ የበኸር እህሎችን በብዛት እንደሚያጠቁ ይናገራሉ:: ከጤፍ እና ከአገዳ እህሎች ማሽላን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያጠፉ ጠቅሰው፣ ለአመጋገባቸው የሚመቻቸውን የሰብል አይነት ካገኙ ከማጥፋት ወደ ኋላ ባይሉም እነዚህን ሰብሎች ግን የማጥፋት አቅማቸው ከፍተኛ ነው ሲሉ ያብራራሉ::
አቶ በላይነህ እንዳብራሩት፤ በአገራችን በአሁኑ ወቅት የተከሰተውን የግሪሳ ወፍ መንጋ የመከላከል ኦፕሬሽን እየተሰራ ነው፤ አሁን ላይ የመከላከሉ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል:: እስካሁን በሰብሎች ላይ ያስከተለው ጉዳት መጠን የመከላከሉ ሥራ ሲጠናቀቅ ተጠንቶ ይታወቃል::
አሁን ላይ በሚታየው ግምታዊ ሁኔታ አርሶ አደሩ ሰብሉን እየጠበቀ መሆኑን ጠቅሰው፣ በሰብሎች ላይ የደረሰ ጉዳት ቢኖርም፣ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል የሚል እምነት እንደሌላቸው አቶ በላይነህ ይገልጻሉ:: የመከላከሉ ሥራ ፈጥኖ መጀመሩና የኬሚካል ርጭት እየተካሄደ መሆኑ ጉዳቱን ሊቀንሰ እንደቻለ ተናግረዋል፤ እስካሁን ባለው ሁኔታ የተወሰነ ጉዳት ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ጠቅሰው፣ ከፍተኛ ጉዳት እንዳልደረሰ ግን አመላክተዋል::
‹‹የግሪሳ ወፎች በራሪ በመሆናቸው ወደ ሚፈልጉበት አካባቢ ይንቀሳቀሳሉ:: በተለምዶ እነዚህን አካባቢዎች ያዘወትራሉ›› የሚሉት አቶ በላይነህ፤ እነዚህ አካባቢዎች ላይ ሰብሉ ከመድረሱ በፊት ቀድሞ የመከላከሉ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው ይገልጻሉ:: አርሶ አደሩ እነዚህ ወፎች አካባቢው ላይ በሚመጡበት ጊዜ ሰብሉን የመጠበቅ ሥራውን አጠናክሮ መቀጠል አለበት›› ይላሉ::
‹‹ መታወቅ ያለበት ዋናው ነገር ግን ወፉን እስከመጨረሻ በአውሮፕላን ኬሚካል እየረጨን መከላከል የሌለብን መሆኑን ነው›› የሚሉት አቶ በላይነህ፤ የሚራቡበት ቦታ ላይ በመለየት በሚሰራ ሥራ የወፉን ቁጥር መቀነስ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ አስገንዝበዋል:: ‹‹አርሶ አደሩም ማወቅ ያለበት ኬሚካል ብቻ መጠበቅ እንደሌለበት ነው:: የኬሚካል ርጭት ግዴታ ሲሆን ብቻ የሚከናወን ነው፤ ምክንያቱም ኬሚካል በምንረጭበት ጊዜ አካባቢ እንበክላለን፤ በዚህም ብዙ ጉዳቶች እናስከትላለን:: ኬሚካሉ በአካባቢው ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ ነው›› ሲሉ ያብራራሉ::
በተለይ የወፍ ጎጆውን ማፍረስ የመራቢያ ቦታውን በማጥፋት ቀጣይ ርቢ እንዳይኖር መስራት ይጠበቃል:: አርሶ አደሩ በዚህ ልክ ከሰራ የወፉን ቁጥር መቀነስ ይቻላል:: በተለይ በአገር ውስጥ የሚራቡትን አእዋፋት ቁጥር በእጅጉ መቀነስ ስለሚቻል በዚህ ላይ በደንብ መስራት እንደሚጠይቅ አመላክተዋል::
ከዚህ በተጨማሪም በበረሃ አንበጣ መከላከል ድርጅት ሥር ያሉት አገራት ተባብረው በጋራ መሥራት አለባቸው የሚሉት አቶ በላይነህ፣ ‹‹ይህ ሲሆን የወፉን ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እየቀነስን ልንሄድ እንችላለን›› ብለዋል:: ይህ አሠራር እየተዘረጋ የሚሄድበትን ሁኔታ ከእነዚህ አገራት ጋር ባለው የጋራ መድረክ በመነጋገር መመቻቸት እንደሚያስፈልግም ይገልጻሉ::
ከዚህም በላይ ሁሉም የራሱን ድርሻ ወስዶ በባህላዊ መንገድ ወፉን የመከላከል ዘዴውን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተው ያስገነዝባሉ:: ‹‹ኬሚካል ብቻ እየጠበቅን የምንከላከል ከሆነ ጉዳቱ የከፋ ይሆናል፤ ኬሚካሉ የመጨረሻው አማራጭ ተደርጎ መወሰድ አለበት:: ከዚህ በፊት ግን ብዙ የሚሰሩ ሥራዎች አሉ:: በእኛ በኩልም ብዙ ሥራዎች መስራት ይጠበቅብናል›› ብለዋል::
የእጽዋት ጥበቃ ሥራ ለአፍታም አይቋረጥም፤ ተከታታይነት ያለው ሥራ መሰራት አለበት የሚሉት አቶ በላይነህ፤ በርካታ ወቅቱን ጠብቀው የሚሰሩ ሥራዎች እንዳሉ ይናገራሉ:: የበረሃ አንበጣ የመከላከል ሥራውም እንዲሁ የሚቆም አለመሆኑን ገልጸዋል::
በቀጣይም አሰሳ የሚደረግባቸው አካባቢዎች ስለመኖራቸው ያነሱት አቶ በላይነህ፤ የዋግ በሽታዎችንም ከአርሶ አደሩ ጋር በመሆን መከላከል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል:: በሌሎችም ጸረ ሰብል ተባዮች ዙሪያ እንዲሁ መስራት ያለባቸው ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመልክተው፣ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር ለእጽዋት ጥበቃ ሥራው ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል::
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 21 ቀን 2016 ዓ.ም