ቅርሶች ያለፈውን፣ ዛሬ ላይ የምንኖረውን እና ወደፊት የሚከሰተውን ሁነት የሚወክሉ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፉ የሰው ልጆች ሀብት ናቸው። ባህላዊ እና ተፈጥሯዊ ቅርሶቻችን የማይተኩ የሕይወት ምንጮች እና መነሻዎች እንደሆኑ ይታመናል። ከዚህ መነሻ ዩኔስኮ ለሰብአዊነት የላቀ ጠቀሜታ ያላቸውን የባህልና የተፈጥሮ ቅርሶችን የመለየትና የመጠበቅ ሥራን ያበረታታል።
ዓለማችን ላይ እነዚህን መስፈርቶች የሚያሟሉ ሀብቶችን የመመዝገብ እንዲሁም የማስተዋወቅ ድርሻንም ይወስዳል። ሀገራትም ይህንን ዕድል በመጠቀም መስፈርቱን የሚያሟሉ ሀብቶቻቸውን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ለማስመዝገብ ይሠራሉ። ይህ ዕድልም ዓለም አቀፍ ቱሪስቶችን ለመሳብ፣ ሀገርን የበለጠ ለማስተዋወቅና ገፅታን ለመገንባት ይጠቀሙበታል።
የማንነት መገለጫ የሆኑ ሀብቶችን ከማስተዋወቅ በዘለለ በቱሪዝም ዘርፉ ሀብቶቹ የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንቶች ናቸው። ኢትዮጵያ እነዚህን መሰል ሀብቶች ለቱሪስት መስህብነት እንዲውሉ በመሥራትና ቱሪዝምን ከዋና ዋና ዘርፎች መካከል አንዱ በማድረግ ትታወቃለች። በተፈጥሮ፣ ታሪክ፣ ባህልና አርኪዮሎጂ ዘርፍ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ 15 የሚደርሱ ቅርሶችን ለዓለም አበርክታለች። ከእነዚህ ውስጥ በ2016 ዓ.ም መባቻ በመስከረም ወር በአዲሱ ዓመት ስጦታነት በይፋ የተመዘገቡ የባሌ ብሔራዊ ፓርክ እና የጌዲዮ ባህላዊ መልከዓ ምድርና ጥብቅ ደን ይገኙበታል።
ባህላዊና ተፈጥሯዊ ሀብቶች በዓለም ቅርስነት ለመመዝገብ በጠንካራ መስፈርቶች ተገምግመው ማለፍ ይኖርባቸዋል። ኢትዮጵያ ያስመዘገበቻቸው፣ በጊዜያዊነት በዩኔስኮ መዝገብ ላይ የሰፈሩ ተጨማሪ ሀብቶችን ለመመዝገብ በሂደት ላይ የሚገኙ ሌሎች መስህቦች እነዚህን ዓለም አቀፍ መስፈርቶች በሙሉ ያሟሉ እንደሆኑ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ከላይ ያነሳነውን ርዕሰ ጉዳይ በዝርዝር ለማውሳት እንዲያመቸን የዝግጅት ክፍላችን በዚህ ወር በይፋ በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡትን የጌዲዮ መልካምድርና ጥብቅ ደን እንዲሁም የባሌ ተራራዎች በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡበትን መስፈርት ለመዳሰስ ፈቅዷል። ከአፍሪካ የሰው ልጅ ወካይ ቅርሶችን በቀዳሚነት በማስመዝገብ ወደር የማይገኝላት ኢትዮጵያ ሀብቶቹን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ያለፈችባቸው ሂደቶችም ይጠቀሳሉ።
ሀገሪቱ ያሟላቻቸውን መስፈርቶች በተመለከተ በሂደቱ ተሳታፊ የነበሩት ባለሙያ አቶ አንዷለም ግርማይ በኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ውስጥ በቅርስ ጥናትና ምርምር ለረጅም ጊዜ ሠርተዋል። ሀብቶቹን ለማስመዝገብ በዳይሬክተርነት እየመሩ ሲሠሩ የነበሩና አሁን ደግሞ በብሔራዊ ሙዚየም መሪ ሥራ አስፈፃሚ በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ።
አቶ አንዷለም እንደሚናገሩት፤ የታሪክ፣ የባህል፣ የአርኪዮሎጂና የተፈጥሮ ቅርሶችን በዓለም አቀፍ ቅርስነት ለማስመዝገብ ጠንካራ መስፈርቶችን ማሟላት የግድ ይላል። ዩኔስኮም የሰው ልጅ ወካይ ቅርሶችን ለማስመዝገብ አስር የሚደርሱ መስፈርቶች አሉት። ከእነዚህ ውስጥ በጌዲዮ ዞን የሚገኘው የጌዲዮ ማኅበረሰብ ባህላዊ መልከዓ ምድርንና ጥብቅ ደንን ለመመዝገብ በባህል ዘርፍ ብቻ ከተቀመጡ ስድስት መስፈርቶች በዋናነት ሁለቱን እንዳሟላ አቶ አንዷለም ይናገራሉ። በዩኔስኮ ሀብቱን ለማስመዝገብ ከእነዚህ መስፈርቶች ውስጥ አንዱን ብቻ ማሟላት በቂ እንደሆነም ይገልፃሉ።
መሪ ሥራ አስፈጻሚው እንዳመለከቱት፤ የጌዲዮ ባህላዊ መልከዓ ምድርና ጥብቅ ደን ለዓለም ቅርስ በዕጩነት የቀረበበት መምረጫ መስፈርትን ሲያብራሩ በስድስት መመዘኛዎች ውስጥ እንደተገመገመ ይናገራሉ። ዩኔስኮ ባህላዊ ሥርዓቱን እና በባህላዊ መንገድ የሚጠበቁ ተፈጥሮዎች እንዲሁም እሴቶችን ለመመዝገብ ከሚጠቀማቸው መመዘኛዎች ውስጥ አንዱ መስህቡ «ድንቅ የሰው ልጅ የፈጠራ ክህሎትን የሚወክል» መሆኑን ማረጋገጥ እንደሆነ ይናገራሉ። በሁለተኝነት ደግሞ መሠረታዊ የሆኑና «በጊዜ ሂደት የሚፈጠሩ የሰው ልጅ እሴቶችን የሚወክሉ» የለውጥ ሂደቶችን ወይም «የዓለም የባህላዊ ሁኔታዎችን የሥነ ሕንፃ ወይም የቴክኖሎጂ እድገቶች፣ የሐውልት ጥበቦችን፣ የከተማ ፕላኖችን ወይም መልክዓ ምድር የሚወክል» መሆን እንደሚጠበቅበት ይገልፃሉ። የጌዲዮ ባህላዊ መልከዓ ምድርም ዩኔስኮ በሁለተኛነት ያስቀመጠውን ይህንን መስፈርት ሙሉ ለሙሉ እንዳሟላ ይናገራሉ።
ሦስተኛውና ባህላዊ ቅርሶች የሚመዘገቡበት የዩኔስኮ መስፈርት «ህያው የሆነ ወይም በአንድ ወቅት የተከሰተ ወይም ተከስቶ የጠፋ ድንቅ ባህል ወይም ሥልጣኔ የሚዘክር» መሆኑ ነው የሚሉት መሪ ሥራ አስፈፃሚው አቶ አንዷለም፣ በዓለማችን ላይ ያሉ ሀብቶች በቅርስነት ለመመዝገብ ይህንን ማሟላት እንደሚጠበቅባቸው ይናገራሉ። የጌዲዮን ጨምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ በባህል ዘርፍ በቅርስነት የተመዘገቡ ሀብቶችም ይህንን መስፈርት እንዳሟሉ ይገልፃሉ።
«የጌዲዮ ባህላዊ መልከዓ ምድር በቀዳሚነት ካሟላቸው መስፈርቶች መካከል ዩኔስኮ ያስቀመጠው አራተኛው መመዘኛ አንዱ ነው» የሚሉት አቶ አንዷለም፤ ይህም መስፈርት ቅርሱ በዓይነቱ ልዩ የሆነ የግንባታ፣ የሥነ ሕንፃ ወይም የቴክኖሎጂ የፈጠራ ውጤት በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ያለፈውን ውጣ ውረድ የሚያሳይ መልክዓ ምድር መሆን እንደሚጠበቅበት የሚገልፅ መሆኑን ይናገራሉ። ከዚህ አንፃር ጌዲዮም በሜጋሊቲክ ሐውልቶቹ በመልካ ምድሩና ባህላዊ የተፈጥሮ አጠባበቅ ሥርዓቱ መስፈርቱን ሊያሟላ እንደቻለ ይገልፃሉ።
ሌላኛውና አምስተኛው የዩኔስኮ መስፈርት ቅርሶች «ባህላዊ የሰው አሰፋፈርን፣ የመሬት አጠቃቀምን፣ ወካይ ባህልንና ሰው ከአካባቢው ጋር ያለውን ግንኙነት በተለይም ሊቀለበስ የማይችልን ለውጥ በማሳየት ረገድ በምሳሌነት ሊገለጹ የሚችሉ ቦታዎች» መሆናቸውን የሚገልፁ እንደሆኑ መረጋገጥ እንዳለባቸው የሚናገሩት አቶ አንዷለም፤ በተጨማሪም በስድስተኛ መስፈርትነት ቅርሶች «የተለዩ ወይም ዓለም አቀፍ ጠቀሜታ ያላቸው በቀጥታና ተጨባጭ በሆነ መንገድ ከድርጊቶች፣ ህያውነት ካላቸው ወግና ልማዶች፣ አስተሳሰቦች፣ እምነቶች የሥነ ጥበብና የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ጋር ተያያዥነት ያላቸው እንዲሆኑ እንደሚጠበቅ በሕግና ደንቡ መዘርዘሩን ይናገራሉ። ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ ያስመዘገበቻቸው ቅርሶች እነዚህን መመዘኛዎች እንደሚያሟሉ ይናገራሉ።
የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር ወይዘሮ ነጃት ጀማል ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለፁት፤ ኢትዮጵያ የበርካታ ብሔረሰቦች ሀገር በመሆኗ ብዛት ያላቸው ባህላዊና ተፈጥሯዊ ቅርሶች ባለቤት ነች። በዚህ ምክንያት ለቅርሶች ጥበቃ እየተሰጠ ያለው ትኩረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ሊሄድ መቻሉን ይገልፃሉ።
ዳይሬክተሯ እንደሚገልፁት፤ ኢትዮጵያ በሀገሪቱ የሚገኙ የመስህብ ሀብቶች ሁሉንም መመዘኛዎች አሟልተው በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገቡ፣ እንዲጠበቁ፣ ለማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎች እንዲውሉና ማኅበረሰቡን እንዲወክሉ ለማስቻል የተለያዩ የሕግ ሥርዓትና ማዕቀፎች ተዘጋጅተው ተግባራዊ እየሆኑ ይገኛሉ። ከዚህ ውስጥ የሚከተሉት ስምምነቶችና የሕግ ማዕቀፎች ይገኙበታል።
ከእነዚህ እርምጃዎች መካከል እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1972 የባህልና የተፈጥሮ ቅርሶች ጥበቃ ስምምነት መሠረት ሀገራት በዩኔስኮ የባህል፣ የተፈጥሮ እና የሁለቱ ጥምር መስፈርቶችን የሚያሟሉ ቅርሶችን በዓለም አቀፍ ቅርስ ዝርዝር ውስጥ የማስመዝገብ ሥርዓት መሆኑን ወይዘሮ ነጃት ይገልፃሉ። በተመሳሳይ በ1987 የፀደቀው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባህላዊ እሴቶቻቸውን በነፃነትና በእኩልነት የመግለጽ፣ የማሳደግና የመንከባከብ መብት መደንገጉን አውስተዋል።
የባህል ፖሊሲን በሚመለከት ተመሳሳይ እርምጃ መኖሩን የሚገልፁት ዳይሬክተሯ፤ በ1990 ዓ.ም የወጣው የባህል ፖሊሲ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባህላዊ እሴቶች እንዲመዘገቡ፣ እንዲጠኑ፣ እንዲጠበቁና በእኩልነት እንዲታወቁ እንዲሁም ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እንዲውሉ አቅጣጫ ማመለከቱን በምሳሌነት ይጠቅሳሉ። ይህም መስህቦቹን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብና የተጠቀሱትን ተግባራት ለማከናወን የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ እንደሆነም ይገልፃሉ።
ዳይሬክተሯ እንደሚያስረዱት፤ ከላይ ከተነሱት ማዕቀፎች ባሻገር በ1992 ዓ.ም የወጣው የቅርስ ጥናትና አጠባበቅ አዋጅ ባህላዊ ቅርሶች ተመዝግበው፣ ተጠንተው፣ ተጠብቀውና ተዋውቀው ለዘለቄታዊ ልማት እንዲውሉና ባህላዊ ይዘታቸውን ጠብቀው ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፉበትን መንገድ መደንገጉን አንስተው፣ በዚህ ሕግና ድንጋጌ መሠረት እየተሠራ እንደሆነ ይናገራሉ። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የቅርሱን ጥበቃ ለማገዝ የወጡ ሌሎች የሕግ ማዕቀፎች መኖራቸውንም ገልፀውልናል።
ወይዘሮ ነጃት በቅርቡ በዓለም ቅርስነት በዩኔስኮ እውቅና አግኝተው የተመዘገቡት የጌዲዮ ባህላዊ መልከዓ ምድርና ጥብቅ ደን እንዲሁም የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ እውቅና ማግኘታቸው በርካታ ፋይዳዎችን ለኢትዮጵያ እንደሚያስገኙ ይጠቁማሉ።
በተለይ የዩኔስኮን መስፈርት ማሟላታቸውና መመዝገባቸው በርካታ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አላቸው የሚሉት ዳይሬክተሯ፤ በመጀመሪያ ደረጃ መረጃዎቹ በዩኔስኮ ድረ ገጽ እና በመሳሰሉት የማሰራጫ ዘዴዎች የሚለቀቁ መሆኑ ቅርሱ ከሀገር አቀፍ ደረጃ አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እንዲያገኝ ያደርገዋል ይላሉ። በሌላ መልኩ የቱሪስት መስህብነታቸው እንዲጨምር፤ በዚያው ልክ ከዘርፉ የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ እንዲያድግ አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ ያስረዳሉ።
«ለቅርሶቹ መንግሥታዊ አካላትና ሌሎች ተቋማት ትኩረት የሚሰጡት በመሆኑ ቅርሶቹ ከቀድሞ በተሻለ ሁኔታ እንክብካቤና ጥበቃ ይደረግላቸዋል» የሚሉት ዳይሬክተሯ፣ ይህም ቅርሶቹ ይዘታቸውን ጠብቀው ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፉ እንደሚረዳ ይናገራሉ። በሌላ በኩል ቅርሶቹ በዓለም አቀፍ ጥበቃና እንክብካቤ የሚያገኙበት መንገድ እንደሚመቻችላቸው ያስረዳሉ።
እንደ ዳይሬክተሯ ገለፃ፤ የዩኔስኮን መስፈርት አሟልተው የተመዘገቡት እነዚህ ቅርሶች የሀገር ውስጥ ቱሪስትን በማበረታታት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እርስበርስ ተዋውቀውና ተከባብረው በሰላም አብረው የሚኖሩበትን ሥርዓት አጠናክሮ ለመቀጠል እንደሚረዱ ይናገራሉ። በተጨማሪም በዓለም አቀፍ ደረጃ ቅርሶቹ እውቅና ማግኘታቸው ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች አጥኚዎችንና ተመራማሪዎችን በመሳብ ተጨማሪ ውጤቶች እንዲገኙ በር ከፋች መሆኑን ያስረዳሉ።
እንደ መውጫ
የኢትዮጵያን ባህላዊ፣ ተፈጥሯዊና አርኪዮሎጂካል ሀብቶች በዓለም ቅርስነት ማስመዝገብ ተገቢ ቢሆንም የመጨረሻው ግብ እርሱ ብቻ መሆን የለበትም። ይህንን ጉዳይ በዘርፉ በርካታ ዓመታት የሠሩ ምሁራንም ይስማሙበታል። በተለይ የዓለም ቅርስነት መመዘኛን የሚያሟሉ (ለምሳሌ በቅርቡ እንደተመዘገቡት የጌዲዮና የባሌ የመሰሉ) ሀብቶች ዓለም አቀፍ እውቅና አንዲያገኙ ከመሥራት በተጓዳኝ ቅርሶቹ ተጠብቀው፣ ለምተውና ተዋውቀው፣ ይዘታቸውን ጠብቀው ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፉ በተለያዩ እርከኖች ላይ የሚገኙ የማኅበረሰብ አካላት ተሳትፎ በማድረግ መጠበቅና ማልማት እንዲችሉ ማስገንዘብ እንደሚገባ ያሳስባሉ። በተጨማሪም ወጣቶች ስለቅርሶቹ ምንነት፣ ይዘታቸውና ታሪካቸው ለማኅበረሰቡ የሚሰጠውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ በተመለከተ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጠንቅቀው መማር፣ ማወቅ፣ መከታተልና መተግበር እንደሚኖርባቸው ምክረ ሃሳብ ሲሰጡ ይደመጣል።
በልዩ ልዩ መድረኮች ላይ ሲነገሩ ከሚደመጡ ምክረ ሃሳቦች መካከል በዚህ ላይ የመገናኛ ብዙኃን የሚኖራቸው ጉልህ ፋይዳ ነው። በዋናነትም በተለያዩ መገናኛ ብዙኃንም ኅብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት ከቅርሶቹ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ጠቃሚ መረጃዎች ዕውቀትና ክህሎትን ወደ ተተኪው ትውልድ ማስረጽ እንደሚያስፈልግ ሲነገር ይደመጣል። መንግሥትም ከቅርሶቹ ጋር በተያያዘ ሕጋዊ ማዕቀፎችን ከማውጣት በተጓዳኝ በጀት በመመደብና የቅርሱ ማከናወኛ ሥፍራዎችን የመጠበቅና መሠረተ ልማት በመገንባት እንዲሁም የማልማት ሥራውን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚኖርበት ከሚሰጡት ምክረ ሃሳቦች መካከል ይጠቀሳል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን መስከረም 20 ቀን 2016 ዓ.ም