የወንዝ ዳርቻ ልማቱን ለዘርፈ ብዙ ፋይዳ

የአዲስ አበባ ወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ግንባታ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ዶ/ር የካቲት 14 ቀን 2011 ዓ.ም በይፋ መጀመሩ ይታወሳል። 29 ቢሊየን ብር ወጪ እንደሚጠይቅ የተነገረለት ይህ ፕሮጀክት፤ በወንዝ ዳርቻዎቿ ላይ ስር የሰደደ ችግር ለሚታይባት አዲስ አበባ መሰረታዊ ለውጥ እንደሚያመጣም ታምኖበት ነው ወደ ስራ የተገባው።

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ ፕሮጀከቱ ሁለት ታላላቅ ወንዞችን ተከትሎ የሚተገበረም ነው። በእዚህ ውስጥም ከእንጦጦ በመነሳት በአፍንጮ በር በግዮን ሆቴል እስከ አቃቂ ወንዝ ድረስ የሚዘልቀው ይገኝበታል። አጠቃላይ ፕሮጀክቱ ግን 50 ስኩየር ኪሎ ሜትር ስፋት እና 56 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚሸፍን ሲሆን፣ መዲናዋ የአረንጓዴ ተፋሰስ ገጸ በረከት ተብሏል።

ግንባታው ሲጠናቀቅም የከተማዋን የአረንጓዴ ሽፋን ፕሮጀክቱ ሲጀመር ከነበረበት ዜሮ ነጥብ ሶስት ሜትር ስኩዬር ወደ ሰባት ሜትር ስኩዬር ያሳድጋል ተብሎ ይጠበቃል። ፕሮጀክቱ ከመጀመሩ ቀደም ብሎም ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ፣ በወንዝ ዳር የሰፈሩ ሰዎች እና ከአካባቢው በሚነሱ ማህበረሰቦች ፍላጎት ላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥናት ተሰርቷል።

ዓለም አቀፍ ሕጎች እንደሚያመለክቱት፤ አንድ ነዋሪ ከወንዞች በትንሹ 25 ሜትር ርቆ ነው መኖር ያለበት። የአዲስ አበባ የከተማ ፕላንም በዚህ መቃኘት ሲገባው ከዚህ በተቃራኒው ሊባል በሚችል መልኩ በወንዝ ዳር በርካታ ሰዎች ሰፍረው ሲኖሩና ለተለያዩ የጎርፍ አደጋዎችና ለጤና መታወክ ሲጋለጡ ኖረዋል።

የከተማዋ ነዋሪዎች፣ የተለያዩ ተረፈ ምርቶችና የኢንዱስትሪ ፍሳሾች ወደ ወንዝ የሚለቀቁ በመሆኑም ቀደም ሲል ንጹህ እና ለመዝናኛ ያገለግሉ የነበሩ የከተማዋ ወንዞች የጤና ጠንቅ ለመሆን ተዳርገዋል። ከከተማዋ በተጨማሪም በአቅራቢያ የሚገኙ አርሶ አደሮች እርሻ እንዲሁም የከተማ ግብርና ለማካሄድ የሚያስችለው የወንዝ ውሃ የተበከለ መሆኑም ተጨማሪ ተግዳሮት መሆኑ ይነገራል።

የወንዝ ዳርቻ መሰረተ ልማት ስራው የከተማዋን ወንዞች ወደ ቀድሞ ተፈጥሯዊ ማንነታቸው ለመመለስ እና የመዝናኛ እና የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ ታስቦ ነው የተጀመረው።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኢንጂነር እንዳሻው ከተማ እንደሚያስረዱት፤ የወንዝ ዳርቻ ልማቱ በአንድ ከተማ አመሠራረት ውስጥ የመሠረተ ልማት ደረጃን ይዞ ወንዝን የሚሸሽ ወይም የሚራቅ አይደለም፤ የወንዝ ዳርቻ ልማቱ የሚጎበኝ፣ የሚዝናኑበት፣ አየር የሚወሰድበት ቦታ መሆን አለበት በሚል እሳቤ እየተሰራ ይገኛል።

አዲስ አበባ ከ600 ኪሎ ሜትር በላይ የሚደርሱ በርካታ ዋና ዋናና ገባር ወንዞች አሏት ያሉት ምክትል ኃላፊው፣ ከእነዚህ ወንዞች መካከልም በአንዱ በዋናነት የወንዝ ዳርቻ ልማቱ ተጀምሮ እየተከናወነ ይገኛል ይላሉ።

እሳቸው እንዳሉት፤ በአዲስ አበባ ከዘመናት በፊት የቀበና ወንዝን የመሳሰሉ ፅዱ እና ሰዎች በውስጣቸው እየዋኙ የሚዝናኑባቸው ወንዞች ነበሩ። በሂደት ማህበረሰቡ በወንዝ ዳርቻዎች አካባቢ ተደባልቆ ከመኖሩ የተነሳ በዙሪያው አላግባብ በሚጣሉ ተረፈ ምርቶች ምክንያት ዛሬ ወንዝ ውስጥ መዋኘት ቀርቶ መሻገርም የሚከብድ ሆኗል።

የቢሮ ኃላፊው እንደሚያብራሩት፤ በወንዞች ዙሪያ ያሉ አንዳንድ ፋብሪካዎችና ለብክለት ምክንያት የሚሆኑ መሰረተ ልማቶች ብክለቱ እንዲባባስ እያደረጉ ናቸው። የብክለት መጠኑ ከላይኛው ተፋሰስ ወደ ታችኛው ተፋሰስ እስኪ ደርስ እየጨመረ መጥቷል። ይህም በማህበረሰቡ ጤና ላይ መታወክን እያስከተለ ይገኛል። በመሆኑም የዚህን ማህበረሰብ ጤና የሚያውኩ ተግዳሮቶችን መፍታት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። ሰዎች ለመኖር መጀመሪያ ጤንነት ያስፈልጋቸዋል። ወንዞቹ መልማትና ከብክለት መጠበቅ ካልቻሉ ይህን መሠረታዊ የሆነውን ጤንነት ማግኘት አይቻልም።

“ከመጀመሪያው ፅዱ በነበሩት ወንዞችና ዳርቻዎቻቸው ላይ ማህበረሰቡ በስፋት ተጠግቶ በመኖሩ የተነሳ ደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻዎች ወደ ወንዞች ይለቀቃሉ” የሚሉት የቢሮው ምክትል ኃላፊ፤ የኢንዱስትሪዎች እንዲሁም የማደያዎች ፍሳሾችም የሚወገዱት ወደ ወንዝ ነው ይላሉ። ይህ ሁሉ ወንዞችን ለብክለት መዳረጉን፣ ችግሩ በታችኛው ማህበረሰብ እና በመሠረታዊነት ኑሮውን ግብርናው ላይ ያደረገውን ክፍል ጭምር ለጉዳት እንዳጋለጠው ይገልፃሉ።

ኢንጂነር እንዳሻው እንደሚያብራሩት፤ የሸገር የወንዝ ዳርቻ ልማቱ በከተማዋ በዋናነት በሁለት ዋና ዋና ወንዞች ላይ እየተከናወነ ይገኛል። በልማቱ የሚሸፈነው ስራ በንድፍ ደረጃም 56 ኪሎ ሜትር የሚደርስ ሲሆን፣ ከ”ባንተ ይቀጡ” ወንዝ ተነስቶ ከቀበና ወንዝ ጋር ፒኮክ አካባቢ ይገናኛል። እነኚህ አንድ ላይ ሆነው አቃቂ ሲደርሱ 56 ኪሎ ሜትር ይሆናል።

በእነዚህ ወንዞችና ዳርቻዎቻቸው ላይ የሚካሄዱ ልማቶችም በመሰረታዊነት የብዙ ሰዎች ህይወትን እንዲሁም የከተማዋን ነባራዊ ሁኔታ ሊቀይሩ የሚችሉ መሆናቸውን የቢሮ ኃላፊው ያስረዳሉ። ፕሮጀክቶቹን የሚለሙት በተለያዩ ባለድርሻ አካላት እንደሆነም ይጠቁማሉ።

እንጦጦ- ወዳጅነት አደባባይ

መነሻውን ከእንጦጦ የሚያደርገው ግንባታው እስከ ወዳጅነት አደባባይ ድረስ በመዝለቅ ከወንዙ ቅርብ እስከ ሆነው መንገድ ድረስ ያካልላል። በአጠቃላይ 5 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ያህል ስፋት የሚሸፍን ነው። ከአፍንጮ በር መስጊድ አካባቢ፣ በራስ መኮንን ድልድይ አርጎ በአራዳ ክፍለ ከተማ ጀርባ የሚያልፈው ይህ የወንዝ ዳርቻ ልማት የዲዛይን፣ ግንባታ፣ የማማከር ስራው በቻይና መንግስት ድጋፍ የሚከናወን ነው።

ፕሮጀክቱን የከተማዋ ውበት እና አረንጓዴ ልማት እና የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በባለቤትነት በጋራ እንደሚመሩትም የቢሮው ምክትል ኃላፊ ይገልፃሉ። የዚህ ሙከራ /ፓይለት/ ስራም በ600 ሜትር ላይ መከናወኑን ነው ያመለከቱት። ፕሮጀክቱን ሙሉ ለሙሉም በስምንት ወር በማጠናቀቅ ሕብረተሰቡ እንዲረከበው እንደሚደረግ አስታውቀዋል። ግንባታው የአካባቢውን የቀደመ ገፅታ የሚያሻሽል እና የቱሪስት ማዕከል ሊሆን በሚችል መልኩ እየተካሄደ መሆኑን ያስረዳሉ። ግንባታው ሲጠናቀቅ አካባቢው ለኑሮ አመቺ፣ ማራኪ እና ሳቢ ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

የቀበና ወንዝ ዳርቻ

ይህ ፕሮጀክት በጣሊያን መንግስት ድጋፍ የሚሰራ ሲሆን፣ የከተማ አስተዳደሩ ጭምር ይሳተፍበታል። በቀበና ወንዝ ላይ የሚተገበረው ፕሮጀክት ሁለት ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር ይሸፍናል። ከጣሊያን ኤምባሲ ተነስቶ ጀርመን ኤምባሲ ይዘልቃል። የወንዝና ወንዝ ዳርቻን የማስዋቡ ፕሮጀክትም ተጀምሮ በግንባታ ላይ እንደሆነ ምክትል የቢሮ ኃላፊው ይገልፃሉ። የፕሮጀክትም የአዋጪነት ጥናት ዳታ ማደራጀት ደረጃ መድረሱን ጠቅሰው፣ ስራዎቹም እ.አ.አ በ2025 ድረስ የሚጠናቀቁ መሆናቸውን ነግረውናል።

ከእንጦጦ ፈረንሳይ ኤምባሲ ጀርመን ኤምባሲ

ይህ ፕሮጀክት በኮሪያ መንግስት ድጋፍ (በኮሪያ ልማትና ትብብር ‘ኮይካ’) የሚሰራ መሆኑን ኢንጂነሩ ጠቅሰው፣ ከእንጦጦ ፈረንሳይ ኤምባሲ በጀርመን ኤምባሲ አድርጎ 11 ነጥብ አራት ኪሎ ሜትር የማስተር ፕላን ጥናት ይሰራል። የዚህ ፕሮጀክት ሙከራም /ፓይለት/ አንድ ነጥብ ስምንት ኪሎ ሜትር ማስተር ፕላን ተጠናቅቆ ተግባራዊ የሚደረግበት ምዕራፍ ላይ መደረሱን ተናግረዋል።

የሙከራ ፕሮጀክቱ በከተማ በአብይ ኮሚቴ እንደሚመራ ጠቅሰው፣ በውበት እና አረንጓዴ ልማት ቢሮ፣ ከክፍለ ከተማ እና ወረዳ ባሉ ባለድርሻዎች ጋር በመቀናጀት ተግባራዊ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

ሸገር አንድ እና ሸገር ሁለት

ኢንጂነር እንዳሻው እንደሚገልፁት፤ ሌላው በአዲስ አበባ የሚካሄደው የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክት አካል ሸገር አንድ እና ሸገር ሁለት የሚባለው ነው። ይህ አካባቢ ቀደም ሲል በጣም የቆሸሸ፣ ሰዎች የሚጠየፉት፣ በቦታው ማለፍ የሚከብድ እንደነበር አስታውሰዋል። ዛሬ ግን ከመዝናኛነት አልፎ የአገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ሁነቶች የሚስተናገዱበት ቦታ ሆኗል። እንደዚህ አይነት ቦታዎችን መፍጠር በመቻሉ እና ቀጣይነት እንዲኖረው በማሰብ ምዕራፍ አንድ የሚባለው የወዳጅነት አደባባይ፣ ሳይንስ ሙዚየም እና የልጆች መጫወቻን ጨምሮ የተለያዩ ሁነቶች የሚከወኑበት አከባቢመፍጠር መቻሉን አስታውቀዋል።

የስራ ዕድል እና የቴክኖሎጂ ሽግግር

ፕሮጀክቶቹ ይዘው የመጡት ዕድል ብዙ ነው፤ የውጭ አገር መንግስታት በራሳቸው ገንዘብ የኢትዮጵያ መንግስትን ለመርዳት ተንቀሳቅሰዋል፤ የዓለም ዲፕሎማቶች መቀመጫና ማዕከል የሆነችው አዲስ አበባ በዚያ ደረጃ እንድትለማ ለማድረግ እየሰሩ ናቸው። ድጋፉ የተገኘው በብዙ የዲፕሎማሲ ስራና ጥረት ነው። ይህንን ተነሳሽነትና ኃላፊነት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ በበላይነት መርተውታል።

በፕሮጀክቶቹ ከኢንጂነሪንግ ባለሙያ ጀምሮ እስከታችኛው የቀን ሙያተኛ ደረጃ እና የግንባታ ምዕራፍ ድረስ ኢትዮጵያውያን እየተሳተፉ ይገኛሉ። ግንባታው ሲጀመር አንስቶ እስከሚጠናቀቅ ድረስ የቀን ሰራተኞቹ፣ ተቆጣጣሪዎች፣ መሀንዲሶቹ ተሳታፊ ሆነዋል። አብዛኛዎቹም ኢትዮጵያውያን ናቸው። በአማካሪነት /በኮንሰልታንት/ እና በተቋራጭነት /ኮንትራክት/ ላይም አካል ሆነው የሚሰሩበት ሁኔታ አለ። ይህም የፕሮጀክቱ ሌላው ፋይዳ መሆኑን የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኢንጂነር እንዳሻው ይገልፃሉ።

በተለይ ልምድ የመውሰድና የቴክኖሎጂ ሽግግሩ ከፕሮጀክቶቹ የተገኘ ትልቅ እድል እንደሆነ ይናገራሉ። የዚህ አይነት የወንዝ ዳርቻ ልማት በአገር በቀል ተቋራጮች መስራት የሚያስችል አቅም እየተፈጠረ መሆኑን ኢንጂነሩ ይጠቁማሉ።

በወንዝ ዳርቻ መሰረተ ልማት ፕሮጀክቱ ግንባታ ወቅት የተፈጠረውን የስራ እድል በተመለከተ የግንባታ ግብዓቶችን በማቅረብ ኢትዮጵያውያን ተጠቃሚ መሆናቸውንም የሚናገሩት ምክትል የቢሮ ኃላፊው፤ በሂደቱ ውስጥም ግንባታቸው ተጠናቋል ከሚባሉት መካከል የወዳጅነት አደባባይ የልጆች መጫወቻ አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኢንጂነር እንዳሻው እንደሚሉት፤ ቀደም ሲል በቂ መዝናኛ ቦታዎች ባለመኖሩ ምክንያት አሁን ለሰርግ፣ ልደት እና ለመሣሠሉት ሁነቶች አመቺ ሆነው እንዲሰሩ ተደርጓል። መዝናኛ ስፍራዎቹ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል ፈጥረዋል። በቡና፣ ፈጣን ምግብ፣ ካፌ፣ የመሳሰሉት መሸጫ ቦታዎችና የስራ እድል መፍጠር ተችሏል።

በወንዞች ዳርቻ ግንባታዎቹ ምክንያት አካባቢው ፅዱ እንደሚሆንና ምቹ የመኖሪያና የስራ ቦታ እንደሚፈጠር የሚገልፁት ምክትል የቢሮ ኃላፊው፤ በተጨማሪነትም የከተማ ግብርና እንደሚስፋፋ ተናግረዋል። ከዚያም አልፎ ወንዞቹ በአረንጓዴ ቀለበት ታጥረው ለአንድ ከተማ ያለውን የአረንጓዴ ስፍራ ኮታ የማሟላት አስተዋፅኦው የጎላ መሆኑንም ነው ያመለከቱት።

“በመዲናዋ ዜጎች ወንዝ ዳር በመኖራቸው የተነሳም ቤታቸው በጎርፍ በተለያዩ አደጋዎች ተጠቂ ይሆናሉ” የሚሉት ምክትል የቢሮ ኃላፊው፤ የወንዝ ዳር ልማት ፕሮጀከቱ የዚህ ዓይነት አደጋዎችን እንደሚቀንስ ይገልጻሉ። በጎርፍ አደጋም ውድ የሆነው የሰው ልጅ ህይወት እንዳይነጠቅ በከተማ ደረጃ በትኩረት እንደሚሰራም ያስረዳሉ።

አዲስ አበባ ከኒውዮርክ እና ጀኔቫ ቀጥላ የዓለም ሶስተኛ የዲፕሎማሲ ከተማ፣ የአፍሪካም መዲና መሆኗንም በመግለፅም፤ ውብ ማራኪ እና ሳቢ ከተማ መሆን እንዳለባት ኢንጂነር አንደሻው ይናገራሉ። በከተማዋ አሁን በወንዝ ዳርቻ ልማት እየተገነቡ ካሉት በተጨማሪ በቅርበት ለመዝናናት የሚያስችሉ 21 ፓርኮች እስከ ወረዳ ድረስ እየተገነቡ መሆናቸውንም አመላክተዋል። እነዚህ ፓርኮች ዜጎች በትርፍ ሰዓታቸው እንዲዝናኑ፣ እንዲያነቡ፣ ማህበራዊ ህይወታቸውን እንዲካፈሉባቸው እንደሚያስችሉም ገልፀዋል።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን  መስከረም 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You