የአሜሪካው የቴክኖሎጂ ኩባንያ በራሪ ተሽከርካሪ መሥራቱን ገለጸ

የአሜሪካው የቴክኖሎጂ ኩባንያ በራሪ ተሽከርካሪ መሥራቱን ገለጸ

በየዘመኑ የተፈበረኩ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች የሰው ልጆችን ሕይወት ሲያቀሉ ቆይተዋል። የሰው ልጆች ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅመው እስከ ጠፈር ድረስ ተጉዘው ማሰስ መቻላቸው፣ የኢንተርኔት አገልግሎት እና አሁን ደግሞ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን እየተገለገሉ ይገኛሉ።

ከዚህ በፊት በቢሆኔ ፊልሞች ላይ ሲታዩ የነበሩ የበራሪ ተሽከርካሪ አገልግሎት እውን ሊሆን የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ይገኛል።

ዋና መቀመጫውን በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ያደረገው አሌፍ ኤሮናውቲክስ የቴክኖሎጂ ኩባንያ አዲስ ፈጠራውን ይዞ ብቅ ብሏል። ይህ ኩባንያው ከሰሞኑ በዲትሮይት የአውቶሞቲቭ አውደ ርዕይ ላይ ለእይታ ያቀረበው በራሪ ተሽከርካሪ የብዙዎችን ትኩረት ስቧል። ይህ በራሪ ተሽከርካሪ ከአሜሪካ አቪዬሽን አስተዳደር ፈቃድ ያገኘ ሲሆን የሙከራ በረራውን በቅርቡ እንደሚያጠናቅቅ ዩሮ ኒውስ ዘግቧል።

ሞዴል ኤ የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ በራሪ ተሽከርካሪ በኤሌክትሪክ እንደሚሠራም ተገልጿል። ኩባንያው የሙከራ በረራውን በአየር ላይ በ320 ኪሎ ሜትር በምድር ላይ ደግሞ በ160 ኪሎ ሜትር ርቀት ውስጥ ያደርጋልም ተብሏል።

ኩባንያው ከአንድ ዓመት የሙከራ በረራውን አጠናቆ በ2025 ለዓለም ገበያ በ280 ሺህ ዶላር ዋጋ እንደሚቀርብ ተገልጿል። የአየር ላይ ታክሲዎች በሌሎች ሀገራትም እየተሠሩ ሲሆን የጀርመኑ ቬሎኮፕተር የመጀመሪያ ምርቱን ከአንድ ዓመት በኋላ በሚካሄደው ፓሪስ ኦሎምፒክ ላይ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ተብሏል።

የአውቶሞቲቭ ቴክኖሎጂ ምሁራን በበኩላቸው የተሽከርካሪዎቹ ዋጋ ውድ መሆን፣ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ገና አለመጀመሩ ለበራሪ ተሽከርካሪ ኢንዱስትሪ ዋነኛ ፈተና ይሆናሉ ብለዋል ሲል የዘገበው አል ዓይን ኒውስ ነው፡፡

 በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን  መስከረም 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You