የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በዚህ ከቀጠለ ሊሰረዝ ይችላል

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ባካሄደው አምስተኛ መደበኛ ፤ ሦስተኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ዙሪያ ትናንት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። በርካታ ጉዳዮች እንደተነሱበት የተነገረው ጉባኤው የክለብ ላይሰንሲንግ ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት እንደተሰጠው በመግለጫው ተጠቁሟል።

በዘልማድ ትኩረት ሳንሰጥ ቆይተናል መስፈርቱን አሟልተን የማንገኝ ከሆነ ክለቦቻችን በአፍሪካ መድረክም የመሳተፍ ፈቃድ ላይኖረን ይችላል ሲሉ የሊግ አክሲዮን ማኅበሩ ፕሬዚዳንት መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ አሳስበዋል። ደረጃውን የጠበቀና ፍቃድ ያለው ክለብ ባለመኖሩም ማሟላት ግድ እንደሚል ተናግረዋል።

ክለቦች በዚህ አመት የግዴታ የክለብ ላይሰንሲግ (የክለብ ፈቃድ) ማውጣታቸው አስፈላጊ መሆኑን የጠቆሙት የሊግ ካምፓኒው ሥራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፈ ለዚህ ድጋፍ እንደሚያደርጉ የገለፁ ሲሆን ክለቦች አስፈላጊውን ፍቃድ ካላሟሉ ሊጉ ሊሰረዝ እንደሚችል ስጋታቸውን አፅእኖት ሰጥተው ተናግረዋል። «መስፈርቱን አሟልተን የማንገኝ ከሆነ ክለቦቻችን በአፍሪካ መድረክም የመሳተፍ ፈቃድ ላይኖረን ይችላል» ሲሉም መቶ አለቃ ፈቃደ አሳስበዋል።

የክለቦች የሕክምና ቡድንን በተመለከተ በወጌሻ ብቻ እንደማይቀጥሉ የገለፁት አቶ ክፍሌ የሊግ ስታንዳርድ ያሟላ የሊጉ የሕክምና ቡድን ማኑዋል እንዲዘጋጅ ስምምነት መደረሱን አስረድተዋል። የፀጥታ ችግር ለውድድሩ እንቅፋት እንዳይሆን ከፌዴራል ፖሊስ ጋር የውል ስምምነት ለማድረግ መወሰኑንም አክለዋል።

ከፀጥታ ጋር ተያይዞ አስተያየታቸውን የሰጡት መቶ አለቃ ፈቃደ «የግል የፀጥታ ኃይሎች ለእኛ አስተማማኝ አይደሉም … የሀገሪቱን ደህንነት የሚያስጠብቀው ፌዴራል ፖሊስ በመሆኑ ከነሱ ጋር ተፈራርመን ወደ ሥራ መግባትን መርጠናል፣ ሊጉ ከስጋት ነፃ ሆኖ ውድድር ማካሄድ እንደምንችል ዲ.ኤስ.ቲቪ ማረጋገጥ ይፈልጋል፣ ይህን የሚያረጋግጠው ደግሞ ፌዴራል ፖሊስ ነው። በቀጣይ መጠጥ ጠጥቶ የገባን 500 ብር ቢቀጣ የተጣላ ደግሞ ሳምንት ትታሰራለህ የሚለው መጠነኛ ፍ/ቤት ሊቋቋም የሚችለው ሁሉ በፌዴራል ፖሊስ ነው» ሲሉ አስረድተዋል።

ከፌዴሬሽኑ ጋር ስላላቸው የሥራ ግንኙነት በተመለከተ ሲያብራሩም ትልቅ ልዩነት የተከሰተው በለገጣፎ ለገዳዲ ፎርፌ ዙሪያ ላይ መሆኑን አምነው አሁን ላይ ግን መግባባት ላይ መደረሱን አስረድተዋል። «ከፌዴሬሽኑ ጋር የየድርሻችንን ኃላፊነት ወስደናል የሚያገናኘንና የሚለየንን ለይተን ተወያይተን ተስማምተናል..በቀጣዩ ሳምንት እንፈራረማለን» ሲሉም ገልጸዋል።

መስከረም 20 የሚጀምረው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር የተሻለ የውድድር ዓመት ለማሳለፍ ዝግጅት መጠናቀቁ የተጠቆመ ሲሆን፣ ሊጉ የሚካሄድበት አዳማ ከተማ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንዲሁም ሲዳማ ቡና ከኢትዮጵያ ቡና በሚያደርጉት ጨዋታ በይፋ ይጀምራል።

በሊጉ ክለቦች የእግር ኳስ ክህሎትን ከማሳደግ ይልቅ ማጭበርበሮቹ ከፍተኛ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ክፍሌ፣ እሳቸው ሥራ አስኪያጅ ሆነው ከመጡ ጀምሮም ማጭበርበሩ እንደቀጠለና ይህን ለማስተካከል ከሕግ ይልቅ አስተሳሰብን መቀየር ወሳኝ እንደሆነ ገልፀዋል። ይህን ለማስተካከል ሊግ ካምፓኒው የሁሉንም ክለቦች አሠልጣኞችና ቡድን መሪዎች ጠርቶ የማጭበርበር ድርጊት እንዳይከሰት አሳስቦ ነበር። በዚህም ከዳኞች መሃል ያሠለጠኑ፣ ያስተማሩ፣ ልምድ ያላቸውን በምስጢር አዋቅሮ የነበረ ቢሆንም የተገኘ ለውጥ ግን አልነበረም። ስህተቱ ዳኞች፣ አሠልጣኞችና ተጫዋቾች እያለ ወረደ፣ አሁን ግን ከሕጉ ጎን ፕሮፌሽናል አስተሳሰብ መያዝ እንዳለበት ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል። መቶ አለቃ ፍቃደ በበኩላቸው፣ አንድ የጨዋታ ዳኛ ቡድኖችን ከአቅም በታች ተጫውተዋል ለማለት የሚያስችለው ሕጎች እንደሌሉ ጠቁመው ሲዳማ ላይ የታየው የተራቀቀ መላቀቅ እየታወቀ ሊግ ካምፓኒው የሕግ መብት ስለሌለው ምንም ማድረግ እንዳልቻለ አስታውሰዋል።

እጅግ እየናረ የመጣውን የተጫዋቾች ደመወዝ ክፍያ አስመልክቶ መቶ አለቃ ፈቃደ ማብራሪያ ሲሰጡም፣ «በደመወዝ ክፍያ ደቡበ አፍሪካ፣ ግብጽና ኢትዮጵያ ከአንድ እስከ ሦስት ያለውን ደረጃ ይዘዋል፣ በኳሱ እድገት ግን ሰማይና ምድር ነን» በማለት ተናግረዋል።

እንደ መቶ አለቃ ፈቃደ ማብራሪያ፣ ክለቦቹ ኢትዮጵያ ውስጥ ለተጫዋቾችና ለአሠልጣኝ ከፍተኛ ደመወዝ ተከፍሎ እግርኳሱ እየተጎዳ ነው። «አንድ በሉን ብለው ሲጠይቁን አድራጊው እነሱ ሆነው እንዴት ጠየቁን ብለን ተገርመናል፣ ዘንድሮ ሰሜን ከፍተኛ ገንዘብ ካወጣ በቀጣይ አመት ሰሜኑ ያወጣል ዝርፊያው በየተራ ይመስላል ምክንያቱ ደግሞ ዋንጫ ለማምጣት ይሉናል፣ ዋንጫ በገንዘብ አይመጣም አሁንም ክለቦቹ ተያይዘው ወደ ገደል እየሄዱ ነው» በማለትም የጉዳዩን አሳሳቢነት አስረድተዋል።

«ከደመወዝ ክፍያ ጋር ክለቦቻችን በአማካይ ለደመወዝ የምናውለው ከ45 ሚሊዮን ብር በላይ ነው ብለዋል፣ ይሄ ግን ልክ አይደለም ለወደፊቱ 99 በመቶ ለደመወዝ አውሎ መቀጠል የለም አደብ የሚያስገዛ ሕግ እናወጣለን፣ ለአሁኑ ግን በጉባኤው በከፍተኛ ደመወዝ ተጫዋች ቀጥራችሁ ሩብ አመት ሳይሞላ ደመወዝ መክፈል ያቅታችኋል፣ በዚህ ዓይነት ውድድሩ እንደሚጨረስ ምን ማስተማመኛ አለን ብለን አልጠየቅንም፣ መክፈል ያልቻለ ክለብ ነጥብ እንቀንሳለን ብለን የምንቀጣበት ሕግም ደግሞ የለም» ሲሉ መቶ አለቃ ፍቃደ የሕግ ክፍተቱን ገልጸዋል።

ስለ ደመወዝ ክፍያ ገደብ የተጠየቁት ፕሬዚዳንቱ «የ50 ሺ ብሩ የደመወዝ ገደብ ድጋሚ እንዲነሳ አንዳንዶቹ ክለቦች ይፈልጋሉ፣ ከዚህ በፊት ክለቦችና ባህልና ስፖርት ሚኒስቴሩ ቁጭ ብለው ገደቡን ወስነዋል ይሄን ለማድረግ የሕግ መብት ግን የለም፣ ካፍም ፊፋ ጋርም የለም፣ አሁንም ግን አንዳንድ ክለቦች ፈልገው ነበር ሕጉ በፍጹም ተመልሶ አይመጣም ሕገወጥ ነው» ሲሉ አብራርተዋል።

 አለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን  መስከረም 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You