ኮሚሽኑ ተስፋ ያደረግናቸውን ብሩህ ነገዎች ተጨባጭ ለማድረግ ትልቁ አቅማችን ነው!

 ሀገራችን በየዘመኑ በውስጣዊና ውጪያዊ ችግሮች በብዙ ከተፈተኑ ሀገራት መካከል በግንባር ቀደምትነት ተጠቃሽ ናት። ከዚህ የተነሳም እንደ ሕዝብ ዜጎቿ መሆን የሚፈልጉትን መሆን አቅቷቸው ዘመናት ተቆጥረዋል። በዓለም አቀፍ ደረጃም የኋላ ቀርነትና የድህነት ማሳያ ለመሆን የተገደዱበት እውነታ የአደባባይ ምስጢር ነው ።

አንዳንዶቹ ችግሮች የተፈቱበት ሆነ፤ የተያዙበት መንገድ ጤነኛ ባለመሆኑ የተነሳም ዘመን ተሻግረው የተጨማሪ ችግር ምንጭ ሆነዋል፤ ላልተገባና የተፋለሰ የታሪክ ትርክት ምክንያት በመሆንም ሀገርና ሕዝብን ያልተገባ ዋጋ አስከፍለዋል፤ ዛሬም እያስከፈሉ ነው።

ከዚህም ባሻገር የትውልዶችን አእምሮ ባልተገባ የጥፋት መንገድ በመምራት ትውልዱ የራሱን መሻት እንዳይኖር፣ ለሀገሩ የሚያስበውን በጎ ሃሳብ ባለው እውቀት እና ጉልበት ሳይቆጥብ ተግባራዊ እንዳያደርግ አድርጎታል። በራሱና በሀገሩ ጉዳይ ባይተዋር እንዲሆን አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥም ከትቶታል።

ከዚያም ባለፈ በዘመናት እንደ ሕዝብ የቀደሙት አባቶቹና አያቶቹ ሀገርን እንደ ሀገር ጠብቀው ካቆዩባቸው ማኅበራዊ፣ መንፈሳዊ እና ባህላዊ እሴቶች እየተጣላ፤ የሀገሪቱ ታሪካዊ ጠላቶች የጥፋት መጥመድ ሰለባ እንዲሆን አድርገውታል፡፡ ለሀገርና ለሕዝብ ተስፋ ከመሆን ይልቅ፤ ስጋት የሚሆንበት የተደጋገሙ ታሪካዊ ክስተቶች ተፈጥረዋል።

በዚህም እንደ ሀገር ብዙ ዋጋዎችን ለመክፈል ተገደናል፡፡ ጦርነት፣ ሞት ፣ ስደት ፣ መፈናቀል እና ረሀብ የሕዝባችን የየዘመኑ መገለጫ መሆን ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል። በየዘመኑ በብዙ ጣር ትውልዶች ያማጧቸው የብሩህ ቀናት ምጦች ጨንግፈዋል፡፡ የብሔራዊ ኀዘንና ቁዘማ ምንጭ ሆነዋል።

እነዚህ ዘመን ተሻጋሪ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ያለማግኘታቸው እውነታ ደግሞ ፤ በየዘመኑ ለሚነሱ የፖለቲካ ቆማሪዎች / ነጋዴዎች አዋጭ እና ርካሽ የፖለቲካ ሸቀጥ ሆኖላቸዋል፡፡ በተለያዩ አዳዲስ የጥፋት ትርክቶች አቅም እየገዙ ሀገርን እንደ ሀገር የህልውና ስጋት ውስጥ መክተት ችለዋል።

ይህ ትውልድም እንደቀደሙት ትውልዶች ሁሉ እነዚህ ችግሮች አሁንም ድረስ በሚነገረው የጥፋት ትርክት ልክ ከፍያለ ዋጋ ስለመክፈሉም ሆነ፣ እየከፈለ ስለመሆኑ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም። ችግሩም ዛሬ ላይ የሀገራችን የሕዝባችን የሰላም እጦት ዋንኛ ምክንያት እንደሆነ የአደባባይ ምስጢር ነው።

በቀደመው የፖለቲካ ሥርዓት እነዚህ ችግሮች ከአቅማቸውና ከአውዳቸው፣ ከዚያም ባለፈ ከዘመኑ እሳቤ ባፈነገጠ መንገድ፤ የፖለቲካ አጀንዳ ተደርገው መወሰዳቸው፤ የሀገርን ህልውና በየትኛውም ሰዓት አደጋ ውስጥ መክተት የሚያስችል አቅም እንዲይዙ አድርጓቸዋል።

ከለውጡ ዋዜማ ጀምሮ ሕዝባችን እንደ ሕዝብ የተነቃቃበትን የለውጥ አስተሳሰብና ለለውጡ ያለውን ቁርጠኝነት፤ እንደቀደሙት ዘመናት የለውጥ ትርክት ተቃርኖ ውስጥ በመክተት፣ ለማቀዛቀዝ ለተለያዩ ጸረ-ለውጥ ኃይሎች መገልገያ ተደርገውም ነበር።

ሀገርን እና ትውልዶችን በየዘመናት ብዙ ዋጋ ሲያስከፍሉ ከመጡ ከነዚህ ችግሮች ለመታደግ ይህ ትውልድ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበት ይታመናል። ይህንን ታሪካዊ ኃላፊነት ለመወጣትም የተሻለ ግንዛቤ፤ ተጨባጭ ተሞክሮ እና መልካም ዕድሎች አሉት።

ከነዚህ ዕድሎች መካከል ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን አንዱ ነው። ኮሚሽኑ እነዚህን ዘመንና ትውልድ ተሻጋሪ ችግሮችን በንግግርና በውይይት ለመፍታት እየሄደበት ያለው መንገድ፤ ለችግሮቹ ዘላቂ መፍትሔ ከማፈላለግ ባለፈ፤ ሀገርን እንደ ሀገር ከግጭት አዙሪት ማውጣት የሚያስችል ትልቅ አቅም ነው።

ከችግሮቹ በስተጀርባ ያሉ የጥፋት ትርክቶችን በማጥራት፤ ለችግሮቹ ዘመኑን የሚዋጅ መፍትሔ ለማፈላለግ ዕድል የሚሰጥ፤ በታሪክ ትርክቶች ልዩነቶችን ከማስፋት ይልቅ፤ ከታሪክ ተምረን አሁናችንን፤ ተስፋ ያደረግናቸውን ብሩህ ነገዎች ተጨባጭ ለማድረግ ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ የሚረዳን ነው!

አዲስ ዘመን  መስከረም 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You