ቡናማዎቹን ከነብሮቹ ያገናኘው ተጠባቂ የፍፃሜ ፍልሚያ

ከአንድ ሳምንት በላይ በአበበ ቢቂላ ስቴድየም ሲካሄድ የቆየው 17ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ዛሬ ይጠናቀቃል፡፡ የፍፃሜ ተፋላሚዎቹ ባለፈው ሰኞ በተካሄዱ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች ሲለዩ ኢትዮጵያ ቡናና ሃዲያ ሆሳዕና ዋንጫውን ለማንሳት ዛሬ የሚፋለሙ ይሆናል፡፡

ሁለቱ ክለቦች በግማሽ ፍፃሜው ፍልሚያ ተጋጣሚዎቻቸውን በመለያ ምት አሸንፈው ለፍፃሜ የቀረቡ ሲሆን ዛሬ የሚያደርጉት ፉክክርም ተጠባቂ ነው፡፡ የውድድሩ ተጋባዥ ክለብ ሃድያ ሆሳዕና በግማሽ ፍፃሜው ኢትዮጵያ መድንን በገጠመበት ጨዋታ ግብ ሳይቆጠር ወደ መለያ ምት አምርቶ ሃድያ ሆሳዕና 5 ለ 4 በማሸነፍ የፍፃሜ ተፋላሚ መሆኑን አረጋግጧል።

በተመሳሳይ ሁለቱን የአዲስ አበባ ተቀናቃኝ ክለቦች ያገናኘው የቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ በመጀመሪያው 45 በተቆጠሩ ግቦች ጥሩ ፉክክር ታይቶበታል። ፈረሰኞቹ አዳማ ከተማን አሸንፈው ወደ ግማሽ ፍፃሜ ሲያልፉ ሁለት ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ የጨዋታው ኮከብ የነበረው ሀሮን አንተር በ13ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ግብ ፈረሰኞቹን መሪ ማድረግ ችሎ ነበር። የፈረሰኞቹ መሪነት የዘለቀው ግን ለአስራ ሶስት ደቂቃዎች ያህል ነበር፣ 26ኛው ደቂቃ ላይ ወልደአማኑኤል ጌቱ ለኢትዮጵያ ቡና የአቻነቷን ግብ አስቆጥሮ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል። በሁለተኛው አጋማሽም ግብ ሳይቆጠር ወደ መለያ ምት አምርቷል።

በዚህም ኢትዮጵያ ቡና በመለያ ምቱ 5 ለ 4 በማሸነፍ የከተማው ዋንጫ የፍፃሜ ተፋላሚነቱን ሲያረጋግጥ በወጣቶችና በተስፋው ቡድን በውድድሩ የተካፈለው ቅዱስ ጊዮርጊስ ለደረጃ ፍልሚያው ኢትዮጵያ መድህንን የሚገጥም ይሆናል።

አምና ወደ ፕሪሚየርሊግ ባደገበት ዓመት አስደናቂ ጊዜን ማሳለፍ የቻለው ኢትዮጵያ መድህን በአሠልጣኝ ገብረመድህን ሃይሌ እየተመራ በዚሁ የከተማ ዋንጫ የመጀመሪያ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስን 3 ለ 1 ማሸነፉ ይታወሳል። ሁለቱ ክለቦች ዳግም በደረጃው ፍልሚያ የሚገናኙ ሲሆን ኢትዮጵያ ቡናም በፍፃሜው የሚገጥመውን ሃዲያ ሆሳዕና ከቀናት በፊት በምድቡ የመጨረሻ ጨዋታ 1 ለምንም ማሸነፉ ይታወቃል።

ሰባት ክለቦች በሁለት ምድብ ተደልድለው ሲፋለሙበት በሰነበተው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ዛሬ በተካሄደው የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች ሃድያ ሆሳዕና ከኢትዮጵያ መድን ጋር ባደረጉት ጨዋታ 0 ለ 0 ተለያይተው በተሰጠ የመለያ ፍጹም ቅጣት ምት ሃድያ ሆሳዕና 5 ለ 3 በማሸነፍ ለዋንጫ ማለፉን አረጋግጧል።

ኢትዮጵያ ቡና በመጀመሪያው የምድብ ጨዋታ የውድድሩን ተጋባዥ ሻሸመኔ ከተማን ሁለት ለአንድ ያሸነፈ ሲሆን፣ በሁለተኛው የምድብ ጨዋታ ደግሞ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ሁለት ለሁለት ተለያይቷል፣ የመጨረሻውን የምድብ ጨዋታ ያደረገው ዛሬ በፍፃሜ የሚገጥመውን ሃዲያ ሆሳዕና የነበረ ሲሆን አንድ ለዜሮ በማሸነፍ ከምድቡ ቀዳሚ ሆኖ የግማሽ ፍፃሜውን ፍልሚያ ተቀላቅላል፡፡ ጠንካራ በነበረው የግማሽ ፍፃሜ ፍልሚያ የከተማ ተቀናቃኙ ቅዱስ ጊዮርጊስን በመለያ ምት አሸንፎም ለፍፃሜ መብቃቱ በዛሬው የዋንጫ ጨዋታ ለድል የተሻለ ግምት እንዲሰጠው አድርጓል፡፡ ቡናማዎች በውድድሩ እስከ ፍፃሜ ሲጓዙ በአጠቃላይ በአራቱ ጨዋታዎች ሰባት ግቦች ሲያስቆጥሩ አራት ተቆጥሮባቸዋል፡፡

የውድድሩ ተጋባዥ ሆነው አስደናቂ የዋንጫ ጉዞ ያደረጉት ነብሮቹ በበኩላቸው በመጀመሪያው የምድብ ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ሁለት ለአንድ፣ በሁለተኛው ጨዋታ ደግሞ ሻሸመኔ ከተማን አንድ ለዜሮ አሸንፈው በሶስተኛው ጨዋታ ዛሬ በሚገጥሙት ኢትዮጵያ ቡና የአንድ ለዜሮ ሽንፈት አስተናግደዋል፡፡ በዚህም ከምድባቸው ኢትዮጵያ ቡናን ተከትለው የግማሽ ፍፃሜውን ፍልሚያ ተቀላቅለዋል፡፡ በግማሽ ፍፃሜው ፍልሚያም በፕሪሚየርሊጉ ጠንካራ የሆነውን ኢትዮጵያ መድህንን በመለያ ምት አሸንፈው ለዋንጫ መቅረባቸው ዛሬ ለቡናማዎቹ ቀላል እንደማይሆኑ ተገምቷል፡፡ ነብሮቹ በአራቱ ጨዋታዎች ሶስት ግብ ብቻ አስቆጥረው ለፍፃሜ ሲደርሱ ሁለት ግብ አስተናግደዋል፡፡

17ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ በሁለት ምድብ የተካሄደ ሲሆን በምድብ ሀ ኢትዮጵያ ቡና፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ሃድያ ሆሳዕና እና ሻሸመኔ ከተማ ተደልድለዋል። በምድብ ለ ያለፉት ሁለት ተከታታይ የፕሪሚየርሊግ ዋንጫ አሸናፊው ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ተጋባዡ አዳማ ከተማ እና ኢትዮጵያ መድን መደልደላቸው ይታወሳል።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን መስከረም 17/2016

Recommended For You