ፈንጂ ወረዳ

“ክቡራትና ክቡራን እንደማመጥ! .. ያለነው እኮ የስብሰባ አዳራሽ እንጂ የገበያ አዳራሽ አይደለም። ጥያቄ ካላችሁ እጃችሁን አውጡ። በዚህ የደቦ ሕዝበ ዝማሬ የማናችሁን ድምጽ ከማን እንለየው? ይብዛም ይነስም እዚህ ያለን አብዛኛዎቻችን አንድም ትሁን ሁለት ነጭ ሽብት አብቅለናል አይደል?!…ታዲያ ምነው አዳራሹን የሕጻናቱ መማሪያ ክፍል ማስመሰላችን!… በሉ አሁን ባለሙያው የጀመረውን ሪፖርት ያጠናቅቅና ጥያቄ ካላችሁም ከዚያ ኋላ የምናደምጣችሁ ይሆናል።

ስለዚህች የ21 ዓመት ኮረዳ ወረዳችን፤ ሁላችንም ያየን የሰማነውንና የተሰማንን ተራ በተራ እናወራለን” ሲሉ የወረዳዋ ምክትል አስተዳዳሪ፤ በአዳራሹ ሞልቶ ለፈሰሰው ለወረዳው ነዋሪ ቀጭን ትዕዛዛቸውን ከማሳሰቢያ ጋር አስተላለፉ። ጸጥታው ሰፍኖ በሁካታው የተቋረጠው ሪፖርት ቀጠለ።

“በእኛ ሴክተር መሥሪያ ቤት በዘንድሮው በጀት ዓመት በርካታ የተዘጉ መንገዶችን አስከፍተናል፤የተከፈቱትንም ቢሆን ወደ አገልግሎት አስገብተናል። ካሳካናቸው ግዙፍ ተግባራት መካከል አንደኛው አዳዲስ መንገዶችን መክፈታችን ነው። በቀበሌ `ሀ፣ ለ እና `መ በሦስቱ ቀበሌዎች በድምሩ የ21 ኪሎ ሜትር ሰፊ የመንገድ ዝርጋታ ያካሄድን ሲሆን፣ በቀበሌ `መ` የተሰራው የ 17 ኪሎ ሜትር የመንገድ ዝርጋታ ዋነኛው ነው…”

በአዳራሹ ከተሰበሰቡት የወረዳዋ ነዋሪዎች መካከል አንድ አዛውንት ለመናገር ሲቁነጠነጡ ቆይተው ጥያቄ ያላችሁ ሲባል አምስት ጊዜ እጃቸውን አውጥተው አምስቱንም ጊዜ ከዓይን እይታ ውጭ ሆነው ታለፉ። በስድስተኛውም ሳይታዩ ቀሩ። በሰባተኛው ግን እራሳቸው ለራሳቸው ዕድሉን በመስጠት ንድድ ብሏቸው “ጥያቄ አለኝ!” ሲሉ ጮክ ብለው ቆመው ድምጻቸውን አሰሙ። ሁሉም ዞር ብሎ በዓይኑ ገርመም አደረጋቸው። “ረጋ ይበሉ እንጂ አቶ ቸኮል! ጥያቄው ወዴት ይሄድብዎታል..እኛም ብንሆን አንበርር ነገር…ኋላ እረሳው እንደሆን ብለው ሰግተው ከሆነ ደግሞ፤ እስከዚያ በወረቀት ጫር ጫር እንዲያደርጉት ብዕራችንን እናውስዎታለን። እንዲህ መሆኑ የስብሰባውም ሆነ የትልቅ ሰው ወጉም አይደለም። በሉ አረፍ ይበሉ። ቀጣዩን ዕድል ሰጥተንዎታል” ተባሉ

አዛውንቱም፣ በለሆሳስ “ዲስኩራም ሁላ! እናንተ ስትደሰኩሩብን መቼ ተራና ወረፋ አልናችሁ” በማለት በዓይናቸው ዙሪያ ገባውን አየት አድርገው ውስጣዊ ስሜታቸውን እያቀዘቀዙ ተመልሰው ወደ መቀመጫው ወረዱ። የማይደርስ የለም ተራው ደረሳቸውና ንግግራቸውንም ጀመሩ። “የዛሬ አምስት ዓመት የጠጠር መንገድ ይሠራላችሁኋል ገንዘብ አዋጡ ብትሉን ጊዜ ደ..ግ ሊያልፍልን ነው ብለን ከሌለን ላይ ተሯሩጠን አዋጣን። እሰይ! ማድረጋችን መልካም..ነገር ግን ይሠራላችኋል የተባለው የጠጠር መንገድ ተሠርቶ ካለቀ በኋላ፤ ሦስቴ እንኳን ተመላልሰን ሳንረግጠው ይሄው በክረምቱ ዝናብ መንገዱ ብልሽት ብሏል። ያለመታደል ሆኖ ጠጠሩም ሟምቷል። ምናልባት ጠጠሩ የተሰራው ከድንጋይ ሳይሆን ከበረዶ ግግር ይሆናል።

መንገዱም ከመንገድነት ወደሚያሰጋ ስምጥ ሸለቆነት ተቀይሯል። እስከ ጥግ ድረስ የተንጣለለው ጎርፍም ለእግረኛም ሆነ ለጀልባ የማይበጅ ሆኗል። ይሁን እንግዲ… እሱንስ ማን አየበት?!… እቺን ብቻ ግን ልጠይቅ፤ በቀበሌ `መ` የተሠራልን መንገድ 14 ኪሎ ሜትር ሆኖ ሳለ አስራ ሰባት ኪሎ ሜትር ነው የሠራንላችሁ የምትሉን ለመሆኑ ሦስቶቹ ኪሎ ሜትሮች ከኛ ተሰውረው ወዴት ገብተው ነው? ወይንስ ቁጥሩም እንደኑሮ ውድነቱ ከቀን ወደ ቀን ያሻቅብ ጀምሯል…” ሲሉ ጊዜ በልብ ያለ ሲነገር ስሜቱ የተኮረኮሩ ያህል ነውና አዳራሹ በሳቅና በሹክሹክታ ተጥለቀለቀ።

እንግዲህ ብዙ ሰማን መድረኩን ፍትሃዊ ለማድረግ አንድ ያለችውን ዕድል ለሴቶች እንስጥ። ወንዶች እስቲ ትንሽ እረፍት አድርጉ። እህሳ… ከአዳራሹ ሴቶች የላችሁም? እያ ምክትል አስተዳዳሪው በዓይናቸው አዳራሹን ከጥግ እስከጥግ ቃኙት። “እኛስ አለን …እንዲያው የቱን ከየቱ እናስቀድመው እያልን ስናስብ እንጂ የምንለውስ መች ጠፍቶ ብለው ነው” በማለት እማማ ትርንጎ ከመቀመጫቸው ብድግ አሉ። “እንግዲህ ኖሮ ኖሮ ተቤት ዞሮ ዞሮ ተመሬት መሆኑ ተዚህ ላለን ለማናችንም ግልጥ ነው። ነገሩ ዛሬ ላይ ተቤታችን ውስጥ ታለን ሁናቴ የተነሳ ኑሮ ቢለያየንም ነገ ሁላችንም ያለመሪና ተመሪ፣ ያለ ሀብትና ድህነት ሁላችንም ተእኩል የምንገናኘው ተያው ተመሬቱ ላይ፤ ተአፈሩ ውስጥ ነው።

ተቀበሌያችን አቅራቢያ መካነ መቃብር ባለመኖሩ በየ ጊዜው ተሊቀመንበራችን ደጅ እየጠናን ስንጮህ ስንማጠን እሄው እኛም አረጀን። በሕይወት ሳለን የተንከራተትን አልበቃ ብሎ ስንሞትም መቃብር ፍለጋ ሀገር ቂጥ እንኳትናለን። የክረምቱስ አይነገር…ዝናቡ ቲዘንብ ወንዙ ተአፍ እስከ ገደፉ ጢፊፍ ብሎ ይሞላል። የቀዬው ሰው እንደሆን ህዳር ህዳር ለሠርግ፤ ክረምቱ ቲገባ ደግሞ ለሞት ይሯሯጣል።

እንግዲህ ጠደይ እስክትገባ ጠብቀህ ሙት አይባል ነገር ሰው የሚሞተው ወዶና መርጦ አይደለም። ታዲያ የክረምቱ የወንዝ ሙላት ባየለ ጊዜ፤ ወዲያ ማዶ ለመሻገር የሞላው እስቲጎድል አስክሬን ይዘን ተወንዙ ዳር ቁጭ ብለን ስናለቅስ ስንላቀስ እንቆያለን። እንባችን ቲደርቅ ጊዜም አፋችንን ከፍተን ስላቦ እያልን እግዜሩንም አየሩንም እንማጠናለን። የኛ ቀዬ ሰውስ እንደሆን ሞቶም አያርፍ፤ ይህቺ ገፊ ይበላት የክፋቷ ዋጋ ነው…እሄ መተተኛ መቼስ ጉዞው ወደ ሲኦል ቢሆን ነው እንጂ ገና አፈሩንም ታይለብስ ስቃዩ ተዚሁ የጀመረው…እያለ ለቀስተኛው ተየስርቻው ቁጭ ብሎ አስክሬኑን ይራገማል።

እንዲያው እግዜሩም እራርቶ ወንዙን ተሻገርን ስንል ወሳንሳ ተሸካሚው ተየመንገዱ ላይ ጭቃው እያዳለጠው ተነአስክሬኑ ባፍ ጢሙ ይደፋል። እሱስ ላንድ ነብሱ አንደኛውን ሞቷል፤ እኛ ግን እስተመቼ ነው ተአስክሬን ጋር ፍዳችንን ስንበላ የምንሰነብተው?” ብለው ፊታቸውን በጥያቄ ቅጭም ሲያደርጉ ልክ ነው በማለት ሕዝቡ በጭብጨባ ድጋፉን አሳያቸው። እማማ ትርንጎ ንግግራቸውን በዚሁ እንደማይቋጩ የተረዳውና ከአወያዮቹ መካከል አንዱ የሆነው የወረዳው የአስተዳደር ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ፤ እንደምንም ጭብጨባውን ታክኮ ገባና “እማማ ትርንጎ ያሉት ነገር በደንብ ገብቶናል። ከሚመለከተው አካል ጋር ተነጋግረን ችግሩንም በቅርቡ የምንፈታው ይሆናል” በማለት የጥያቄ እሩጫቸውን በምላሹ ገታው።

ይህችው የፈንጂ ወረዳ፤ ወደ ወረዳነት አድጋ በአዲስ መልክ ከተወለደች ድፍን 21 ዓመታትን ብታስቆጥርም አሁንም ግን የምትኖረው ገና አይኑን እንዳልከፈተ ሕጻን ልጅ ነው። ከመሠረተ ልማት ይልቅ መሠረታዊ ጥፋቶች ገዝፈው ይታያሉ። በወረዳነት በተያዘችበት ወቅትም በሥሯ ከነበሩ በርካታ ጎስቋላ ከተሞች መካከል ለሁሉም ይበጃል የተባለው አንደኛው ጎስቋላ ተመርጦ ዋና ከተማ እንዲሆን ተወሰነ። ከዚያን ጊዜ አንስቶም የወረዳዋ መቀመጫ ለኔ ነው የሚገባኝ በሚል ውዥንብር በሁለት የተለያዩ ቀብሌዎች መካከል ለአምስት ተከታታይ ዓመታት ያህል የእርስ በርስ ጦርነት ተካሄደ። ጦርነቱ የድንጋይና የዱላ ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚም ጭምር ነበር።

አርሶ አደሩንና ነጋዴውን በዚህ የጦርነት ቀለበት ውስጥ አስገብቶ በመዘወር ጦርነቱን የሚያፋፍሙት ደግሞ ወጣቶቹ ናቸው። በቀበሌ ሀ የሚገኝ አርሶ አደር ምርቱን ለመሸጥ ወደ ቀበሌ ለ ገበያ መግባትም ሆነ ድንበር አቋርጦ ማለፍ አይችልም። ነጋዴውም ከብቶችንና የሸቀጥ እቃዎቹን ይዞ እንዲገባም ሆነ እንዲወጣ አይፈቀድለትም። ሁለቱም የሚታውቁበት የራሳቸው የሆነ ምርት ስልነበራቸው የኢኮኖሚው ጦርነት ተፋፍሞ የራሺያና የአሜሪካንን ጦርነት የሚያስንቅ ነበር።

ትኩሳቱ ሲጨምር ደግሞ ሀገር አቆራርጠው የሚመጡ የሕዝብ ትራንስፖርቶችም ሆኑ መንደር ለመንደር ውር ውር የሚሉ ባለ ሁለትና ሦስት እግር ተሽከርካሪዎች ወደየትም ውልፍት እንዳይሉ ማቀብ ይጣልባቸዋል። በሁለቱም ወገን የሚገኙ ሞገደኞቹ የውስጥ ቆስቋሾች በየጊዜው የማጥቂያ ስልታቸውን እየነደፉ በስሜት የጋለውን የመንደር አርበኛ እየመለመሉ የክተት አዋጅ ያውጃሉ። ሰበብ አስባብ ፈልጎ ማታ ማታ እያደቡ ወደ ሌላው ቀበሌ ሰርጎ በመግባት ቤት አቃጥሎ የሌላውን ሀብት ንብረት መዝረፍ ለሌባው ያመቸ ግርግርና የዘረፋ እንኪያ ሰላምታቸው አደረጉት።

አፈ ጉባዔው ያሉትን ካሉ በኋላ ማይክራፎኑን በተራ ለአስተዳዳሪው ሰጥተውት ንግግር በማድረግ ላይ ነበሩ። ከንግግራቸው መሃልም “በአዲስ መንፈስ ወደ ሥራ የገባንበት የመጀመሪያው ዓመት የአንደኛ ዕሩብ ዓመታችን የሥራ አፈጻጸም ከአምናው የግማሽ ዓመት የተሻለ ሆኖ ተግኝቷል” በማለት ለጭብጨባዊ ምላሽ ሕዝቡን በዝምታ ሲመለከቱት አንዳንዱ በልቡ፤ የምናጨበጭበው ለአምናው ውድቀት ነው ለዘንድሮው ስኬት እያለ ቀርቶ እንዳይቀርበት ሲል ሞቅ አድርጎ አጨበጨበ፡፡

በዚሁ መሃል ድንገት በአካባቢው ከተደባዳቢነቱ የተነሳ ካራቲስቱ እየተባለ የሚጠራው ታዋቂው እብድ፤ ምንጩ የተባለውን የኔ ቢጤ ከኋላው አስክትሎ ሰተት ብሎ ያለፍርሃት ወደ አዳራሹ ዘልቆ ገባ። ሁሉም ጭብጨባውን ገታ አድርጎ ፊቱን ወደ በሩ አዞረ። “ምን ፈልጋችሁ ነው ውጡ” አለ አንደኛው አስተናባሪ ለመጠጋት ፈራ ተባ እያለ።

እብዱ አይኑን አጉረጥርጦ “ከዳቦውም… ከቡናውም እንድትሰጡን እንፈልጋለን!” አለ፤ በማይወላውል አቋም። ያውቁታልና ከአንዱ ጥግ ተቀምጠው እንዲበሉ ተደረገ። አስተዳዳሪው ንግግራቸውን ቀጥለው አፍታም ሳይቆዩ እብዱ በአንደኛው እጅ ዳቦውን በሌላኛው እጅ ሲኒውን እንደያዘ ብድግ ብሎ ቆመ። እሺ አሁን ደግሞ ምን ፈለግህ? አሉት አስተዳዳሪው በንዴት ማይክራፎኑን እንደጨበጡ ድምጻቸው የማጉያውን ስፒከር እያንቀጠቀጠ። የኔ ቢጤው በድንጋጤ ሹልክ ብሎ እግሬ አውጪኝ ሲል ዘሎ ቢወጣም፤ እብዱ ግን ምንም ሳይመስለው ጅንን ብሎ “አበል እፈልጋለሁ…እኔ አበል እንድትስጡኝ ነው የምፈልገው..እንኩ ዳቧችሁን እናንተው ብሉት…” እየፈረፈረ ወለሉ ላይ በተነው።

ፈንጂ ወረዳ ግራና ቀኝ ፊትና ኋላ ከተኮለኮሉት ቤቶች የተነሳ የ21 ዓመት ዕድሜ ያለው ከተማ ሳይሆን የስደተኛ ካምፕ ነው የሚመስለው። “እኔ ምለው!” አሉ ሃምሳ አለቃ በአንደኛው የስብሰባ ዕለት ምርር እያሉ” እኔ ምለው ግን…ከተማችን የወረዳው ንኡስ ከተማ የሚል ማዕረግ ሳይለጠፍበት በፊት ሌላው ቢቀር በውሃ አንቸገርም ነበር። ከአምስት ዓመታት በፊትም ቢሆን ከታንከሩ በጀኔሬተር ሃይል እየተሳበ በሳምንት አራትም ሦስትም ቀን ከቧንቧችን ይፈስ ነበር። አሁን ታዲያ ሌላው ያደረገው አይቅርብን ብላችሁ ውሃውንም ለአምፖል እንኳን በናፈቀን የመብራት ሃይል ማድረጋችሁ ምን የሚሉት ፌዝ ነው? ከውሃ እጦት የተነሳ ላንቃችን ደርቆ ቧንቧዎቻችንም የሸረሪት ድር ማድሪያ ሆነዋል…” ከማለታቸው የውሃ ቢሮው ሃላፊ ብድግ ብሎ “ሃምሳ አለቃ ይህን ያደረግነው እኮ እኛም ተቸግረን ነው።

የማንቀሳቀሻ ጄኔሬተሩ ስለተበላሸ ቤንዚን ሞልተነው ገና ዞር ከማለታችን ምጥጥ አድርጎ አላየሁም አልሰማሁም በማለት ዓይኔን ግንባር ያድርገው ይላል። ያፈስስ እንደሆን እያልን መሬቱን ብንመለከትም ሊፈስስበት ቀርቶ ለዓይን የሚታይ ጠብታም አይገኝበትም” እያለ ሲመልስ ሃምሳ አልቃም “ታዲይ ማሸኑን ከዓይናችን ሰውራችሁ? ከወዴት አኖራችሁት?…” ብሎ ለመጠየቅ ዳዳቸውና መፍትሔ ላይገኝ የምን ምላስ ማንቀዝ ነው ብለው ቁጭ አሉ።

ሌላኛው የማይድን እራስ ምታትዋ፤ ከዞኑ ዋና ከተማ የሚያገናኛት የአስፋልት መንገድ ነው። ከተጀመረ ዘመናት ቢያልፉትም ፍጻሜው ግን የህልም እንጀራና እንደምጽአት ቀን የራቀ ነው። ይህን መንገድ ተራ በተራ እየተፈራረቀ ያልቦጫጨረው ስካቫተርና ዶዘር፣ ያልነካካው የመንገድ ሥራ ተቋራጭ አልነበረም። ነገር ግን ሁሉም የድርሻቸውን ተቆራጭ እያደረጉ እብስ ከማለት ውጪ የፈየዱላት አንዳችም ነገር የለም።

በጀቱ ተበዘበዘ፤ ወጣቱም ተመረዘ። ነገሩን ቢያይ ቢያይ ምንም ጠብ የሚል ነገር ያጣው የወረዳው ወጣት፤ አንዳንዱ በገዛ ዳቦዬስ ልብ ልቡን ስለምን አጣለሁ…አንዳንዱ የአባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ …ሌላኛውም እኔ ባልበላውም መበላቱ እንደሆን አይቀር፤ እያለ የተባብረን እንብላ ዘመቻውን ከፈተ። እየተመሳጠሩ መብላት እየጠረጠሩ መቆርጠም… ይሄኔ ነው።

የፈንጂ ወረዳ ነዋሪዎች ስብሰባቸውን ከመጨረሳቸው በፊት አንድ ጉምቱ መምህር ተነስተው የሚከተለውን ሃሳብ ሰጡ፡፡ ወዳጆቼ ስነወቃቀስ ብንውል ፋይዳ የለውም፡፡ አንዳችን አንዳችንን ስንከስ ብንውል ማናችንም ከጥፋተኝነት አንድንም፡፡ ጥፋቱ የሁላችንም ነው፡፡ በመንግሥት ኃላፊዎች ላይ ጣታችንን ብንቀስርም እነርሱም ከእኛ ጉያ የወጡ ናቸውና በተለየ ዓይን ልናያቸው አንችልም፡፡ ደግሞም ጥፋታችው ብቻ ሳይሆን ልማታቸውም ሊታየን ይገባል፡፡ ያው ፍላጎታችን ብዙ ስለሆነ እንጂ የተሰራውን ነገር እንደቀላል ማየት አይገባንም፡፡ በልማቱ እንደምንደስት ሁሉ ችግሮችም ሲያጋጥሙ ከመወነጃጀልና አንዳችን አንዳችን ላይ ጣት ከመቀሰር ጉድለቶቻችንን በጋራ ለማስተካከል መነሳት ይገባናል፡፡ይህ ሲሆን እኛ ከችግሮች በላይ ሆነን ከራሳችን አልፈን ለሌሎችም ምሳሌ መሆን እንችላለን›› ብለው ሃሳባቸውን ገቱ፡፡የወረዳው ህዝብም አጨብጭቦ ስብሰባው አበቃ፡፡

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን መስከረም 17/2016

Recommended For You