ደካማው ማን ነው፣ ጥበብ ወይስ ጠቢቡ?

ዛሬ ዛሬ “ጥበብ ሞቷል”፣ “ሙዚቃ ድሮ ቀረ”፣ “ሥነጽሑፍ ተዳክሟል”፣ “ፊልም ወርዷል”፣ “ትያትር ‘ለመሆኑ አለ እንዴ?’” ወዘተ አይነት አስተያየቶች ሲዘወተሩ ይሰማል።

“ታሪክን አወላግዶ ስለ ጻፈ የከሸፈው ጸሐፊው እንጂ ታሪክ አይደለም” የሚል አገላለፅም የበርካታ ብዕረኞችን ድጋፍ አግኝቶ ለአደባባይ ሲበቃ ተመልክተናል። “የአንድ ጥበብ ክዋኔ ደካማ መሆን የ‘ጠቢቡ’ን እንጂ የጥበብን ድክመት አያመለክትም” የሚለውም እንደዛው።

በዚህ ሳያነቡ የሚጽፉ፣ ሳያጣሩ የሚያወሩ… በበዙበት ዳፍንት ዓለም “ጥበብ ሞቷል” ባዮች ቢበዙ ምን ይደንቃል፤ እራሱ ጥበብ ማለት ምን ማለት እንደ ሆነ በማይታወቅበት በዚህ ዘመን “አርት ድሮ” ቀረ ባዮች ቢደመጡ ምን ይገርማል ባዮች ደግሞ “የሞተው ጠቢብ ተብየው እንጂ ጥበብ አይደለችም” ነው የሚሉት።

ጥበብ በተፈጥሮዋ ደካማ ሆና አታውቅም። ደካማ የሚያስመስላት ተጠበብኩ ባዩ ያለ ሙያው ገብቶ ሲያተራምስ፤ ሲያጎሳቁላት ነው። ጥበብ እውነተኛ ጠቢብ ካገኛት እያበበች፤ እየፈካች፤ እየደነደነች … ከመሄድ ወዲያ ሌላ ጠባይ የላትም።

እውቁ ዜመኛ አብዱ ኪያር በ“የኔ ማር” ዜማው (ብዙ ሰው የልጅቷን ውበት ከማድነቅ ባለፈ ሌላኛውን፣ የተሸፋፈነውን መልእክት የተረዳለት አይመስልም) “ቃላት ላይ / ፊደል ላይ ሥልጣን የሌለው ሰው፤ አይችልም አይችልም ውበትሽን ሊገልፀው” እንዳለው (አፅንኦቱን ልብ ይሏል) እማይችሉትን እንደ ማይችሉት አውቆ ወደ እሚችሉት ማቅናቱ ነው የሚመከረው።

አብዱ፤

ውበት ቁንጅናሽን በቃል ለማስረዳት፣

የቋንቋ እውቀት ያለው ያስፈልጋል ረዳት።

ሲልም (ከሰማሁት ቆየት ስላለ ዝንፈት ካለ ይቅርታ እጠይቃለሁ) ጉዳዩን ከፍ ከማድረግም በላይ በ“እውቀት” መሠረት ያሲዘዋል።

እዚህ ላይ “ውበት”ን ብቻ እንኳን ብንወስድና ከ“ቢዩቲ” ከፍ አድርገን የዓለም ድንቅ ፈላስፎች ጊዜና እውቀታቸውን ያፈሰሱበትን “ሥነውበት” (ኤስተቲክስ)ን ብንመረምር “የቋንቋ እውቀት ያለው ያስፈልጋል ረዳት።” የሚለው ተገቢ ሆኖ እናገኘዋለን። ምክንያቱ ደግሞ ውበትን ለመግለፅ ኮልታፋ አንደበትና ዱልዱም ብዕር ምንም ፋይዳ የሌላቸውና ጉዳዩ እጅጉን የባለሙያን የተባ አእምሮና ብዕር መፈለጉ ነው። የመፈለጉ ጉዳይ ደግሞ ውበት እጅጉን ረቂቅና እንዲህ በቀላሉ ሊንፈላሰሱበት የማይቻል መሆኑ ሲሆን፤ ይህንን ማድረግ ያልቻለና ውበትን ያህል ነገር የሚያርመጠምጥ ከመጣ የተርመጠመጠው እሱ እንጂ ጥበብ አይደለችም ማለት ይሆናል።

ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን በ“መትፋት ያስነውራል” ዘለግ ያለ ግጥሙ፤

“እፍ አንቺ መብራት ጥፊ፣

እፍ አንቺ መብራት ክሰሚ፣

ጥፊ፣ ጨልሚ፣ ውደሚ” . . .

አለ አሉ ሼክስፒር ቄሱ፣

መቸም አያልቅበት እሱ።

መድረክ ላይ ኩስ ከሚተፉ

አዎን ሕይወት ረሷ ትጥፋ . . . (ሙሉ ግጥሙን ይመለከቷል።)

እንዳለው ሁሉ፤ የጥበብን ገበታ ከማበላሸት አርፎ መቀመጥ በራሱ ጠቢብነት ነው። (ፀጋዬ መድረክ ሲረክስ ከማየት ሕይወት ራሷ ብትጠፋ የሚሻለው መሆኑን ልብ ይሏል።)

ብዙዎች እንደደረሱበት፤ ደርሰውበትም እንድንደርስበት እንዳደረጉት ሁሉ ጥበብ የሕይወት ጥሪ እንጂ የነሸጠው ሁሉ የሚገባባት መዋኛ ገንዳ አይደለችም። ነፍሱን ይማረውና ባለቅኔው ጎሞራው (ኃይሉ ገብረዮሃንስ) በአንድ ወቅት በወቅቱ ስለነበሩት የሥዕል ሥራዎች አስተያየቱን እንዲሰጥ ተጠይቆ “አንድ ገረወይና ቀለም ይደፋና ‘ምንድን ነው?’ ሲሉት ‘አብስትራክት ነው’ ይላል። [. . .] ውበት ከእነ እንቶኔ ብብት ስር የሚወጣ አይደለም።” ያለውንም ባናብራራው እንኳን እዚህ አስፍረነው ለማለፍ እውነቱ ግድ ይለናል።

ከላይ ያነሳናቸው ልሂቃን አስተያየት የሚነግረን በርእሳችን ያነሳነው ሃሳብ ትክክል መሆኑን ብቻ ሳሆን፤ ከዛም በላይ በመሄድ ጥበብ መነገጃ አለመሆኗን፤ የጠቢባን የፍሬ ውጤት መሆኗን ጭምር ነው።

ነገሮችን ከእውነታው ጋር እያሰባጠርን እንያቸው ካልን ጥበብ የጠቢባን ተግባር እንጂ የማንም ሆና አታውቅም። “ጥበብ አስተማሪ ነች” ካልን የጠቢባን ሥራ ስለመሆኗ ማረጋገጫ ነው። “ጥበብ የሕይወት ነፀብራቅ ነች” ካልን የትጉሀን ተግባር ስለ መሆኗ ሌላው ማረጋገጫ ነው። በመሆኑም አብዱ ኪያር አፅንኦት ሰጥቶ “አይችልም አይችልም” እንዳለው ማንም እየተነሳ፣ ጥበብ የሕይወቱ ጥሪ ያልሆነው ሁሉ፤ በጥበብ ጆሮ ላይ ስሙን ማንጠልጠል የናፈቀው ሁሉ፤… ሁሉ ብድግ እያለ የጥበብን አይን ይደነቁል ዘንድ አልተፈቀደለትም። ወይም፣ አብዱ እንዳለው አይችልም።

ሰለሞን በስሙ ላይ “ጠቢብ” የሚለውን ማእረግ የደረበው ስለፈለገ፤ ወይም ስለተመኘው አይደለም። ጠቢቡ ሰለሞን የተባለው ሆኖ ስለተገኘ ነው። ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን ሎሬትነትን የተጎናፀፈው ስለፈለገው ወይም ስለተመኘው ሳይሆን ሆኖ ስለተገኘ ነው። ሌሎችም እንደዚሁ።

“ገና በልጅነቴ ይህንን የግጥም መጽሐፍ በማሳተሜ የተሰማኝ ደስታ” . . . በማለትና ራስን ማንቆለጳጰስ፤ እንዲሁም፣ “በዚህ እድሜህ ይህንን የመሰለ መጽሐፍ በማሳተምህ እንኳን ደስ አለህ” በማለት ከንቱ ውዳሴን ማዝነብ ጥበብን ምንም የሚጎዳት ነገር የለውም – “ጥበበኛ”ውን ከማሳቀል በስተቀር። በስመ ስፖንሰር በፈጠራ ሥራዎች ውስጥ ማስታወቂያዎችን ማጎር ጥበበኛው ከደረጃ በታች መጫወቱን ብቻ ሳይሆን አላዋቂ ሳሚ . . . መሆኑን ከማሳየት በስተቀር የጥበብ ክብር በጭራሽ ዝቅ አይልም። ጉዳዩን ወደ ታሪክም መውሰድ እንችላለን።

አሁን አሁን የኢትዮጵያ ታሪክ ባለሙያ ያልሆነ ሰው ማግኘት እየከበደ ሁሉ ያለ ይመስላል። “ሁሉም” በሚመስል ደረጃ የታሪክ ጸሐፊ ሆኗል። ሁሉም በፈለገው አይነትና መጠን ሲመነዝረው ይታያል። እንደፈለገ ያድርገው እንጂ የኢትዮጵያ ታሪክ እንደ ሆነ ያው የኢትዮጵያ ታሪክ ከመሆን ከፍም ዝቅም ሊል አይችልም። በመሆኑም፣ ጉድ የሆነው የኢትዮጵያ ታሪክ ሳይሆን የኢትዮጵያን ታሪክ አጠናሁ፣ ጻፍኩ … ያለው ብቻ ነው።

በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ፖርቹጋላዊው ሮማን ፕሮቻዝካ የተሰማራበት የስለላ ተግባር ተነቅቶበት ተይዞ ወደ ሀገሩ በመላኩ ምክንያት ሀገሩ ከገባ በኋላ ደበበ እሸቱ “የባሩዱ በርሜል” በሚል ርእስ የተረጎመለትን አሳፋሪ መጽሐፍ አሳትሟል። የሚገርመው መጽሐፍ ማሳተሙ አይደለም። የሚገርመው መባረሩን እንደ ቂም በመያዝ ለኢትዮጵያንና ኢዮጵያውያን ያለ ስማቸው ስም መስጠቱ፤ ያለ ባህርያቸው ባህሪን ማላበሱ፤ ያለውሏቸው ማዋሉ ነው።

የኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ደመኛ ጠላት የሆነው ይህ ሰውዬ (በኋላ የገዛ ሀገሩን ሁሉ በመክዳት ለቅጣት ተዷርጓል) እኛን በዛ መልክ ይግለፀን እንጂ ሳይውል ሳያድር ከማንነት ሚዛን ላይ የወደቀው እሱ እንጂ እኛ አይደለንም። ወይም፣ አይከስሩ ክስረት የከሰረው እሱ እንጂ የኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ታሪክ አይደለም። (እዚህ ላይ ጋሽ ደበበ እሸቱ አንድ ነገር የሳተ ሲሆን፣ እሱም ቢያንስ ሰውየው ልክ መጽሐፉን እንዳሳተመ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ስለ ማንነቱ የሀገሪቱን አምባሳደር ሁሉ ሳይቀር በማናገር ለእማኝነት ያበቁትን ጽሑፍ በ“መቅድም” ወይም ሌላ መልክ በትርጉም ሥራው አለማካተቱ ነው። ሰውየው በሀገሩ መንግሥት ሁሉ ሲሳደድ እንደነበረ፤ በኋላም ሀገሩን ሁሉ ለባእድ አሳልፎ እንደሰጠ በፓንክረስት ጽሑፍ በዝርዝር ሰፍሯል።) ይህ የሚያሳየን፣ ልክ እንደ ጥበብ ሁሉ፣ የተዛባ ታሪክ ጸሐፊው እንጂ ታሪክ ራሱ ሊወድቅ እንደማይችል ነው።

እንደምናውቀው የጥበብ መመዘኛ እራሱ ጥበብ ነው። ጥበብን የታጠቀ ጠቢብ ጥበብን፣ “እንደ በሬ ሻኛ” (እንዳለችው ትእግሥት) ከላይ ያውላታል። ከእነ ማእረጓ ከፍ አድርጎ ያውለበልባታል፤ እንደ ቀሲሱ ሼክስፒር፣ እንደ ሎሬቱ ፀጋዬ ያነግሳታል እንጂ ያዋረዳት መስሎት አይዋረድባትም። ያንኳሰሳት መስሎት አይንኳሰስባትም። ምን እያልን ነው፣ ጥበበኛ ተብዬው እንጂ ጥበብ አትወድቅም።

ጥበብ ያው ጥበብ እንጂ ሌላ ልትሆን አትችልም። ማለትም፣ ከፍም ዝቅም ማለት አይሆንላትም። ያው የተፈጥሮ ባህርይዋን ይዛ ከመዝለቅ ውጪ ከነፈሰው ጋር ልትነፍስ፣ ከወደቀው ጋር ሁሉ ልትከሰከስ አትችልም። በመሆኑም፣ ችግሩ የጥበብ ሳይሆን የ“ጥበበኛ”ው ሆኖ ይቀራል ማለት ነው።

ችግሩ የተደራጊው ሳይሆን የአድራጊው ሆኖ የመቅረቱን ጉዳይ በላይኛው ምሳሌ (በጠቀስነው ፖርቹጋላዊ ሰላይ) ልናየው እንችላለን። ወደ ጥበባችን እንምጣ።

ማንም “ግስ ግሳንግሱን ይዞ፣ ብዕሩን ቀስሮ ወረቀት ተመቸኝ ብሎ ስለ ቸከቸከ ብቻ ጠቢብ ሊሆን አይችልም። አንድ ገረወይና ቀለም ስለ ደፋ ብቻ የተዋጣለት ሠዐሊ ሊሆን፤ ወይም፣ ሊባል አቅሙ አይፈቅድለትም። የጥበብ ሰው፤ ወይም፣ እንደ ሠለሞን “ጠቢቡ …” ለመባል ጥበብ “የሕይወት ጥሪ” ልትሆን ይገባል። ካልሆነ ደካማው እሱ እንጂ ጥበብ (አርት) አይደለችም።

እዚህ ላይ ከአሁኑ ዘመን አንድ የቅርብ ምሳሌ እንውሰድና ማን እንደወደቀ እንመልከት።

እውነቱን ስንናገር ያለንበት ዘመን መፍጠር በመገልበጥ የተተካበት፤ የፊደል ዘርን ያልለየ ሁሉ የደራሲና ባለቅኔዎችን ጎራ የተቀላቀለበት ጊዜ ነው። ለዚህ ደግሞ ሙዚቃችንን የሚያክል ማሳያ የለም። እንደው፣ እስቲ አንድ በመንደር ጎረምሳ ያልተገለበጠና ዳግም ያልተዜመ ምርጥ የቀድሞው፣ የወርቃማው ዘመን ዜማ አለ? ከጥላሁን ገሠሠ ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎች ምን ቀረ፤ የመሀሙድ ቁንጮ ቁንጮ ሥራዎች ተፌዞባቸዋል። ሙሉቀን፣ ሂሩትና ብዙነሽ በቀለ፤ አስቴር ከበደ … ምናቸው ነው ያልተዘረፈው? በዋናው ድምፃዊና በሥራዎቹ መካከል ግድግዳ በመሆን የሰውን ሁሉ ዜማ እያስነኩት አይደለምን?

ወደ መጽሐፍም ብንመጣ ያው ነው። “የሚያቃጥል ፍቅር”ን እንዳለ በቁሙ ዘርፎ፣ በሕግ ተጠያቂ እንኳን ላለመሆን ማተሚያ ቤቱን በሀገር የሌለ፣ “ጠጅ ሳር ማተሚያ ቤት” ብሎ በአደባባይ መቸብቸብን ምን ይሉታል? በጥበብና ፈጠራ ላይ ይህ ሁሉ በደል ቢፈፀምም ዞሮ ዞሮ የወደቀው፣ በታሪክም ተጠያቂው ዘራፊው ቡድን እንጂ ጥበብ አይደለችም።

ሎሬት ፀጋዬ በ“እሳት ወይ አበባ“ው “ሥነግጥም የፈጠራ ሁሉ፣ የሥነጽሑፍ ሁሉ የደም ጠብታ ነው።” ካለ የቆየ ቢሆንም፣ የሚሰማ ጠፍቶ በእነ “የቀንድ አውጣ ኑሮ” መድበል ውስጥ እንደነ “ባጃጅ” አይነት ግጥሞችን እናነብ ዘንድ የተፈረደብን ጉዶች ከመሆን አላመለጥንም። እኛ አናምልጥ እንጂ የወደቅነው እኛ ሳንሆን ባለ “ባጃጁ” መሆኑን ግን ሁሉም ያውቃል። ዛሬ ላይ ሆኖ ሲያስበው እራሱ ገጣሚው ከጥበብ ማማ ላይ መንከባለሉን በሚገባ ስለ መረዳቱ መጠራጠር አይቻልም። (ልክ ሚሌኒየሙ መግቢያ አካባቢ “የድሮ ገጣሚያን ጨለምተኞች ናቸው። እኛም ጨለምተኝነትን ከእነሱ ነው የተማርነው።” ያለው የያኔው ጎረምሳ በቅርቡ “የድሮዎቹ በከፈቱልን መንገድ ነው እኛ እየሄድን ያለነው። የእነሱ ሥራዎች ባይኖሩ ኖሮ እኛ ሥራዎቻችንን ለመሥራት እንቸገር ነበር። ባለውለታዎቻችን ናቸው።” እንዳለው ገጣሚ ማለት ነው።)

ኢትዮጵያ በደንና ጫካ ሀብቷ አትታማም። ይሁን እንጂ ፊልሞቻችን (አንዳንዶቹ በሞባይል ቪዲዮ የተቀረፁ ናቸው ተብለው ይታማሉ) በሁለት ባህርዛፎች መካከል እየሮጡ ጫካ ለማስመሰል ሲደክሙ ማየት ብርቅ አይደለም። የልጅቷ አስፈላጊነት ምን እንደ ሆነ ግልፅ ባልሆነበት ሁኔታ አንዲት ቆንጆ መጥታ ፈገግታዋን ስትረጨው ማሳየት፣ ክንዱ ላይ ስትዝለፈለፍና አይኗን ስታንከባልል መመልከት የዘፈንና ዘፋኞቻችን “ሁሉ” የጋራ ባህርይ ነው። በሥነጽሑፍ ሥራዎቻችን ውስጥ የሥርዓተ ፆታ ፍልሚያን ማንበብ በጣም ከተለመዱት ዘመን አመጣሽ ጭብጦች መካከል ቀዳሚው ነው። ይህ ሁሉ ሲሆን ጥበብ ሞቷል፤ ጥበብ ወርዷል … የሚሉ መኖራቸው እየታየ ነው። ይህ ስህተት ነው። የወረደው፣ የወደቀው፣ የሞተው ያ ሥራና ሠሪው እንጂ ጥበብ አይደለችም። እድሜ ለጥበብ አምላክ ጥበብ አትሞትም – በትጉሃን አማካኝነት እያበበች ትሄዳለች እንጂ። እስቲ ወደ ሥነቃላችን ደግሞ እንሂድና “አንድ” እንበል።

የማህበረሰቡን ማህበረ-ባህላዊ እሴት መናድ ላይ ወገባቸውን አስረው የተሰማሩ ወገኖች እያደረጉት እንዳለው ከሆነ የሥነቃል ሀብታችን ሁሉ እየተከረከመና በእነሱ ልክ እየተሰፋ ይገኛል። ለዚህ ማስረጃ ይሆነን ዘንድ ደግሞ “የእነ ቶሎ ቶሎ ቤት ግድግዳው ብሎኬት” እና ሌሎችንም ማስታወሱ ብቻ በቂ ነው። ይህ ሁሉ ወንጀል ይፈፀም እንጂ ከጠቢብና ጥበብ ማማ ላይ የወደቀው ማን እንደ ሆነ ሁሉም ያውቀዋል። በተወለጋገደ ብዕር ሥነቃላችንን ለማወላገድ መሞከር ደግሞ ውጤቱ ከዚህ ውጪ ሌላ ምንም ሊሆን አይችልም።

በመጨረሻም፣ ኢትዮጵያ ጥበብ ሞልቶ የተረፈባት፣ ታፍሶ ያልተጨረሰባት ሀገር ነች። ከፊደላቷ ጀምሮ የራሷ የሆኑቱ ቁጥራቸው ከቁጥር በላይ ነው። አያልነህ ሙላት እንደሚለው የድራማ ጥበብ ከማንም በፊት እኛ ነበረን። ሙላቱ አስታጥቄ እንደደረሰበት የፖሊስ ማርሽን የሚመራው ፊት መሪ “ዘንግ” ነጮቹ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ወስደውና አዘምነው መልሰው ለኛ የሰጡን ነው። ፕሮፌሰር ፓንክረስት እንዳሉት ኢትዮጵያ በሀገር በቀል እውቀት የሚደርስባት የለም፤ ታዲያ ምን ያደርጋል … ።

ፕሮፌሰር ክላውድ ሰምነር እንደሚሉት ለመካከለኛው ዘመን የዓለም ፍልስፍና ፈር ቀዳጇ (በፈላስፋው ዘርዓያዕቆብ አማካኝነት) ኢትዮጵያ (አፍሪካ) ነች። የኦፕን ዩኒቨርሲቲዋ ዶ/ር (ስማቸው ተዘነጋኝ) “An­cient African Mathematics from Ethiopia” በሚል ርእስ እንደለቀቁት ዘጋቢ ፊልም ለአሁኑ ዘመን ኮምፒውተር መሠረቶቹ ያለ ፍራክሽን የሂሳብ ስሌትን ይጠቀሙ የነበሩት የጥንት ኢትዮጵያውያን ሲራራ ነጋዴዎች ናቸው። በርካቶች እንዳረጋገጡት ንግሥተ ሳባን የሚያክል በዓለም ታሪክና ሥነጽሑፍ ውስጥ ስሙ የተጠቀሰ ታላቅ ሰው በዓለም የለም (በእውቀቱ በ“ከአሜን ባሻገር” ቢያዋርዳትም)። እንደ ድሩሲላ (Drusilla Dunjee Houston. Wonderful Ethiopians of The Ancient Cushite Empire; 1926) ከሆነ የሁሉም ነገር ምንጭ ኢትዮጵያ ነች። ዘርዝረን አንጨርሰውም። በእነዚህ ሁሉ ውስጥ የኢትዮጵያ ጥበብ ነበር፤ አለ፤ ይኖራልም። በመሆኑም መውደቅ ካለ የሚወድቀው ጥበባችን ሳይሆን ያጎደፋት ነው።

 ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን መስከረም 17/2016

Recommended For You