ስኬታማውና ለተሻለ ውጤት የሚተጋው የድሬዳዋ ኢንቨስትመንት

በኢንዱስትሪ መነኸሪያነታቸው ከሚታወቁት የኢትዮጵያ ከተሞች መካከል አንዷ የሆነችው ‹‹የበረሃዋ ገነት›› ድሬዳዋ፣ የነዋሪዎቿ እንግዳ ተቀባይነትና አስደናቂ ኅብር ለኢንቨስትመንት ሥራ ምቹና ተመራጭ ያደርጋታል።ድሬዳዋ በማምረቻ ዘርፍ (Manufactur­ing Sector) የተሻለ የኢንቨስትመንት አቅምና ምቹ ሁኔታ አላት።የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመርን ተከትላ የተቆረቆረችውና ‹‹የኢንዱስትሪ ኮሪደር›› በመባል የምትታወቀው ድሬዳዋ፣ በንግድ ማሳለጫነቷ ተጠቃሽ ከተማ የነበረች ቢሆንም፣ ይህ የንግድ መነኸሪያነቷ ተቀዛቅዞ ቆይቷል።

የድሬዳዋ የንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ ከተማዋ ቀደም ሲል ወደምትታወቅበት የንግድ መነኸሪያነቷ ለመመለስ ጥረት እያደረገች ትገኛለች።የዚህ ጥረቷ ማሳያ ከሆኑ ተግባራት መካከል አንዱ ደግሞ በኢንቨስትመንት ዘርፍ እያደረገችው ያለው እንቅስቃሴ ነው።ይህ እንቅስቃሴዋም ሰምሮላት ውጤት እያገኘችበት ነው።የከተማዋን የኢንቨስትመንት ዘርፍ ችግሮችን በመፍታት የኢንቨስትመንት ፍሰትን ለመጨመር ዘርፉ በቦርድ እንዲመራ ተደርጓል።ይህም ሁሉም የኢንቨስትመንት ዘርፍ ጉዳዮች በቦርዱ እየታዩ የዘርፉ ችግሮችም ሆኑ የባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ጥያቄዎች ፈጣንና የተደራጀ ምላሽ እንዲያገኙ ለማድረግ ታስቦ የተወሰደ ርምጃ ነው።

በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ የኢንቨስትመንት ጥናትና ፕሮሞሽን ቡድን መሪ አቶ አበራ መንግሥቱ፣ በድሬዳዋ ከተማ ያለው የኢንቨስትመንት ዘርፍ እንቅስቃሴ አበረታች ለውጦች እየተመዘገቡበት እንደሚገኝ ያስረዳሉ።ከተማዋ ባለፈው የበጀት ዓመት በኢንቨስትመንት ዘርፍ ጥሩ አፈፃፀም አሳይታለች።አቶ አበራ እንደሚሉት፣ በ2015 የበጀት ዓመት በዘርፉ እንዲከናወኑ ታቅደው ከነበሩ ተግባራት መካከል አንዱ ለአዳዲስ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መስጠት ነበር።በዚህም መሠረት በ2015 የበጀት ዓመት ለ450 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መስጠት ታቅዶ፣ 347 ባለሀብቶች (በአገልግሎት 206፣ በማምረቻ 104፣ በኮንስትራክሽን 22፣ በግብርና 15) ፈቃድ ወስደዋል።ባለሀብቶቹ ያስመዘገቡት የካፒታል መጠን ከ34 ቢሊዮን ብር በላይ ሲሆን፣ ፕሮጀክቶቹ ከ21ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድሎችን የመፍጠር አቅም አላቸው፡፡

የኢንቨስትመንት ፈቃድ ከወሰዱት ባለሀብቶች መካከል ለሦስት ሺ952 ዜጎች የሥራ እድሎችን መፍጠር የቻሉ ስምንት ፋብሪካዎች እና አራት የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ፕሮጀክቶች ሥራ ጀምረዋል።ይህም ከበጀት ዓመቱ የዘርፉ ስኬቶች መካከል በግንባር ቀደምነት የሚጠቀስ አፈፃፀም ነው።ባለሀብቶች ወደ ከተማ አስተዳደሩ እስከሚመጡ በመጠበቅ ሳይሆን ወደ ባለሀብቶች በመሄድ ሥራዎቻቸውን ለመመልከትና ለችግሮቻቸው መፍትሄ ለመስጠት ያስቻሉ ተግባራትም ተከናውነዋል፡፡

የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ካሏቸው ፋይዳዎች መካከል አንዱ ፕሮጀክቶቹ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በሚከናወኑባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረጋቸው ነው።የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርም ባለሀብቶችን ወደ ከተማዋ ሲያስገባ ባለሀብቶች በተለያዩ መንገዶች የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ እንዲያደርጉ በማሰብ ነው።ማኅበረሰቡ ከኢንቨስትመንት ሥራዎች በሥራ እድል ፈጠራ፣ በምርትና አገልግሎት አቅርቦት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በገበያ እድል ተጠቃሚ እንዲሆን ይጠበቃል።በዚህ ረገድ በከተማዋ የሚከናወኑ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ለከተማዋና አካባቢው ህብረተሰብ ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎች እንዳሏቸው አቶ አበራ ይገልፃሉ።

‹‹በከተማዋ የሚገኙ ባለሀብቶች በሚያከናውኗቸው የኢንቨስትመንት ተግባራት አማካኝነት የሥራ እድል ከመፍጠር በተጨማሪ፣ ልዩ ልዩ ድጋፎችን በማድረግ ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ይገኛሉ።ለተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁሶች ድጋፍ የማድረግና አቅመ ደካሞችን የማገዝ ተግባራት የዚህ ማሳያ ናቸው።የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎችንም ይሠራሉ።ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ሥራዎቻቸውን በሚሠሩባቸው አካባቢዎች የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ተግባራትን ስለሚያከናውኑ የአካባቢው ኅብረተሰብ በዚህ ተግባር በኩል ተጠቃሚ ይሆናል።ይህ የማኅበረሰቡ ተጠቃሚነት ማኅበረሰቡ ለኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች አዎንታዊ አመለካከት እንዲኖረው አድርጓል›› ይላሉ።

ባለፈው የበጀት ዓመት ድሬዳዋ በኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ መልካም አፈፃፀም ማስመዝገቧ ባይካድም በዚህ አፈፃፀሟ ላይ መሰናክል የሚፈጥሩ ተግዳሮቶች እንደነበሩ አቶ አበራ ይገልፃሉ።የኢንቨስትመንት ፈቃድና መሬት ወስደው በገቡት ውል መሠረት ሥራቸውን ማከናወን ያልቻሉ ባለሀብቶች ለሚያቀርቧቸው ጥያቄዎች ፈጣን ምላሾችን በመስጠት እና ርምጃዎችን በመውሰድ ረገድ የነበሩ የአፈፃፀም ክፍተቶች ከችግሮቹ መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

ሀገራት የወጪና ገቢ ንግዳቸውን ለማቀላጠፍና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰታቸውን ለማሳደግ ብሎም አጠቃላይ ምጣኔ ሀብታዊ እድገታቸውን ለማሻሻል ከሚተገብሯቸው አሠራሮች መካከል አንዱ ነፃ የንግድ ቀጣናዎችን (Free Trade Zones) ማቋቋም ነው።ነፃ የንግድ ቀጣና ‹‹ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣና›› (Special Economic Zones) የሚባሉት የንግድና ኢንቨስትመንት መከወኛ ሥፍራዎች አካል ሲሆን እሴት የሚጨምሩ የምርት፣ የሎጂስቲክስ፣ የፋይናንስ አቅርቦትና መሰል ተግባራትና አገልግሎቶች የሚከናወንበት ቦታ ነው።በዚህ ስፍራ ምርቶችን ከማምረት በተጨማሪ አስመጪና ላኪዎች ዕቃዎችን ወደ ሀገር ውስጥ በማምጣት በቀጣናው ውስጥ የሚያከማቹበት፣ የሚያቀነባብሩበት እንዲሁም መልሰው ለውጭ ገበያዎች የሚያቀርቡበት እንዲሁም ሒደቱን ለማሳለጥ ቀልጣፋ የሆነ የሎጂስቲክስ አገልግሎት የሚቀርብበትም ነው።የተቀናጁ የፋይናንስና የምክር አገልግሎቶችም ይሰጥበታል።

ይህን ታሳቢ በማድረግም የኢትዮጵያን የወጪና ገቢ ንግድ በማቀላጠፍና የኢንቨስትመንት ፍሰቱን በመጨመር ለሀገራዊ ምጣኔ ሀብት እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ተስፋ የተጣለበት የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና (Dire Dawa Free Trade Zone)፣ ነሐሴ 8 ቀን 2014 ዓ.ም በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተመርቆ ሥራ እንደጀመረ ይታወሳል።

አቶ አበራ እንደሚሉት፣ ድሬዳዋ በንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ የላቀ አፈፃፀም እንድታስመዘግብ ከሚያስችሏት መልካም እድሎችና ግብዓቶች መካከል አንዱና ዋናው የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ነው።በአሁኑ ወቅት በርካታ ባለሀብቶች በነፃ የንግድ ቀጣናው ለመሰማራት ፍላጎት እያሳዩ ነው።ከዚህ ቀደም ከነበረው የተሻለ የባለሀብቶች ፍሰት እየታየ ነው።ነፃ የንግድ ቀጣናው ወደ ከተማዋ የሚገባውን የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲጨምር ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል።

‹‹ከውጭ የሚገቡ ባለሀብቶች ቀዳሚ ፍላጎታቸው ወደ ነፃ የንግድ ቀጣናው ገብተው ለመሰማራት ነው።ባለፈው ዓመት በተካሄደው ‹‹ኢንቨስት ኢትዮጵያ›› የኢንቨስትመንት ፎረም ላይ የተሳተፉ 27 የውጭ ባለሀብቶች የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣናን ጎብኝተዋል።ነፃ የንግድ ቀጣናው የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲጨምር ትልቅ እገዛ ያደርጋል›› በማለት የንግድ ቀጣናው ለድሬዳዋ ኢንቨስትመንት ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ይናገራሉ።

ባለፈው የበጀት ዓመት ስኬታማ አፈፃፀም ያሳየው የድሬዳዋ ኢንቨስትመንት፣ በ2016 የበጀት ዓመትም የተሻለ ስኬት እንዲያስመዘግብ ታቅዶ እየተሠራ እንደሚገኝ አቶ አበራ ያስረዳሉ።በ2016 የበጀት ዓመት ለ500 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለመስጠት ታቅዷል።ባለሀብቶቹ ከ42 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘግባሉ ተብሎ ይጠበቃል።ከእነዚህ ባለሀብቶች መካከል 35 ፕሮጀክቶች ግንባታዎቻቸውን አጠናቅቀው ምርት ማምረት እንዲጀምሩ ለማድረግም እቅድ ተይዟል።የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከከተማዋ የኢንቨስትመንት አቅምና ራዕይ አንፃር ብዙ ባለሀብቶች በማምረቻ ዘርፍ እንዲሰማሩ ፍላጎት አለው።ይሁን እንጂ ባለሀብቶቹ የእውቀት ደረጃቸው፣ የገንዘብ አቅማቸውና የሥራ ልምዳቸው ውጤታማ ሊያደርጓቸው በሚችሉት ዘርፎች የመሰማራት ምርጫቸው የተጠበቀ ይሆናል።የዳያስፖራ ማኅበረሰብ አባላት በድሬዳዋ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሰማራት ከፍተኛ ፍላጎት እያሳዩ ነው።

ከሥራ እድል ፈጠራና ከአካባቢ ልማት በተጨማሪ፣ ኢንቨስትመንት ከሚፈለግባቸው ምክንያቶች አንዱ የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማሳደግ ነው።በዚህ ረገድ የድሬዳዋና አካባቢው ተወላጅ የዳያስፖራ ማኅበረሰብ አባላት ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ወደ ድሬዳዋ በመምጣት የቴክኖሎጂ ሥልጠናዎችን ሰጥተዋል።ይህ ተግባር በተያዘው የበጀት ዓመትም ተጠናክሮ ይቀጥላል።ባለሀብቶች ከውጭ በሚያመጧቸው ባለሙያዎች የሚያከናውኗቸውን ሥራዎች ኢትዮጵያውያን በአጭር ጊዜ የተግባር ልምምድ የውጭ ዜጎችን ተክተው እንዲሰሩና የቴክኖሎጂ ሽግግሩ እውን እንዲሆን በማድረግ ረገድ አበረታች ውጤቶች እየተመዘገቡ ይገኛሉ፤ በርካታ አምራቾች ይህን አሠራር ተከትለው የኢንቨስትመንት ሥራዎቻቸውን እያከናወኑም ይገኛሉ፡፡

የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን ለማሻሻል በተደረጉ ጥረቶች አንዳንድ የኢንቨስትመንት ዘርፍ አገልግሎቶችን በኦንላይን (Online) መስጠት ተጀምሯል።የኢንቨስትመንት ፈቃድንም በኦንላይን ለመስጠት ጥረት ይደረጋል። እንደአቶ አበራ ገለፃ፣ ለባለሀብቶች የሚሰጠው የአንድ መስኮት አገልግሎት ባለሀብቶች ለፕሮጀክቶቻቸው አስፈላጊ የሆኑ የግብዓቶቻቸውን ጥያቄዎች በቀላሉ እንዲያቀርቡና በፍጥነት ምላሽ እንዲያገኙ የሚያስችል ነው።ይህ አሠራር ቀደም ሲል የሀብት (የጊዜና የገንዘብ) ብክነት ያስከትል የነበረውን የሥራ ሂደት የለወጠና ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት ያስቻለ ነው፡፡

በመሠረተ ልማት አቅርቦት ረገድ ደግሞ ከተማዋ ከዚህ ቀደም የተሻለ የመሠረተ ልማት አቅርቦትን እውን በማድረግ የባለሀብቶችን ፍሰት ለመጨመር ጥረት ማድረጓን አቶ አበራ ያስታውሳሉ።202 ሄክታር ስፋት ያለው የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ መንደር የራሱ የኃይል ማከፋፈያ አለው።ከከተማው የኃይል አቅርቦት ጋር የሚገናኝ ባለመሆኑ የኃይል መቆራራጥ ስጋት የለበትም።ባለሀብቶችም ለዚህ አበረታች የመሠረተ ልማት አቅርቦት ጥሩ እይታ እንዳላቸው ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።የኢንዱስትሪ መንደሩ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ ቀደም ሲል በተደጋጋሚ እየተቆራረጠ በኢንቨስትመንት ተቋማት ምርታማነት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ሲያሳድር ለነበረው የኃይል አቅርቦት ችግር አስተማማኝ መፍትሄ የሰጠ የመሠረተ ልማት አቅርቦት ነው።በ2016 የበጀት ዓመት የአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪ ልማትን ከሚመራው መሥሪያ ቤት ጋር በመተባበር የኢንዱስትሪ መንደሩን የውስጥ ለውስጥ መንገድ ደረጃውን ለማሻሻል ታቅዷል።

ባለሀብቶችን ለማበረታታት የሚተገበረው የአሠራር ሥርዓት በሀገር አቀፍ ደረጃ የተዘጋጀ ሕጋዊ ማዕቀፍ እንዳለው ይታወቃል።በዚህ ረገድ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርም ሕጋዊ ማዕቀፎቹን መሠረት በማድረግ ወደ ከተማዋ የሚገቡ ባለሀብቶችን ለማበረታታት የሚያስችሉ አሠራሮችን ተግባራዊ ያደርጋል።በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚተገበረው የማበረታቻ መመሪያ መሠረት የሚፈፀሙት መሬት ከሊዝ ነፃ የማቅረብ፣ ቀልጣፋ አሠራሮችን የማመቻቸትና ሌሎች ተግባራት ባለሀብቶችን የማበረታቻ ርምጃዎች አካል ናቸው።

የበጀት እጥረት በኢንቨስትመንት ተግባራት፣ በተለይም በመሬት ዝግጅት፣ ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል አቶ አበራ ስጋታቸውን ይገልፃሉ።የኢንቨስትመንት ባለድርሻ አካላት ለኢንቨስትመንት ስኬት ግብዓት የሆኑ ተግባራትን በእኩል ፍጥነትና ብቃት የመፈፀም ጉዳይም ሌላው በበጀት ዓመቱ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ሊያጋጥሙ ይችላሉ ተብለው ከተለዩት ችግሮች መካከል ይጠቀሳል።‹‹የኢንቨስትመንት ዘርፍ ባለድርሻ ሆነው የሚንቀሳቀሱ 12 ተቋማት አሉ።እነዚህ ተቋማት በእኩል አፈፃፀም ፍጥነትና ብቃት የመራመዳቸው ነገር ትልቅ ትኩረት ይፈልጋል።እቅድን ከማስተዋወቅ ጀምሮ እየተናበብን ለመሄድ ጥረት አድርገናል።ይህ ጥረት ዘላቂ እንዲሆን አስተማማኝ ዋስትና የሚሰጥ የሥራ ፍጥነትና ብቃት ያስፈልጋል›› በማለት ይናገራሉ፡፡

አንተነህ ቸሬ

አዲስ ዘመን መስከረም 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You