ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቶችን – ለንግዱ ዘርፍ ማነቃቅያ

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከሚሠራቸው ሥራዎች መካከል ንግድና ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት አንዱ ነው፡፡ ንግድና ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋትም የተለያዩ ዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ ባዛርና ኤግዚቢሽኖችን ያዘጋጃል፡፡ ምክር ቤቱ የንግዱን ማህበረሰብ በማሰባሰብ በሚያዘጋጃቸው ዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ የንግድ ትርዒቶች አባላቱ ተሳታፊ በመሆን ምርትና አገልግሎታቸውን እንዲያስተዋውቁ፣ ገበያ እንዲያፈላልጉና ትስስር እንዲፈጥሩ ያደርጋል። በዚህም የተነቃቃ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲኖር ዕድል ይፈጥራል፡፡

ምክር ቤቱ በዘንድሮ 2016 ዓ.ም ብቻ ሶስት የተለያዩ የንግድ ትርዒትና ኤግዚቢሽኖችን ሊያዘጋጅ መሰናዳቱን ከሰሞኑ አስታውቋል፡፡ ይህን ባሳወቀበት ወቅት የተገኙት የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ አቶ ሺበሺ ቤተማርያም እንዳሉት፤ ምክር ቤቱ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ የንግድ ትርኢቶችን በማዘጋጀትና ሌሎችንም ንግድና ኢንቨስትመንትን የሚያበረታቱ ተግባራትን በማከናወን ሲሰራ ቆይቷል፡፡

ዘንድሮም ሶስት የተለያዩ የንግድ ትርዒቶችንና ኤግዚቢሽኖችን በተለያየ ጊዜ ለማካሄድ አስፈላጊውን የዝግጅት ሥራዎች አከናውኗል። ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢቶችና ኤግዚቢሽኖቹ ግብርናና ምግብ ማቀነባበር፣ ማኑፋክቸሪንግና ቴክኖሎጂ ላይ የሚያተኩሩ ናቸው፡፡ እነዚህ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቶችና ኤግዚቢሽኖችም በሀገሪቱ ያለውን ምርትና አገልግሎት ለማስተዋወቅ፣ ገበያ ለማፈላለግ፣ የቴክኖሎጂ ልውውጥ ለማድረግ፣ የሥራ አጋርነትን ለማጠናከርና ለዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር ጉልህ ሚና ይጫወታሉ ብለዋል፡፡

ምክር ቤቱ ከዛሬ 28 ዓመት ጀምሮ የንግድ ትርዒቶችን ሲያካሄድ መቆየቱን ያስታወሱት ዋና ጸሐፊው፤ ዓለም አቀፍ ስጋት ሆኖ በቆየው የኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ላለፉት ሁለት ዓመታት የንግድ ትርዒቱና ኤግዚቢሽኑ ሳይካሄድ መቆየቱን ገልጸዋል።

ዘንድሮ የሚካሄዱት ሶስት የንግድ ትርዒትና ኤግዚቢሽኖች በአዲስ ቻምበር ብራንድ የሆኑ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቶች ስለመሆናቸው ያመለከቱት ዋና ጸሐፊው፤ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ለሁለት ዓመታት ተቋርጦ ዘንድሮ ለ26ኛ ጊዜ የሚካሄደው የንግድ ትርዒትና ኤግዚቢሽን አንደኛው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በማኑፋክቸሪንግ የተለያዩ ዘርፎች እንዲሁም ትኩረቱን በቴክኖሎጂ ዘርፍ ላይ የሚያደርገው ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒትና ኤግዚቢሽን ሁለተኛው መሆኑን አስታውቀው፤ በግብርናና በምግብ ማቀነባበር ዘርፍ የሚደረግ የንግድ ትርዒትና ኤግዚቢሽን ሶስተኛው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቱና ኤግዚቢሽኑ አጠቃላይ ትኩረቱ፤ የንግዱ ማህበረሰብ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ተሳታፊ መሆን እንዲችል ሲሆን፤ ሌላኛው የፈጠራ ሥራን በማበረታታት ልማትን ማቀጣጠልና ማዝለቅ የሚል ተልዕኮ የያዘ ስለመሆኑ አመላክተዋል፡፡ ዓለም ወደ ዲጅታል ኢኮኖሚ እየገባ መሆኑን ጠቅሰው፣ ዲጅታል ኢኮኖሚው በኢትዮጵያም የማይቀር ድልና ፈተናም ጭምር በመሆኑ ምክር ቤቱ ሥራ ፈጠራን ያስፋፋል ብለዋል፡፡

የወጣቶችን የሥራ ፈጠራ ለማበረታታትና ለማሳደግ ምክር ቤቱ የቢዝነስ ማዕከል ማስገንባቱንና ወደ ሥራ ማስገባቱንም ተናግረዋል፡፡ ይህም በፈጠራ ሥራቸው የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ መቀየር የሚችሉ ወጣቶች እንዲበረታቱ እንደሚያደርግም ገልጸዋል። በተለይም በቴክኖሎጂ ዘርፍ የሚዘጋጀው የንግድ ትርዒትና ኤግዚቢሽን ሥራ ፈጣሪ የሆኑ ወጣቶችን የሚጋብዝ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ በዚህም ምክር ቤቱ ንግድና ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት፣ የሥራ እድል ለመፍጠር፣ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ ተግባራትን ለማከናወን የሚያስችሉ እድሎችን ለመፍጠር ጭምር እንደሚጠቀም ነው ያስረዱት፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ በግብርናው ዘርፍ የሚዘጋጀው የንግድ ትርዒትና ኤግዚቢሽንም ትኩረቱን እሴት ጭመራ በማድረግ በምግብ ማቀነባበር ዘርፍ የኢትዮጵያ የምግብና ምግብ ነክ ምርቶች በንግድ ትርዒቱ የሚተዋወቁበት ይሆናል፡፡

በንግድ ትርዒቱም ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ 100 የሚደርሱ የውጭ ኩባንያዎችም ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡ ቃል የገቡ ኩባንያዎች አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከልም አንደኛው የቱርክ ኩባንያ ሲሆን፣ ይህ የቱርክ የቢዝነስና የንግድ ማስፋፋያ ተቋም በተለያዩ ዘርፎች ተሳታፊ ይሆናል፡፡ ከቱርክ በተጨማሪም በኢትዮጵያና በአፍሪካ የሚገኙ የቻይና ኩባንያዎችና ሌሎችም ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡

በዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቱና ኤግዚቢሽኑ በሚኖረው የንግድ ልውውጥና የገበያ ትስስር ከመፍጠር ባሻገር የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ ማሳየት የሚቻልበት አጋጣሚ እንዳለም ዋና ፀሐፊው ይገልጻሉ፡፡ በዚህም የሀገሪቱን በጎ ነገሮች ማጉላት ተገቢ ነው ይላሉ፡፡

‹‹ቢዝነስ ያለ ሰላም፤ ሰላምም ያለ ቢዝነስ የሚታሰቡ ጉዳዮች አይደሉም›› ያሉት ዋና ፀሐፊው፤ የሰላም ግንባታን በማጠናከር የቢዝነስ ሥራዎችንና ሥራ ፈጠራን በማሳደግ ሀገሪቷን ከድህነት ማውጣት እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ለማንኛውም ሥራና ንግድ አመቺ መሆኗን ጠቅሰው፣ በዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒትና ኤግዚቢሽን ለሰላም ትኩረት በመስጠት ንግድ የሚስፋፋበትንና ኢንቨስትመንት የሚጠናከርበትን መንገድ ማመቻቸት እንደሚያስፈ ልግ አስታውቀዋል፡፡ ለዚህም ሚዲያው ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበት ገልጸው፤ ሀገሪቷ የሰላምና የሥራ መፍጠሪያ እንደሆነች ማሳወቅና ማስተላለፍ እንደሚገባ ጭምር አመላክተዋል፡፡

ዋና ፀሐፊው እንዳሉት፤ በአሁኑ ወቅት ቢዝነስ ለቢዝነስ የሆኑ ግንኙነቶችን ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒትና ኤግዚቢሽኑ ለኢትዮጵያ ፖሊሲ አመንጪዎች ጥሪ የሚቀርብበትም ይሆናል። በየዘርፉ ያሉ ለንግድና ኢንቨስትመንቱ ማነቆ የሆኑ ጉዳዮችንና ከውጭ ምንዛሪ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር የንግዱ ማህበረሰብ የጋራ ውይይት የሚያደርግበት መድረክም ይሆናል፡፡ የውይይት መድረኮቹም አጠቃላይ በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ የሚነሱ ችግሮች ጎልተው የሚሰሙበት፣ ጥሪ የሚቀርብበትና መፍትሔ የሚፈለግበት በመሆኑ የንግዱ ማህበረሰብ በሙሉ ተሳታፊ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መሰንበት ሸንቁጤ በበኩላቸው እንዳስ ታወቁት፤ ንግድና ኢንቨስትመንትን ማስፋፋትና ማሳደግ የምክር ቤቱ ዋና ሥራ ነው፡፡ የግል ዘርፉን ማገዝና መደገፍ ለሀገራዊ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወሳኝ ይሆናል፡፡

የንግድ ሥራ በባህሪው ከፍተኛ የሆነ የሰዎችን መቀራረብና መግባባት የሚፈልግ ሥራ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቷ፣ ዓለም አቀፍ ስጋት በነበረው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ባለፉት ሁለት ተከታታይ ዓመታት የንግድ ትርዒትና ኤግዚቢሽን ማካሄድ ሳይቻል መቅረቱን አስታውሰዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ያለውን ሰላማዊ እንቅስቃሴ መሠረት በማድረግ ምክር ቤቱ ወደ ሥራ በመግባት የንግድ ዘርፉን ለማነቃቃት ዝግጁ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ሥራ መሥራት ዋና ዓላማው መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህንን በማንኛውም ጊዜና ሁኔታ ውስጥ ሆኖ እንደሚሰራ ይናገራሉ፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት የንግድ እንቅስቃሴው የተገደበ በመሆኑ ዘርፉ አሉታዊ ተጽዕኖ ደርሶበት ቆይቷል ያሉት ፕሬዚዳንቷ፤ ያም ቢሆን ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ተከስቶ የንግድ እንቅስቃሴው በተዘጋበት፣ ሀገራዊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በተዳከመበትና የሰላም እጦትና የቢዝነሶች መቀዛቀዝ ባለበት ጊዜ ሁሉ ምክር ቤቱ የተለያዩ ሥራዎችን ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል፡ ፡ ለዚህም ዋናው ምክንያት ቢዝነስና ኢኮኖሚያዊ ልማት ለበርካታ ሀገራዊ ችግሮቻችን መፍትሔዎች በመሆናቸው እንደሆነ አመላክተዋል፡፡

ምክር ቤቱ በቀጣይ የሚያዘጋጃቸው ሶስት ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒትና ኤግዚቢሽኖች የሀገሪቱን የንግድ እንቅስቃሴ ማነቃቃት እንደሚችሉ ያላቸውን ዕምነት የገለጹት ወይዘሮ መሰንበት፤ ከተለያዩ ሀገራት የሚመጡ ኩባንያዎችም በሀገር ውስጥ ያለውን ትልቅ አቅም መረዳት የሚያስችላቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በተያያዘም ከተለያዩ ሀገራት መጥተው በንግድ ትርዒቱ የሚሳተፉ አባላት በሀገር ውስጥ ከሚገኙ የንግዱ ዘርፍ አባላት ጋር የገበያ ትስስር በመፍጠርና የልምድ ልውውጥ በማድረግ በሌላው ዓለም ያለው የንግድ እንቅስቃሴ ምን እንደሚመስል መረዳት የሚያስችላቸው መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

ወይዘሮ መሰንበት እንዳሉት፤ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት አባላቱ ከሌላው የዓለም ክፍል ጋር እኩል ተወዳድሮ መሥራትና የንግድ ልውውጥ ማምጣት የሚችልበትን መንገድ ለማመቻቸት ይሠራሉ፡፡ አባላቱ በወጪና ገቢ ንግድ እንዴት አድርጎ መሥራት እንዳለበት ጭምር ያግዛሉ፡፡ በተለይም ዓለም አቀፍ በሆኑ የንግድ ትርዒቶች ላይ የልምድና የዕውቀት ሽግግር በማድረግ ብዙ የሚማሩበት ዕድል ይፈጠራል፡፡ በንግዱ ማህበረሰብ የሚስተዋሉ የዕውቀት፣ የግንዛቤና ሌሎች ችግሮችንም እንዲሁ ለመፍታት ተቀራርቦ መሥራት ያስፈልጋል፤ በተለይም መሰል ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቶች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ይኖራቸዋል፡፡

በሀገር ውስጥ ያለው አብዛኛው የንግዱ ማህበረሰብ በተለይም በወጪ ገቢ ንግዱ ትልቅ ፈተና ያለበት መሆኑን ያመለከቱት ወይዘሮ መሰንበት፤ አንደኛ ምርቱን የሚቀበለው ሰው ማን እንደሆነ እንዲሁም እንዴት መግባባት እንዳለበት ጭምር አያውቅም ብለዋል፡፡ በመሆኑም በርካቶች የተሻለ ጥራት ያለው ምርት አምርተው ለውጭ ገበያ ማቅረብ ሳይችሉ የሚቀሩበት አጋጣሚ እንደሚስተዋል ይጠቅሳሉ፡፡ ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ የገበያ ትስስር መፍጠር የሚቻለው ዓለም አቀፍ ትላልቅ የንግድ ትርዒቶችን ማዘጋጀት ሲቻል እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ በቀጣይ በ2016 ዓ.ም የሚዘጋጁት የንግድ ትርኢቶች ምርትና አገልግሎቶችን ለማስተዋወቅ፣ ገበያ ለማፈላለግ፣ የቴክኖሎጂ ልውውጥ ለማድረግ፣ የሥራ አጋርነትን ለማጠናከርና ለዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር ጉልህ ሚና ይጫወታሉ፡፡ ስለዚህ የንግዱ ማህበረሰብ በእነዚህ የንግድ ትርኢቶች ላይ በንቃት በመሳተፍ የሚፈጠሩ እድሎችን አሟጠው መጠቀም ይኖርባቸዋል፡፡

ምክር ቤቱ ዘንድሮ የሚያካሂዳቸው ሶስት ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቶች 26ኛው አዲስ ቻምበር ዓለም አቀፍ ንግድና ትርኢት፣ 14ኛው የግብርናና ምግብ ንግድ ትርኢትና 6ኛው የማኑፋክቸሪንግና ቴክኖሎጂ የንግድ ትርኢቶች ናቸው፡፡ እነዚህን የንግድ ትርዒቶች ለማዘጋጀት ዝግጅቱን አጠናቅቋል። የግብርናና ምግብ ንግድ ትርኢት ከኅዳር 27 እስከ ኅዳር 29 ቀን 2016 ዓ.ም፤ አዲስ ቻምበር ዓለም አቀፍ ንግድ ትርኢት ከየካቲት 14 እስከ የካቲት 18 ቀን 2016 ዓ.ም እንዲሁም የማኑፋክቸሪንግና ቴክኖሎጂ ንግድ ትርኢት ከግንቦት 15 እስከ ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚካሄዱ ጠቁሟል፡፡

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን መስከረም 16/2026

Recommended For You