ሰላም የምትጠይቀውን ዋጋ ሁሉ ከፍላችሁግዟት እንጂ በፍጹም አትሽጧት!

 ሰላም ከበጎ ህሊና እና ንጹሕ ልብ የሚመነጭ ፣ ለራሳችንና ለሌሎች ሁለንተናዊ መረጋጋትና የሀሳብ መቃናት፤ የግል ጥቅሞቻችንን ተሻግረን የምንከፍለው በየደረጃው በተግባር የሚገለጽ ውድ ዋጋ ነው።

ሰላም በነፍስ ወከፍ ከእያንዳንዱ ሰው ለሌሎች፣ ከሌሎችም ለሰው ልጆች ሁለንተናዊ መረጋጋት ፣ የሀሳብ መቃናት ፣ ማኅበራዊ እረፍት ማግኘት ፣ዘርቶ መቃም፣ ወልዶ መሳምና የህይወት መሻሻል ከግል ጥቅም መጠበቅ ባለፈ ለብዙኃን የሚከፈል በምንም አይነት መለኪያ ልተመን የማይችል ርካታና ውስጣዊ ደስታን ጭምር የሚፈጥርም ይሆናል።

በየደረጃው የሚገለጽ የሰላም ጥረት በተገኙበት ሁሉ እያደረጉ ያሉ ዜጎችን የሚገልጽ ባይሆንም ፤በተለምዶ የራሳችንን ፣የአካባቢያችንንና የሀገራችንን ሰላም ሕዝባዊ ተልዕኮና አደራ የተሰጣቸው ውስን አካላት ብቻ እንዲያስጠብቁልን አዘውትረን የምንፈልግ መሆኑ ዘላቂ የሰላም ግንባታ እንቅስቃሴያችን የሚፈለገውን ያህል ውጤት እንዳያመጣ አድርጎታል።”ጥንታዊ የባቢሎን ሰዎች የጋራ ከተማቸውን ለመገንባት እያንዳንዳቸው ጡብ እንዳቀበሉ ሁሉ “የየድርሻችንን የሰላም አስተዋጽኦ ከግል ጥቅም ስሌት በጸዳ መልኩ ስለሌሎችና ሀገር ዘላቂ ዕድገት ማበርከት ማኅበራዊ ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት መቻል ከመሆኑም ባለፈ የዜግነት ግዴታም ጭምር መሆኑ የሚዘነጋ አይሆንም።

“ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ” እንደሚለው የታላቁ መጽሐፍ የሰላም መልዕክትና እንደ ሌሎችም ሃይማኖቶች የሰላም አስተምህሮ ሁሉ”ዘወትር ስለ-ሰላም ገደቦችን ሁሉ አልፈን በመሄድ በማኅበራዊ መስተጋብራችን ለሚጎዳኙን ሰዎች ፣ ከፍ ሲልም ለዜጎችና እና ሀገር ሁለንተናዊ ሰላምና መረጋጋት የበኩልን የነብስ ወከፍ ማኅበራዊ ኃላፊነት ያለቀስቃሽ በሚገባና በሚመጥን መልኩ መወጣት መቻል የጋራ ሰላምን ለማረጋገጥና ለማጽናት አስተዋጽኦው የላቀ እንደመሆኑ ከአዳራሽ ግርግር ባለፈ የሁሉንም ተግባራዊ ተጨባጭ የሰላም ጥረት የሚጠይቅ ነው።

የሰላም ጥረትን ወደ ሌሎች የሚገፉና ከሌሎች የሚጠብቁ አካላት የሚፈጥሩትን ውስን ክፍተት በመጠቀም በተቃራኒው ኃላፊነት የጎደላቸው አንዳንድ ግለሰቦች በህቡዕ አደረጃጀት በመሰባሰብ፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለግጭት መንስኤ የሚሆኑ አጀንዳዎችን በማዋለድ እንደተጠመዱ ይገኛሉ። ርካሽ የፖለቲካ ትርፍ በመፈለግ በዜጎች ሕይወትና የትውልድ ዕጣ ፋንታ ላይ ቁማር እየተጫወቱ የሚገኙ መሆናቸው የአደባባይ ሚስጥር ከሆነ ሰነባብቷል። በየደረጃው ግጭት የማዋለድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ኃይሎች በሚያገኙት የሚዲያ አማራጭ ሁሉ እያስተላለፉ እንደሚገኙት ለአንድነት የማይበጅ አፍራሽ መልዕክት አማካኝነት ለሁላችንም ግልጽ አድርገው እያሳዩን እንደመሆናቸው በዚህ ረገድ የሀገር አንድነትን ለመከላከል መሰባሰብ ከሁሉም የሚጠብቅ ነው።

ውድ ሀገራችንን ጨምሮ፣ በተገኘንበት የዓለም ዳርቻ ሁሉ ስለ ሰው ልጆች ሁለንተናዊ እረፍትና መረጋጋት ምክንያት እንጂ፤የሰላም እጦት መንስኤ ሆነን ላለመገኘት ራሳችንን መግዛት፣ ማረቅና መግራት ፣ሰላምን ለሁሉም መተው ከእያንዳንዳችን የሚጠበቅ ማኅበራዊ ኃላፊነት ከመሆኑም ባለፈ የዜግነት ግዴታም ጭምር እንደሚሆን ይታሰባል። ከዚህም በተጓዳኝ ለእያንዳንዱ የሰላም እጦት ክስተት ራስን የመፍትሔ አካል አድርጎ ማቅረብ ደግሞ በሁሉም ረገድ የሚገለጽ ዘላቂ ሰላምን በተገኘንበት የሀገራችን ክፍል ሁሉ ለማስፈን፤ የሚያስችለን እንደመሆኑ ዘወትር በነብስ ወከፍ ዕለት – እለት ስለ አካባቢያችን ሰላም የበኩላችንን ተደማሪ አስተዋጽኦ በሚፈለገው ልክና አግባብ ማዋጣት የተገባን መሆኑ ግልጽ እንጂ ሌሎች በቅስቀሳ መልክ ግንዛቤ የሚፈጥሩልንና የሚያስረዱን ሊሆን አይገባም።

ትናንት በታሪካችን ላጋጠመን ስብራት ሁሉ፤ የሀገርን ህልውናና ቀጣይነት ማዕከል ያደረጉ አካታችና እውነተኛ ውሳኔዎችን ማስተላለፍ መቻል፤የነገ ዕጣ ፈንታችን ለመወሰን አስተዋጽኦው የላቀ መሆኑ አያጠያይቅም። ቀጣይ የሀገር ግንባታ ራዕያችንን ጨምሮ ብሔራዊ ጥቅሞቻችንን በምንገኝበት የምስራቅ አፍሪካ ቀጠናና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስከበር እንዲያስችለን ፤እውነተኛ ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን መገንባትና ፍጹም በማይነጣጠል ወንድማማችነት በአንድነት መቆም የሚገባን መሆኑን በታሪካችን የተመለከትነው የጋራ ጥንካሬያችን ምሳሌያችን ነው። ዘመናትን የዘለቀውን በመከባበር ፣ በአብሮነትና በወንድማማችነት ጽኑ መሠረት ላይ የቆመውን በዓለም የተመሰከረለትን ኢትዮጵያዊ አንድነት ጠብቀን ከማስቀጠል ውጪ ለሁላችን የሚሆን ሁለተኛ ምርጫ ፈጽሞ ሊኖረን እንደማይችል ለሁላችንም ግልጽ በመሆኑ መሰባሰባችን ተጽዕኗችንን በይበልጥ ከፍ የሚያደርገው ይሆናል።

አሁን በምንገኝበት ወቅት እንደ ሀገር፣ ከውስጥና ከውጭ በርካታ ሕብረ-ብሔራዊ አንድነታችንን ፣ ዘመናትን የተሻገረ ወንድማዊ አብሮነታችንን የሚገዳደር ፈተና ተጋርጦብናል። የእርስ በርስ ጦርነትን ጨምሮ በርካታ ማኅበራዊ ፖለቲካዊና የገበያ ውንብድና እንዲሁም አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪን ያካተተ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ለሰላም እጦት መንስኤ ከመሆኑም ባለፈ የዜጎችን ሕይወት እያከበደውም መሆኑም ይስተዋላል ።ሀገር ከውስጥም ከውጭም በሚሰነዘርባት ልዩ ልዩ ቀውስ የሚፈጥር ሁኔታ ውስጥ እያለፈች ባለችበት በዚህ ጊዜ፤ እያንዳንዱ ሀገሩን የሚወድ ዜጋ የእለት -ዕለት ተግባሮቹን በሚያከናውንበት ወቅት ሁሉ በተጓዳኝ ለሰላም የሚያበረክተው አስተዋጽኦ በሁሉም ዘንድ በፍጹም ቸል ልባል የሚገባው አይሆንም።

የሀገርን ሁለንተናዊ ሰላምና መረጋጋት የሚሻ የትኛውም የዲጂታልና የሳይበር ሚዲያ የመረጃ መለዋወጫ አማራጭ ተጠቃሚ ሁሉ፤በየደረጃው ያልተጣራና ሀሰተኛ ግጭት አባባሽ መልዕክት ከማጋራት በመቆጠብ የመፍትሔ አካል መሆን የሚጠበቅበት ይሆናል።

በኢትዮጵያ አሁናዊ ተጨባጭ ሁኔታ፣ መንግሥት ሰላምን ለማረጋገጥ በየደረጃው ከሚወስዳቸው እርምጃዎች በተጓዳኝ የሃይማኖት ተቋማት ፣ የማኅበረሰብ አንቂዎች ፣ፖለቲከኞች ፣ሊህቃን፣በየደረጃው የሚገኙ የትምህርት ተቋማት ፣ የሀገር ሽማግሌዎች ፣መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት እንዲሁም የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ሰላም ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ዜጎችና ልዩ ልዩ አደረጃጀቶች የመፍትሔ አካል ሆነው የየድርሻቸውን ማኅበራዊ ኃላፊነት በአግባቡ በመወጣት የሰላም ሂደቱን ሊደግፉ እንደሚገባ በበርካቶች እየተጠየቀ የሚገኝ መሆኑ ይታወቃል።

ከሕዝብ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የሚኖራቸው ፖለቲከኞች፣ የኪነጥበብ ሰዎች፣ ማኅበራዊ አንቂዎችና ሌሎችም አካላት ፤ በቀውስ ወቅት የሚደረጉ የተግባቦት ባህሪያትን ማዕከል ባደረገ መልኩ በመንቀሳቀስ ግጭት ከሚያባብሱ ድርጊቶች ተቆጥበው ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት መቻል ለሀገር ሁለንተናዊ መረጋጋት አስተዋጽኦ የጎላ ነው።

በበርካታ ሀገራትና በዓለም ላይ፤ ግጭቶች ተወግደው ሰላምና እርቅን ለማስፈን እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች በሙሉ የአሳታፊነት ውስንነት ስለሚገጥማቸውና እያንዳንዱ ግለሰብ ለአካባቢው፣ ለሀገሩና ለዓለም ሁለንተናዊ ሰላም በሚፈለገው ልክ የድርሻውን ማህበራዊ ኃላፊነት መወጣት ባለመቻሉ ሳቢያ አንጻራራዊ ሰላም እንጂ ፋይዳው የላቀ ዘላቂ ሰላም በዓለም ላይ ለማስፈን አልተቻለም ።

አንደኛውና ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በሰላም ድርድር መቋጨቱን ተከትሎ፣ ሀገራችንን ጨምሮ በበርካታ የዓለም ሀገራት ቁጥራቸው በሚፈለገው ልክ ባይሆንም የሰላምን ሁለንተናዊ ፋይዳና አስፈላጊነት በሚመለከት የሚያስተምሩ፣የሚጽፉና ጊዜያቸውን ለዚህ የተቀደሰ ዓላማ አሁንም ሰጥተው የሚወተውቱ ግለሰቦችና ገለልተኛ ተቋማት እንዳሉ ይታወቃል።

በዓለም ላይ እንደ አብነት ከሚጠቀሱ ስለ-ሰላም የበኩላቸውን የላቀ አስተዋጽኦ ካበረከቱ ግለሰቦች መካከል በፈረንጆች 1867 ፤ልዩ ልዩ ጦር መሳሪያዎችንና የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ግድቦችን ለመስራት የሚያገለግል ዳይናማይት የተባለ ንጥረ ነገርን ጨምሮ በርካታ የሳይንስና ምርምር የተዋጣላቸው ሥራዎችን ለዓለም ያበረከተው አልፈርድ በርንሃርድ ኖቤል አንዱ ነው። ይህ የሲውዲን ዜግነት ያለው የኬሚካል ምንድስና ጠበብት፤ እሱ ለዓለም ባበረከተው ንጥረ ነገር በተሰራ የጦር መሳሪያ፤ በዓለም ላይ በተደረጉ ግጭቶች ሳቢያ ላጋጠመ የሰው ሕይወት ጥፋት፣የአካል ጉዳትና የንብረት ወድመት ሁሉ ከልብ በመጸጸት ብዙሃንን የሚያስተምር ልዩ ልዩ የካሳ እርምጃዎችን ወስዷል።

ከነዚህም እርሱ ደረጃ በደረጃ ከወሰዳቸው የማካካሻ ርምጃዎች መካከል በዋናነት የሚጠቀሱት ዕድሜ ዘመኑን በሙሉ ልዩ ልዩ የጤና ዕክል የገጠማቸው 355 ሕሙማን ግዜና የሚያስፈልጋቸውን አሟልቶ መንከባከብን ጨምሮ አጠቃላይ ዳይናማይት ከተሰኘው ንጥረ ነገር ሽያጭ የተገኘውን ገንዘብ በዓለም ላይ በሁሉም ረገድ ሰላም እንዲሰፍን፤ ልዩ ልዩ ስኬታማ አስተዋጽኦዎችን እያበረከቱ የሚገኙ ግለሰቦችን ለማበረታታት የሚያስችል የኖቤል ሽልማት የተሰኘ ድርጅት መመስረት ችሏል።

ሲውዲናዊው አልፈርድ እንደ ግለሰብ ለሚገኝበት የአውሮፓ አህጉር ፣ለሚኖርበት አካባቢና ሀገር ፣ ቀጠናና ዓለም ሁለንተናዊ ሰላም መረጋገጥ የበደል ካሳን ጨምሮ አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎችን ጨርሶ በማሟላትና ተገቢ የሰላም ዋጋዎችን ከጥቅም ስሌት በጸዳ መልኩ ጨርሶ መክፈል የቻለ የድርሻውን ማኅበራዊ ኃላፊነት መወጣት እንደሚችል በተግባር ሆኖ ያሳየ የዘመኑ ጀግና የሰላም አምባሳደርም ጭምር ነበር። ኬሚስቱ አልፈርድ በዓለም ላይ ስለ ሰላም በጎ ተጽዕኗቸውን ያኖሩ የሰላም አምባሳደሮች መታየት መንስኤ የነበረ፤ አሁንም ምሳሌነቱ ከመቃብር-በላይ ከፍ ብሎ የሚነገርለት እንደመሆኑ ሁሉ ስለሀገራችን ሰላም መሆን ከአርአያነቱ ልንማር የተገባን ምሳሌ የሚሆን የላቀ አስተሳሰብና ስብዕና ባለቤትም ነው።

በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተውን ጦርነት አላስፈላጊነት በመረዳት ኢትዮጵያውያን ወደ ራሳቸው ወደ ውስጥ ተመልክተው፤ የፖለቲካ ልዩነቶቻቸውን በአፍሪካ ኅብረት ማዕቀፍ ውስጥ ለመፍታት ደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተጓዙ መሆናቸውም እንዲሁ አይዘነጋም። “ልዩነቶችን በሰለጠነ ንግግር መፍታት የምንችል እኛም የአባቶቻችን ልጆች ነን” በሚል መርህ ፤ ለሰላም መቼም ረፍዶ አያውቅምና ደቡብ አፍሪካ ፕርቶሪያ ላይ ለአፍሪካዊ መፍትሔ ቅድሚያ በሰጠ መልኩ በሰላማዊ ንግግር ችግሩን መፍታት መቻሉ የቅርብ ግዜ ትውስታችንም ጨምር ነው።

የሰላም ድርድሩን እዚሁ በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር በተሳካ ሁኔታ መቋጨት መቻሉ ፤በአፍሪካውያን ዘንድ ለአህጉሩ ሁሉን አቀፍ ችግሮች፤ አህጉራዊ መፍትሔ ማመንጨት የሚቻል መሆኑን ጨምሮ በመሰል የጦርነት አዙሪት ውስጥ እያለፉ ላሉ ሀገራት በቂ ትምህርት የሚሰጥና ምሳሌ በሚሆን መልኩ የተደረገ መሆኑም በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በተለየ ትኩረት በወቅቱ እንዲዘገብ አድርጎታል።

ኢትዮጵያውያን ዓድዋ ላይ ዘምተው ጣሊያንን ድል ማድረጋቸውን ተከትሎ ኢትዮጵያኒዝም የሚል ስያሜ በሰጡት የፀረ-ቅኝ ግዛት ትግል በርካታ የአፍሪካ ሀገራት፤ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የዘመን አቆጣጠር በ1960 ነጻ መውጣት መቻላቸውን የዓለም ታሪክ ያስረዳል። አሁን በምንገኝበት ወቅት የአፍሪካ ኅብረት በፈረንጆች 2063 ፣የጥይት ድምጽ የማይሰማበትን አፍሪካ መፍጠር እንዲቻል በአህጉር ደረጃ ይፋ የተደረገውን ግብ ለማሳካት እንዲቻል፤ ኢትዮጵያውያን በፕሪቶሪያ ልዩነቶቻቸውን በእውነተኛ ወንድማማችነት ላይ መሰረት አድርገው የፈቱበት መንገድ በተጨባጭ ልምድና ተሞክሮ የሚሆን ነው በበርካቶች እየተባለም ይገኛል።

የኢትዮጵያ መንግሥት፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ በፕሪቶሪያ ከሕወሓት ጋር ያደረገውን ፍሬያማ የሰላም ንግግር ተከትሎ፤ ኦነግ ሸኔ ተብሎ ከሚጠራው ኃይል ጋር ተመሳሳይ የሰላም ንግግሮችን በታንዛኒያ ማስጀመሩም ይታወሳል። ሁለቱም ጥረቶች ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ መንግሥት የድርሻውን ኃላፊነት በተጨባጭ እየተወጣ የሚገኝ መሆኑን የሚያመላክቱም ናቸው!

እንደ መውጫ

በሀገራዊ ምክክርና የእርቀ-ሰላም ኮሚሽን አማካኝነት፤ ብሔራዊ ምክክር በሚያሻቸው አጀንዳዎች ሁሉ ላይ መክሮ የማያሻማ ውሳኔ ማስተላለፍ መቻል፤ የሀገሪቱን የወደፊት በየደረጃው የሚገለጽ ሁለንተናዊ ዕድገትን ጨምሮ በምትገኝበት ቀጠናና አህጉር እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጽዕኖዋ በሚፈለገው ልክ መጎልበት እንዲችል ፋይዳው የላቀ ነው። ይህ በእንዲህ እንዳለም ከሀገር አቀፍ ምክክሩ ሂደት የሚገኘው አካታች የመፍትሔ ሀሳብ ለሕዝቦች የጋራ ዕጣ ፋንታ መስመር፣ ለሀገሪቱ የህልውና ቀጣይነት፣ ግዛታዊና የሕዝቦቿ በወንድማማችነት ላይ የተመሠረተ አንድነት መጠበቅ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የላቀ እንደመሆኑ ዜጎች በየአካባቢው የሀገራዊ ምክክር እና የእርቀ-ሰላም ኮሚሽን አባላት የምክክር ሂደቱን ለማሳለጥ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ያልተቆጠበ ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል።

በጋዜጠኛና ሲኒየር የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያ ላንዱዘር አሥራት

አዲስ ዘመን መስከረም 16 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You