ሊቢያ ከጎርፍ አደጋው ጋር በተያያዘ የዴርና ከተማ ከንቲባን አሰረች

በከፍተኛ ጎርፍ ተጥለቅልቃ አሰቃቂ አደጋ ያስተናገደችው የሊቢያዋ ከተማ ዴርና ከንቲባ ከክስተቱ ጋር በተገናኘ መታሰራቸውን ታውቋል።

አብዱልመናን አል ጋሃኣቲ የተባሉት ከንቲባ ከሳምንታት በበፊት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በተቀጠፉበት የጎርፍ አደጋ ምክንያት ክስ ከተመስረተባቸው በርካታ የመንግሥት ባለስልጣናት አንዱ ናቸው።

ባለፈው ሳምንት በክስተቱ የተቆጡ የዴርና ከተማ ነዋሪዎች ባደረጉት ተቃውሞ የከንቲባውን ቤት እሳት ለቀውበታል።

በትሪፖሊ የሚገኘው የሀገሪቱ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤት ትላንት ባወጣው መግለጫ ባለስልጣናቱ በጎርፍ የፈረሰውን “የአካባቢውን ግድብ መሠረተ ልማት የማስተዳደር ኃላፊነት ነበረባቸው” ብሏል።

በዚህም ሳቢያ የወንጀል ክስ እንደከፈተባቸው ጠቅሷል። ከንቲባ አል አል ጋሃኣቲን ጨምሮ የተወሰኑ ባለሥልጣናት ከፍርድ ሂደቱ ቀደም ብሎ ታስረዋል።

የጠቅላይ አቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤቱ በመግለጫው በዴርና ከተማ ከፍተኛ ጎርፍ እንዲከሰት ምክንያት ለሆነው የግድቡ መፍረስ ተጠያቂ ያደረገ ሲሆን ግድቡን ለመጠገን የቀረበውን ገንዘብ ተገቢ ባልሆነ መንገድ አስተዳድረዋል ብሏል።

የከንቲባው ጽሕፈት ቤትም ከጎርፍ ጋር በተያያዘ በርካቶች እንዲሞቱና ሊቢያም የኢኮኖሚ ኪሳራ እንዲገጥማት ባደረገው አደጋ ባለሥልጣናት ቀድመው ርምጃ ለመውስድ ቸልተኛ ሆነዋል ብሏል።

ከንቲባ አብዱልመናን አል ጋሃኣቲ ሥልጣንን ያለአግባብ በመጠቀም ሌላ ክስ እንደሚጠብቃቸውም ተነግሯል። ሊቢያ በምሥራቅና ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ ተቀናቃኝ ኃይሎች አስተዳደር ስር የምትገኝ ሀገር ናት።

በትሪፖሊ የሚገኘው ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የምዕራብ የሀገሪቱን ክፍል እንደመያዙ በምሥራቁ ያሉ ተጠርጣሪዎች ለመያዝ ትዕዛዝ ምን ያህል ርቀት እንደሚጓዝ ግልጽ አይደለም።

ባለፈው እሁድ የምሥራቁ የሀገሪቱ መንግሥት በጎርፍ አደጋው እንደሞቱ የተረጋገጡ ሰዎች ቁጥር 3 ሺህ 868 መደረሱን ገልጿል።

የጠቅላይ አቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤት ከአደጋው ጋር በተያያዘ እየተደረገ ያለው ምርምራ እንደቀጠለ ገልጾ ሌሎች ተጨማሪ የሚታሰሩ ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ አመላክቷል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን መስከረም 16/2026

Recommended For You