አዲሱ የኢትዮጵያዊያን ዓመት ባስቆጠራቸው ሁለት ሳምንታት ሁለት የዓለም ክብረወሰኖችን ለኢትዮጵያዊያን በማስረከብ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ የተሳካ ዓመት መሆኑን ከወዲሁ በማስመስከር ላይ ይገኛል:: የሴቶች የ5ሺ ሜትር የዓለም ክብረወሰን ወደ ኢትዮጵያ በተመለሰ በቀናት ልዩነት የሴቶች ማራቶን ፈጣን ሰዓት መመዝገቡ ለበርካቶች አግራሞትን የሚጭር ስለመሆኑ አያጠያይቅም:: የዓለም ድንቃድንቅ ሁነቶችን በመመዝገብ የሚታወቀው ጊነስ ቡክም ይህንኑ የኢትዮጵያዊቷን አትሌት ትዕግስት አሰፋ ገድል በክብር ገጹ አስፍሯል::
የበርሊን ማራቶን እና የማራቶን ክብረወሰን ዓመታዊ ቀጠሮ ያላቸው ይመስላል:: በዓለም አትሌቲክስ የፕላቲኒየም ደረጃ ከተሰጣቸው ስድስት የጎዳና ሩጫዎች አንዱ የሆነው ይህ ማራቶን፤ የዓለም ክብረወሰንን በተደጋጋሚ ለመስበር የተመቸ ነው:: ይህንንም ተከትሎ በስፖርቱ ድንቅ አቋም ላይ የሚገኙ አትሌቶች ይመርጡታል:: ዘንድሮ ለ49ኛ ጊዜ በተካሄደው የበርሊን ማራቶን ውድድር በኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትዕግስት አሰፋ ያልተጠበቀ አዲስ የማራቶን የዓለም ክብረወሰን ተመዝግባል::
ለየትኛውም የዓለማችን ድንቅ አትሌት የዓለም ክብረወሰን ማሻሻል የምን ጊዜም ህልምና በስፖርቱ የደረሰበት የልዕልና ደረጃ ማሳያ ነው:: ትዕግስት ባለፈው እሁድ ያስመዘገበችው የማራቶን ክብረወሰን ደግሞ በፅናት የተገኘ በከባዱ ማራቶን የደረሰችበት ልዕልና ማሳያ ነው::
አዲሷ የርቀቱ ንግስት ከረጅም ጊዜ የህክምና ክትትል በኋላ የመጀመሪያ ማራቶኗን በሳውዲ አረቢያ ያደረገች ሲሆን፣ አትሌቷ በወቅቱ ያስመዘገበችው 2:34:01 የሆነ ሰዓት ነበር:: ባለፈው ዓመት ደግሞ በዚሁ የበርሊን ማራቶን 2:15:37 በሆነ ሰዓት በመሮጥ የውድድሩን
ክብረወሰን እንዲሁም የዓለም ሁለኛውንና የኢትዮጵያ የርቀቱ ክብረወሰን የሆነውን ፈጣን ሰዓት ማስመዝገብ ችላ ነበር:: አትሌቷ በዚህ ወቅት የገባችበት ሰዓት ቀድሞ ከነበራት ወደ 19 የሚሆኑ ደቂቃዎችን ያሻሻለችበት መሆኑ በርቀቱ ያላትን የወደፊት ተስፋ በግልጽ ያመላከተ ነበር:: ከዓመት በኋላ ዳግም በሮጠችበት በዚሁ ውድድር ላይም ይህንኑ ተስፋ እውን በማድረግ ቀድሞ በነበራት ሰዓት ወደ 4 ደቂቃ በማሻሻል ብቃቷን እንዲሁም በርቀቱ የወደፊት ተጽእኖ ፈጣሪነቷን ማስመስከር ችላለች::
ትዕግስት ዓለምን ያስደነቀውን ያልተጠበቀ ክብረወሰን ካስመዘገበችበት የእሁዱ ከውድድሩ በኋላ ‹‹ይህ ውጤት ባለፉት ዓመታት ጠንክሮ በመስራት የተገኘ ነው:: የማራቶን ክብረወሰንን መስበር ብፈልግም እንዲህ ይሆናል ብዬ ግን አልጠበቅኩም ነበር›› ስትል አስተያየቷን መስጠቷን ዘ ጋርዲያን በድረገጹ አስነብቧል:: የ26 ዓመቷ አትሌት በእርግጥም ክብረወሰኑን መስበሯ እንዳስገረማት ከሁኔታዋ ለመረዳት ይቻላል:: እአአ በ2016 የሪዮ ኦሊምፒክ በ800 ሜትር ሀገሯን የወከለችው ትዕግስት በተያዘው ዓመት መጨረሻ በሚካሄደው የፓሪሱ ኦሊምፒክ ላይ የኢትዮጵያን የማራቶን ቡድኑን እንደምትመራ ከወዲሁ አረጋግጣለች:: ከዚህ ጋር ተያይዞም ከስካይ ኒውስ ጋር በነበራት ቆይታ ‹‹ውሳኔው የኦሊምፒክ ኮሚቴው ቢሆንም በዚህ ውድድር ግን ወሳኝ ውጤት ማስመዝገብ ችያለሁ›› ስትል ተናግራለች::
በሆለታ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በ100 ሜትር እና 200 ሜትር ርቀቶች በመሳተፍ የአትሌቲክስ ህይወትን የተቀላቀለችው አትሌቷ፤ በ2003 ዓም የኦሮሚያ ፖሊስ አትሌትክስ ክለብን ተቀላቀለች:: ይህም እአአ በ2012 በሱዳን በተካሄደው የምስራቅ አፍሪካ ቻምፒዮና በ400 ሜትር ሃገሯን እንድትወክል ሲያደርጋት ውድድሩን ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ነበር ያጠናቀቀችው:: በዚያው ዓመት በአፍሪካ ቤኒን ላይ በተደረገው የአፍሪካ ቻምፒዮና ተፎካካሪ ሆናለች:: በቀጣዩ ዓመት በሞርሺየስ የአፍሪካ ወጣቶች ቻምፒዮና በ400 ሜትር እና 800ሜትር ርቀቶች በመሳተፍ ለሜዳሊያ በቅታለች:: ይህ ችሎታዋ ሃገሯን በተደጋጋሚ እንድትወክል ሲያበቃት እአአ በ2016ቱ የሪዮ ኦሊምፒክ ላይም ለኢትዮጵያ ተሰልፋለች::
ይሁንና አትሌቷ እአአ ከ2014 አንስቶ በኦሊምፒክ ተሳታፊ እስከሆነችበት ዓመት ድረስ ከተረከዝ ጅማት ህመም ጋር ጠንካራ ትግል በማድረግ ነበር ያሳለፈችው:: ይኸው ጉዳቷ እየጠነከረ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞም የህክምና ባለሙያዎች ሩጫን እንድታቆም ነገሯት፤ ይሁንና ከአንድ ዓመት ማገገም በኋላ በድጋሚ ወደ ውድድር ተመልሳ ነበር:: ከህምሙ ሙሉ ለሙሉ ማገገም አለመቻሏም እአአ በ2019 የቫሌንሺያ ግማሽ ማራቶንን እንዳጠናቀቀች በድጋፍ ወደ ህክምና ስፍራ እንድትሄድ አድርጓታል:: በወቅቱ በክራንች እየታገዘች በሄደችባቸው የአውሮፓ የህክምና ማዕከላትም በተመሳሳ ሩጫን እንድታቆም ቢነገራትም የጽናት ተምሳሌት የሆነችው አትሌት ግን ከህመሟ አገግማ ወደ ቀድሞ አቋሟ ለመመለስ ሳትሰለች በመስራት በጎዳና ላይ ሩጫዎች ወደ አትሌቲክስ ህይወቷ ለመመለስ ችላለች::
በሁለት ዓመት ውስጥም የማራቶን አትሌት በመሆን ከማሸነፍ ባለፈ የዓለም ክብረወሰን በመሰባበር ጭምር የዓለም ቁጥር አንዷ አትሌት መሆኗን አረጋግጣለች:: በእርግጥም ያለፉት ዓመታት የማገገሚያ ብቻም ሳይሆኑ ለዛሬ ሲያዘጋጇት የቆዩ ስለመሆኑ የበርሊን ማራቶንን የመጨረሻዋን መስመር ስትረግጥ ያሳየችው ሁኔታ ይናገራል::
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መስከረም 15/2016