በዩኔስኮ የተመዘገቡ ቅርሶችና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸው

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ኢትዮጵያ ከወትሮ ለየት ባለ መልኩ ረዘም ያለ የዝናብ ወራትን ማስተናግዷ ይታወቃል:: የክረምቱ ወራት ደመናው፣ ከባዱ ዝናብና ጭጋጉ አልፎ መስከረም በመጥባቱ ሕዝቡ የፀሐይን ሙቀት ማጣጣም ጀምሯል::

ወርሃ መስከረም ደግሞ በባህሪው በርካታ ተስፋዎችን ሰንቆ ከተፍ የሚል እንደመሆኑ የክረምቱን ማለፍና የመስከረምን መጥባት ተከትሎ የሚከወኑ የአደባባይ በዓላት ወሩን ልዩ ያደርጉታል:: ወሩ በከፍተኛ ድምቀት የሚከበሩት የመስቀል ደመራ እና የኢሬቻ በዓል ኢትዮጵያን የቱሪስቶች መዳረሻ ከሚያደርጋት ወራት መካከል ዋናው እንደመሆኑ ብዙዎችም በናፍቆት የሚጠባበቁት ጭምር ነው::

ከሰሞኑን ደግሞ በሳዑዲ አረቢያ ሪያድ በተካሔደው 45ኛው የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በተካሔደው የዓለም ቅርስ ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ ሁለት የቱሪስት መዳረሻዎችን በዓለም ቅርስነት ማስመዝገቧን የኢፌዴሪ የቱሪዝም ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል:: እነዚህ በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ ሁለቱ ቅርሶች የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር እና የባሌ ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ መሆናቸውም ተጠቅሷል::

ኢትዮጵያ ከዛ በፊት ከደርዘን በላይ የሆኑ ተፈጥሯዊም ባህላዊም የሆኑ ቅርሶችን ያስመዘገበች ሀገር መሆኗ የሚታወቅ ነው:: የቅርቦቹን ሁለቱን ቅርሶች ሳያካትት በዓለም ቅርስነት ያመዘገበቻቸው ቅርሶች የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የሰሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ፣ የፋሲል ግንብ፣ የአክሱም ሃውልት፣ የታችኛው አዋሽ ሸለቆ፣ የጢያ ትክል ድንጋይ፣ የታችኛው ኦሞ ሸለቆ የአርኪዮሎጂ ሥፍራ፣ የሐረር ጀጎል ጥንታዊ ከተማ፣ የኮንሶ መልካምድር በእርከን የታጠሩ መንደሮች፣ የመስቀል በዓል፣ የፍቼ ጨምባላላ በዓል፣ የገዳ ሥርዓት እና የጥምቀት በዓል ናቸው::

እንደሚታወቀው ከሁለት ሳምንት ቀደም ብሎ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገቡ ውሳኔ የተላለፈላቸው ቅርሶች በደቡብ ክልል የሚገኘው የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር እና በኦሮሚያ ክልል የሚገኘው የባሌ ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ናቸው:: እነዚህ ሁለት ቅርሶች ኢትዮጵያ በዓለም ቅርስነት ያስመዘገበቻቸውን ቅርሶች ቁጥር ወደ አስራ አምስት ከፍ ያደርጉታል::

እርግጥ ነው የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የጌዴኦ ባሕላዊ መልክዓ ምድርን እና የባሌ ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክን በቅርስነት ያስመዘገበ እንደሆነ የሚታወቅ ነው፤ ለምሳሌ የተመዘገበው የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር፣ የመሬት አያያዝ፣ ታሪካዊ ቅርሶች፣ ትክል ድንጋዮች የዋሻ ላይ ጽሑፎች እና በባህላዊ መንገድ ብቻ የሚተዳደሩ ደኖች እንደሚገኙበት ከጌዴኦ ዞን ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል:: በተመሳሳይ በ1962 ዓ.ም መመስረቱ የሚነገርለት የባሌ ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ወደ 16 ዓመታት ያህል ማስቆጠሩም ተጠቁሟል::

ኢትዮጵያ በቅርቡ ያስመዘገበቻቸውን እነዚህን ሁለት ቅርሶች ጨምሮ ቀደም ሲል የተመዘገቡ ቅርሶች ያላቸው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ምንድን ነው ስንል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህር የሆኑት ዶክተር ብርሃኑ ደኑን በጠየቅናቸው ጊዜ እንደተናገሩት፤ በተለያየ ጊዜ የሚመዘገበውን ቅርስ ከዘላቂ የልማት ግቦች ጋር አያይዞ ማየቱ ተገቢነት ያለው ነው:: የአካባቢ ጥበቃ እንደሚገባ መከናወን እንዳለበትም አመላካች ነው::

ዘላቂ የልማት ግቦችንና ዘላቂ እድገትን ለማስገኘት በተለይም ታዳጊ ሀገራት አካባቢያቸውን እንደሚገባ መጠበቅና መንከባከብ እንዳለባቸው የሚያሳይ ነው የሚሉት ዶክተር ብርሃኑ፣ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ አካባቢን በደን ለመሸፈን እየተደረገ ያለው ጥረት አበረታች ሥራ ነው ብለዋል:: ለአብነት ሲጥቅሱ እንዳሉትም፤ ባለታሪክ ሕንጻዎችን እና የተፈጥሮ አካባቢዎች ማለትም ሰሞኑን እንደተመዘገቡ ሁለቱ የሚዳሰሱ ቅርሶች ዓይነት በዓለም ቅርስነት የመመዘገቡ ነገር በርካታ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አለው::

እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ ቅርሱ አንዴ በዓለም ቅርስነት ከተመዘገበ በዛ አካባቢ ያለውን የዱር እንስሳትን ሆነ በአካባቢው ያለውን ደን እንደቀደመው ሁሉ መጨፍጨፍ አይቻልም:: ለዚህም ደግሞ በየጊዜው ቁጥጥር ይደረጋል:: ኢንተርናሽናል ኮሚቴ ኢኮሎጂካል ሳይት ማኔጅመንት (International Committee Ecological Site Management – ICEM) የሚባል በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለ ተቋም ቅርሱን ሁልጊዜ ይከታተለዋል:: ጥናትም ያደርግበታል::

ይህ ሁሉ ተደማምሮ የሚያመጣው ትልቅ ነገር ቢኖር ቱሪስቶችን ወደ አካባቢዎቹ አቅደው እንዲመጡ ነው:: ከዚህ ጋር ተያይዞ በሀገር ውስጥ ቱሪስቶችን ለመቀበል የሚደረግ እንቅስቃሴ ይኖራል:: ይህ ደግሞ ለየሰው የሥራ እድል ይከፍታል:: ለመንግሥትም ታክስ ያስገኛል:: ከዚህ በተጨማሪ የአካባቢው ነዋሪዎች በሚገባ ሕይወታቸው እንዲሻሻል ይረዳል:: ይህ ሲሆን በኢኮኖሚው ውስጥ መነቃቃትንና መነሳሳትን የመፍጠር እድል ይኖረዋል::

የምጣኔ ሀብት ባለሙያ አቶ ወሰንሰገድ አሰፋ በበኩላቸው፤ በተለይም ሰሞኑን በዩኔስኮ ውሳኔ መሠረት የተካሔደው የቅርሶቹ መመዝገብ ለሀገር ውስጥ ቱሪዝም የዚያን ያህል ለውጥ ላያመጣ ይችላል ይላሉ:: ይሁንና የእነዚህ ቅርሶች መመዝገብ በትክክለኛ መረጃ ለሚንቀሳቀሱ ለአደጉ ሀገራት ቱሪስቶች ወሳኝ በመሆኑ ወደ ሀገራችን እንደመጡ የሚያደርግ ነው::

የውጭ ሀገራት ቱሪስቶች በዩኔስኮ የተመዘገበውን ቦታ ማየት ይመርጣሉ:: ልክ ሰው መድኃኒት ገዝቶ መጠቀም የሚፈልገው በመድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ሲረጋገጥ እንደሆነው ሁሉ አንድ ቱሪስትም ለመጎብኘት ቅድሚያ የሚሰጠው ዩኔስኮ ራሱ ያረጋገጠውን ቦታ ነው:: ዩኔስኮ የኤክስፐርቶች ቡድን በመሆኑ በዚህ እውቅ ቡድን እውቅና ማግኘታችን ደግሞ የውጭ ሀገር ቱሪስቶችን ወደ ሀገራችን እንዲመጡ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር በመሆኑ ውስንነት ያለብንን የውጭ ምንዛሬ ማግኘት እንደሚቻል ተናግረዋል:: የተለያዩ ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የውጭ የቱሪዝም ኢንቨስትመንት በሰፊው የተሳለጠ እንዲሆን እንደሚያደርግም ጠቅሰው፤ በዚህ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን ማሳደግ እንደሚቻል አመልክተዋል::

ከቱሪስቶች ጋር ተያይዘው የሚመጡ በርካታ ጠቀሜታዎች አሉ የሚሉት ደግሞ ዶክተር ብርሃኑ ሲሆኑ፣ ከዚህ መካከል አንዱ የሕዝብ ለሕዝብ ትውውቅ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል:: ይህ ሲሆን የአካባቢው ባህል እንዲታወቅ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል:: ለአብነትም ኢትዮጵያን በተመለከተ በአንዳንድ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ላይ የሚነገሩ አግባብነት የሌላቸው አገላለጾች እና አሉታዊ ትርክቶችን በማስወገድ የዓለም አቀፍ ወይም የውጭ ኢንቨስትመንት ስበትን እንዲበረታታ እና እንዲጠናከር ያደርጋል ብለዋል::

እንደ እርሳቸው አባባል፤ ቱሪስቶችም ሆነ ኢንቨስተሮች ካፒታላቸውን ማፍሰስ የሚችሉት ስለ አንዲት ሀገር ለምነትና መልካምነት ብሎም ስለሕዝቧ ሥነ ምግባር መሟላት አጢነው ነው:: ከዚህ የተነሳ አንዲት ሀገር ባስመዘገበችው ቅርስ የተነሳ በቱሪስቶች የመጎብኘቷ ጉዳይ የማይቀር በመሆኑ ከመጎበኘቷ ጋር ተያይዞ የሚመጣው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ከፍ ያለ ነው::

በሌላ በኩል ከቱሪስቶች የምናገኘው የውጭ ምንዛሬ በመኖሩ እኛ ያለንን ውስን የውጭ ምንዛሬ ሊያሰፋልን ይችላል የሚሉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው፣ ከዚህ በተጨማሪ የሚመጡ ቱሪስቶች የተለያየ ሙያ ባለቤት ስለሚሆኑ የቴክኖሎጂ ሽግግርም ሊኖር ይችላል ብለዋል::

ዶክተር ብርሃኑ እንደሚሉት፤ በእኛ በኩል ግን የተፈጠረውን እድል በአግባቡ ለመጠቀም ያስችለን ዘንድ ማድረግ የሚገቡን ጉዳዮች መኖራቸው የማይቀር ነው:: ለምሳሌ ቱሪስቶችን ለመቀበል የሚደረጉ ሥራዎች አሉ:: ለአብነትም በቅርቡ በተለያዩ ቦታዎች የተሰሩ ሪዞርቶች አሉ:: እነዛ ሪዞርቶች በመንግሥት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶባቸው የተሰሩ በመሆናቸው በጣም አበረታች ናቸው:: በተመሳሳይ በእነርሱ ዓይነት የሚሰሩ ሪዞርቶች መበራከት ይኖርባቸዋል:: ምክንያቱም የሚከናወኑ መሠረተ ልማቶችም ሆኑ ሆቴሎች ምቹ መሆናቸው ቱሪስቶችን ለመሳብም ሆነ ለተከታታይ ቀናት ይዞ ለማቆየት ወሳኝ ናቸው:: ይህ ሲሆን የገቢ ማግኛ መንገዳችን ከፍ ይላል:: ወደ ውጭ ከምንልከው እቃ ጎን ለጎን ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባ ቱሪስት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ሊያስገኝ ይችላል:: ይህ ትልቅ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ነው::

በሌላ በኩል የአካባቢ ጥበቃ ለዘላቂ እድገት በጣም ወሳኝነት አለው በሚል አጽንኦት የሚሰጡት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው፣ የአካባቢ ደን ከተጠበቀ ዝናብ ሲዘንብ ጎርፍ እያጥለቀለቀ የሚያስቸግረን ሁኔታ ይወገዳል:: የዝናብ ማጣትም ሆነ ድርቅ ይወገዳል:: በዚህም በኩል በጣም ሊጠቅም ስለሚችል ነው በዓለም አቀፍ ደረጃ የአካባቢ ጥበቃ እንዲበረታታ የሚደረገው:: ስለዚህ ዩኔስኮ የእኛን አካባቢ እስካሁን በዓለም ቅርስነት ከመዘገበው በተጨማሪ የጌዴኦ ባህላዊ ተፈጥሯዊ የእርሻና መልከዓ ምድር እና የባሌ ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ በቅርስነት መመዝገቡ ከፍተኛ ለሆነ ለዘለቄታዊ የኢኮኖሚ እድገት ትልቅ እገዛ የሚሰጥ ነው ብለዋል::

ነገር ግን ይላሉ ዶክተር ብርሃኑ፣ ከዚህ ጋር መታየት ያለበት ቱሪስቶች ስለመጡ ብቻ የኢኮኖሚ እድገት ይኖራል ማለት ሳይሆን ቅርሱ የተመዘገበባቸው አካባቢዎች በአግባቡ መተዳደር መቻል አለባቸው:: አመራሩ፣ አስተዳደሩ ሁልጊዜ ንቁ ከመሆን በተጨማሪ አካባቢው በባለሙያ እንክብካቤ ሊደረግበት እንደሚገባ አስረድተዋል::

ዶክተር ብርሃኑ እንደሚሉት፤ የአካባቢው ነዋሪ በሚገባ የአካባቢው ተጠቃሚ ለመሆን ቅርሱን በሚገባ ሊንከባከበው ይገባል:: አስተዳደሩም እንዲሁ ሊያደርግ ያስፈልጋል:: ጥቅሙ ለራስ ነውና ወደ አካባቢው የሚመጣውን ቱሪስት በተገቢው መልኩ ማየት የተገባ ነው:: ከዚህ ጎን ለጎንም በሚመለከተው አካል የአካባቢው ኅብረተሰብ ግንዛቤ እንዲያገኝ ማድረግ መልካም ነው:: ስለጥቅሙም ማስረዳትም የግድ ነው:: ለምሳሌ ከቅርሱ መመዝገብ የተነሳ የአካባቢው ማኅበረሰብ ቤት በማከራየትና ሥራ በማግኘትም ጭምር ጥቂት የማይባል ጥቅም የሚያገኙት እንደሆነ በማስረዳት ጥቅሙ የራስ ጭምር መሆኑን መግለጽ ወሳኝ ነው:: እንዲህ ሲባል ግን ልማዳዊ በሆነ መንገድ ሳይሆን በዘመነ መልኩ ወጣቶችም ተደራጅተው ሥራቸውን መሥራት ይጠበቅባቸዋል::

ከቱሪዝም ኢንዱስትሪው ጋር አብረው የሚሄዱ ሥራዎች አሉ የሚሉት ደግሞ አቶ ወሰንሰገድ ናቸው:: በተለይም በመዳረሻዎቹ አካባቢዎች ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች፣ ሪዞርቶች፣ ሎጂዎችና ሌሎች መዝናኛ ሥፍራዎች መኖራቸው አሊያም መገንባታቸው ወሳኝ እንደሆነም ይናገራሉ:: ከዚህ ጎን ለጎን ባህላዊ እቃዎች የመሸጡም በእግረ መንገድ ማንነትንም የማስተዋወቅም ሁኔታ አለ:: እንኳን ከውጭ ሀገር ሰው መጥቶ ቀርቶ እኛ ኢትዮጵያውያን ካለንበት አካባቢ ወደሌላው አካባቢ ለጉዳይ ሔደን ስንመለስ በአካባቢው ያለውን ማስታወሻ ይዘን የመምጣቱ ልምዱ እንዳለን የሚታወቅ ነው:: ከዚህ አኳያ የጎብኚዎችን ፍሰት ተከትሎ እንደየጎብኚው ፍላጎት በሚደረግ ሸመታ የኢኮኖሚው እንቅስቃሴ የተነቃቃ ይሆናል:: ይህ በመሆኑ ባለሀብቱ የቱሪስቱን ፍላጎት እየተከተለ አብሮ መታሰብ ያለበትን ሁሉ በማሰብ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸውን እንቅስቃሴዎች ማድረግ እንደሚጠበቅበት ያመለክታሉ::

ልክ እንደ ዶክተር ብርሃኑ ሁሉ እርሳቸውም ለአብነት የሚጠቅሱት በቅርብ በዩኔስኮ የተመዘገቡትን ቅርሶች ነው:: ለምሳሌ የባሌ ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክን አካባቢ ቱሪስቱን ለቀናት ያህል በምቾት ሊያቆይ የሚችል ደረጃውን የጠበቀ ሆቴል ባለሀብቱ መክፈት ይጠበቅበታል፤ ይህ ለራሱ፣ ለሀገሩም ሆነ ለአካባቢው ኅብረተሰብ ሚናው የጎላ ነው:: ቀድሞ የተከፈተም ካለ ደረጃ የማሳደግ ሥራ መሥራት ይገባዋል:: ይህ እንቅስቃሴ ብቻውን የሚለካ ሳይሆን ተያይዞ የሚመጣው የኢኮኖሚ ንቅናቄ ከፍ ያለ ስለሚሆን የቅርሱ መመዝገብ በራሱ ያመጣው ከፍተኛ ድል ነው ይላሉ::

እንደ አቶ ወሰንሰገድ ገለጻ፤ የቱሪስት መዳረሻ የሆኑ አካባቢዎችም ሆኑ በቅርቡ ይህንኑ የተቀላቀሉ አካባቢዎች የተመዘገቡ ቅርሶቻቸውን በአግባቡ መጠበቅ አለባቸው:: ከመፍረስ፣ ከዘራፊዎች መጠበቅም ይገባቸዋል:: ይህን በታማኝነት ሲያደርጉ ተጠቃሚ የሚሆኑት ራሳቸው ናቸው:: በዚህ አግባብ የዘርፉ ባለሙያዎች ለአካባቢው ሕብረተሰብ ግንዛቤ ማስጨበጥ ይጠበቅባቸዋል::

ያነጋገርናቸው የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎቹ አንድ በአጽንኦት የገለጹት ነገር ቢኖር በቅርቡ የተመዘገቡትም ሆኑ ቀደም ሲል የተመዘገቡ ቅርሶች ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸው ላቅ ይል ዘንድ የሀገርም ሆነ የየአካባቢው ሰላም መሆን ትልቁን ድርሻ መያዙን ነው:: ከዚህ ጎን ለጎን ቅርሶችን ለመጎብኘት የሚመጡ ቱሪስቶችም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ጎብኝተው መሔድ ይችሉ ዘንድ ጥንቃቄ ሊደረግላቸው የግድ መሆኑን ተናግረዋል::

ዶክተር ብርሃኑ እንዳሉት፤ በየአካባቢውም ሆነ እንደ ሀገርም ሰላም ወሳኝ ነው:: በቱሪስቱ ላይ ጥቃት መፈጸምም ሆነ ረብሻ ማካሔድ እንደ አሸባሪ የሚያስቆጥር ነውና መንግሥት እዚህ ላይ ትኩረት ማድረግ ይጠበቅበታል:: ቅርሶች የዛሬው ትውልድ ብቻ ሳይሆኑ የቀጣዩም ትውልድ ጭምር ንብረት ናቸውና በአግባቡ ተጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ ማሻገርም የእኛ ኃላፊነት ነው:: ሌሎችም የራሳቸውን የሚጠብቁት በሰለጠነ መንገድ ነው:: ይህ ካልሆነ የምናገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ያሳጣናል::

የቅርሶች ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ላቅ ይል ዘንድ የሀገር ሰላም ያስፈልጋል የሚሉት ደግሞ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ወሰንሰገድ ናቸው:: እኔ እንደ ፖለቲካ ሳይንስ ተማሪነቴ መንግሥት የሁሉም ታላቅ ነው ባይ ነኝ:: በመሆኑም በሀገር ውስጥ የሚስተዋለውን የሰላም መታጣት ላይ አበክሮ መሥራት ይጠበቅበታል ብለዋል:: ለዚህ ምክንያት ደግሞ ከሰላም መታጣት የተነሳ በቅርቡ ያጋጠሙ ችግሮችን ማየትና በኢኮኖሚ በኩል የደረሰብንን ኪሳራ ማጤን ብቻ በቂ ነው የሚሉት አቶ ወሰንሰገድ፣ ከዚህ የተነሳ የሚነሳ ጥያቄዎችንም በማጤን በመነጋገርና በመወያየት ሰላም የሚመጣበትን መንገድ ለማመቻቸት መነሳሳት መልካም ነው ብለዋል::

ሰዎች ከአንድ ቦታ ወደሌላው ቦታ ያለስጋት ለመሄድ መቸገር የለባቸውም፤ ከአንድ ቦታ ወደሌላው ቦታ በመኪና መሄድ ችግር ሆኖ በአውሮፕላን እስከ መሄድ መድረስ የለበትም፤ ይህ የመጣው ከሰላም መታጣት የተነሳ በመሆኑ ሊጤን ይገባል:: መንግሥት ትልቅ ነው፤ ከዚህ የተነሳ ነገሮችን ሁሉ በሰላም ለመቋጨት ቢነሳሳ ከቱሪዝም መዳረሻዎችም የሚገኘው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው የበለጠ ላቅ ያለ ይሆናል ብለዋል::

 አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን መስከረም 15/2016

Recommended For You