የሴቶች የማራቶን ክብረወሰን ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ እጅ ገባ

ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትዕግስት አሰፋ የማራቶንን የዓለም ክብረወሰን ትናንት በርሊን ላይ ሰበረች። ባለፈው አመት በዚሁ በርሊን ማራቶን የቦታውን ክብረወሰን በማሻሻል አሸናፊ የነበረችው ትዕግስት ዘንድሮ ለሁለተኛ ተከታታይ ድል ወደ በርሊን ስትመለስ የዓለምን ክብረወሰን ትሰብራለች ብሎ የጠበቀ አልነበረም። ያምሆኖ አስደናቂዋ አትሌት ያልታሰበውን አሳክታ ክብረወሰኑን በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ እጅ አስገብታለች።

አስደናቂዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ከባዱን የማራቶን ክብረወሰን 2:11:53 በሆነ አዲስ ሰዓት ለማመን በሚከብድ ብቃት አነክታዋለች። ይህም 2019 ላይ ኬንያዊቷ አትሌት ብሪጊድ ኮስጌ በቺካጎ ማራቶን ካስመዘገበችው የቀድሞው 2:14:04 ከሁለት ደቂቃ በላይ የተሻለ ሆኗል።

አትሌት ትዕግሥት ወደ ማራቶን ውድድር የገባችው ብዙም ትኩረት ሳይሰጣት ነው። ከዚህ ውድድር በፊት በማራቶን የሩጫ ዘርፍ የተወዳደረችው ሁለት ጊዜ ብቻ ነበር። ከባለፈው ዓመት የበርሊኑ ውድድር ቀድሞ የተሳተፈችው በሳዑዲ አረቢያ በተዘጋጀው የሪያድ ማራቶን ላይ ሲሆን 2:34:00 በሆነ ሰዓት ነበር ያጠናቀቀችው።

ትናንት በበርሊን በተካሄደውና ሁለተኛዋ በሆነው የበርሊን ማራቶን ውድድር የራሷን ሰዓት በሦስት ደቂቃ ገደማ አሻሽላለች። ለረዥም ጊዜያት የ800 ሜትር ሯጭ የነበረችው ትዕግሥት፣ በቅርቡ ነው ወደ ጎዳና ሩጫ ፊቷን ያዞረችው። በ2016 ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን ወክላ በ800 ሜትር ተሳትፋለች። ሆኖም ከግማሽ ፍጻሜው ማለፍ ባለመቻሏ ከውድድሩ ውጪ ሆና ነበር። ትዕግሥት ከ800 ሜትር በተጨማሪ በ400 ሜትርም ስትወዳደር ቆይታለች።

አትሌቷ ቀደም ሲልም የግማሽ ማራቶን ውድድሮችን ለማሸነፍ በቅታለች። ትዕግስት የዛሬ አመት ስታሸንፍ የገባችበት 2:15:37 ሰዓት በወቅቱ የኢትዮጵያ የሴቶች ማራቶን ክብረወሰን ሆኖ ነበር:: አሁን ደግሞ በልምምድ ጓደኛዋና በዓለም ቻምፒዮኗ አማኔ በሪሶ 2:14:58 እጅ ተይዟል:: ትዕግስት አሰፋ አንድ ወቅት በጉዳት ምክንያት አትሌቲክስ በቃሽ ተብላ ነበር፣ እንኳን ለመሮጥ መራመድ ይቸግርሻል ተብላ የነበረችው አትሌት ግን ተስፋ ሳትቆርጥ የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት ሆናለች::

በዓለም አትሌቲክስ ውድድር ውስጥ ከፍተኛ የሚባለው የፕላቲኒየም ደረጃ ያለው የበርሊን ማራቶን የተጀመረው እንደ አውሮፓውያኑ በ1974 ነው። በጀርመን መዲና የሚካሄደው ውድድር ፈጣን ሰዓት ከሚመዘገብባቸው የማራቶን ውድድሮች መካከልም አንዱ ነው። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በዚህ ውድድር በተለያዩ ጊዜያት ያሸነፉ ሲሆን ኃይሌ ገብረሥላሴ እና ቀነኒሳ በቀለ ቀዳሚዎቹ ናቸው።

በሴቶች በኩል ጌጤ ዋሚ ውድድሩን ለማሸነፍ የቻለች የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት ናት። ጌጤ እንደ አውሮፓውያኑ በ2006 እና በ2007 ውድድሩን በተከታታይ ማሸነፍ ችላለች።

በበርሊን ማራቶን 12 ጊዜ የዓለም ክብረወሰን ተሻሽሏል ዘጠኙ በወንድ ሦስቱ በሴቶች። ኃይሌ ገብረሥላሴ እና ኢሉድ ኪፕቾጌ ሁለት ሁለት ጊዜ የዓለም ክብረ ወሰንን ያሻሻሉት እዚህ በርሊን ማራቶን ነው::

17 ጊዜ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በርሊንላይ አሸንፈዋል። ኃይሌ ገብረሥላሴ(4ተከታታይ ጊዜ)፣ ቀነኒሳ በቀለ(2ጊዜ) እና ጉዬ አዶላ በወንዶች ያሸነፉ ናቸው:: ኬንያዊው የርቀቱ ፈርጥ ኪፕቾጌ ትናንት ይህን ውድድር ለአምስተኛ ጊዜ በማሸነፍ የመጀመሪያ የሆነበትን ታሪክ ሠርቷል። በማራቶን ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፈው ማርክ ኮሪር ኪፕቾጌን ተከትሎ የገባ ሲሆን፥ ኢትዮጵያዊው አትሌት ታደሰ ታከለ 3ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።

ጌጤ ዋሚ(2ጊዜ)፣ አበሩ ከበደ(3ጊዜ)፣ አፀደ ሀብታሙ፣ አሸቴ በክሪ፣ ትርፌ ፀጋዬ፣ ጎትይቶም ገብረሥላሴ እና ትዕግስት አሰፋ ሴት ኢትዮጵያውያን የበርሊን ማራቶን ከዚህ ቀደም አሸናፊዎች ናቸው::

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን  መስከረም 14 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You