በሀገራችን ተፈጥሯዊ የውበት መጠበቂያዎችን መጠቀም የተለመደ ነው። በተለይ ዘመናዊ መዋቢያዎች ከመምጣታቸው በፊት ከተፈጥሮ ንጥረ ነገሮች በባህላዊ መልኩ የሚዘጋጁ መዋቢያዎች በብዛት ጥቅም ላይ ይውሉ ነበር። አሁንም ቢሆን በአብዛኛው የገጠሪቱ አካባቢዎች የተለያዩ የተፈጥሮ መዋቢያዎች በቤት ውስጥ እየተዘጋጁ ጥቅም ላይ ይውላሉ። ለእዚህም ወሎ አካባቢ በሴቶች ዘንድ በስፋት ጥቅም ላይ የሚውለውን የወይባ ጭስ በአብነት መጥቀስ ይቻላል።
ዘመናዊ የውበት ሳሎኖች በተበራከቱባቸው ከተሞችም ቢሆን በዘመናዊና በባህላዊ መልኩ የተዘጋጁ መዋቢያዎችን እናገኛለን። ይህም ተጠቃሚዎቹ የፈለጉትን አይነት መዋቢያ መርጠው እንዲጠቀሙ አማራጭ ይፈጥርላቸዋል። ምንም እንኳን በከተሞች አካባቢ በዘመናዊ መንገድ መዋብና ማጌጥ የተለመደ ቢሆንም፣ አሁን አሁን የተፈጥሮ መዋቢያዎች በብዙዎች ዘንድ በብዛት ተመራጭ እየሆኑ መምጣታቸውን ይስተዋላል።
በተለምዶ የፊት ቆዳንም ሆነ ሌሎች የሰውነት ክፍሎችን ውበት ለመጠበቅ የምንጠቀምባቸው የተፈጥሮ መዋቢያዎች በአብዛኛው ከተለያዩ እጸዋት ዝርያዎች የሚቀመሙ ናቸው። የእጸዋቱን ቅጠል፤ ፍሬ፣ ስር እና መስል ነገሮች በማዋሀድ ለውበት መጠበቂያ እንዲውል ሲደረግ ይታያል።
ኬሚካል የተቀላቀለባቸው የፋብሪካ ምርቶችን መጠቀም የራሱ የሆነ ጥቅም ቢኖረውም የጎንዮስ ጉዳት ሲያስከትልም ይስተዋላል። እንደሚታወቀው በኛ ሀገር በባህላዊ መንገድ የሚዘጋጁ ውበት መጠበቂያዎች የቆዩና በጥንት ጀምሮ በቤት ውስጥ እየተዘጋጁ እናቶቻችን ሲጠቀሙባቸው ቆይተዋል፤ አሁን እየተጠቀሙት ይገኛሉ። ፡ እነዚህ መዋቢያዎች ከተፈጥሮ ውህዶች የሚሰሩ ስለሆኑ በአካባቢያችን ላይ በቀላሉ ሊገኙ የሚችሉ ናቸው። የጎንዮሽ ጉዳት ይዘውብን ይመጣሉ የሚል ስጋትን የሚያስቀሩና አዘገጃጀታቸውም ሆነ አጠቃቀማቸው በጣም ቀላል እንደሆነ በብዙዎች ዘንድ ይነገራል።
የፊትን ፣ የቆዳን፣የጽጉርን፣ የእጅና የእግር ጥፍርን፣ የሰውነት ቆዳን እና ሌሎችን የሰውነት ክፍሎች ለማስዋብ የሚያገለግሉ ከተፈጥሮ ነገሮች የሚዘጋጁ ባህላዊ መዋቢያዎች በርካታ ናቸው። መዋቢያዎቹ በዱቄት፣ በፈሳሽ እና በጭስ እና በመሳሳሉ መልክ ተዘጋጅተው የሚቀርቡ ሲሆን፤ አብዛኞዎች በቀላሉ በቤት ውስጥ የሚዘጋጁ ናቸው። እንዲሁም ማንኛውም ሰው በሚፈልገው መልኩ አዘጋጅቶ በቀላሉ ሊጠቀምባቸው ይችላል። እንደ እንሶስላ ወይም እንሾሽላ፣ ወይባ ጢስ እና ቀሲል አይነቶቹ ከተፈጥሮ ነገሮች የሚገኙ መዋቢያ በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች በሚባል ደረጃ ይታወቃል።
በዛሬው የፋሽን ገፅ አምዳችን በስፋት ልንዳስሰው ያሰብነው የተፈጥሮ ውበት መጠበቂያ በምስራቁ የሀገራችን ክፍሎች በደንብ ጥቅም ላይ እየዋለ የሚገኘው “ቀሲል”ን ነው። መጠሪያው የተወሰደው ከሶማሊኛ ቋንቋ ነው። ይህ ዱቄት መሰል መዋቢያ በድሬዳዋና በጅግጅጋ አካባቢዎች በስፋት ይታወቃል። በእነዚህ አካባቢዎች የሚገኙት ሰዎችም ውበታቸውን ለመጠበቅ ይጠቀሙበታል። በተለይ የፊት ቆዳን ለማስዋብ ፍቱን እንደሆነ ይነገራል። በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳት የደረሰበትን የፊት ቆዳ ይህንን ተፈጥሯዊ መዋቢያ በተደጋጋሚ በመጠቀም በሂደት ለውጥ በማምጣት ውበት ለመጠበቅ እንደሚያስችል ተጠቃሚዎች ይጠቁማሉ።
“ቀሲል” ቅጠሉ ሲሆን ለመዋቢያ የሚያገለግለው ቅጠል ደርቆና ተፈጭቶ ዱቄት ከሆነ በኋላ አገልግሎት ላይ ይውላል። የቀሲል ዱቄት ቀለሙ አረንጓዴ ነው፤ አጠቃቀሙ ዱቄቱ ከእርድ ጋር ተደባልቆ በውሃ ከተበጠበጠ በኋላ ውህዱን የፊት ቆዳን በመቀባት ውበትን መጠበቅ የሚያስችል ነው።
ወጣት ቤተልሔም የውብሸት ነዋሪነቷ በድሬዳዋ ከተማ ሲሆን ይህንን የተፈጥሮ መዋቢያ ታዘወትራለች። ቀሲልን ከእርድ እና ከውሃ ጋር ደባልቃ በመጠቀም የፊቷን እና የእጆቿን ውበት ትጠብቃለች። ይህንን መዋቢያ ቢያንስ በሳምንት ሁለት ጊዜ እንደምትጠቀም ወጣት ቤተልሔም ትናገራለች።
እሷ እንደምትለው፤ቀሲል ተፈጥሯዊ መዋቢያ ስለሆነ ብዙዎች ይጠቀሙታል። በተለይ ፊታቸው ላይ የተለያዩ ነጠብጣብ ነክ ነገሮች እና ማዲያት ያለባቸው ሰዎች በብዛት ይፈልጉታል ትላለች።
እሷ እንደምትለው፤ ቀሲል በገበያ ላይ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚቀርብ በመሆኑ ማንኛውም ሰው በቀላሉ ገዝቶ ሊጠቀምበት ይቻላል። ተፈጥሯዊ በመሆኑም ምንም አይነት የጎንዮሽ ጉዳት በፊት ቆዳ ላይ አያስከትልም። ቀሲል ለፊት ቆዳ ውበት መጠበቂያ የሚያገለግል ተፈጥሯዊ ንጥረ ነገር ያለው በመሆኑ በተለይ ለሴቶች የፊት ቆዳ ተስማሚ ነው። በዚህ ምክንያት አብዛኛዎቹ ሴቶች እንደሚጠቀሙት ትናገራለች። አሁን ላይ ይህንን ተፈጥሯዊ መዋቢያ ሌላ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ገዝተው ሲጠቀሙበት ማየቷን ትናገራለች።
ቀሲል ሁሉም ሰው በቤቱ ውስጥ አዘጋጅቶ ሊጠቀመው የሚችልና አጠቃቀሙም ቀላል ነው የምትለው ቤተልሔም፤ አንድ ቀሲልን የምትጠቀም ሴት የቀሲሉን ዱቄት ከገዛች በኋላ እንደምትጠቀመው መጠን ብዛት የቀሲሉን ዱቄት ከእርድና ውሃ ጋር በማዋሀድ እንዳይቀጥንም በጣም ወፍራም እየመጠነች በመጨመር ፊቷ ለአንድ ጊዜ መቀባት እንዲያስችላት ውህድ አዘጋጅታ መጠቀም ትችላለች። ቀሲል ውበትን ከመጠበቅ ባሻገር ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው ይታመናል።
እንደ ቤተልሔም ገለፃ፤ ከጥንት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ጥቅም ላይ እየዋለ የሚገኘው ይህ ተፈጥሯዊ ውበት መጠበቂያ በሌሎች አካባቢዎች በጥቂቱ ቢኖርም በጅግጅጋና በድሬዳዋ አካባቢ ያሉት ነዋሪዎች በስፋት እየተጠቀሙበት ይገኛሉ። በፋብሪካ የተቀነባበሩት ውበት መጠበቂያዎች እንደ ቀሲል ብዙ ሰዎች እንዳይጠቀሟቸው የሚያደርገው ይዘው የሚያመጡት የጎንኞሽ ጉዳት መሆኑንም ታነሳለች።
ቤተልሔም እንደምትለው፤ በዘመናዊ መልኩ የሚመጡ የውበት መጠበቂያ “ሜካፖችን” የሚጠቀሙ ብዙ ስዎች አሉ። መጠቀሙ ጥሩ ሆኖ ሳለ የሚያመጡት የጎንዮሽ ጉዳትም ታሳቢ መደረግ አለበት። እንዲሁም ከዋጋ አንጻር ከውጭ ሀገር በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚገቡ በመሆኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተጠቃሚውም ሲጨምር ዋጋቸው እየናረ መጥቷል። አሁን ላይ ባለው ሁኔታ የመዋቢያዎቹ ዋጋ የህብረተሰቡን አቅም ያገናዘብ ስላልሆነ ብዙ ሰዎች ውበታቸውን መጠበቅ እየፈለጉ የሚተውበት ሁኔታ ያጋጥማል።
“ይህንንና መሰል ሀገር በቀል ተፈጥሯዊ መዋቢያዎችን ማስፋፋት ቢቻል ከራስ አልፎ ለሌላው መትረፍ ይቻላል” የምትለው ቤተልሔም፤ በቀላሉ በቤታችን አዘጋጅተን መጠቀም ስንችል ለአላስፈላጊ ውጪ መዳረግ እንደማይገባም ትናገራለች። ባህላዊ የውበት መጠበቂያዎችንና እሴቶችን ጠብቆ ለትውልድ የማስተላለፍ ኃላፊነት የሁሉም እንደሆነም ትገልፃለች። በባህላዊ መንገድ የሚዘጋጁና በቀላሉ ማግኘት የምንችላቸው ተፈጥሮዊ መዋቢያዎችን መጠቀም መልመድ ጠቀሜታ እንዳለው ትገልጻለች። ከዚህ አለፍ ሲል ደግሞ ለሌሎችም እንዲተዋወቅ ማድረግን እንደሚጠይቅ ጠቅሳ፣ ከዚህ አኳያ ብዙ ሥራዎች መስራት እንዳለባቸው አመልክታለች፤ ፋሽን እየተባለ ከውጭ ለሚመጣው ብቻ ትልቅ ዋጋ ከምንሰጥ የራሳችንን ማበረታታት ይገባል ስትል ምክረ ሃሳቧን ትለግሳለች።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን መስከረም 14 ቀን 2016 ዓ.ም