በሌላው ዓለም፣ በተለይም በአደጉት ሀገራት የትውልድ ጉዳይ የእለት ተእለት አጀንዳ ነው። ስለ ትውልድ ይመከራል፣ ስለ ትውልድ ይጠናል፣ ስለ ትውልድ ፖሊሲ ይቀረፃል፣ ይሻሻላል፤ አዳዲሶችም ይወጣሉ።
በሰለጠነው ዓለም የአንድ ሕገመንግሥት አይነኬ እድሜ 19 ሲሆን፣ ከዛ በኋላ ይፈተሻል፣ ይከለሳል፤ ይበረዛልም። “ምክንያት?” ከተባለም፣ ሌላ አዲስ ትውልድ አዳዲስ ጥያቄዎችንና ፍላጎቶችን ይዞ መጥቷልና “ባለውና በነበረው ተገዛ” ይሉ ፈሊጥ የማይሰራ በመሆኑ ነው።
በሰለጠነው ዓለም ስለ ትውልድ የሚመክሩ መድረኮች ተቆጥረው አያልቁም፤ በነዚህ አገራት ስለ ትውልድ የሚጠበቡ አረጋዊያን እልፍ አእላፍ ናቸው። በዲሞክራት አገራት ስለ ትውልድና የተሻለ ነገ የሚጨነቁ የፖለቲካ ድርጅቶች ብዙ ናቸው። “ስለ ትውልድ ያገባናል፣ ኃላፊነትም አለብን” የሚሉ ተቋማት ቁጥራቸው ዳር ድንበር የለውም። ባጭሩ፣ በትውልድ ስም የተቋቋሙ፣ ትውልድ ላይ ለመስራት ወገባቸውን አስረው የተነሱ ተቋማት በዓለማችን አራቱም መአዘን ሞልተዋል።
መጪዋ ዓለማችንን ያለ መጪው ትውልድ ማሰብ እራሱ አለማሰብ ነው በማለት ትውልድ ላይ መስራት እንዳለባቸው ወስነው እየሰሩ ያሉ አካላት ሞልተዋል። ችግሩ “ውጤቱስ?” ካልሆነ በስተቀር ትውልድ ላይ የሚፈሰው መዋእለ ነዋይ፣ ስለ ትውልድ ሲባል የሚወጣው ጉልበትና እውቀት ከግምት በላይ ነው። ይሁን እንጂ፣ ከዚህ ሁሉ ወጪ አንዳንዶቹ አገራት ሲያተርፉ ቀሪዎቹ ደግሞ ሲከስሩ ነው የሚታዩት።
እዚህ ላይ ለተሻለ ትውልድ መምጣት፣ መፈጠር፣ ለተሻለ ነገ …ስለሚሰሩት አነሳን እንጂ፣ ሆን ብለው፣ በጀት፣ የሰው ኃይል፣ ጊዜ … መድበው የተኮላሸ ትውልድ እንዲፈጠር የሚሰሩ የሉም እያልን አይደለም። በዓለማችን የትኛውም ክፍል እንደ እነዚህ አይነት መርገምቶች ሞልተው ተትረፍርፈዋል። እነዚህ ወገኖች የልፋታቸውን አላገኙም ማለት በማይቻል ደረጃም ዓላማቸውን እያሳኩ ሲሆን፣ ማህበረ-ባህላዊ እሴቶችን መናድ ላይ የተሰማራው ወጣትና መሰል የህብረተሰብ ክፍል (በተለይ በፖለቲካው አለም ያሉ) የእነዚህ ተቋማትና ቡድኖች፣ እንዲሁም ግለሰቦች የ“ልፋት”ና ምኞቶቻቸው ውጤቶች ናቸው።
ይህንን አገላለፃችንን መሬት ለማሳረፍ ደግሞ የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ የካቲት 24 ቀን 2014 ዓ.ም ጂንካ ላይ ባደረጉት ንግግር «በቅርብ በተደረጉ ጥናቶች እንደተረጋገጠው 3ኛ ክፍል ከደረሱ ተማሪዎች መካከል 65 በመቶዎቹ ማንበብ አይችሉም። ለዚህ ምክንያቱ ባለፉት 27 አመታት በትምህርቱ ላይ የተሠራው አሻጥር ነው።» ያሉትን ብቻ መጥቀሱ ከበቂ በላይ ይሆናልና የነበረው የትምህርታችን ይዞታ ይህንን ይመስል ነበር። ከዚህ አኳያ ነው እንግዲህ የትምህርት ሚኒስቴርን “ትምህርት ለትውልድ” መርህን በማድነቅ፣ በመደገፍና ወደዚህ ገጽ በመምጣት “እሰየው” ለማለት የተፈለገው።
ምናልባት ከ70 በመቶ በላይ ወጣት ያላት አፍሪካ ተዘናግታ ካልሆነ በስተቀር፣ በተቀረው ዓለም በራሱ፣ በወጣቱ ሳይቀር ለወጣቱ እየተሰሩ ያሉ ተግባራት አያሌ ናቸው። ከእነዚህ ተቋማት መካከል ደግሞ የትምህርት ተቋማት ቀዳሚዎቹና ልዩ ትኩረት የተሰጣቸው ናቸው።
ኢትዮጵያ ወጣ ገባ እያለችም ቢሆን ስለ ትውልድ ጉዳይ መጨነቋ አልቀረም። ከ“ወጣት የነብር ጣት” ጀምሮ “ያለ ወጣቱ ታስትፎ አብዮቱ ግቡን አይመታም” ድረስ ሄዳለች። ከ“የወጣቶች ማህበር” እስከ “የወጣቶች ሊግ” ብቻ ሳይሆን ወጣቶችና ስፖርትንም እስከ ማቋቋም ድረስ ገፍታበታለች። “ውጤቱስ?” ከተባለ ዝቅ ብለን የምናየው ይሆናል። (እዚህ ጋ “ያ ትውልድ” (ትውልዱን ለማስታወስ በሰሜን አሜሪካ «ያ ትውልድ ተቋም» በኢትዮጵያዊያን መቋቋሙን ልብ ይሏል)፣ “ይሄ ትውልድ”፣ “የዛሬ ልጅ”፣ “የድሮ ልጅ” … የሚሉ አተካሮዎች ውስጥ መግባቱ አያስፈልግም በሚል እንጂ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የትውልድ ጉዳይ ሥርዓት ባለው መንገድ እየተመራ ነው ለማለት ጊዜው ገና ይመስላል።)
እዚህ ላይ “እቅድህ የ10 አመት ከሆነ ዛፍ ትከል፤ እቅድህ የ100 አመት ከሆነ ትውልድን (ልጅህን) አስተምር” የሚለውን የቻይናዊያን (ኮንፊሺየስ) አስተምህሮ ማንሳት አስፈላጊ ነው። በአገራችንም ወጣቱንና ትውልድን ማእከል አድርገው በመስራት የሕይወት ዘመናቸውን ያሳለፉ ግለሰቦች የነበሩ ሲሆን፣ ይህ ጸሐፊ እስከሚያውቀው ድረስ፣ እንደ ኢትዮጵያዊው ምሑር፣ የመብት ተሟጋች፣ ፖለቲከኛና ሐያሲ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም (1922 – 2013 ዓ.ም)፣ በስማቸው “መስፍን ወልደማርያም ፋውንዴሽን” የሚል ተቋም ተመስርቷል (ፋውንዴሽኑ በፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ስም የተሰየሙ ቤተ መጻሕፍት እና ማዕከላት በሁለተኛ ደረጃ እና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንዲከፈቱ የማድረግ እቅድ እንዳለው በምስረታው እለት ተገልጿል)፣ ወጣት ተኮር ስራዎችን የሠራ አለ ለማለት ሞራሉ አይኖርም። ሰውየው ለወጣቱ ጥብቅና እንደ ቆሙ፣ ወጣቱን እንደ ገሰፁ፣ ወጣቱን እንዳስተማሩ፤ ያላቸውን ሁሉ ለወጣቱና መጪው ትውልድ እንደ ወረወሩ፤ ወጣቱን እንዳወያዩ፣ ከወጣቱ ጋር እንደ ተወያዩ ነው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ። በመሆኑም ነው፣ ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሀውልታቸው ላይ አዘወትረው የሚናገሯትና “ነገ የወጣቱ ነው“ የምትለው አገላለፃቸው እሳቸውን ለትውልድ ትገልፅ ዘንዳ ስፍራ የተቸራት።
“የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ” መጽሐፍ አዘጋጅ፣ ዶ/ር እጓለ ዮሀንስንም እዚሁ ጋ ጠቅሶ ማለፍ የግድ ይሆናል። ሌሎችም ብዙ ብዙ አሉ፤ ችግሩ አንዱ የገነባውን ሌላው (በተለይም መጪው) ማፍረሱ ሆነ እንጂ።
“ትውልድ“ ከዚህም ባለፈ በተለያዩ የፖለቲካው አለም ሰዎችም ሲጠቀስ፣ ሲወደስ … ይሰማል። ከተወዳጆቹና ተወዳሾቹም አንዱ የአሁኑ (ወይም፣ መጪው? ትውልድ) ሲሆን፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ብያኔ ይህ ትውልድ የአባቶቹ ልጅ፣ “የመደመር ትውልድ” እንጂ በየ “ጓጥ ስርጓጉጡ” ተወሻሽቆ በአገሩ ላይ ብሽሽቆሽ የሚጫወት ትውልድ አይሆንም።
ወደ ፈጠራው አለም ስንመጣ የማይታለፉ ሰዎችን የምናገኝ ሲሆን፣ ቀዳሚውም የ“ተማር ልጄ” ባለቤት ድምፀ ሸጋው አለማየሁ እሸቴ ነው። “ተማር ልጄ / ወገን ዘመድ የለኝ / ሀብት የለኝም ከጄ” . . . የተሻለ ትውልድን ከመፍጠር፤ የተሻለ ነገን እውን ከማድረግ አኳያ የአባቶችን ሚና ብቻ ሳይሆን የአሁኑ ትውልድ ለነገው ዛሬ ምን ማድረግ እንዳለበት ሁሉ የሚመክር “ዜማ!!!”።
እንደሚታወቀውና ከላይ እንደ ተመለከትነው፣ ከታችም እንደምንመለከተው ትምህርት ሚኒስቴር እና የትውልድ ጉዳይ ተነጣጥለው የሚታዩ አይደሉም። “ትምህርት” የሚለው እስካላምታታን ድረስ ሁለቱ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው።
ትምህርት ሚኒስቴር ወደ ሪፎርም ከገባ ወዲህ ለውጥ ካመጣባቸውና እያመጣባቸው ካሉ አሰራሮች፣ አካሄዶችና አስተሳሰቦች አንዱ ይኸው “ትምህርት ለትውልድ” ሲሆን፣ የማህበራዊ ድረገጽ መግቢያ ገፁን መክፈቻ ያደረገውም ይህንኑ ሞቶና ሎጎ (አርማ) ነው።
ሳይገድሉ ጎፈሬ፣ ሳያጣሩ ወሬ እንዳይሆንብን፣ ከፈረሱ አፍ እንዲሉ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ የሚሉትንም እንስማ።
ጳጉሜ 02/2015 ዓ.ም የትምህርት ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት ሠራተኞች የ2015 ዓ.ም ስራ አፈጻጸምና የ2016 ዓ.ም እቅድ ላይ ውይይት ባካሄዱበት እለት “የቀጣዩ ትውልድ ዕጣ ፋንታ በእጃችን በመሆኑ በላቀ የኃላፊነትና ተጠያቂነት ስሜት እንሰራለን” ለሚለው ከፍተኛ አፅንኦት የሰጡት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የቀጣዩን ትውልድ ዕጣ ፋንታ በመወሰን በኩል የትምህርት ዘርፉ ሠራተኞች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው ሁሉም ሠራተኛ በየተሠማራበት የሥራ መስክ በላቀ የኃላፊነትና ተጠያቂነት ሰሜት ሊሠራ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
በውይይቱም፣ በአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ “ትምህርት ለትውልድ”ን መሰረቱ ያደረገው የአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ትግበራ፤ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና፣ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ማሻሻያ፣ በአዲሱ የትምህርት ቤቶች ዲዛይን መሠረት አዳዲስ ትምህርት ቤቶችን የመገንባት ሥራዎችና ሌሎችም ሥራዎች ስኬታማ በሆነ መልኩ የተተገበሩና የተጀመሩ መሆናቸው በውይይቱ ወቅት የተነሱ ሲሆን፣ ያለፈውን አመት ጥንካሬዎች ይበልጥ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉና ያጋጠሙ ክፍተቶችን በማረም በመጪው 2016 ዓ.ም በለውጥ ሥራዎችም ሆነ በመደበኛ ሥራዎች ከፍተኛ ስኬት ለማስመዝገብ እንደሚሠራም የጋራ ግንዛቤ ስለመያዙ ተነግሯል።
ሌላዋ፣ ጳጉሜን 5 “የትውልድ ቀን” መሆኑን ተከትሎ መልእክት ያስተላለፉት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ሲሆኑ፤ “አዲሱ ትውልድ ሀገሩን የሚወድ፣ የሚያነብ፣ የሚመራመርና ችግር ፈቺ ሊሆን ይገባል” የሚለው የመልእክታቸው ኃይለ-ቃል ነበር።
የትምህርት ሚኒስቴር የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ባዘጋጁትና ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶችና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በዚሁ መድረክ ላይ “ትውልዱ በትምህርት የታነጸ፣ ታሪክና ባህሉን የሚያውቅና ስለሀገሩ የሚቆጭ፤ የማንበብ ባህልን በማዳበር ችግር ፈቺ ሆኖ ሀገሩን የሚያሻግር ሊሆን ይገባል።” ሲሉም ነው ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ያሳሰቡት።
ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብት የታደለች መሆኗን የጠቆሙት ፕሬዚዳንቷ ትውልዱ ተስፋ ሰጪ የፈጠራ ችሎታውን በማዳበር ሀገሩን መለወጥ እንዳለበት መክረዋል። የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ በበኩላቸው አዲሱ ትውልድ በማንበብ፣ በማሰላሰልና ምክንያታዊ በመሆን ሀገሩን ሊያሻግር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በተመሳሳይ፣ ወጣቱም ሆነ መጪው ትውልድ አገርን መውደድና መጠበቅ፣ ስልጣኔን ማስቀጠል፤ እንዲሁም፣ የዓለምን ፈተና መሻገር የሚችል መሆን እንደሚጠበቅበት፤ በእሳቸው ዘመን የነበረው ትውልድ ለስልጣኔ የሚቆጭ ግብረገብ፣ በማንበብና በማሰላሰል የሚያምን እንደነበረም ፕሮፌሰር ብርሀኑ ወደ ኋላ አስታውሰዋል።
በጉዳዩ ላይ ገፋ አድርገው የሄዱት በደርግ ዘመን የተወሰደውን አስከፊ ርምጃና ታሪካዊ ስህተት ሲገልፁት “አንድ ትውልድ የመመተር እርምጃ” በማለት ሲሆን፣ ይህም በቀይ እና ነጭ ሽብር ስያሜ የተወሰደውን መተላለቅ እና የስልጣን ሽኩቻ፤ እንዲሁም ያለቀውን ወጣት ለማመልከት መሆኑን ይገልፃሉ።
በኢህአዴግ ዘመን ያለውን የመረመሩ ደግሞ ወጣቱ በተለያዩ ሱሶች የደነዘዘበትና ለባለ ዲግሪ ሥራ አጥነት የተዳረገበት መሆኑ ላይ ይስማማሉ።
ከለውጡ በኋላ ያለውን በተመለከተ ይህንን ያህል ለውጥ መጥቷል ለማለት መረጃው ባይገኝም፣ በትምህርቱ ዘርፍ ግን በርካታ መታየት የጀመሩ እንቅስቃሴዎች መኖራቸው ላይ የብዙዎቻችን ግንዛቤ አለ።
የ“ትምህርት ለትውልድ”ን እንደ መርህ መጠቀም አንድምታውም ሆነ ፋይዳው ምንድን ነው? የሚለውን መቃኘት ካስፈለገ በወርድና ስፋቱ ጥልቀትና ርዝመቱ ምክንያት መመለሻ ልናጣበት የምንችል ከመሆኑ በስተቀር ተግባሩ ያስኬዳል። ሆኖም ግን ለዚህ ጽሑፍ ሲባል ብቻ ቀንብበን መመልከቱ ጠቃሚ ይሆናል።
ከላይ ለመጠቋቆም እንደ ሞከርነው ትምህርትና ትውልድ የሚነጣጠሉ ጉዳዮች አይደሉም። የመጀመሪያው ሁለተኛውን መቅረጫ ሲሆን፣ ሁለተኛው የተዋጣለት ይሆን ዘንድ የመጀመሪያው እጅግ አስፈላጊ መሆኑ ከሁሉም በላይ ሊሰመርበት ይገባል። በተለይ በዚህም ይሁን በመጪዎቹ ዘመናት የሁለቱ መስተጋብር የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የግዴታና ተፈጥሯዊ ነውና በጉዳዩ ላይ ደግሞ ማሰብ፣ ደጋግሞ ሀሳብ መለዋወጥ፤ ሳይታክቱም መስራትን ይጠይቃል።
ሁለቱን ነጥለን ማየት አይቻልም ስንል፣ እድሜያቸውን ትውልድ ቀረፃ ላይ ያሳለፉት አርቲስት፣ ደራሲና የመድረክ ባለሟሉ አባባ ተስፋዬ (ተስፋዬ ሳህሉ) በጥኡመ ልሳናቸው “ልጆች፣ የዛሬ አበባዎች / የነገ ፍሬዎች” በማለት ሲያስተምሩ እንደ ኖሩት በትምህርት ዓለም ውስጥ ያሉ ልጆች የዛሬ አበባዎች፤ የነገ ፍሬዎች ናቸውና ትምህርትም ሆነ አጠቃላይ የትምህርት ሥርዓቱ ከተበላሸ ልጆችም (በተራዛሚው ትውልዶች) ተበላሹ ማለት በመሆኑ “የነገ ፍሬዎች” ብሎ ነገር አይኖርም ማለት ነው። ይህ ማለት ደግሞ አገርም ሆነ ህዝብ አለ ማለት የማያስችልበት ደረጃ ያደርሳልና ድስት ጥዶ ከማልቀስ ከወዲሁ አንድ ነገር ማድረጉ የግድ ይሆናል።
የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ሰኔ 25 ቀን 2015 ዓ.ም እኩለ ቀን ላይ በጽሕፈት ቤታቸው በመገኘት ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ በሰጡበት ወቅት እንደተናገሩት፤ አሁን በሀገራችን ያሉ ትምህርት ቤቶች አብዛኞቹ ከደረጃ በታች ከመሆናቸው የተነሳ ለመማር ማስተማር ሥራው ምቹ አይደሉም። በመሆኑም ይህንን ለመቅረፍ «ትምህርት ለትውልድ» የትምህርት ቤቶች መሠረተ ልማት ማሻሻል ሀገራዊ ንቅናቄን በሀገር አቀፍ ደረጃ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ በተገኙበት የተጀመረው በሁሉም ክልሎች ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን ሁሉም ገንዘቡ፣ እውቀቱና ጉልበቱ ያላቸው ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን መርሀ ግብሩን እንዲደግፉት የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።
ከዚህም ሆነ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ “ሞቶ” (ትምህርት ለትውልድ) መረዳት የሚቻለው መንግሥትና የመንግስትን ፕሮግራም አስፈፃሚው መሥሪያ ቤት (ሚኒስቴሩ) ያለፈው ስህተት እንዳይደገም፤ መጪዎቹ ዘመናት መልካም ሥነ ምግባር ያለው፣ የእውቀት ባለቤት የሆነ፣ የእውነት አራማጅ፣ ለሀገርና ወገኑ ከፍተኛ አክብሮትና ፍቅር ያለው፣ ሰርቶ የማይጠግብ፣ ዘርቶ የሚቅም፣ ወልዶ የሚስም … ትውልድ ማፍራት ላይ በሙሉ ኃይል እየሰሩ መሆኑን ነውና፣ ትምህርት ባለ ድርሻዎቹ በርካቶች እንደ መሆናቸው መጠን፣ የሚመለከተው ሁሉ ሊያብርና ሊተባበር፤ ከሚኒስቴሩ ጎንም ሊሰለፍ ይገባል እንላለን።
መልካም አዲስ አመት፤ መልካም የትምህርትና መማር-ማስተማር ዘመን!!!
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን መስከረም 14 ቀን 2016 ዓ.ም