ተስፋ ሰጪዎቹ የክልሉ እምቅ ሀብቶች- ቡና፣ሻይና ቅመማ ቅመም

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በተፈጥሮ ሀብት የታደለ ክልል ስለመሆኑ በስፋት ይነገራል። ክልሉ በተፈጥሮ ሃብት የታደለ እንደመሆኑ በርካታ የሰብል ምርቶችን ጨምሮ፤ አትክልትና ፍራፍሬ፣ የቅባት እህሎች እንዲሁም ቡና ሻይና ቅመማ ቅመም በስፋት ይመረታል።

አቶ በላይ አጁአብ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ዘርፍ ዋና ዳይሬክተርና የልማትና ጥበቃ ዘርፍ ኃላፊ ናቸው። እሳቸው እንደሚገልጹት፣ ክልሉ በተፈጥሮ የታደለና ስነምህዳሩም ለበርካታ የሰብል፣ የአዝዕርትና የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች የተመቸ ነው። በተለይም በቡና፣ በሻይና በቅመማ ቅመም ምርት ክልሉ ዕምቅ አቅም ያለው ሲሆን ለውጭ ምንዛሪ ግኝት ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያበረክተው ቡና በክልሉ በስፋት ይመረታል። 560 ሺ ሄክታር መሬት በቡና የተሸፈነ ሲሆን፤ ከ88 ሺ 300 ሄክታር በላይ መሬት ደግሞ በቅመማ ቅመም እንዲሁም ሁለት ሺ 776 ሄክታር መሬት በሻይ ልማት ተሸፍኗል።

ክልሉ ለቡና፣ ለቅመማ ቅመምና ለሻይ ምርቶች ካለው የስነ ምህዳር ምቹነት አንጻር በክልሉ ከሚገኙ ስድስት ዞኖች መካከል አራቱ ቡናን በተለየ መንገድ ስፔሻላይዝ የሚያደርጉና ዋና ሰብላቸው አድርገው የሚያለሙ እንደሆኑ የሚናገሩት አቶ በላይ፤ በዘርፉ ሰፊ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ያስረዳሉ። እሳቸው እንደሚሉት፤ በክልሉ ከሚገኘው ሶስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ህዝብ ውስጥ ከግማሽ በመቶ የሚበልጠው በቡና፣ በቅመማ ቅመምና በሻይ ምርቶች ልማት ላይ የሚሳተፍ ነው።

በክልሉ የቡና፣ የቅመማ ቅመምና የሻይ ምርት በሰፊው መመረት ብቻ ሳይሆን የሚመረተውን ምርት በጥራት በማምረትና ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ሥራ በመሥራት ወደ ማዕከላዊ ገበያ እንዲሁም ወደ ውጭ ገበያ ይላካል። ይህም ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ግኝት አይነተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ሲሆን፤ በተለይም የቡናን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ እንዲሁም በጥራት በማምረት አገራዊ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማሳደግና ዘርፉን እንዲደግፍ ታቅዶ እየተሠራ ስለመሆኑ አስረድተዋል።

እሳቸው እንዳሉት ፤ በ2015 በጀት ዓመት ክልሉ 64 ነጥብ አምስት ሺ ቶን የቡና ምርት ለመሰብሰብና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ባቀደው መሰረት ዕቅዱን ለማሳካት ሰፋፊ ሥራዎችን ሲሰራ ቆይቷል። ለአብነትም ለባለሙያዎች ስልጠና የመስጠት እና ከአቅራቢዎች ጋር ምክክር በማድረግ የኢንዱስትሪ ባለቤቶች ወደ ሥራ እንዲገቡ የማድረግ ሥራ ተሰርቷል። በዚህም 42 ሺ ቶን ቡና ለገበያ በማቅረብ የዕቅዱን 65 በመቶ ማሳካት ተችሏል።

ክልሉ በበጀት ዓመቱ 47 ሺ ቶን የቅመማ ቅመም ምርት በማምረት ወደ ማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ አቅዶ፣ 43 ሺ ቶን ምርት ሰብስቦ ለማዕከላዊ ገበያ ማቅረብ ችሏል። በዚህም የዕቅዱን 90 ነጥብ ዘጠኝ በመቶ በማሳካት በዘርፉ ከተያዘው ግብ አንጻር ከቡናና ሻይ የተሻለ አፈጻጸም ማስመዝገብ እንደቻለ ተናግረዋል። በሻይ ልማት ዘርፍ ካለፈው ጊዜ የተሻለ እንቅስቃሴ ስለመኖሩ ያነሱት አቶ በላይ፤ በበጀት ዓመቱ ሰባት ሺ ቶን የሻይ ምርት ለማቅረብ ታቅዶ፤ ከስደስት ሺ ቶን በላይ በማቅረብ የዕቅዱን 89 በመቶ ማሳካት ስለመቻሉ ነው የገለጹት።

በበጀት ዓመቱ በክልሉ የተመዘገበው የቡና ምርት መጠን ዝቅተኛ እንደሆነ ያነሱት አቶ በላይ፤ በተለይም በ2014 ዓ.ም ከነበረው የምርት መጠን (64 ሺ ቶን) ጋር ሲነጻጸር በ35 በመቶ ቀንሷል። ይህም በተለያዩ ችግሮች ምክንያት የተከሰተ እንደሆነ ያስረዳሉ።

አቶ በላይ እንደሚሉት፤ በክልሉ የቡና ምርት መቀነስ ተስተውሏል። ‹‹አንድ የቡና ዛፍ በተከታታይ ዓመት ጥሩ ምርት ከሰጠ በቀጣይ ዓመት በተወሰነ መጠን የምርት መቀነስ ያጋጥማል። ይህም ተፈጥሯዊ ነው። ነገር ግን ከዚህ ባለፈ የክልሉ የቡና እንክብካቤ ሥራ ጠንካራ ባለመሆኑ የተፈጠረ ነው። ምክንያቱም መንታ የወለደች እናት ጥሩ ቀለብ እንደሚያስፈልጋት ሁሉ፣ በተለይም ጥሩ ምርት ለሚሰጠው ቡና የተሻለ እንክብካቤ በማድረግ ምርትና ምርማነትን ሊያሳድጉ የሚችሉ እንደ ኮምፖስትና ብስባሽ ያሉትን በመስጠት፣ በአረምና ኩትኳቶ ሥራው ላይ ተከታታይነት ያለው ስራ በመስራት በኩል ደካማ አፈጻጸም ነበር›› በማለት ለቡና ምርት መቀነስ አንዱ ምክንያት እንደሆነ በግምገማ መለየት መቻላቸውን ተናግረዋል።

ሌላው ከፍተኛ መጠን ያለው ቡና ወደ ገበያ መውጣት ያልቻለበት ምክንያት ዓለም አቀፍ የቡና ዋጋ ከመውረድ ጋር ተያይዞ እንደሆነ ያነሱት አቶ በላይ፤ ይህም እንደ ሀገር ካሳደረው ተጽዕኖ ባለፈ በክልሉም ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደሩን ገልጸዋል። በመሆኑም በክልሉ የሚገኙ ቡና አቅራቢ ነጋዴዎችና አርሶ አደሩም ጭምር ዓለም አቀፍ የቡና ዋጋ መውረዱን ተከትሎ ዋጋው ሲሻሻል ይዞ ለመውጣት በሚል ወቅቱ የሰጠውን ቡና እንኳን ወደ ገበያ ለማውጣት ፈቃደኛ ባለመሆን በቤቱ እንዳስቀመጠ ነው የተናገሩት። በዚህም በርካታ መጠን ያለው ቡና በክምችት ደረጃ መኖሩን ተዘዋውረው መመልከት እንደቻሉ ነው የታዘቡት። በሌሎች ተጨማሪ ምክንያቶች ጭምር ባለፈው በጀት ዓመት ክልሉ በመጠን ያነሰና የቡና ምርት በሚፈለገው ልክ ለገበያ ማቅረብ አለመቻሉን አስረድተዋል።

የቅመማ ቅመም ምርትን አስመልክቶ አቶ በላይ ሲገልጹ፤ ክልሉ ከቅመማ ቅመም ምርት የተሻለ ምርት ማግኘት እንደተቻለ አንስተው፤ ዘርፉ የህግ ማዕቀፍ የሌለው በመሆኑ የተለያዩ ችግሮች ገጥመዋል። ይህም ምርቱን ከባዕድ ነገር ጋር የመቀላቀልና ገበያ ላይ ማቅረብ አንዱ ሲሆን፤ ይህን ለመቆጣጠር የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ አለመኖሩ ችግር ባለበት ሁኔታ ከምርት አቅርቦት አንጻር የተሻለ ምርት የተመረተበትና ወደ ማዕከላዊ ገበያ የቀረበበት አግባብ ስለመኖሩ አስረድተዋል።

በክልሉ በዋናነት ከሚመረቱና ውድ ከሆኑ የቅመማ ቅመም ምርቶች መካከል ኮረሪማ፣ ሄል፣ ቁንዶ በርበሬ፣ ጥምዝ፣ ጠረፍ፣ ሮዝመሪ፣ ሎሚናት፣ ዝንጅብልና ሌሎችም ይገኙበታል ያሉት አቶ በላይ፤ ክልሉ ለቅመማ ቅመም ምርቶች በተለይም ኮረሪማን ጨምሮ የተለያዩ ውድ የሆኑ የደጋ ቅመሞችን ለማምረት እጅግ በጣም ምቹና ሰፊ አቅም ያለው በመሆኑ በዘርፉ መሳተፍ የሚፈልጉ ባለሃብቶች ልማቱን በማስፋፋትም ሆነ በምርቱ ላይ እሴት በመጨመርና በማቀነባበር በማስፋትም ለመሳተፍ የሚፈልግ ማንኛውም አካል ወደ ክልሉ ቢመጣ የሚቀበሉ መሆኑን ገልጸው፤ ባለሃብቱም ውጤታማ መሆን የሚችል እንደሆነ አመላክተዋል።

‹‹ክልሉ በቅመማ ቅመም ዘርፍ የዕቅዱን መቶ በመቶ ማሳካት ያልቻለው፤ በዘርፉ ከፍተኛ የሆነ የህገወጥ ንግድ ዝውውር በመኖሩ ነው›› ያሉት አቶ በላይ፤ ውድ ዋጋ ያላቸው የቅመማ ቅመም ምርቶች ለአብነትም ኮረሪማ፣ ሄልና ቁንዶ በርበሬ እንደሆኑ ጠቅሰው፤ በእነዚህ የቅመማ ቅመም የሰብል ምርቶች ላይ ከፍተኛ የሆነ የህገወጥ የንግድ ዝውውር አለ ብለዋል። ከምርት ጥራቱ ጋር ተያይዞም በአፈርና በአመድ በማሸት ጥራቱን የመቀነስ ተግባራት ስለመኖሩ አመላክተው፤ ለዚህም በቀጣይ ተግባራዊ በሚሆነው የህግ ማዕቀፍ ችግሩን ለመከላከል ጥረት የሚያደርግ ይሆናል። በዚህም ህገወጥ ንግድ ላይ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በቀጣይ በቡና፣ በቅመማ ቅመምና በሻይ ዘርፍ የተሻለ የምርት መጠን ለማቅረብ በትኩረት የሚሠራ ይሆናል ብለዋል።

የሻይ ምርትን በተመለከተ በተለይም በከፋና በሸካ ዞን በሁለት የልማት ድርጅቶች በስፋት እየለማ መሆኑን የጠቀሱት አቶ በላይ፤ የሻይ ምርቱ ውሽውሽ እና ኢስት አፍሪካ በተባሉ የልማት ድርጅቶች እየለማ ያለ መሆኑን ጠቅሰዋል። በእነዚህ የልማት ድርጅቶች ዙሪያ የሚገኙ አርሶ አደሮች እያለሙ ለልማት ድርጅቶቹ የሚያቀርቡበት ሂደት መኖሩን ገልጸው፤ ነገር ግን የሽፋኑን መጠን ለማስፋት ማነቆ የሆኑ ችግሮች ስለመኖራቸው አንስተው ባለፈው ዓመት የሻይ የምርት ሽፋንን ወደ 27 ሄክታር ተጨማሪ የሻይ ልማት ለማሳደግ ታቅዶ አምስት ሄክታር ሽፋን ብቻ ማሳደግ መቻሉን ነው የገለጹት።

እሳቸው እንዳሉት፤ ለዚህም በርካታ ማነቆዎች ስለመኖራቸው ነው ያነሱት። በዋናነት ምርቱ በአርሶ አደሩ ጭምር እንዳይሰፋ ያደረገው በክልሉ በቂ የኢንዱስትሪዎች ያለመኖር ነው። የልማት ድርጅቶች ብቸኛ በመሆናቸውና ተወዳዳሪና ተፎካካሪ ድርጅቶች የሌላቸው በመሆናቸው የሻይ ምርቱን ከአርሶ አደሩ የሚገዙት በዝቅተኛ ዋጋ ነው። ይህም አርሶ አደሩ ላይ ተስፋ የመቁረጥና ተነሳሽነትን የሚቀንስ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለአብነትም የአንድ ኪሎ ግራም ሻይ ምርት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አምስት ብር እንደሆነ ነው የገለጹት። ይሁንና አርሶ አደሩ የምርት ዋጋን የሚሸፍን አለመሆኑን በመወያየትና በማስረዳት፤ ወደ 25 ብር አካባቢ ያደገበት አግባብ ስለመኖሩና አሁንም በቂ እንዳልሆነ ነው የተናገሩት። ከምርት ወጪ አንጻር ድርጅቶቹ እየገዙበት ያው ዋጋ ዝቅተኛና አርሶ አደሩ ምርቱን ወደ ማሳ የሚወስድበትን ተነሳሽነት የሚቀንስ ነው ብለዋል።

ክልሉ በሻይ ምርት ዕምቅ አቅም ያለው በመሆኑ ችግሮቹን በመቅረፍ ምርቱ በክልሉ አቅም ልክ መመረት እንዲችል መሥራት የሚጠይቅ ነው ያሉት አቶ በላይ፤ ለዚህም በክልሉ የተለያዩና ተወዳዳሪ መሆን የሚችሉ የጎጆ ኢንዱስትሪዎችን መትከል ተገቢ ነው። በማለት የኬንያን ተሞክሮ ይጠቅሳሉ። ‹‹ኬንያ ላይ አርሶ አደሩ በራሱ ማሳ ላይ የሻይ ምርቱን ካሰፋ በኋላ የጎጆ ኢንዱስትሪዎች እየተስፋፉ ምርን የሚያነሱ ሲሆን፤ በዚህም በአሁኑ ወቅት ኬንያዎች ሻይ ላይ ያላቸው ልምድ እያደገና ምርቱም እየሰፋ የሄደበት ሁኔታ ስለመኖሩ ጠቅሰዋል። ኢትዮጵያም ከዚህ ተሞክሮ በመውሰድ አገሪቷ ያላትን ዕምቅ አቅም አሟጦ በመጠቀም ከዘርፉ አገር ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ማግኘት እንድትችል የጎጆ ኢንዱስትሪዎችን በማስፋፋት ሻይን ማቀነባበር ያስፈልጋል። ይህ ካልሆነ በስተቀር አርሶ አደሩ ምርቱን ቢያሰፋ እንኳን ምርቱን አውጥቶ የሚሸጥበት ዕድል የለውም። ከዚህ በተጨማሪም የሻይ ምርት ከሌሎቹ ሰብሎች በበለጠ መቀነባበርን የሚፈልግና ሳይቀነባበር እንዲሁ ተመርቶ ብቻ ለገበያ የሚቀርብ ሰብል አይነት ባለመሆኑ አርሶ አደሩን እየፈተነ ያለና ምርቱ በሚፈለገው መጠን ማደግ አልቻለም›› በማለት አስረድተዋል።

 ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን  መስከረም 14 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You