የጥፋት ምንቸት ውጣ፤የልማት ምቾት ግባ

 ያለንበት ወቅት አዲስ ዘመን የባተበት አዲስ ተስፋ የፈነጠቀበትና ይህንኑ ብሩህ ተስፋ የምንሰንቅበት ነው። ምንጊዜም አዲስ ዓመት ሲመጣ ሰዎች በጎ በጎውን ያልማሉ ተስፋም ያጭራሉ። ክረምት ወጥቶ፣ አሮጌው ዓመት አልፎ መስከረም የጠባበት ምድር በልምላሜ መስኩን የሚያለብስበት፣ በአደይ አበባው የምትዋብበት፣ ገበሬው በክረምቱ የዘራው ዘር ፍያሬያማ መሆኑን አውቆ አረሙን እየነቀለ ዘሩ አጨዳ እንዲደርስ ተስፋ የሚያደርግበት ነው።

መስከረም ክረምቱ አልፎ መስኩ በልምላሜ፣ በአሸንዳ፣ በእንግጫ (በኦሮሚፋ ቡቂሳ ይባላል) በአደይ አበባ ተውባ የምትታይበት ነው። በርዕሳችን የጥፋት ምንቸት ውጣ ፤ የልማት ምቾት ግባ ያልነውም ይህንኑ ተስፋን ሰንቀን ነው። በአዲሱ ዓመት መናቆርና መቃቃር እንዲቀር መፋቀርና መጣመር እንዲሰምር በመመኘት መሆኑ ይሰመርበት።

አዲስ ዓመት ሲመጣ ችቦ ሲለኮስ ሴቶች የጎመን ምንቸት ይውጣ የገንፎ ምንቸት ይምጣ (ይግባ) እንደሚሉ የደስታ ተክለወልድ ሐዲስ የአማርኛ መዝገብ ቃላት ይገልፃል። ምንቸት እንስራ ፣ማሰሮ መሳይ አነስ ያለ ሁለት ጆሮ ያለው ምግብ ማብሰያ ነው። በገጠር ክረምት ሲገባ ጎመን፣ ድንች የመሳሰሉ ምግቦች በብዛት የሚበስሉበት ነው። በተለይ በክረምቱ እንደጎመን ዓይነት ቅጠላ ቅጠሎች ሁነኛ ምግብ ማባያ ሆነው በገበታ ይቀርባሉ። ይህም ብርዱን ለመከላከል ያግዛል።

በተለይ በክረምት ጎመን በብዛት በገጠር በየጓሮው ስለሚበቅል ወጣወጥ ለመሥራት የተቸገሩ ሁሉ ከጓሮ በክረምቱ ዝናብ የበቀለውን ጎመናቸውን ቀንጥሰው ምግባቸውን ያዘጋጃሉ። ከዚሁ በተጨማሪ ገበሬው ከክረምቱ እርሻ መልስ እቤቱ የስንዴ ፣የበቆሎ፣ የባቄላ ንፍሮ በብዛት እየበላ ብርዱን የሚረሳበት የእርሻውን ድካም የሚያስታግስበት ነው።

2016 ዓ.ም የህዳሴ ግድብ አራተኛ የውሃ ሙሌት በስኬት የተጠናቀቀበት፤ አብዛኛው የዓባይ ግድብ ሥራ ፍሬ አፍርቶ ዜጋው ሁሉ ተስፋ የሰነቀበት ነው። ዜጋው ከጨለማው ክረምት እየወጣ እንዳለው ሁሉ የዓባይ ግድብም ከኢትዮጵያም አልፎ ለጎረቤቶች ጭምር የኤሌክትሪክ ብርሃን የሚሆንበት፤ የሀገራቱን የምጣኔ ሀብት ትስስሩ የበለጠ የሚጠናከርበት እንደሚሆን ይታመናል ፤ ሀገሪቱም የውጭ ምንዛሪ የምታፈራበት በዚህም ድህነትን ለመዋጋት ለጀመረችው ጥረት አቅም የምትገዛበት ነው።

ስለ ዓባይ ግድብ ስናነሳ ወደ ኋላ ወደ ንጉሱ ዘመን ማቅናታችን አይቀርም። ንጉሡ / በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ /ዓባይን በመገደብ ለአንግሎ ኤጅብት፤ ማለትም በወቅቱ በእንግሊዝ ቅኝ ለነበረችው ግብፅና ሱዳን እናከራየዋለን የሚል ሃሳብ እንደነበራቸው። ይህንኑ እውን ለማድረግ የተለያዩ የውጭ ሀገር የጥናት ባለሙያዎችን በመጋበዝ በግድቡ ዙሪያ ጥናት ማስጠናታቸውን ሰነዶች ያስረዳሉ።

ንጉሡ ጥናቱን ቢያስጠኑም፤ለግንባታው የሚሆን ሀብት ብድርና እርዳታ ፈልገው ሊያገኙ አልቻሉም። ከዚህ የተነሳም ‹‹ እኛ ዓባይን እንገድብ ብንል አቅም የለንም። የውጭ ሀገራት ደግሞ ዓባይን ለመገደብ እርዱን ብንል ግብጽን ላላማስቀየም ፈቃደኛ አይሆኑም ። ቀጣዩ ትውልድ ግን በራሱ ንዋይ(ገንዘብ) ይገነባዋል›› በሚል ትንቢት መሰል ንግግር አድርገው ሥራው በይደር መቆየቱን መረጃዎች ያመላክታሉ።

ከ12 ዓመት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የዓባይን ግድብ ሰነዱ አቧራ አራግፈው ኢትዮጵያውያን በራሳቸው አቅም ግድቡን እንዲሰሩ መሠረት ጥለዋል፤ መሪዎች ሲለዋወጡ ግንባታው እንደ ዱላ ቅብብል ቀጥሎ ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዘመን ግንባታው ወደ ፍጻሜ እያመራ ነው። አራተኛው የግድቡ የውሃ ሙሌት በስኬት ተከናውኗል። ይህም ለሕዝቡ ትልቅ የአዲስ ዓመት ስጦታም ተደርጎ ተወስዷል።አዲሱን ዓመትም አድምቆታል።

በትምህርታችን ውሃ ሕይወት ነው ተብሎ ተደጋጋሚ ሲነገር እሰማ እንደነበር አስታውሳለሁ። በርግጥም ሰውን ጨምሮ እንስሳቱ አራዊቱ አዕዋፋቱ እፅዋቱ ውሃን ይሹታል፣ይጠጡታል ይጎነጩታል፣ ይተጣጠቡበታል፣ ይዋቡበታል ይዝናኑበታል፣ ይጽናኑበታል ይዋኙበታል፣ ይኖሩበታል (አዞንና ዓሣን ያስቧል)፤ይህን ስናስብ በርግጥም ውሃ ለሁሉም መሠረታዊ እንደሆነ እንረዳለን።

በኢትዮጵያ ካሉት 122 ቢሊዮን ሜትር ኩዩብ የገፀ ምድር ውሃ 70 በመቶ ዓባይ ወንዝ ተፋሰስ ላይ እንደሚገኝ መረጃዎች ያመለክታሉ። ከነባሩቹ ዘጠኝ ክልሎች ስድስቱ ለዓባይ የሚገብሩ ወንዞች አላቸው። ሀገሪቱ ካሉዋት በመስኖ ሊለሙ ከሚችሉ መሬቶች 2/3ኛው በዚሁ ተፋሰስ ውስጥ የሚገኝ ነው። ተፋሰሹ 40 ሚሊዮን ሕዝብ በዓባይ የሚኖር ፣ በሀገሪቱ የቆዳ ስፋት 37 በመቶ የሚሆነውን የሚሸፍን ጭምር ነው።

የግድቡ ግንባታ ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካም ሆነ በአፍሪካ ደረጃ ያላት ተፅዕኖ ፈጣሪነት እንዲጎለብት አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረውም ይታመናል ። ለሀገሪቱም ብሎም ለጎረቤት ሀገሮች ብርሃን ፈንጣቂ የዘመኑ ትልቅ ስጦታ ነው። በበጎ ህሊና ማየት ከተቻለ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዙሪያዋ ላሉት ለጎረቤት ሀገሮች የግድቡ የመጨረሻ የውሃ ሙሌት የምሥራች የሚሆን ነው።

በርግጥም ‹‹ድር ቢያብር አንበሳ ያስር›› እንደሚባለው ሀገርኛ ብሂል ኢትዮጵያውያን የዓባይን ግድብ በመገንባት ከድህነት የሚወጡበትን ፣የጠላት ምንጭ የሚያደርቅበትን፣ የውጭ ምንዛሪ የሚፈጥሩበትን፣ ድህነት የሚዋጉበትን ጥልቅ ሥራ ሠርተዋል። ይህም መጪው ጊዜ የጥፋት ምንቸት ውጣ የልማት ምቾት ግባ የምንልበት ለመሆኑ አንድ ማሳያ ነው።

ይቤ ከደጃች.ውቤ

አዲስ ዘመን  መስከረም 14 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You