
ሕዝባዊ እና ሃይማኖታዊ የአደባባይ ባህሎቻችን የእኛነታችን መገለጫ በዓለም ማኅበረሰብ ዘንድም የምንታወቀባቸው መለያችን ናቸው፡፡ ከቀናት በኋላ የምናከብራቸው የመስቀል ደመራና የኢሬቻ በዓላትም በሀገራችን በድምቀት ከሚከበሩ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ክብረ በዓላት መካከል ዋነኞቹ ናቸው፡፡
የመስቀል በዓል ትውፊታዊም መንፈሳዊም ነው። በመስቀል በዓል የርስ በርስ የመተሳሰብ፣ የአብሮነት፣ የፍቅር፣ የሰላም መገለጫ ሲሆን፤ በሥራም ሆነ በሌላ አጋጣሚ ተራርቆ የቆየ ሁሉ የሚገናኝበት፣ ዘመድ ከዘመዱ የሚጠያየቅበት፣ የሚረዳዳበት እንዲሁም አዲስ ጎጆ የሚቀለስበት ጊዜ መሆኑ ልዩ ቦታ ይሰጠዋል።
በተመሳሳይ የኢሬቻም በዓል ስለአብሮነት የሚሰበክበት፤ አብሮነት ከንግግር ባለፈ በተግባር የሚኖርበት እርቅና ሰላም የሚሰበክበት የአብሮነታችን ማጠናከሪያ ገመድ ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን ደስታና ችግሮችን በአብሮነት ያሳለፍንና የምናሳልፍ ሕዝቦች ነን። በታሪክ ከመቆራኘት ባለፈ የጋራ እሴቶች፣ ባህል እና አኗኗር ያለን ሕዝቦች መሆናቸንንም የምንገልጸው በነዚህ በዓላት ነው፡፡
እነዚህ እሴቶች የመላው ኢትዮጵያውያን እሴቶች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያውያን መገለጫ የሆነውን የአብሮነት እሴት በማጠናከር የሕዝብን አንድነት ማጽናት የቻሉ ናቸው፡፡ከእኛም አልፎ ለዓለም ሕዝብ ያስተዋወቁን ናቸው፡፡ ሁለቱ በዓላት ከጠንካራ ክረምት ወደ አዲስ ተስፋ በምንሸጋገርበት መስከረም ወር መከበራቸው ሁሌም የተለዩና በአዲስ መንፈስ አብሮነታችንን አጠንክረን ለመዝለቅ ዕድል ይሰጡናል፡፡
ሁለቱም በዓላት የአደባባይ በዓላት ከመሆናቸው ባሻገር በዩኔስኮ በማይዳሰሱ ቅርሶች የተመዘገቡ በመሆናቸው በተለይ ወደ መዲናችን አዲስ አበባ ከሁሉም የዓለማችን ክፍሎች የሚመጡ ቱሪስቶች እና ከአጎራባች ክልሎች በዓላቱን ለማክበር የሚመጡ ሰዎችን በፍቅር ተቀብለን በፍቅር መሸኘት ይጠበቅብናል፡፡
ኢትዮጵያ የበርካታ ባህላዊና ታሪካዊ ሀብት ባለቤት ብትሆንም እምቅ አቅሟን በተገቢው መንገድ ማልማትና ማስተዋወቅ ባለመቻላችን ከዘርፉ የምናገኘው ገቢ እንዳላደገ ይታወቃል፡፡ አንድነታችንን አጠናክረን እነዚህን ሀብቶቻችን ማልማት፣ መጠበቅና መንከባከብ አለብን። ይህ ደግሞ የቱሪዝም ዘርፍ እንዲነቃቃ ያደርገዋል። በተጨማሪም ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር ይቻላል።
እነዚህ ተዝቀው የማያልቁ ቱባ ባህሎቻችን የኢኮኖሚ ምንጭ ሆነው ለቀጣዩ ትውልድ እንዲሸጋገሩ ባህላዊ እሴቶቻችንን በደንብ አልምተን እንደ አንድ የቱሪዝም ገቢ ምንጭ በማድረግ ለሀገራዊ ብልጽግናችን መሠረት የምንጥልበት መሆን ይኖርባቸዋል።
ለዚህም እንደ መስቀል ደመራና ኢሬቻ ያሉ ቱባ ባህሎቻችን አከባበራቸው ሳይሸራረፍ ለትውልድ በማስተላለፍ ዘረኝነት፣ ጥላቻና ቂም በቀልን በማስወገድ የሀገራችንን ብልፅግና ለማረጋገጥ ሁሉም ዜጋ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል።
ሁለቱም በዓላት የአደባባይ በዓላት እንደመሆናቸው እና በርካታ የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚሳተፉባቸው ከመሆናቸው ባሻገር የሀገርን ገፅታ የሚገነቡ በመሆናቸው ለሰላምና ለፀጥታ ሁሉም ኃላፊነት አለበት፡፡ የመስቀል ደመራ እና የኢሬቻ በዓላትን ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ እሴቶቻቸውን ሳይለቁ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፉና በሰላም እንዲከበሩ በተለይም ወጣቶች ያለባቸው ኃላፊነት ትልቅ ነው፡፡
ስለሆነም መላው ኢትዮጵያዊ የመስቀል ደመራ እና የኢሬቻ በዓላት በድመቀት ሲከበሩ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ እሴቶቻቸውን ጠብቀው ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፉ እና በሰላም ተጀምረው እንዲጠናቀቁ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል፡፡ ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት በዓላቱ በድምቀት እንዲከበሩ ወጣቶች በየአካባቢያችን ለሰላምና ፀጥታ አስፈላጊውን ትብብር ማድረግ ይኖርባቸዋል። ለዚህም ከፀጥታ አካላት እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ሊሠሩ ይገባል፡፡ እነዚህ በዓላት በሕዝቦች መካከል ለዘመናት የዳበረውን የአብሮነት እሴት ለማስቀጠልና ትውልድ ለማስተላለፍ ጠቀሜታቸው የጎላ ነው።
በአዲሱ ዓመት ማግስት እነዚህን በዓላት ስናከብር ለአብሮነት ትኩረት በመስጠት እርስ በርስ ለመተባበር፣ ለመረዳዳት እና አንድነትን በማጠናከር መንፈስ ሊሆን ይገባል፡፡ ይህም በሠላምና በፍቅር የተሳሰረ ጠንካራ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ጠቀሜታው የጎላ መሆኑም አብሮነትን ማጠናከርና እሴቱንም በትውልዱ ውስጥ በማስረጽ የተጀመረውን ሀገራዊና ሁለንተናዊ የብልጽግና ጉዞ ማፋጠን ይገባል!
አዲስ ዘመን መስከረም 14 ቀን 2016 ዓ.ም