ከጎደፉ የስፖርት ታሪኮች ማህደር

ኢንስ ጌፔል እአአ ከ1980ዎቹ ስኬታማ ከሚባሉ የአጭር ርቀት ሴት አትሌቶች መካከል አንዷ ነበረች፡፡ ጀርመናዊቷ አትሌት ከምትታወቅበት ከ100 ሜትር እስከ 4በ 100 ሜትር የዱላ ቅብብል ውድድር ባለፈ በዝላይ ስፖርቶችም ስኬታማ ነበረች፡፡ ባስመዘገበቻቸው ሰዓቶች ምክንያትም ስሟ በክብረወሰን መዛግብት ላይ ሰፍሮ ቆይቷል፤ አሁን ግን ድምቀታቸው ወይቦ እንዲሰረዝ ተደርጓል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ‹‹በስፖርት አበረታች ንጥረ ነገሮች የተመረዙ ውጤቶች በመሆናቸው ነው›› ስትል ራሷ ምስክርነቷን ትሰጣለች፡፡

እአአ በ1980ው የሞስኮ ኦሊምፒክ በውሃ ዋና ውድድር የወርቅ እና ብር ሜዳሊያዎችን ያጠለቀችው ጀርመናዊት ዋናተኛ ፔትራ ቼንደርም ‹‹በክብር መዛግብቱ ላይ የሰፈሩት ተፍቀው መዝገቡ እንዲጸዳ እፈልጋለሁ›› ስትል ይህንኑ ሃሳብ ትደግማለች፡፡ እነዚህን አትሌቶች ጨምሮ 10ሺ የሚሆኑ ወንድ እና ሴት ስፖርተኞች በወቅቱ ሁለገብ የስፖርት የበላይነቱን ለመያዝ ሲባል በሚስጥር አበረታች መድሃኒቱን እንዲወስዱ ተደርገዋል፡፡ አትሌቶቹ ምንም በማያውቁት የአበረታች ንጥረ ነገር ተጠቂ ከመሆናቸው ባለፈ የልፋታቸውን ተነጥቀው ባዶ እጃቸውን ሊቀሩ የግድ ሆኗል፡፡ አሁንም ድረስ በሕይወት ያሉትም የደረሰባቸውን የጤና እክል በማስታመም ላይ ናቸው፡፡

ምስራቃዊቷ ጀርመን ግን ዜጎቿ ላይ በደል ትፈጽም እንጂ ተሳክቶላት እአአ በ1976ቱ የሞንትሪያል ኦሊምፒክ 40 የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብ ሩሲያን ተከትላ ሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችላለች፡ ፡ ከአራት ዓመት በኋላም በተመሳሳይ የሞስኮ ኦሊምፒክ ላይ በሰበሰበቻቸው ሜዳሊያዎች ብዛት ሁለተኛውን ደረጃ ልትይዝ ችላለች፡፡ ከስፖርቱ ዓለም ጥቁር ነጥቦች መካከል አንዱ የሆነው ይህ ታሪክ ምስራቅ ጀርመንን ከሁሉ በላይ የማድረግ ዓላማን ባነገቡ አላዋቂዎች የተፈጸመ ሲሆን፤ የስፖርትን ታሪክ ካጎደፉ ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳል፡፡

ነገሩ እንዲህ ነው፤ ጀርመን ለሁለት ከተከፈለች በኋላ ምዕራብ ጀርመን እአአ በ1960ዎቹ በስፖርት ተጽዕኖ ፈጣሪ ሀገር ነበረች፡፡ እአአ ከ1970 በኋላ ባሉት ዓመታት ግን ምስራቅ ጀርመን ድራማዊ የሆነ ለውጥ በማምጣት የውድድሮች ቁንጮ ሆና ብቅ አለች፡፡ በእርግጥ ነገሩ ሀገሪቷ በስፖርቱ ዓለም ብልጫ እንድታገኝ ከማድረግ ያለፈ ዓላማ የነበረው ሲሆን፤ ሁኔታውን ተጠቅሞ የበላይነትን የመገንባት ፖለቲካዊ ፍላጎትም ነበረበት፡፡ እአአ ከ1972ቱ ሙኒክ ኦሊምፒክ አንስቶም በምታስመዘግበው ውጤት ከእነ አሜሪካ እና ሩሲያ ጋር ለመሰለፍ በቃች፡፡ በወቅቱ 16 ሚሊዮን ህዝብ የሚወክለው ብሄራዊ ቡድኗ ኦሊምፒክን በመሰሉ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ያለምንም ተቀናቃኝ በውጤታማነታቸው ቁንጮ የሆኑትን አሜሪካንና ሩሲያን በመብለጥ ምስራቅ ጀርመንን ከድል ማማ ላይ ለማስቀመጥ ሲባል የስፖርቱ አመራሮች በስፖርቱ ዓለም እጅግ አስነዋሪውን ጉዳይ ፈጸሙ፡፡

በዚህ ሁኔታ ምስራቅ ጀርመን በስኬታማነቷ ዓመታን ካስቆጠረች በኋላ ለሁለት የተከፈለችው ሀገረ ጀርመን ተዋህዳ በመካከላቸው የተገነባው ግንብም ፈረሰ፡፡ ነገር ግን ጀርመን የሚለው ስም ከኦሊምፒክ የደረጃ ሰንጠረዥ አናት ላይ ለመታየት የወሰደበት 35 ዓመታት እንደሆነ ከዩኔስኮ ዲጂታል ላይብረሪ የተገኘው መረጃ ያብራራል፡፡ በ1970ዎቹና 80ዎቹ የሆነው ታውቆ በምርመራ ሊለይ የቻለውም ከዓመታት በኋላ ሲሆን፤ ተጠቂዎች የገንዘብ ካሳ ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት እንደነበራቸው የተረጋገጠባቸው ጥፋተኞች ደግሞ ለእስር ሊዳረጉ ችለዋል፡፡

የወቅቱ ምርጥ አትሌት የነበረችው ጌፔል ‹‹ሕይወታችንን ሰረቁ፤ አካላቶቻችንንም እንደ ተራ ዕቃ ቆጠሩት›› ትላለች ስለነገሩ ስታብራ፡፡ አትሌቶቹ አበረታች ንጥረ ነገሮቹን በሃኪሞች ትዕዛዝ ‹‹የቫይታሚን እንክብሎች ናቸው›› በሚል ነበር እንዲወስዱ የተደረገው፡፡ በጊዜ ሂደትም በዚህ አደገኛ ነገር ተጠቂ የሆኑ አትሌቶች የተለያዩ ለውጦችን በጡንቻዎቻቸው፣ በድምጻቸው፣ በጸጉራቸው እንዲሁም በተለያዩ የአካል ክፍሎቻቸው ላይ ማስተዋል ችለዋል፡፡

ለአብነት ያህል ሄዲ ክሪገር(አሁን ላይ አንድሬስ ክሪገር) የተሰኘችው በሴቶች የአሎሎ ውርወራ ተወዳዳሪ አትሌት በተሰጣት አበረታች ንጥረ ነገር በአካሏ ውስጥ በርካታ የወንድ ሆርሞን እንዲመነጭና በጡንቻዎቿም ላይ በርካታ ለውጦች እንዲታዩባት ምክንያት ሆኗል፡፡ ይኸው ሁኔታ ቀጥሎም በወቅቱ የአትሌቷ የቴስቴስትሮን የተባለ ሆርሞን በእጅጉ ጨምሮ በመገኘቱ ከተፈጥሮ ሕግ በተቃራኒ የወንድ ጡንቻና የተክለ ሰውነት ልትላበስ ችላለች፡፡ ሌሎች ሴት አትሌቶችም ወልደው መሳም እንዳይችሉና የተቀሩት ደግሞ በአፈጣጠራቸው ላይ እንከን ያለባቸውን ልጆች እንዲወልዱ ምክንያት ሆኗል፡፡

በዓለም ታሪክ ከታዩና በሀገር ደረጃ ከተከወኑ ስፖርታዊ ወንጀሎች መካከል በቀዳሚነት የሚቀመጥ ነው፡፡ ነገሩ አሁንም ድረስ ከስፖርታዊ የጸረ አበረታች ንቅናቄዎችና የግንዛቤ ማስጨበጫዎች ላይ እንደ ማሳያ የሚነሳ ሲሆን፤ በሰው ሕይወት ላይ ያደረሰው ጉዳት ግን በቃላት ሊገለጽ ከሚችለው በላይ ነው፡፡

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን መስከረም 13/2016

Recommended For You