ዛሬ መስከረም 13 ቀን በድምቀት የሚከበረው የወላይታ ህዝብ ባህላዊ እሴት የሆነው የጊፋታ በዓል የመላው ኢትዮጵያውያንም ኩራትና ሀብት ምንጭ ነው። ማስረጃዎች እንደሚጠቁሙትም፤ “ጊፋታ” የአዲስ ዓመት በዓል ሥነ ሥርዓት ነው። የዘመን መለወጫ ክብረ በዓሉን መላው ኢትዮጵያውያንም በወላይታ ዞን እና በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች በሚከበረው በዚህ በዓል በድምቀት እንደሚሳተፉ የወላይታ ዞን የባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊው አቶ ተሾመ ሀብቴ ነግረውናል።
የ2016 ዓ.ም የወላይታ ዘመን መለወጫ የጊፋታ በዓል ከወትሮ በላቀ ደረጃ እየተከበረ እንደሚገኝ የዞኑ አስተዳደር አሳውቋል። የዝግጅት ክፍላችን ያነጋገራቸው የመምሪያ ኃላፊው አቶ ተሾመ ሀብቴ በዓሉን በደማቅ ሁኔታ ለማክበር የሚያስችል የንቅናቄ መድረክ ከማዘጋጀት አንስቶ በየደረጃው ልዩ ልዩ ዝግጅቶች መደረጋቸውን ነው የሚገልጹት።
“ጊፋታ በወላይታ ህዝብ ዘንድ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ታላቅ የዘመን መለወጫ በዓል ነው” ያሉት ኃላፊው፤ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣና የብሔሩ ማንነት መገለጫ የሆነውን ይህ በዓል ዘንድሮ በተለየ መልኩ እየተከበረ እንደሆነ ያመለክታሉ።
የወላይታ ዞን የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ አሳምነው አይዛ በበኩላቸው ፤ የብሔሩ ታሪክ አዋቂ ሽማግሌዎችን መረጃዎች ጠቅሰው፣ ጊፋታ በብሔሩ ትልቅ ስፍራ ያለው ከማይዳሰሱ ቅርሶች ውስጥ የሚጠቀስ ታላቅ በዓል መሆኑን ነው የተናገሩት።
“ጊፋታ ማለት ‘ታላቅ ወይም መጀመሪያ’ እንደ ማለት ሲሆን በሌላ በኩል ጊፋታ ማለት መሻገር ማለት ነው” የሚሉት የዞኑ የመንግሥት ተጠሪ፤ በወላይታ የዘመን አቆጣጠር ጊፋታ የዓመቱ የመጀመሪያ ወር ስያሜ ነው። ይህም ከአሮጌ ወደ አዲስ፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን መሻገር የሚለውን ይገልጻል ሲሉም ያብራራሉ። ጊፋታ በወላይታ ህዝብ ዘንድ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ታላቅ የዘመን መለወጫ በዓል መሆኑንም አመልክተው፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣ የብሔሩ ማንነት መገለጫ መሆኑን ይናገራሉ።
የዝግጅት ክፍላችንም ዛሬ የሚከበረውን በዓል አስመልክቶ “የጊፋታን ታሪካዊ ዳራዎች፣ ባህላዊና የሥነ ፈለግ እውቀቶች አጠቃላይ ሥርዓቱ ምን እንደሚመስል” ለመዳሰስ ወድዷል። በዚህም የዘመን አቆጣጠሩን፣ ህብረተሰቡ በዓሉን ለማክበር የሚያደርገውን ዝግጅትና ከበዓሉ ጋር የተያያዙ የብሄረሰቡን እሴቶች እንዳስሳለን።
የዘመን አቆጣጠር
ይህንን ደማቅ “የወላይታ ብሔር የዘመን መለወጫ “የጊፋታ” በዓልን ሥርዓት፣ ምንነት እና አጠቃላይ ባህላዊ ሥነ ሥርዓቶችን አስመልክቶ የባህል የታሪክና ቅርስ ተመራማሪው አቶ አዳነ እንደሚገልጹት፤ የወላይታ ብሔር የራሱ የሆነ የዘመን መቁጠሪያ (calendar) አለው። በወላይታ ባህላዊ የዘመን አቆጣጠር መሠረት ጊፋታ የዓመቱ የመጀመሪያ ወር ስያሜ ነው። የዘመን መለወጫ በዓል ስናወሳ የዘመን አቆጣጠርን ነጥለን ማየት አንችልም፤ ምክንያቱም እያንዳንዱ የዘመን መለወጫ በዓል መነሻው የዘመን አቆጣጠር ነውና። የዓለም ህዝብ የጊዜ አቆጣጠር ሥርዓት የፀሐይ (solar) ፣ የጨረቃ (lunar) ወይም ሁለቱን አንድ ላይ የጨረቃና የፀሐይ (luni-solar) ኡደትን ተከትሎ እንደሆነ ይታወቃል።
“በዚህ ዙሪያ በተደረጉ ጥናቶች እንደተረጋገጠው የወላይታ የዘመን አቆጣጠር የግማሽ ጨረቃና የግማሽ ፀሐይ ኡደትን የተከተለ (Lunisolar) ነው” የሚሉት ተመራማሪው፤ ወላይታዎች ቀን (Gallassa) ብለው ሲጠሩ ፀሐይ ስትጠልቅ ወይም ሲመሽ ደግሞ ቃማ (Qammaa) ብለው ይጠራሉ። ቀንና ሌሊትን አንድ ላይ አንድ ቀን (Issi wontta) እንደሚባል ይገልፃሉ።
አቶ አዳነ እንደሚሉት፤ ወላይታዎች ሳምንታትን የሚቆጥሩት በአካባቢው የሚውለውን ትልቁን ገበያ መነሻ በማድረግ ነው። በዚህም ከአንዱ የገበያ ቀን እስከሚቀጥለው የገበያ ቀን ያለውን ጊዜ እንደ አንድ ሳምንት እንደሚቆጥሩት ያስረዳሉ። ይህም (Naa”u Giyaa) ወይም ሁለት ገበያ ማለት እንደሆነ ይናገራሉ።
ይህንን ጥበብ በምሳሌ ሲያስቀምጡት፤ በአንድ አካባቢ የሚውል ትልቁ ገበያ ቅዳሜ ከሆነ እስከሚቀጥለው ቅዳሜ ድረስ ያለውን ጊዜ የመጀመሪያውን ቅዳሜ አንድ ብሎ ቀጥሎ በሳምንቱ የሚመጣውን ቅዳሜ ሁለት በማለት ሁለት ገበያ (Naa”u Giyaa) በማለት እንደሚጠሩት ያስረዳሉ። በዚህም መሠረት አምስት ገበያ (Ichchashu Giyaa) አንድ ሙሉ የጨረቃ ኡደት አንድ ወር (Issi Aginaa) መሆኑን ይናገራሉ። ጨረቃዋ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየችበትን ቀን (Aginiyaa xeeraasu) በማለት አንድ ብሎ መቁጠር እንደሚጀምሩ ነው የሚገልፁት።
“በማህበረሰቡ ዘንድ ጨረቃ አዲስ ከመታየቷ በፊት ባሉት ሁለት ቀናት ውሃ ውስጥ ትውላለች የሚል እምነት አለ” የሚሉት የባህልና ታሪክ ተመራማሪው አቶ አዳነ፤ እነዚህ ቀናት ጤሮ ጨገና (xeero ceggennaa) በመባል እንደሚታወቁ ይናገራሉ። ይህም ህብረተሰቡ የጨረቃን መውጣት በመጠባበቅ ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጅት የሚያደረግበት ወቅት መሆኑን ያስረዳሉ።
የአባወራዎች ተግባር
“የጊፋታ በዓል ዝግጅት የሚጀምረው በቁጠባ ‘Qoraphphuwaa’ነው” የሚሉት የታሪክ የባህልና ቅርስ ተመራማሪው አቶ አዳነ፤ በጊፋታ ዕለት አባት ልጁን አስከትሎ በሬ ወደሚታረድበት ቤት በመሄድ ያደለቡትን በሬ በጋራ በማረድ በመደብ በመደብ እንደሚከፋፍሉ ይገልፃሉ። በዚህ ሁኔታ ከሁሉም የሥጋ ብልቶች ትንሽ ትንሽ ቆርጠው በባለተራው ቤት በተዘጋጀው ማባያ ማለትም ቆጮ፣ቂጣ፣ዳጣ በርበሬ ጋር ከቅርጫው አባላት (Amuwaa) ጋር ስለሚቋደሱ ይህም አንድነትን፣ፍቅር ማብሰሪያ ተደርጎ ይወሰዳል። ከዚያም የየራሳቸውን ድርሻ ሥጋ ከመውሰዳቸው በፊት ለመጪው ዓመት በሬ መግዣ አሁን በታረደው በሬ ቆዳ ላይ ቁጠባ ይጀምራሉ።
ይህም ሥርዓት የጊፋታ በዓል ከተሸኘ በኋላ በየሳምንቱ እንደሚቀጥል የሚናገሩት ተመራማሪው፤ በመጨረሻም ዓመቱ ሲጠናቀቅ ተሰብስበው በሬ ከገዙ በኋላ የሚተርፈውን ገንዘብ ለቤት ውስጥ ወጪ እንደሚጠቀሙት ያስረዳሉ። ተጨማሪ የአባወራዎችን ተግባር መኖሩን የሚገልፁት አቶ አዳነ፣ ሥርዓቱን እንደሚከተለው በዝርዝር ያቀርቡታል።
የተለያዩ የሰብል ዓይነቶችን በዘር ወቅት መዝራት፣ መሰብሰብና ለጊፋታ ለይቶ ማስቀመጥ፣ በዓሉ ሲቃረብ ለልጆች አዳዲስ ልብሶችን መግዛት፣ ለማጣፈጫና ለቅመማ ቅመም መግዣ የሚሆን ገንዘብ ለእናቶች መስጠት እና ለጊፋታ የሚታረድ በሬ መግዛት የአባወራ ተግባራት ናቸው። ለእርድ ቀን ከሁለት ወር በላይ የሚሆን ጊዜ ሲቀረው በሬ በመግዛት እስከ እርድ ቀን ድረስ ለሚንከባከብ ተረኛ (Ariyawaa) ይሰጣል። ለበሬው ምቹ ቦታ ቀድሞ በዚህ ቤት እንዲዘጋጅ ይደረጋል።
የጊፋታ በሬ እንደሙሽራ ስለሚታይ ሰው እንዳያየው የተለየ ጋጣ ተዘጋጅቶ ሁሉም ቀዳዳዎች ከምግብ መስጫ ጠባብ በር ውጪ በደረቅ የኮባ ቅጠል (Qonashiyaa) ሙሉ በሙሉ ይሸፈናል። የአሙዋ አባላትም ስኳር ድንች፣ የበቆሎ አገዳ፣ በቆሎ እና የመሳሰሉትን በልጆቻቸው እያሸከሙ ወይም በአህያ እየጫኑ በየተራ በማምጣት ይቀልባሉ። ቀጥሎም በየ 15 ቀኑ ተሰብስበው በሬውን ወደ ውጪ በማውጣት ያለበትን ደረጃ በማየት በጣም እየወፈረ ከሆነ ተንከባካቢውን እያሞገሱ አስተያየት ይሰጣሉ፤ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ የጊፋታ በሬ ይቀለባል።
ሌላው በአባቶችና በወንድ ልጆቻቸው የሚከናወን የአካባቢ ጽዳትና የቤት እድሳት ሥራ ነው። ይህም በወላይታ ብሔር አዲስ ዓመት የመታደስ ምልክት ስለሆነ ሰዎች የቤታቸውን የሳር ክዳን በአዲስ ሳር መቀየር፣ በቤት ውስጥ ያረጁትን ነገሮች ከውጪ ደግሞ በቤቱ ዙሪያና በአካባቢው የሚገኙ ቆሻሻዎችን በማጽዳት በዓሉን እንደሚቀበሉት አቶ አዳነ ይናገራሉ።
የእማወራዎች ተግባር
“እማወራዎች ለጊፋታ በዓል ከሚያደርጓቸው ዝግጅቶች የመጀመሪያው ቁጠባ (qoraphphuwaa) ነው፤ ይህም የቅቤ እቁብ መጀመር ነው” የሚሉት ተመራማሪው፤ በዚህም መሠረት ዓመቱን በሙሉ የቆጠቡትን በጊፋታ ሰሞን ሁለተኛ ሳምንት ገበያ (Bobbooda) አጥቢያ በቅቤ ዕቁብ ሰብሳቢያዋ ቤት የቅቤ ቡና ከጠጡ በኋላ የየድርሻቸውን ተከፋፍለው እንደሚወስዱ ይናገራሉ። ጊፋታ ካለፈ በኋላም ለቀጣይ ዓመት በየሳምንቱ ቁጠባውን እንደሚቀጥል ይገልፃሉ።
እናቶች ከሰኔ ወር መጨረሻ አካባቢ ጀምሮ ለተለያዩ ባህላዊ ምግቦች ማለትም “ቆጮ፣ ሙቹዋና ባጪራ” በመባል ለሚታወቁ ባህላዊ ምግቦች የሚሆኑ የደረሱ እንሰቶችን ከጓደኞቻቸውና ከሴት ልጆቻቸው ጋር ሆነው በመፋቅ ዝግጅት እንደሚያደርጉ የሚናገሩት የባህል ተመራማሪው፤ ከዚህም በተጨማሪ ዳጣ በርበሬ፣ የተለያዩ መጠጦች ማለትም ቦርዴ፣ ጠላ፣ ጠጅ፣ ቃሪቦ እና ወተት በትልቅ እንስራ እንደሚዘጋጅ ያብራራሉ። በተጨማሪ “ጋዚያ” በመባል ለሚታወቀው ባህላዊ ጨዋታ የሚሆን ሎሚ ገዝተው በቀዝቃዛ ቦታ ያስቀምጣሉ፤ የተለያዩ መዋቢያ ጌጣጌጦችን እንደሚገዙ፤ ለምግብነት የሚውሉ የተለያዩ የእህል ዓይነቶችን ገዝተው እንደሚያጠራቅሙ ይናገራሉ።
“የዳጣ በርበሬ በጊፋታ የቤተሰብ የሥራ ክፍፍል በጣም የጠበቀ በመሆኑ ሁሉም የራሱን ሥራ ያለማንም አዛዥ ወቅቱ ሲደርስ ያከናውናል” የሚሉት ተመራማሪው፤ ወጣት ወንዶች የጉሊያ እንጨት ከመቁረጥና ከማቆም ጀምሮ ለከብቶች ሳር በማጨድና በመከመር፣ እንጨት በመፍለጥ ለበዓሉ ጊዜ ከማስቀመጥ በተጨማሪ ከዘር እና ከአጨዳ ወቅት ጀምሮ ሁሉንም የጊፋታ ዝግጅት ሥራዎችን ከአባቶቻቸው ጎን በመሆን እንደሚከውኑ ይገልፃሉ። ልጃገረዶች እንሶስላ ከመሞቅ ፣ የጋዚያ ጨዋታ ከመጫወት ከመሳሰሉ በግል ከሚፈፅሟቸው ተግባራት በተጨማሪ በሁሉም ሥራዎች እናታቸውን እንደሚደግፉ ያስረዳሉ።
የባህል፣ የታሪክና ቅርስ ተመራማሪው የጊፋታ ክብረ በዓል ተጨማሪ እሴቶች እንዳሉት ጠቁመው፣ ከእነዚያ ውስጥ እዳ መክፈል፣ የቤት እድሳትና የአካባቢ ፅዳት፣ የመንፃት ሥርዓት እንዳገኙበት ይናገራሉ። እነዚህን እሴቶች ከዚህ እንደሚከተለው በዝርዝር ያብራሯቸዋል።
ዕዳ መክፈል
ከጊፋታ በዓል ቅድመ ዝግጅቶች አንዱ ያደረ ዕዳ መክፈል ነው። በወላይታ ብሔር ሰዎች ከዕዳ ጋር አዲሱን ዓመት አይቀበሉም። ምክንያቱም የግለሰብም ሆነ የመንግሥት ዕዳ ተሸክመው አዲሱን ዓመት የሚቀበሉ ከሆነ ዓመቱን በሙሉ በረከት አይኖረውም ተብሎ ይታመናል። በሌላ በኩል ደግሞ እዳውን ለመክፈል ዳተኛ የሆነ ሰው በማህበረሰቡ ከፍተኛ ነቀፌታ ይደርስበታል። ስለሆነም አንድ ገንዘብ ወይም እህል ያስፈለገው ሰው ከሌላ ሰው ሲበደር አበዳሪው ይህ ዕዳ እጅግ ቢዘገይ እስከ ጊፋታ በዓል ድረስ እንደሚመለስ በጣም እርግጠኛ ሆኖ የሚያበድረው በመሆኑ በብሔሩ ከጊፋታ በፊት ዕዳን አሟጦ መክፈል ነባር ባህል ነው።
የቤት እድሳትና የአካባቢ ጽዳት
የጊፋታ በዓሉ እየተቃረበ ሲመጣ ማህበረሰቡ አዲሱን ዓመት አዲስ ቤት በመሥራት ወይም አሮጌውን ቤት በማደስ መቀበል ነባር ባህል ነው። በመሆኑም ነባሩን አሮጌ ቤት ፈርሶ አዲስ የሚሠራ ከሆነ በደቦ ወይም በማህበር ያከናውናሉ። ነገር ግን የቤት ዕድሳት ብቻ ከሆነ አባወራው ከቅርብ ጓደኞቹ ወይም ለአቅመ አዳም ከደረሱ ልጆቹ ጋር ያከናውናሉ። በአሮጌው ዓመት ማብቂያ ቤታቸውን፣ ጓሯቸውንና አካባቢያቸውን በማጽዳት በዓሉን በተሟላ ንጽህና ይቀበላሉ።
የመንፃት ሥርዓት
በወላይታ ነባር ባህል የዘመን መለወጫ በዓሉ እንደነገ ሊከበር ማለትም (በ2016 ዓ.ም በ12 ቀን ቅዳሜ ለእሁድ አጥቢያ) እኩለ ሌሊት ላይ አዲሱን ዓመት ከመቀበላቸው በፊት ሁሉም የማህበረሰቡ አባላት ከአሮጌው ዓመት እድፍና ቆሻሻ ጋር አዲሱን ዓመት አንቀበልም” በሚል እምነት ውሃ አሙቀው ገላቸውን ይታጠባሉ። ምክንያቱም ወላይታዎች ሁልጊዜ አዲሱን ዓመት የሚቀበሉት በሽታ፣ ረሃብ፣ ድርቅ የሌለበት መልካም ዝናብ የሚጥልበት፣ መልካም ነፋስ የሚነፍስበት፣ የጥጋብ ዓመት እንዲሆን ከአለፈው ዓመት ኃጥያት መንጻት አለብን ብለው ስለሚያምኑ ነው። ለህዝቡ አዲስ ዓመት ሁል ጊዜ አዲስ ተስፋ ይዞ ስለሚመጣ ንፁህ ሆነን መቀበል አለብን የሚል የፀና እምነት አለ።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም