በኢትዮጵያ በርካታ የስፖርት ዓይነቶች ቢዘወተሩም አብዛኞቹ በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ በክለብ ደረጃ አይዘወተሩም። በኢትዮጵያ እምቅ አቅም እንዳለ በሚታመነው የውሃ ዋና ስፖርት ከእነዚህ መካከል አንዱ ነው። ክለቦች ተደራጅተው የእርስ በእርስ ውድድሮች ማድረጋቸው ለስፖርቱ ማደግና ተወዳዳሪ መሆን የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የላቀ እንደሆነ ይታመናል። ይህንን ከግምት በማስገባትም ሀገር አቀፍ የውሃ ዋና ስፖርት ክለቦችን የመቋቋም ሃሳብን እውን ለማድረግ የኢትዮጵያ ውሃ ስፖርቶች (ኢትዮጵያን አኳቲክስ) ፌዴሬሽን ወደ እንቅስቃሴ ተገብቷል።
በኢትዮጵያ ስፖርት ፖሊሲ መሰረት አንድ ስፖርት ፌዴሬሽን ተብሎ ሊጠራ የሚችለው በአምስትና ከዚያ በላይ ክልሎች ወይም ከተማ አስተዳደሮች ሲዘወተር ነው። በተመሳሳይ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ፌዴሬሽን የመሆን ህጋዊ እውቅና የሚያገኙት በትንሹ አምስት ክለቦችን ማቋቋም ሲችሉ ነው። በመሆኑም በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተጠቀሰውን ያህል ክለቦች እንደሚኖር የኢትዮጵያ ውሃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን እምነት ነው።
ፌዴሬሽኑ ይህንን ለማጠናከርና የረጅም ጊዜ እቅዱ የነበረውን የክለብ ምስረታ ወደ መሬት ለማውረድ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ መድረስ ችሏል። በዚህም መሰረት በፌዴሬሽን ደረጃ የክለብ ምስረታ ለማድረግ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በሚደረገው ግንኙነት መልካም የሚባሉ ምላሾችን አግኝቷል። ክለብ በማቋቋም ወደ ተግባር መግባት የቻሉ እና በሂደት ላይ ያሉ ክለቦችም እንዳሉም ተጠቁሟል። መከላከያ እና አየር ኃይል ክለብ ለማቋቋም ወደ እንቅስቃሴ ከገቡ ተቋማት በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ። መከላከያ ክለብ ለማቋቋም ሥራ የጀመረ ሲሆን አየር ኃይል ከፌዴሬሽኑ በቀረበለት ጥያቄ መሰረት ክለብ ለማቋቋም በጎ ምላሽ መስጠት ችሏል።
የኢትዮጵያ ውሃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት መሠረት ደምሱ ‹‹የአንድ ስፖርት ማደግ ዋና መሰረቱ የጠንካራ ክለቦች መኖር ነው›› ሲሉ ይጠቁማሉ። በየክልሉ አምስት ክለቦች ይኖራሉ ተብሎ ቢታሰብም በተግባር ለማረጋገጥና የቁጥጥር ስራውን በአንዴ ለማጥራት ግን አስቸጋሪ ነው። ፌዴሬሽኑ የክለብ ውድድሮችን ለማድረግ ጥረት በሚያደርግበት ወቅት የሚፈለገውን ያህል ክለብ ከክልል ማግኘት ባለመቻሉም ሀገር አቀፍ ክለቦችን ለመመስረት እንዳስገደደውም ይናገራሉ። በሚፈለገው መጠንና ብቃት ክለቦች እየተሳተፉ ባለመሆናቸውም ፌዴሬሽኑ እነዚህን የክልል ክለቦች ወርዶ በተገቢው መልኩ ቁጥጥር ለማድረግ እቅድ ይዟል። ክለቦች በምንያህል ደረጃ እንደ ተጠናከሩ፤ ከሌሉም ፌዴሬሽን ለመባል ያለውን መስፈርት ማሟላታቸውን የማጣራት ሥራ ይከናወናል።
በፌዴሬሽን ደረጃ ክለብ ለማቋቋም ጠንካራ የሆነ እምነት በመኖሩ የተለያዩ ተቋማት ጋር ደብዳቤዎችን በመለዋወጥ ክለቦችን ለማቋቋም ሂደቱን የጀመሩ ተቋማት መኖራቸውንም ፕሬዚዳንቷ ያስረዳሉ። ፌዴሬሽኑ በያዘው እንቅስቃሴ በመቀጠልና በማስፋት በሀገር አቀፍ ደረጃ ጠንካራ የውሃ ዋና ክለቦች የሚመሰረቱበትን ሁኔታ በማቀድ እየሰራም ይገኛል። እነዚህን በፌዴሬሽን ደረጃ የሚቋቋሙ ክለቦች ለመመስረት ተቋማት ለስፖርቱ የሚያስፈልገውን መሰረተ ልማት ማሟላት ይኖርባቸዋል። ክለብ በሚመሰረትበት ወቅት በግል ማሟላት ባይቻልም ስፖርተኞቹን ተከራይቶ የሚያሰሩበት የውሃ ዋና ገንዳ ሊኖራቸውም ይገባል። በተጨማሪም አሰልጣኝ መቅጠርና ለስፖርተኛው ደመወዝ የሚከፍሉበት እና ለስፖርቱ የሚያስፈልገውን ቁሳቁስ ማሟላት ለክለብ ምስረታው እንደ መስፈርት መቀመጡንም ፕሬዚዳንቷ አስረድተዋል።
ክለቦቹ ከተቋቋሙ በኋላ አዲስ የውድድር ሥርዓት በመፍጠር የክለቦች ውድድር ይካሄዳል። እስከ አሁን በነበረው የውድድር ሥርዓት የክለብና የክልል ውድድር በአንድ ላይ ይከወን ነበር። በዚህና በውድድሩ አለመጠናከር ምክንያትም ክልሎቹ ለመሳተፍ ፍቃደኛ አልነበሩም። ይህም የተጠናከረ ክለብ ያለመኖሩ ዋና ማሳያ ጭምር ነው። ውድድር መስፋቱ ጥሩ ስፖርተኞችን ለማፍራትና ስፖርቱን ለማስፋት ቁልፍ ጉዳይ በመሆኑ ፌዴሬሽኑ ውድድሮችን ለማስፋት ቁርጠኛ እንደሆነም ፕሬዚዳንቷ አስረድተዋል። ሆኖም ከመሰረተ ልማትና ከፋይናንስ ጋር የተያያዙና የክልሎችና ክለቦች ፌዴሬሽኑ በሚፈልገው ልክ እንዳይሰራ ማነቆ ሊሆንበት ችሏል። በቀጣይም ከክልሎቹ ጋር በመነጋር ክለቦቹ የሚጠናከሩበትንና በሀገር አቀፍ ደረጃ ትልልቅ ክለቦች የሚቋቋሙበትን ሁኔታ በመፍጠር የሚሰሩ ይሆናል።
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን መስከረም 12 ቀን 2016 ዓ.ም