የዓባይ ግድብ የከፍታ ላይ ከፍታዎች

የዓባይ ግድብ ግንባታ ብዙ ፈተናዎች አልፎ እነሆ በየጊዜው የምስራች ማሰማቱን ቀጥሏል። ባለፉት አመታት የግድቡን ሦስተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ዜና ሰምተናል፤ በ2014 ዓ.ም ሚያዝያ ወር ላይ ደግሞ በአንድ ተርባይን ኃይል ማመንጨት በመጀመሩ ብርሃን ለመሆን መንደርደሩን ተመልክተናል፤ ሌላው ተርባይንም እንዲሁ ወደ ኃይል አመንጪነት ተሸጋግሮ ብርሃን የመሆን የመጨረሻ ህልሙን በድልብስራቱ አብስሮናል። በቅርቡም አራተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቅ እንደቻለ ተመልክተናል።

መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም በአምስት ቢሊዮን ዶላር (80 ቢሊዮን ብር) የተጀመረው የዓባይ ግድብ ፕሮጀክትን ለማጠናቀቅ የተያዘለት የጊዜ መርሐ ግብርም አምስት አመት እንደነበር ይታወሳል። የግድቡ የግንባታ ሂደትም በርካታ ፈተናዎችን በማለፍ አስራ ሁለት አመታትን አስቆጥሯል። ይሁንና ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ከአምስት ዓመታት ወዲህ ግንባታው እየተፋጠነ ይገኛል። በመሆኑም ግድቡ ከከፍታው ማማ ከፍ ብሎ መታየት ችሏል። በቅርቡም አራተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ተጠናቅቋል። ግድቡ የያዘው የውሃ መጠንም ከ42 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ ነው።

በኢትዮጵያውያንና መንግሥታቸው አንጡራ ሀብት የሚገነባውና ለታለመለት ዓላማ መዋል የጀመረው ይህ የዓባይ ግድብ ከአፍሪካም ከዓለምም ግዙፍ ፕሮጀክቶች አንዱ ከመሆኑም በላይ የኢትዮጵያውያን እንዲሁም የመንግሥታቸው ራእይ ውጤት በመሆኑ ኢትዮጵያውያን በሙሉ እንደ ዓይናቸው ብሌን ይሳሱለታል።

በአዲስ አመት ዋዜማ አራተኛውን የውሃ ሙሌት ምክንያት በማድረግ ግድቡ በሚገኝበት ስፍራ አንድ ሁነት መካሄዱ ይታወሳል። የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጨምሮ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች በተገኙበት በዚህ ሁነት ላይ የዓባይ ግድብ ወግ ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ግድቡ የደረሰበትን ደረጃ፣ የታለፉ ፈተናዎችን፣ በርካታ ትርጉሞች ያሉት መሆኑን አብራርተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ 42 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ውሃ መያዙ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ውስጥ በተፈጥሮ ያሉ ጣና፣ አብጃታ፣ ላንጋኖ፣ ሻላን ጨምሮ ሁሉም ሐይቆች ተደምረው አሁን ያላቸው አቅም 70 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ነው። እስካሁን በሀገራችን ትልቁ ሐይቅ ጣና ነበር። አንድ ሰው ሰራሽ ግድብ በተፈጥሮ ኢትዮጵያ እስካሁን ያሏትን ሐይቆች በሙሉ የሚበልጥ የውሃ ክምችት ያለው ሆኖ ይታያል። ከጣና አኳያም ሲታይ ጣና 33 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ ይይዛል። የሕዳሴ ግድቡ አሁን በደረሰበት 42 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ የመያዝ አቅም፣ ከጣና በ9 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ይበልጣል። በሚቀጥለው ዓመት ደግሞ ጣናን እጥፍ ይሆናል። ይህም ሰው በእውቀቱ በገንዘቡ በአቅሙ ሁሉ ቢተባበር ምን ሊያደርግ እንደሚችል የሚያመላከት ነው በማለት አብራርተዋል።

‹‹ግድቡ ከፍተኛ አቅም ያለው የኤሌክትሪከ ኃይል የሚያመነጭ በመሆኑም ለኃይል ምንጭ፤ ለቤት ውስጥ ሥራ፤ ኢንዱስትሪ ለማስፋፋት ጉልህ ፋይዳ አለው›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የኃይል ምንጭ ብቻም ሳይሆን አካባቢን የማይበክል ንጹህና ታዳሽ የኃይል ምንጭ መሆኑን ጭምር አንስተዋል።

ዓለም ላይ በርካታ ኢንዱስትሪዎች የኢነርጂ ምንጫቸው ንጹህ ባለመሆኑ የተነሳ ከአካባቢ ጋር ተያይዞ በርካታ ክሶች እና ወቀሳዎች የሚነሱባቸው መሆኑን አመላክተው፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግን ኃይል ከማመንጨቱ ባሻገር እነዚህን ችግሮች የሚያስቀር በመሆኑ ተፈላጊ እንደሚያደርገው ገልጸዋል።

የዓባይ ግድብ የተገነባበት አካባቢ ከዚህ ቀደም ሞቃታማ እና በረሃማነት የበዛበት እንደነበርም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውሰው፣ አሁን ግን ግድቡ ውሃ መያዝ ከጀመረ ወዲህ በከፍተኛ ደረጃ አካባቢውን እያቀዘቀዘውና ንጹህ እያደረገው መሆኑን ተናግረዋል። አካባቢው ተፈጥሯዊ ውበት እንዲያገኝ ማስቻሉንም ገልጸዋል። ‹‹የዱር እንስሳት ወደ አካባቢው ይመላለሳሉ፣ የተለያዩ እፅዋቶች ያድጋሉ፣ ከኢኮ ቱሪዝም አኳያም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንደሚኖረው አብራርተዋል።

ግድቡ የፈጠረውን የሥራ አቅም አስመልክተው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲያብራሩ፤ በግንባታው ስፍራ ከሚሠሩ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሠራተኞች መካከል በትንሹ 99 በመቶው ሠራተኛ ኢትዮጵያዊ እንደሆኑና አብዛኛዎቹ ሠራተኞችም ወጣቶች መሆናቸውን ነው የጠቀሱት።

ሠራተኞቹ በግድቡ ለዓመታት ያገለገሉ እና ደጋግመው እየሠሩ በተግባር መማር የቻሉና ትልቅ እውቀት የጨበጡ መሆናቸውን አመልከተው፣ ይህ አቅም መበተን የሌለበት መሆኑን ተናግረዋል። መሰል ግድቦችን በሀገራችንም ሆነ በአፍሪካ መገንባት የሚያስችል ትልቅ አቅም የተፈጠረበት አጋጣሚ እንደሆነም ተናግረዋል፤ ለሀገራችንም ለሌሎች ሀገሮችም አዳዲስ ግድቦችን ለመሥራት የሚተርፍ አቅም እንዳይበተን፣ እንዳይበላሸ መጠበቅ ይገባልም በማለት ሂደቱ ግድብ ብቻ ሳይሆን አብሮ የተፈጠረው አቅምም አለ ብለዋል።

ግድቡ በእኔ እምነት ለብዙ አፍሪካውያን ዳግም ዓድዋ ነው። የነፃነት ምልክት፣ ራስን የመቻል፣ ከልመና የመገላገል፣ የልማት፣ የብልጸግና፣ የዕድገትና የአልንበረከክም ምልክት መሆኑን ጠቅሰው፣ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለብዙዎች ትምህርት እንደሚሆነም አብራርተዋል።

የግድቡ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ በወቅቱ ግድቡ ከዲፕሎማሲ፣ ከቱሪዝም፣ ከኢንቨስትመንት፣ ከሀብትና ከዓሣ ልማት አኳያ ያለውን ፋይዳ አብራርተዋል። እርሳቸው እንዳሉት የዋናው ግድብ አፈጻጸም 98 በመቶ ደርሷል። የሰድል ዳም ወይም የኮርቻ ግድብ ግንባታ ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል። አጠቃላይ የግድቡ ግንባታ አፈጻጸም በአሁኑ ወቅት 93 በመቶ ላይ ደርሷል።

የግድቡ የውሃ ሙሌት ባለፉት ሦስት አመታት ለሦስት ጊዜ የተካሄደ ሲሆን፣ ባሳለፍነው ሳምንት ደግሞ በ2016 ዘመን መለወጫ ዋዜማ አራተኛው ሙሊት ተከናውኗል። በመጀመሪያ ዓመት ሙሊት አምስት ቢሊዮን ኪዩቢከ ሜትር ውሃ መያዝ የታቸለ ሲሆን፣ በሁለተኛው ዓመት ሙሊትም ሦስት ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር አንዲሁም በሦስተኛ ሙሊቱ ዘጠኝ ቢሊዮን ኪዩቢከ ሜትር ውሃ መያዝ ተችሏል። ከሰሞኑ የተደረገው አራተኛ ዙር ሙሊት አጠቃላይ የተያዘውን የውሃ መጠን 42 ቢሊዮን ኪዩቢከ ሜትር አድርሶታል።

አጠቃላይ የግድቡ ሁኔታ ሲታይም ግድቡ 98 በመቶ ተጠናቋል ሲባል ግድቡ ግራና ቀኝ አለው፤ የመካከል አካልም አለው። የግራና ቀኙ ከ645 እስከ 635 የሚሆን ደረጃ ያለው ሲሆን ይሄንን ለማጠናቀቅም ከ9 እስከ 10 ሜትር ብቻ ይቀራል። መካከለኛው 20 ሜትር ብቻ ይቀራል።

የዛሬ ዓመት በዚህ ጊዜ የግድቡ መካከለኛው ክፍል ተጠናቅቆ እናያለን ያሉት ኢንጂነር ክፍሌ፣ ከዚህ በኋላም የሚሠራው ቀሪ ሥራ ግራና ቀኙን የሚያገናኝ ድልድይ ብቻ መሆኑንም ጠቁመዋል። ከአራት ወራት በኋላ የግድቡ ግራና ቀኝ መጨረሻ ላይ 645 ሜትር ላይ ደርሶ እናገኘዋለንም ብለዋል።

በሌላ በኩል የኤሌክትሮ ሜካኒካል ተከላዎች እየተከናወኑ እንደሆነ ጠቅሰው፣ አሁን በሁለት ዩኒት እየመነጨ ያለው በ2016 ተጨማሪ አምስት ዩኒቶችን በማስገንባት ወደ ሰባት ዩኒቶች ለማድረስ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን ነው ያስረዱት።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው ሰሞኑን ከመገናኛ ብዙኃን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ይህንኑ አረጋግጠዋል። በዓባይ ግድብ ከዚህ በፊት ወደ ሥራ ከገቡት ሁለት ተርባይኖች በተጨማሪ በ2016 ዓ.ም አምሥት ተርባይኖች የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያመነጩ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህም ኃይል የሚያመነጩት ተርባይኖች ቁጥር ሰባት እንደሚደርስም ነው ያመለከቱት።

እሳቸው እንዳሉት፤ የሰባቱ ተርባይኖች ኃይል መጠን የበለስ፣ የግልገል ጊቤ አንድና ሁለት እንዲሁም የተከዜ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ከሚሰጧቸው አማካይ አንድ ሺህ 180 ሜጋ ዋት ተመጣጣኝ ወይም የሚበልጥ ኃይልን ለማመንጨት ያስችላል።

ይሁንና ከአቀማመጡና ከውሃ ፍሰቱ አኳያ የአምስቱ ተርባይኖች ኃይል የማመንጨት አቅምን አሁን መግለጽ እንደማያስችል የገለጹት ሚኒስትሩ፤ የግድቡ ግንባታ ሲጠናቀቅ በ13ቱ ተርባይኖች አምስት ሺህ 150 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይልን ወደ ብሔራዊ የኃይል ቋት እንደሚቀላቀል ጠቁመዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ፤ በግድቡ የሚገጠሙት ተርባይኖች በአማካይ ከ375 በላይ ሜጋ ዋት ኃይልን ያመነጫሉ ተብሎ ይጠበቃል። በቀጣዮቹ ስድስት ዓመታት የኢኮኖሚውን ፍላጎት ማሟላት የሚችል ኃይል ከውሃ፣ ከንፋስ፣ ከፀሐይ እና ከከርሰምድር እንፋሎት ለማመንጨት ታቅዷል።

በአሁኑ ወቅት በሀገር አቀፍ ደረጃ ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም አምስት ሺህ 420 ሜጋ ዋት ደርሷል። ይህንን ቁጥር የሕዳሴው ግድብ እጥፍ ያደርገዋል። እዚህ ላይ የኮይሻና ሌሎች የኃይል ምንጮች ሲጨመሩበት በቀጣይ ስድስት ዓመታት የኢትዮጵያ ኃይል የማመንጨት አቅም 17 ጊጋ ዋት ይደርሳል ነው ያሉት።

የዘንድሮውን ሙሊት ልዩ የሚያደርገው ባለፉት ሦስት ዓመታት መያዝ የተቻለው 22 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ በመሆኑና በአራተኛው ዙር ሙሊት 20 ቢሊዮን ሜትር ኪዩበ ውሃ መያዝ በመቻሉ ነው። በዚህም 42 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ላይ መደረሱ ትልቅ ስኬት እንደሆነ ሚኒስትሩ አንስተው፤ ከአሁን በኋላም በዓባይ ግድብ የሚሞላው ትርፍ ውሃ የሚመጣው ከላይ በኩል ሳይሆን እኛ በሚገባ ከሠራን በኋላ ውሃውን የምንለቅበት ደረጃ ላይ ማድረስ መቻል ሌላው ስኬት ነው ብለዋል።

ግድቡ የደረሰበት ደረጃ ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ቁመናዋ ባገኘችው ልምድ እና እውቀት 60 የሚሆኑ በርካታ ግድቦችን መሥራት እንደምትችል ያመላከተ መሆኑንም ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

እሳቸውም እንዳሉት፤ የግድቡ ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ የሲቪል ሥራው ወይም በሲሚንቶ የሚሠራው ሥራ በግራ እና ቀኝ የግድቡ ቁመት 145 ሜትሩ ተጠናቋል። በመካከል ያለው እና አሁን ውሃ የሚፈስበት 120 ሜትር ቦታም እስከሚቀጥለው ሰኔ ወር ድረስ እንደሚጠናቀቅ ጠቁመዋል። ኮንክሪቱ ከተሞላ በኋላም ውሃው ከታች በኩል ቁጥጥር እየተደረገበት የሚወጣ መሆኑ አንድ ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል።

የግድቡን አራተኛ ዙር ሙሌት ይፋ ባደረጉበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያውያን ተባብረን በመሥራታችን የዓባይ ግድብ አራተኛ ዙር ሙሌትን በስኬት አጠናቀናል። በግድቡ ሥራ በገንዘባችሁ በእውቀታችሁ በጉልበታችሁ እና በጸሎታችሁ የተሳተፋችሁ ሁሉ እንኳን ደስ አላችሁ። ይህ ኅብረት በሌሎች ጉዳዮቻችንም እንዲሁ ሊደገም ይገባል በማለት ገልጸው፤ ለግድቡ የሚደረገው ማናቸውም ድጋፍ እስከ ፍጻሜው መቀጠል እንዳለበትም አደራ በማለት ጭምር መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የግድቡ ፕሮጀከት ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፍቅርተ ታምር ከሰሞኑ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ «ቃላችንን ዳግም በማደስ ግድባችንን እናጠናቅቅ» በሚል መሪ ቃል ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከንግድ ባንክ፣ ከልማት ባንክ፣ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክና ከሌሎችም አጋር አካላት ጋር በመተባበር ለአንድ ወር የሚቆይ ሀገር አቀፍ የሀብት ማሰባሰቢያ ንቅናቄው ተጀምሯል። በዚህም ከ500 ሚሊዮን እስከ 700 ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ የሚሠራ መሆኑ ተጠቅሷል።

ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቱ በሀብት ማሰባሰብ ሥራ በ2015 በጀት ዓመት እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2015 ድረስ ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ሀገር ቦንድ እና ስጦታ እና በ8100 ከአንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡም ተጠቁሟል። በየዓመቱ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ለማሰባሰብ እየተሠራ መሆኑን አስታውሰው፣ በቀጣይ 2016 በጀት አመት ከአንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በላይ ለማሰባሰብ መታቀዱን ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።

መንግሥት እና ኅብረተሰቡ በተባበረ ክንድ መሥራታቸው ግድቡ አሁን ላለበት 93 በመቶ መደረሱንም ገልጸዋል። ባለፉት አስራ ሁለት ዓመታት የኅብረተሰቡን ተሳትፎ በማጠናከር እስከ ሐምሌ 2015 ድረስ ከ18 ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር በላይ ተሰባስቧል። እንዲሁም በጉልበት፣ በእውቀት፣ በሀሳብ ጭምር በርካታ ድጋፎች መደረጋቸውን ነው የተጠቀሱት።

የግድቡ ከፍታ 145 ሜትር ሲሆን፣ ርዝመቱ ደግሞ 1800 ሜትር ነው። ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ የሚውል 74 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ የመያዝ አቅም አለው። 13 ተርባይኖች የሚገጠሙለትና በዚህም አምስት ሺ150 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጭ ይሆናል።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን  መስከረም 12 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You