ስለኢትዮጵያ

አሁን አሁን “ስለኢትዮጵያ” ለጆሮ እንግዳ የሆነ ርእሰ ጉዳይ አይደለም። ከአንድ ዓመት በላይን አስቆጥሮ ሁለተኛውን ጀምሮታልና ከብዙዎቻችን ጋር ትውውቅ አለው።

በግልፅ እንደሚታየው “ስለኢትዮጵያ” ከስያሜው ጀምሮ ብዙ የታሰበበት፣ ብዙም የተለፋበት። ራዕይ፣ ግብ . . . ያለው፤ በትክክል ወቅቱን ያገናዘበ (ዘግይቷል ካልተባለ በስተቀር) ከአንድ ተቋም የመነጨ፤ ግን ደግሞ በይዘቱ ሀገራዊ የሆነ ግዙፍ ሥራ ነው።

“ስለኢትዮጵያ” ኢትዮጵያ ተኮር እንደ መሆኑ መጠን ከስያሜው ጀምሮ (ስሜት ፈንቃይነቱ የባህርይው ነው እንኳን ብንል) መሰረቱ ኢትዮጵያዊ፤ መደላድሉም ማህበረ- ባህላዊ እሳቤ ነው። ስለእመብርሃን፤ ስለእግዚአብሔር፣ ስለገብርኤል፣ በኣላህ… እንዲሉ የሃይማኖት አባቶችና ምእመን፤ “ስለኢትዮጵያ”ም ተማፅኖው ይህንኑ ባህላዊ (ባህል፣ በአንድ በኩል ቁሳዊና ነባራዊ፣ በሌላ በኩል መንፈሳዊ፣ ህሊናዊ፣ ማህበራዊና የግል የፈጠራ ጥረት ገፅታዎችን የሚያካትት ሲሆን፤ ኃይማኖት በባህል ውስጥ ያለ አንድ ግዙፍ ማህበረ-ባህላዊ እሴት መሆኑን ልብ ይሏል) እሴት የተንተራሰና በዚሁ እሴት ምት፣ ቅላፄና ተማፅኖ አገርን ማሻገር ላይ ያተኮረ ተማፅኖና ምልጃ… ነው።

“ስለኢትዮጵያ” ኢትዮጵያዊ ለሆነ ሁሉ ሃይል ሰጪ፣ ብርታት ለጋሽ፣ ሞራል ገንቢና ማግኔቲክ የሆነ ጥልቅ ጽንሰ- ሃሳብ ነው።

እርግጥ ነው። “ስለኢትዮጵያ” የአንድ ትልቅና ታስቦበት ወደ ሥራ የተገባበት ፕሮጀክት ስያሜ ነው። “ስያሜ” እንበለው እንጂ ከስያሜው ጀርባ ጥሪ አለ፤ ከጥሪው ጀርባ “እባካችሁ፤ ስለ ኢትዮጵያ ብላችሁ” አለበት። ከእባካችሁ ጀርባ የትብብር፣ የአብሮነት፣ የፍቅር፣ የመተሳሰብ፣ የልማት፣ የተስፋ፣ የሠላም፣ የወንድማማችነት፣ የታሪካዊና ሥነልቦናዊ ጉዳዮች ሁሉ በአንድ ቋጠሮ አንድ ማህፀን ውስጥ የሚገኙበት ነው። ወቅታዊና ታሪካዊ ሁነቶችና ኩነቶች በአንድ የተሰናሰሉበት ነው – “ስለኢትዮጵያ”።

“ስለኢትዮጵያ” በፎቶግራፍ ኤግዚቢሽን፣ በፓናል ውይይቶችና ምሁራዊ ዲስኮሮች ይታጀብ እንጂ፣ ከሁሉም በላይ በ“የአንድነት አስተምህሮት” ላይ መልህቁን የጣለ ስለመሆኑ በሥርዓተ-ነጥብ ካልታጠረ (ሃሳቡ ካልተዘጋ፣ ለውይይት፣ ንግግር፣ ለተጨማሪ አስተያየት ክፍት ከሆነው – – -) ስያሜው የበለጠ የሚናገር ማንም የለም። ከምክንያትና ምክንያታዊነት ጋር በእጅጉ ቁርኝት ያለውና በሰዋሰው ክፍሉ “አያያዥ” ከሆነው “ስለ—” በላይ ሌላ ማስረጃ ማምጣት ትርፉ ዘጥ ዘጥ እንጂ ሌላ አይሆንም።

“ስለኢትዮጵያ” ዜጎችን ብቻ ያማከለ አይደለም። “ስለኢትዮጵያ” ኢትዮጵያን የሚሉ ሁሉ ስለ እሷ ብለው (እሷን ምክንያት አድርግው) ወደ አንድ እንዲመጡ፤ በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲሰባሰቡ፤ ጠመንጃን “ደህና ሁን” ብለው እንዲሰናበቱ፤ ለውይይት እጅ እንዲሰጡ፤ ለዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ የበኩላቸውን እንዲያበረክቱ፤ ስለሀገራቸው፣ ሕዝብና ወገናቸው ሲሉ ሁሉም ወገኖች የዘንባባ ዝንጣፊን በመያዝ ይቅር ለእግዚአብሔር እንዲባባሉ፤ እጅ ለእጅ እንዲያያዙ፤ ለሀገረ-መንግሥትም ሆነ ብሔረ-መንግሥት ግንባታው (ዝቅ ብለን እናያቸዋለን) ሥራ ያላቸውን እንዲወረውሩ (ደበበ ሰይፉ “በትን ያሻራህን ዘር / ይዘኸው እንዳትቀበር” እንዳለው) … “እባካችሁ!!!” በማለት ጮኽ ብሎ የሚጣራ ሀገር በቀል እሳቤ ነው።

ኢትዮጵያ ጃንጥላዋ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምእራብ እስከ ምስራቅ፣ ከጫፍ እስከ ጫፍ የተዘረጋ እንደመሆኗ ሁሉ፣ “ስለኢትዮጵያ”ም ከተማና ገጠር፣ መሀልና ዳር በሚል የተቀነበበ አይደለም። ሁሉንም ስፍራዎች፣ ሁሉንም ኢትዮጵያዊያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን፣ አፍቃሬ ኢትዮጵያን፣ የኢትዮጵያ ወዳጆችን፣ የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል፣ ይመለከተናል – – – የሚሉትን ሁሉ የሚመለከት፤ በዱር በገደሉ፣ በጫካ በምሽጉ – – – ያሉትን ሁሉ “ስለኢትዮጵያ” በማለት የሚማፀን መርሀ ግብር ነው። በመሆኑም፣ እድሜ፣ ፆታ፣ ሃይማኖት፣ ብሔር ብሎ ጣጣ የ“ስለኢትዮጵያ” ጉዳይ አይደሉምና ጥሪው “ሁላችሁም ተጋብዛችኋል” አይነት ነው።

“ስለኢትዮጵያ” ሃሳብ ነው፤ ለሀገርና ሕዝብ የሚጠቅሙ፣ ወንዝ የሚያሻግሩ፣ የአፈሙዝ ላንቃን የሚያዘጉ፣ አብሮነትን የሚያጠናክሩ፣ ታሪክን የሚነግሩ … ሃሳቦች፤ የኢትዮጵያዊነት ምስጢር አቁማዳ ነው።

“ኢትዮጵያ ሲባል ማን ዝም ይላል ሰምቶ” እንዲል ቴዎድሮስ ካሳሁን፣ “ስለኢትዮጵያ” ሲታሰብም ሆነ ሀሳቡ ሲፀነስ፣ ወደ ተግባርም ሲወርድ “ማን ዝም ይላል ሰምቶ”ን ታሳቢ አላደረገም ማለት ባይቻል እንኳን፣ በኢትዮጵያዊያን ጥግ ድረስ የመተማመን ሁኔታዎች ስለመኖራቸው ምንም ጥርጥር የለም።

“ስለኢትዮጵያ” በኢትዮጵያ ጨክኖ “ወግድ” የሚል አካል እንደማይኖር የሚተማመን መድረክ እንደ መሆኑ መጠን፣ በውስጡ “ኢትዮጵያ ትቅደም!!!” (መርህ ነው)፣ “ይቻላል!!!”፣ “እናት ሀገር” …የሚሉ አሰባሳቢ መሰረተ ሃሳቦችን የቋጠረ ነው ብሎ መደምደም ይቻላል። (በነገራችን ላይ፣ “ኢትዮጵያ ትቅደም!!!” የሚለው መርህ ዝም ብሎ የተነገረ፣ ድንገት መጥ ሃሳብ አለመሆኑንና ምን ያህል እንደተደከመበት፣ በስንትና ስንት ምሁራዊ ጥናቶች፣ ደንብና መመሪያዎች እንደተደገፈ ወዘተ የቀድሞው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ ብርሀኑ ባይህን መጽሐፍ በማንበብ መረዳት ጥሩ ሲሆን፤ “ስለኢትዮጵያ”ም ምን ያህል ተደክሞበት እንደሆነ ወደፊት ይነገረናል ብለን እናምናለን።)

“ስለኢትዮጵያ”ን ስናጠይቅ (ጀስቲፋይ ስናደርገው) ያገሩን ሰርዶ ባገሩ በሬ ብቻ ሳይሆን፣ እሳቤያዊ ማዕቀፍ (conceptual Framework) ሆኖም ነው የምናገኘው። በመሆኑም፣ ስላለንበት አጠቃላይ ሁኔታና ይዞታ “መላምታዊ” ምላሽን ይሰጣል። ስለ ወደ ፊቱ የእኛና ሀገራችንን ጉዞ በተመለከተ ጥቁምታዎች አሉት። እንደ ሀገር ከገባንበት አዘቅት መውጫ መንገዱ ምን እንደሆነ ያመላክታል። “ሀገር”፣ “ሕዝብ” እና መሰል ቁልፍ እሳቤዎችን ቆም ብለን እንድናስብ ብቻ ሳይሆን ልናደርጋቸው ስለሚገቡን ተግባራት “መላምታዊ” አቅጣጫን ይሰጠናል። ኢትዮጵያን የሚጎዱ ነገሮች መኖር እንደሌለባቸው ያሰርፃል። ነገሩ ሁሉ “በኢትዮጵያ የመጣ በዐይኔ የመጣ …” አይነት ነው።

ስለእመብርሃን (ሎሬት ፀጋዬ “ምነው እመብርሃን ቀኝ እጅሽን እረሳሻት” እንዳለው ቢሆንም/ባይሆንም)፣ ስለማርያም (ምኒልክ “ማርያምን አልምርህም” እንዳሉት ቢሆንም/ባይሆንም – የሀገር ጉዳይ እዚህ ድረስ መሄዱን ልብ ይሏል)፣ በአላህ … እንደምንለው ሁሉ፣ “ስለኢትዮጵያ” ሀገርን ስለመውደድ የሚያቀነቅን፣ አገራችንን እንድንወድ የሚማፀን፣ “ሀገሬን እወዳለሁ” የሚል ማንኛውም ሰው እውነተኛ ሀገር ወዳድነቱ የሚለካበት ስነ-ልቦናዊ ውቅርን (ሚዛንም ልንለው እንችላለን) መሰረት ያደረገ እሳቤ ነው። ኢትዮጵያዊ ሁሉ ለሚወዳት ሀገሩ የጊዜ፣ የጉልበት፣ የእውቀት፣ ካስፈለገም የሕይወት መስዋእትነት እንዲከፍል የሚጋብዝ “የእናት ሀገር ጥሪ” አይደለም ካልን (ምናልባት ካለን) ሌላ ምን ልንል እንደምንችል ግልፅ አይደለም። ወደ አካዳሚው ደብር እንምጣ።

በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ረዳት ፕሮፌሰር ሀብታሙ ግርማ “ሀገር ማለት ምን ማለት ነው??? ሀገርን መውደድ እንዴት ይገለጣል??? በሚል ርእስ ባቀረቡት ጥናታቸው ላይ እንዳሰፈሩት “ሀገርን የመውደድ መገለጫ[ዎች] ሶስት” ሲሆኑ፤ “አንደኛው ሀገሪቱን ለማወቅ በመጣር፤ ሁለተኛው ለሀገሩ ግንባታ በሚበጁ ተግባራት ላይ በመሰማራት ሀገሩን የራሱ ለማድረግ መጣር፤ ሦስተኛው ሀገሩን ለማቆየት በሚከፍለው መስዋዕትነት ነው።”

ረ/ፕ/ር ሀብታሙ በዚሁ ጥናታቸው “ኢትዮጵያን መውደድ ማለት ምን ማለት ነው? መገለጫውስ ምንድ ነው??? በሚለው ንኡስ ርእስ ስርም “ሀገሬን እወዳለሁ የሚል ሀገሩን ስለመውደዱ የሚገልጽ ከቃላት (ከዘፈን) ባለፈ ተጨባጭ ነገር ሲተገብር መታየት አለበት፤ ሀገርን ማወቅ ሲባል ቢያንስ የሚከተሉትን ሦስት ጉዳዮችን ለማወቅና ለመመርመር መጣር ማለት ነው። አንደኛው ሀገር የምንለው ጽንሰ ሃሳብ ምን ማለት እንደሆነ፣ በዚህም ኢትዮጵያን እንደ ሀገር መረዳት፤ ሁለተኛው ሀገር ሀብት መሆኑን መገንዘብ፤ ሦስተኛው የሀገርን (የኢትዮጵያን) ሥነ-ሕዝባዊ እና ሥነ-መንግሥታዊ ታሪክን በአግባቡ በመረዳት ሀገሪቱን ለማስቀጠል የሚያስፈልገውን መረዳት እና/ወይም ዋጋ መክፈል መቻል ነው።” ማለታቸውንም ሳይጠቅሱና ከ“ስለኢትዮጵያ” ጋር ያለውን ቅን ተዛምዶ ሳያስታውሱ ማለፍ አይቻልም።

በ“ስለኢትዮጵያ” ውስጥ ያለችው ኢትዮጵያ ያው ሀገር ነችና አጥኚው በዚሁ በሴፕቴምበር 2021 ጥናታቸው “ሀገር” የሚለውን ጽንሰ ሃሳብም “ሕዝቦች የጋራ ጥቅሞቻቸውንና የሚጋጩ ፍላጎቶቻቸውን ለማስጠበቅ በአንድ መንግሥት ስር ለመተዳደር የሚገቡት ቃልኪዳን ነው፤ በመሆኑም ሀገር በሚለው ጽንሰ ሃሳብ ውስጥ ሕዝቦች (ዜጎች)፣ መንግሥት፣ የተለያዩ ተፎካካሪ እና/ወይም የሚጋሩት ፍላጎቶች ያላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ እነዚሁ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች እንደ አንድ ሀገር ሕዝብ ሆነው በጋራ ለመተዳደር መነሻ ወይም መሰረት የሚሆናቸው የጋራ ጉዳይ፤ ይህን የጋራ ጉዳይ የሆነውን በአንድነት የመኖር አጀንዳ ሊያሳኩበት የሚችሉበት መንገድ (ሂደት)፤ እንዲሁም እነዚህ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች በአንድነት ለመኖር እንዲችሉ በጋራ የሚስማሙበት የጥቅም እና ግዴታ የውል ስምምነት ሰነድ ናቸው። ስለሆነም ሀገር በሚለው ጽንሰ ሃሳብ ውስጥ ሀገረ-መንግሥት፣ ሕገ-መንግሥት፣ የፖለቲካ ልሂቃን እና ብሔረ-መንግሥት የሚባሉ ጉዳዮች አሉ። በመሆኑም ሀገር ስለሚባለው ነገር የሚኖረን ዕውቀት እነዚህን ጉዳዮች ማወቅ ነው።” በማለት ያሰፈሩትን ስንጠቅስ ሃሳቡ የ“ስለኢትዮጵያ”ን ከፍታ ያሳይልናል ከሚል ጉጉት በመሆኑ አጥኚውን አመስግነን ወደ ሌላው እንሂድ። ከዛ በፊት ግን፣ አንድ ለመንገድ እንዲሉ፤

በአንድ ሀገር የሚኖሩ የተለያዩ ፖለቲካዊ ፍላጎት ያላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ፖለቲካዊ ልዩነቶቻቸውን በጎን አድርገው፣ ነገር ግን የጋራ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ተግባራትን የሚከውን አካል ሀገረ-መንግሥት ይባላል፤ ሀገረ-መንግሥቱ ይህን የሕዝቦች የጋራ ጥቅም የማስጠበቅ ኃላፊነቱ በዝቅተኛ ደረጃ ሊከውን የሚገባው ተግባር ሲሆን፣ ዋነኛ ተግባሩ ብሔረ-መንግሥት ለመመስረት ለሚደረጉ ሂደቶች መሰረት የሆኑ ተግባራትን ማካሄድ ነው፤ ይህም የተራራቁ የፖለቲካ ፍላጎቶችን ለማቀራረብ የሚስችሉ ሕገ-መንግሥታዊ፣ ተቃማዊ እና አስተዳደራዊ መሰረተ-ልማቶችን (Soft infrastructures) መገንባት ነው፤ በመሆኑም የሀገረ- መንግሥት አስፈላጊነት የተለያየ የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ወደፊት በጋራ አብረው መኖራቸው ጥቅም እንዳለው ማሳየት፣ የአብሮነታቸው ዋስትና እንዲኖር መሰረት የሚሆነውን የጋራ ኑሮ መመስረቻ የውል ሂደትን ማስተባበር፤ በጋራ የተስማሙበትን የቃልኪዳን ሰነድ ውሎች ሳይሸራረፉ እንዲከበሩ የማድረግ ኃላፊነት ያለበት ሕዝባዊ መንግሥት እንዲቋቋም ማድረግ ነው። (ዘኒከማሁ)

ከአካዳሚው ዓለም እንውጣና ወደ ራሳችን እንመለስ።

የሚመለከታቸውና የጉዳዩ ባለቤቶች ሲናገሩ እንደ ተሰማው “ስለኢትዮጵያ”ን የሚገድብ ድንበርም ሆነ ቀዬ የለም። በሁሉም ክልሎች እኩል መስተንግዶ የሚደረግለት፣ በሁሉም አካላት እኩል ተሳትፎ እየተጠናከረ የሚሄድ፤ ሁሉንም “ስለኢትዮጵያ” ስትሉ ኑ አብረን እንሁን፣ ኑ አብረን እንስራ፣ ኑ አብረን እንምከር፣ ኑ እንወያይ፣ ኑ ችግሮቻችንን እኛው እንፍታ፣ ኑ … የሚል ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊያንን ማእከል ያደረገ ሰፊ መድረክ ነው። (ከእሳቤው “እባካችሁ፣ ስለኢትዮጵያ ብላችሁ ስሙኝ፤ አንዴ አዳምጡኝ፤ እርዱኝ፤ ደግፉኝ፤ እጅ ለእጅ ተያያዙ (እንያያዝ)”፤ ይህችን ታሪካዊት ሀገራችንን አናስቀይማት ወዘተርፈ የሚሉ ድምፆች አይሰሙም? ወይም፣ “ስለእማምላክ፣ ስለእግእዚትነ ማርያም፣ ስለአላህ … እያለ(ች)ና እጁ(ጇ)ን እያርገበገበ(ች) የሚ(ምት)ለምን ሰው አይ(ት)ታያችሁም? እነዚህ ምናባዊ ድርጊቶች ካልተሰሙና ካልታዩ የዚህ ጸሐፊ ጆሮና ዐይን “አደጋ” ላይ ነው ማለት ነው።)

እውነት ነው፣ የተለያዩ ሀገራት የተለያዩ ችግሮች ሲገጥሟቸው ነው የኖሩት። ከችግሮቻቸው ለመውጣትም የተለያዩ ብልሀቶችን መጠቀማቸውም እንደዚሁ የታወቀ ነው። በአሁኑ ሰአት ለገጠመን መከራም የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት (ኢፕድ) “ስለኢትዮጵያ” ብሎ ሲነሳ፣ ሲማፀን ከችግሮቻችን መውጫ መንገድ ይሆነን ዘንድ በማሰብ ነውና ሁላችንም ለሁላችንም የወንድ በር ልንሰጥና መውጫ መንገዱን አስተማማኝ ልናደርግ ይገባል።

ፈረስ ያደርሳል እንጂ … እንደሚባለው ፕሬስ ድርጅት እድሉን ይፈጥራል፣ መድረኩን ያመቻቻል እንጂ ስራው የዜጎች ሁሉ ነው። ኃላፊነቱ የእያንዳንዳችን ነው። “ደህና ሁን ጠመንጃ” (አገላለፁም ሆነ ሃሳቡ የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ነው) ማለት ወይም አለማለት የሁላችንም ፋንታ ነው። ለሚቀጥለው ትውልድ ማሰብ ወይም አለማሰብ የማንኛችንም ጉዳይ ነው። ሀገርና ትውልድን የማስቀጠሉ መሰረታዊ ተግባርም እንደዛው። በመሆኑም መድረኩን ፍሬያማ ማድረግ የሁሉም ግዴታ ይሆናል ማለት ነው። ካልሆነ “ስለኢትዮጵያ” የሁላችንም ቋንቋ አልሆነም ማለት ነው። ያ ደግሞ ወደ ኋላ እንጂ ወደ ፊት ስለማያራምድ እዳው ገብስ አይደለም።

6 ታህሳስ 2019 (እአአ) ቢቢሲ “ሃምሳ የሚሆኑ ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የተወጣጡና በኢትዮጵያ የወደፊት እጣ ፈንታ ላይ ሚና ይኖራቸዋል የተባሉ ፖለቲከኞች፣ ምሁራን፣ አክቲቪስቶች፣ ጋዜጠኞችና ሌሎችም ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ለ11 ቀናት አብረው ውለው፣ 8 ቀን አብረው አድረው ስለኢትዮጵያ የወደፊት እጣ ፈንታ መክረዋል።” በማለት ዜና አስነብቦ ነበር። የእነዚህ ውጤቱ የት እንደደረሰ ለጊዜው ግልፅ ባይሆንም፣ የኢፕድን “ስለኢትዮጵያ” ከዚህ የሚለየው ሁሉንም በያሉበት እየሄደ፣ በየተገኙበት እየተገኘ አብሮ መምከሩ፣ እንዲመክሩም እድሉን እያመቻቸ መቀጠሉ፤ ዙሩንም እያከረረ መሄዱ ነው የሚሉ ብዙዎች ናቸው።

ወደ ማጠናቀቂያችን ከመሄዳችን በፊት፤ ስለእመብርሃን፣ በአላህ … ስነልቦናዊ እንደመሆናቸው መጠን የ“ስለኢትዮጵያ” ማጠየቂያም በተመሳሳይ ስነልቦናዊ ነው። በቁጥር አይለካም፤ በሚዛን አይመዘንም፤ በቁና አይሰፈርም … በ“ስለኢትዮጵያ” ባዩ (ተማፃኙ)ና ተቀባዩ መካከል ያለው ግንኙነት ስነልቦናዊ እንደመሆኑ መጠን ለስኬታማነት የሁለቱን እኩል መረዳትና መረዳዳት ይጠይቃል። ተማፃኙ “መቸም ስለ ኢትዮጵያ ብዬ እሚያልፈኝ ኢትዮጵያዊ የለም” የሚል መተማመኛም ያለው ይመስላልና አሁንም “ማን ዝም ይላል ሰምቶ”ን እዚህም እናስታውስ ዘንድ ግድ ይለናል።

በመጨረሻም፣ አንድ ለእናቱ የሆነው ጥላሁን ገሠሠ “ሁሉም ባገር ነው” እንዳለው ሁሉ፣ ሌሎችም በየመስካቸው እንዳረጋገጡት ሁሉ፣ እኛም በሕይወት ልምድም ሆነ አብሮ መኖር እንዳረጋገጥነው ሁሉ …. ነግዶ ማትረፍ በሀገር ነው። ሰርቶ ማደር፤ ዘርቶ መቃም፣ ወልዶ መሳም በአገር ነው። አንገትን ቀና አድርጎ መሄድ በሀገር ነው፤ ጸቡም ፍቅሩም የሚያምረው በሀገርና በሀገር መሬት ላይ ነው። በመሆኑም፣ የ“ስለኢትዮጵያ” መድረክ ወቅታዊና አስፈላጊያችን ነው ስንል በምክንያት ነው።

ስለኢትዮጵያ ዝም አንልም!!!

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን  መስከረም 12 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You