ለሰላም ግንባታ የሃይማኖት ተቋማት ሚና

ብዙ ጊዜ በግጭት እና መከፋፈል በሚኖርባት ዓለም ላይ የሃይማኖት ተቋማት ለሰላም ግንባታ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ወሳኝ ነው። በእምነት ተቋማት፣ በእምነቱ አስተማሪዎች እና በምዕመናን መካከል የሚኖሩ የሰላም ውይይቶችም ለማጽናት አስተዋጿቸው ከፍ ያለ ነው፡፡

በተለይም ኢትዮጵያ ያሉ በርካታ አማኝ ሕዝብ ባለባቸው ሀገራት የተቋማቱ መሪዎች ማህበረሰቦች ማህበረሰባዊ ሰላምን ለማጽናት የማይናቅ ሚና ይኖራቸዋል፡፡ አዲስ ዘመን በእዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ሁለት የሃይማኖት አባቶችን አነጋግሯል፡፡

መላከ ኃይል አባ ጽጌ ድንግል ፋንታሁን ይባላሉ፤ የቅድስት ስላሴ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት ናቸው። ሃይማኖት መሠረቱ ሰላም ነው ይላሉ። ባልንጀራህን እንደራስህ አድርገህ ውደድ የሚለው መመሪያ በቅዱሳን መጽሐፍት ውስጥ ጥልቅ ስፍራ የሚሰጠው ነው፡፡ ባልንጀራን እንደራሱ በመውደድ ሰላምን ማጽናት ቀላል ነው። አሁን ዓለም ላይ ትልቅ ችግር የሆነው እና ለብዙ ግጭቶች መንስኤ እየሆነ ያለው ራስ ወዳድነት ነው።

ክርስቶስ ዓለም ላይ በነበረበት ጊዜ ስለ ሰላም ሰብኳል የሚሉት የሃይማኖት አባቱ፤ የሰላም መጀመሪያዎች ግለሰቦች ናቸው፡፡ ግለሰቦች የራሳቸውን እና አካባቢያቸውን ሰላም የሚጠብቁ ከሆነ የግለሰቦች ስብስብ ማህበረሰብን እና ሀገርን ከመወከሉ አኳያ በሁሉም በኩል ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚቻል ይገልጻሉ። ከላይ ካለው አመራር ጀምሮ እስከ ታችኛው እርከን እስካለው አመራር ድረስም በኃላፊነት መሥራትን የሚጠይቅ ነው፡፡

ሰላም ከሌለ ሀገር የለም፡፡ ሰዎች እንደልባቸው ሠርተው መኖር አይችሉም፡፡ ተማሪዎችም በአግባቡ አይማሩም። ሰላም የሁሉም ተግባር መጀመሪያ መሆኑን በመገንዘብ ሰላምን ለማጽናት የሃይማኖት ተቋማት እና ሁሉም ማህበረሰብ ርብርብ ሊያደርግ ይገባል ይላሉ፡፡

ሰዎች ግጭት ከሚያስከትለው ውድመት በፊት የሰላምን ዋጋ ሊገነዘቡ ይገባል፤ ይህንንም የሃይማኖት አባቶች እና ተቋማቱ ለምዕመኖቻቸው ሊያስተምሩ ይገባል ባይ ናቸው፡፡ ይህም የሃይማኖታዊ ተልእኳቸው አካል መሆኑን በመጥቀስ፤ ለእዚህ የሚሆን ዝግጁነት መፍጠር እንደሚጠበቅባቸው ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ ኡለማዎች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሺህ መሃመድ ዘይን በበኩላቸው፤ የእስልምና ሃይማኖት እና እስልምና የሚለው ስርወ ቃል ከመነሻው ጀምሮ ‹ሰሊመ› ከሚለው ዐረብኛ ቃል የተወሰደ ሰላም ሆነ፣ ደህና ሆነ፣ አማረ፣ ተመቸው የሚል ፍቺ አለው ይላሉ፡፡ ሰላም አስፈላጊ መሆኑን ከሚያሳዩ ጉዳዮች አንዱ ከፈጣሪ (አላህ) ስሞች አንዱ ‹አሰላም› የሚለው ነው ይላሉ፡፡

የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮችም በቀን ብዙ ጊዜ ሰላም የሚለውን ቃል ያነሳሉ፡፡ በየሰላቱም “አሰላም አለይኩም” ይላሉ፡፡ የቁርአን አንቀጾች ውስጥም ስለሰላም ተጠቅሷል፡፡ በአጠቃላይም ሃይማኖቱ ከአሰያየሙ ጀምሮ እስከ ትግበራው ስለሰላም ያነሳል ትምህርትም ይሰጣል ብለዋል፡፡

እንደ ሼሁ ገለጻ፤ ከግጭት፣ ከጠብ እና ከሁከት ማንም አትራፊ አይሆንም፡፡ ወንድማማቾች እና የአንድ ሀገር ዜጎች ግጭት ውስጥ ሲሆኑ ሌላው ከሀገር ውጭ

ያለው ሰው ትርፍ ብሎ የሚያስበውን ነገር ሊያገኝ ይችላል፡፡ መሣሪያ ይሸጣል፣ ሀገሪቱ ውስጥ ያለውን ሀብት ለመዝረፍም እድል ይሰጠዋል፡፡

ከግጭቱ አንዱ ወገን አሸናፊ ሆኖ የሚፈልገውን ቢያሳካም ብዙ ወንድሞችና እህቶቹን መስዋዕት አድርጎ እና ሀገር አጥፍቶ በመሆኑ እንደማሸነፍ አይቆጠርም። ሕዝቦችም ሰዎች በመሆናቸው ብቻ ቅሬታ እና ጥያቄ ቢኖራቸውም በሰላማዊ መንገድ ጥያቄአቸውን የማያሳኩ እና እርስ በርሳቸው እልህ ውስጥ በመግባት ግጭቶችን በማባባስ ልዩነቶችን ሊያሰፉ አይገባም፡፡ ከግጭት ኪሳራ እንጂ ትርፍ የለም ብለዋል፡፡

ሰዎችም ሰላምን ለማጽናት ብዙ ሥራዎችን መሥራት አለባቸው፡፡ በቅድሚያ ግጭቶች እንዳይፈጠሩ መትጋት እና ግጭቶች ከተከሰቱ በኋላ ለግጭቶቻቸው መነሻ

የሆኑትን ጉዳዮች ለይተው በማውጣት ለእነዛ ጉዳዮች መፍትሔ መፈለግ አለባቸው፡፡ ይኼም ኃላፊነት በዋናነት የሚሰጠው ለሃይማኖት አባቶች ነው፡፡ ማህበረሰቡ በሃይማኖት አባቶች ላይ ትልቅ እምነት ያለው በመሆኑ አባቶች ምዕመኖቻቸው ግጭትን እንዴት መፍታት እንዳለባቸው ሊያስተምሩ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

የሃይማኖት አባቶች እና ተቋማት ክፍያቸው ምድራዊ ሳይሆን ሰማያዊ በመሆኑ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው መሥራት እና ከማንም ምንም ሳይጠብቁ የከፋውን ጠግነው፤ ያጠፋውን ተቆጥተው ሰላምን ለማረጋገጥ መሥራት አለባቸው፡፡ የሃይማኖት አባቶቹም የሰላም ባንዲራ ይዘው ሊንቀሳቀሱ ይገባል፡፡ እርስ በርሳቸውም በመናበብ እና አስበው በመንቀሳቀስ ማህበረሰቡን ወደ ትክክለኛ መስመር ሊያስገቡት ይገባልም ብለዋል፡፡

መክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 21 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You