«የብሪክስ አባልነት ተጨማሪ ወዳጆችን በተለየ መልክ የማፍራት ዕድል ያስገኛል»አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የደህንነት ቋሚ ኮሚቴ አባል

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዳይሬክተር ጀኔራል ሆነው ሠርተዋል- አምባሳደር ዲና ሙፍቲ። በዚሁ ተቋም በተለያዩ ጊዜያት ሁለቴ በቃል አቀባይነት አገልግለዋል። በአሜሪካ እና በካናዳ ኤምባሲዎች አማካሪ ሆነው ሠርተዋል። በስዊድን የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛም ነበሩ። በዙምባቡዌ፣ በኬንያ እና በግብፅ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች አምባሳደር ሆነው ሠርተዋል። አሁን ደግሞ የውጭ ግንኙነት እና የደህንነት ቋሚ ኮሚቴ አባል ሆነው በመሥራት ላይ ይገኛሉ።

እኚህ በዲፕሎማሲው መስክ በስፋት የሠሩት አምባሳደር ዲና፤ ያለፈው ዓመት የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴን እንዴት አዩት? የሀገሪቷን የዲፕሎማሲ ዘርፍ ተግዳሮት እና ስኬቷን በተመለከተ ምን ይላሉ? ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ከመሆኗ ጋር ተያይዞ የሚገኘው ጥቅም እና የሚያስከትለው ስጋት እንዲሁም ስለወደፊቱ የዲፕሎማሲ መንገድ በማንሳት ቆይታ አድርገን እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል። መልካም ንባብ፡-

 አዲስ ዘመን፡- ያለፈው ዓመት የሀገሪቱ የዲሎማሲ ጉዞ ምን ይመስላል ከሚለው ብንጀምርስ?

አምባሳደር ዲና፡- ባሳለፍነው አሮጌ ዓመት በዲፕሎማሲው መስክ በርካታ ተግዳሮቶች የመኖራቸውን ያህል በጥሩ መልኩ ሊጠቀሱ የሚችሉ ትልልቅ ውጤቶችም ነበሩ። ተግዳሮቶቹ የሚታወቁ ናቸው። ዋነኛው በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የነበረውን ጦርነት ተከትሎ የነበረው ዲፕሎማሲያዊ ሁኔታ ነው። ነገር ግን ያም ቢሆን በሰላማዊ መንገድ የተደረጉት እንቅስቃሴዎች ውጣ ውረዶች ቢኖራቸውም መጨረሻ ላይ ችግሩን በመፍታት፣ ስምምነት ላይ መደረሱ አንድ ትልቅ ውጤት ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል። እዚህ ላይ ተጠቃሽ ሊሆን የሚችለው የፕሪቶሪያው ስምምነት ነው። ይህ እንደ አንድ የዲፕሎማሲ ውጤት ሊወሰድ ይቻላል። ምክንያቱም ሁልጊዜም ተግዳሮቶች በሌላ በኩል ዕድሎችን ይዘው የሚመጡ ሲሆን፤ በዚህም መንገድ የሠላም ዕድል ተገኝቷል።

ሌላው በዚህ ዓመት በተጠቀሰው ጦርነት ምክንያት ከተለያዩ አቅጣጫዎች እና ከተለያዩ ወገኖች በርካታ ጫናዎች ነበሩ። እነዚህን ጫናዎች ለመቋቋም የተደረጉ ጥረቶች ከሞላ ጎደል ስኬታማ ናቸው። ይኸው ጫናም እያለ ከሞላ ጎደል ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ተመዝግቧል።

ባሳለፍነው ዓመት ሌላው እንደትልቅ ውጤት የሚታየው የኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነት ነው። አንደኛ የኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነት የዲፕሎማሲውን ምህዳር ያሰፋል፤ ከነበሩት ወዳጆች ጋር ያለው ግንኙነት እንዳለ ሆኖ፤ ተጨማሪ ወዳጆችን በተለየ መልክ የማፍራት ዕድል ያስገኛል። ይህ ንግድን በማሳለጥ፣ ኢንቨስትመንትን በመጨመር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማፋጠን እና በአጠቃላይ የዲፕሎማሲና የፖለቲካ መደጋገፍን በመፍጠር ረገድ የሚያመጣው ውጤት ትልቅ ነው። ስለዚህ የብሪክስ አባልነት እንደአንድ ትልቅ ግኝት ሊጠቀስ የሚችል ነው።

በተጨማሪ ኢትዮጵያ በተለያዩ መድረኮች ስትሳተፍ ቆይታለች። አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ መድረኮች ላይ ነበረች። እነዚህ መድረኮች ላይ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስጠብቁ አቋሞች የተራመዱባቸው እና ተፈላጊ ውጤቶችም የተገኙባቸው መድረኮች ናቸው። ይህ እንግዲህ ኮቪድ፣ ጎርፍ እና አልፎ አልፎ ድርቅ እንዲሁም ከሰሜኑ አካባቢ በተጨማሪ በሌሎች አካባቢዎችም ግጭቶች እያለ የተደረጉ መሆናቸው መረሳት የለበትም።

በአጠቃላይ ባሳለፍነው ዓመት የሀገራችን የዲፕሎማሲ ቁመና ሀገራችንን ከተግዳሮት፣ ከጫና ለማላቀቅ የተደረጉ ጥረቶች ውጤታማ ሆነው የታዩ ናቸው ማለት ይቻላል። በተገኙት ጥሩ ጥሩ ውጤቶች ላይ ተመስርቶ ወደ ፊት በስፋት መሠራት አለበት።

አዲስ ዘመን፡- አሁን ላይ ኢትዮጵያ የምትከተለው የዲፕሎማሲ ፖሊሲ አካታች ነው ይባላል። ምን ማለት ነው?

አምባሳደር ዲና፡– አካታች ዲፕሎማሲ የምንለው የሀገራችንን ጥቅም እስካራመደ ድረስ፤ የሀገር ጥቅም ሲባል ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ሌሎችም የኢንቨስትመንት፣ የቱሪዝም …ወዘተ ጥቅሞች፤ እያልን ልንዘረዝር የምንችለውን ጥቅም ለኢትዮጵያ እስካስገኘ ድረስ ከየትኛውም ሀገር ጋር መገናኘት እና አብሮ መሥራትን የሚመለከት ነው ።

የትኛውም ሀገር በሚያራምደው ርዕዮተ ዓለም ምክንያት፣ በድንበር፣ በቦታ ርቀት ወይም በአቀማመጡ እና በሚከተለው የተለየ መንገድ ምክንያት ኢትዮጵያ አታገልለውም፤ ችግር ቢኖርበትም ኢትዮጵያ ከዚያ ሀገር የምትፈልገው የለም ማለት አይደለም፤ ከዚያ ሀገር የምትፈልገው እና ያ ሀገር የሚጠቅማት ከሆነ ከእዚያ ሀገር ጋር ትገናኛለች ማለት ነው። እዚህ ላይ ግን ዞሮ ዞሮ ሰጥቶ በመቀበል መርህ፤ ሁሉን ባካተተ መልኩ፤ የሌሎቹንም ሆነ የእኛን ሀገር ጥቅም ግምት ውስጥ በማስገባት፤ ያንንም በማራመድ ላይ መመስረት ማለት ነው።

በዚህ በመሠረታዊ የውጭ ግንኙነት መርሆች የሚካሔድ፤ ሁሉንም ወገኖች ማለትም በየትኛውም ማዕዘን ያሉ የዓለም ሀገሮች እና በየትኛውም አካባቢ ያሉ ተቋማት፤ አህጉራዊም ሆነ ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶችን ያካተተ አካሔድ አካታች የዲፕሎማሲ መንገድ ነው ማለት ይቻላል። አካታች ዲፕሎማሲ በቀላሉ የኢትዮጵያን ጥቅም መሠረት አድርጎ ከሁሉም ጋር መደራደር እና መገናኘት ማለት ነው።

አዲስ ዘመን፡- አሁናዊ የዓለም የኃይል አሰላለፍን በተመለከተ ምን ይላሉ?

 አምባሳደር ዲና፡– ዓለማችን የተለያዩ የኃይል አሰላለፎችን ያስተዋለችባቸው የተለያዩ ዘመኖች አሉ። አንድ ዘመን አንድ ብቸኛ ሀገር ልዕለ ኃያል ሆና የቆየችበት ዘመን ነበር። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የሁለት ዋልታ ሥርዓት (ባይ ፖላር ሲስተም) የተሰኘ ሁለት ልዕለ ኃያላን የነበሩበት ዘመን ነበር። በአንድ በኩል ወደ ብዙ ሀገሮች የተከፋፈለችው ሶቪየት ኅብረት የተባለች ሀገር እና በሌላ በኩል አሜሪካ በአንድ በኩል ሆነው ነበር። እነዚህ ሁለት ዋልታዎች ናቸው፤ እዚህ ላይ ሁለት ኃያላን ነበሩ። በዚያ ጊዜ የአንዱ ዋልታ ላይ መሆን ግድ ነበር። ከሁለቱም ገለል ለማለት የሞከሩም ነበሩ። ያም ብዙ የሚያዋጣ አልነበረም፤ ለማንኛውም ግን ሁለት ዋልታ ነበር፤ ይህ አልፏል።

ቀጥሎ የብዙ ዋልታዎች ሥርዓት (መልቲ ፖላር ሲስተም) ዓለም አለ። ይህ አሁን ያለው ዓለም ማለት ነው። አሁን ላይ ሁለት ብቻ ሳይሆን ሌሎች ኃያል ነን የሚሉ የመጡበት ዘመን ነው። እዚህ ላይ የተለያዩ ሀገራት ኢኮኖሚያዊ ጡንቻቸውን ያዳበሩበት፤ በኢኮኖሚ አቅማቸውም የጠነከሩበት ተፅዕኖ ማሳረፍ የሚችሉበት ሁኔታ የተፈጠረ በመሆኑ፤ አሁን ዓለማችን የብዙ ዋልታዎች ዓለም ናት ማለት ይቻላል። ባለአንድ ዋልታ አልፏል፤ ሁለት ዋልታም የለም። አሁን እዚህም እዚያም የተለያዩ ኃያሎች አሉ። ተፅዕኗቸውም በሁሉም በኩል የተለያየ ነው። ለምሳሌ ቀይ ባህር አካባቢ ራሳቸውን እንደኃያል ሀገር የወሰዱና ቀይ ባህር አካባቢ የፖለቲካውንም ሆነ የደህንነቱን ሁኔታ ለመቆጣጠር የሚሞክሩ አሉ።

በሌላ በኩል የሚሻኮቱ አሉ፤ በተለይ ወታደራዊ መሠረት ለመጣል ሽኩቻዎች መኖራቸው የሚካድ አይደለም። ከፍተኛ የጦር መሣሪያ ዝውውርም አለ። አሁን ባለው ሁኔታ ግን ውድድሮች እና ሽኩቻዎች፤ እዚህ እና እዚያ መገፋፋቶች የበዙበት ጊዜ ነው። ስለዚህ አሁን ዓለም ብዙ ዋልታዎች ያሉባት ሲሆን፤ ይህ አሁን ላይ እየሠከነ ሳይሆን ብዙ ሂደትን ተከትሎ እየዘለቀ ነው። ልዕለ ኃያል የሚሆነው ማን ነው? የሚለው ገና ወደ ፊት የሚታወቅ ይሆናል።

አዲስ ዘመን፡- የብሪክስ መፈጠር የዓለምን የኃይል አሰላለፍ አይቀይረውም?

አምባሳደር ዲና፡- ብሪክስ በፊትም ነበር። ብሪክስ ውስጥ ያሉት አምስት አባል ሀገራት ማለትም ቻይናን እና ራሺያን የመሳሰሉ ልዕለ ኃያል ሀገሮች አሉ። ከእኛ ክፍለ አህጉር ደቡብ አፍሪካ አለች። ከላቲን አሜሪካ ብራዚል እና ከኤዢያም ሕንድ አለች። አሁን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አምስት ሀገራት ተጨምረዋል። ወደ ፊት ሌሎችም የሚጨመሩ ይሆናል። አሁን ብሪክስ አምስት ሀገራትን በጨመረ በጥቂት ቀናት ውስጥ (የጂ 20) ቡድን ሃያም አፍሪካን እንደአንድ አባል አድርጎ ወስዷል። እዚህ እና እዚያ አንዱ ሌላውን የመመልመል እና የመሳብ ነገር ይታያል።

በእርግጥ እነዚህ የብሪክስ ሀገራት መካከል ልዩነት የለም ማለት ባይቻልም እርስ በእርስ ይነግዳሉ። ለምሳሌ ቻይና ከአሜሪካን ጋር ትነግዳለች። የድሮ ቻይና አይደለችም። ሩሲያም ከዩክሬን ጋር ጦርነት ውስጥ በመግባቷ የተነሳ የተለየ ጦርነት የተፈጠረ ቢሆንም፤ እርስ በእርስ መገናኘትም አለ፤ መገፋፋትም እንዲሁ እየታየ ነው። ስለዚህ የዓለም የኃይል አሰላለፍ እዚህ ጋር ነው። የበላይ ሆኖ ዓለምን የሚያሽከረክረው ይኸኛው ነው፤ ለማለት ይከብዳል። ሁሉም የራሱ ሚና አለው። በብሪክስም ተመሳሳይ ነው።

ብሪክስ እየተጠናከረ የመሔድ ዕድሉ በጣም ሰፊ ነው። አሁን ብሪክስ ብዙ ሀገራትን እየተቀበለ ነው። ሳዑዲን ግብፅን እና ኢትዮጵያን ጨምሮ አምስት ሀገሮችን አካቷል። አባላት በጨመረ ቁጥር ሀብት ይጨምራል፤ ሀብት በጨመረ ቁጥር ቴክኖሎጂ ይጨምራል። ቴክኖሎጂ በጨመረ ቁጥር ወታደራዊ ኃይሉም ብቃቱም ይጨምራል። ዞሮ ዞሮ የዓለም የበላይነት ያልለየለት የመገፋፋት ነገር እንዳለ መረሳት የለበትም። ነገር ግን እኛ ከእዚህ የኃይል አሰላለፍ መጠቀም አለብን። ከሁሉም ጋር እንደየጥቅማችን እና ፍላጎታችን፤ የሚደርሰንን ነገር የማግኘት እና ግንኙነታችንን የማሳደግ ዕድል አለን።

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ የብሪክስ ቡድን አባል መሆን በሌሎች ዘንድ እንደመልካም ላይታይ ይችላል። እዚህ ላይ ምን ይላሉ?

አምባሳደር ዲና፡- ትክክል ነው። ብሪክስ ውስጥ ያሉ ሀገራት ይታወቃሉ። በተለይ አንዱ የብሪክስ ሀገር ጦርነት ውስጥ መግባቱን ተከትሎ ጦርነት ውስጥ የገባው ሀገር፤ ከአንዳንድ ምዕራባውያን ጋር ትልቅ ቅራኔ ውስጥ ገብቷል። ስለዚህ ከብሪክስ ጋር መቀላቀል ከእዚያ ሀገር ጋር ቅራኔ ውስጥ ከገቡ ሀገራት ጋር የተለየ ስሜት ይፈጥራል። እከሌ የተባለ ሀገር ለምን ብሪክስን ተቀላቀለ? የሚል ምስቅልቅል ያጋጥማል፤ ሆኖም ምንም ማድረግ አይቻልም።

ኢትዮጵያ ብሪክስ ውስጥ የምትገባው ከእነርሱ ጋር ለመሟገት እና ለመጣላት ሳይሆን የራሷን ጥቅም ለማስከበር እስከሆነ ድረስ የእነርሱን ጥቅም ለመንካት አይደለም የሚለው በደንብ መወሰድ አለበት። ነገር ግን እነዚህ ቅሬታዎች የማይቀሩ መሆናቸውን ለመካድ አይቻልም። ሃሜቶች እና ግምቶች ይኖራሉ። ለምሳሌ ኢትዮጵያ ብሪክስ የገባችው እንዲህ ስለሆነ ነው ሊባል ይችላል። ይህ ብዙም አይጠቅምም። ዋናው የሚጠቅመው እውነታውን ማየት ነው።

ሁልጊዜም ተራማጅ የሆነ ሊተገበር እና ውጤታማ መሆን የሚችል የውጭ ግንኙነት ያስፈልጋል። ይህ መንገድ እጅግ ጠቃሚ ነው። ምንጊዜም ጂኦግራፊ እና የሚከተሉት የፖለቲካ ሥርዓት መስፈርት አይሆንም። መስፈርቱ ከብሔራዊ ጥቅም አኳያ መታየት አለበት። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ምንጊዜም ጠቃሚ እና ወደፊትም ውጤታማ የሚያደርግ ነው።

አዲስ ዘመን፡- በብሪክስ ሀገሮች መካከል ያለው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ግንኙነት ብሪክስ ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ ምን ያህል ነው? እዚህ ላይ ለምሳሌ በሕንድ እና በቻይና መካከል ያለውን የድንበር ውዝግብ መጥቀስ ይቻላል። እዚህ ላይ ምን ይላሉ?

አምባሳደር ዲና፡- ከላይ እንደገለፅኩት ነው። በሀገሮች መካከል ፍፁም የሆነ ግንኙነት የለም። በተለይ ጉርብትና ያላቸው ሀገሮች ግንኙነታቸው ትንሽ ክፍተት ሊኖረው ይችላል። አንዱ ሌላውን የሚጠረጥርበት፣ አንዱ ሌላውን የሚገፋበት፣ በሀብት ምክንያት፣ በድንበር እና በሉዓላዊነት ምክንያት የተለያዩ መሻከሮች ሊኖሩ ይችላሉ። ይሔ በጥያቄው እንደተነሳው በፊትም የነበረ እና ያለ ነው። ይህ እያለም ቢሆን የሀገሮቹን ሁኔታ እነርሱ የሚገልፁበትን መንገድ እነርሱ ሊገልፁት ይችላሉ። ነገር ግን የብሪክስ ሀገሮችም የሚያዩት በዋናነት የሀገራቸውን ጥቅም ነው። በመካከላቸው ያለው ነገር እንዳለ ሆኖ ትልቁን ስዕል አይተው የተሰበሰቡ በመሆኑ የብሪክስን ጠቀሜታ ይዘው ይቀጥላሉ ማለት ነው።

አዲስ ዘመን፡- ብሪክስ ግን የአንዳንድ ምዕራባውያንን ጫና ከመቋቋም አንጻር ስኬታማነቱ ምን ያህል አስተማማኝ ይሆናል ብለው ይገምታሉ?

አምባሳደር ዲና፡– ስኬታማነቱ አባል ሀገራቱን የሚመስል ነው። አባል ሀገራቱ ደግሞ እነማን እንደሆኑ ይታወቃል። አሁን ቅድም በተባሉት ሀገራት መካከል ልዩነቱ አለ። ጫናው ሊኖር እና ሊቀጥል ይችላል። ጫናው ግን ይታወቃል። በዓለም አንዱ አንዱን የመግፋት፤ አንዱ ሌላውን የመጥቀም፤ አንዱ አንዱን የማቅረብ እና አንዱ ሌላውን የማራቅ አለ። ይህ እንዲሁ እንዳለ ይቀጥላል ማለት ነው። ጫና ይኖራል፤ ጫናው አንፃራዊ በሆነ መልኩ ውጤቱ የሚታይ ነው። ብሪክስ ነበር፤ አሁንም አለ። ወደ ፊትም ይቀጥላል። አሁን ደግሞ ሀገራትን እየጨመረ በመሆኑ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሆኖ እየዳበረ የሚሔድ ዕድሉ በጣም ሰፊ ነው ብሎ መደምደም ይቻላል።

አዲስ ዘመን፡- የብሪክስ መፈጠር ለታዳጊ ሀገራት ምን ያህል ይጠቅማል?

አምባሳደር ዲና፡- ታዳጊ ሀገራት ሀብታቸውን በአግባቡ ለመጠቀም ያግዛቸዋል። አግባብ ያለው ንግድ መሳብ ይችላሉ። ምክንያቱም አባል ሀገሮቹ ትልልቅ ናቸው። የእነርሱንም ኢንቨስትመንት የመሳብ ዕድል ያገኛሉ። በቱሪዝም መስክም ብዙ ቱሪስቶች ከእነዚህ ሀገሮች የሚመጡበት ሁኔታ ይኖራል። በቴክኖሎጂ በኩልም የአንዱን ቴክኖሎጂ አንዱ የመሳብ ዕድል ይኖረዋል። ይህ በአጠቃላይ ለመጠቃቀም የሚመች ሲሆን፤ በተለይ ለታዳጊ ሀገሮች እጅግ ይጠቅማል።

አዲስ ዘመን፡- እሺ ኢትዮጵያ አሁን አባል ሆነች። በዚህ ምክንያት አንዳንድ ምዕራባውያን ቅር ሊሰኙ እንደሚችሉ ይገመታል። ሀገሪቱ አባል ስትሆን የሚኖረው ጥቅም እና የሚያስከትለው ጉዳት ምን ያህል ተጠንቷል?

አምባሳደር ዲና፡- ኢትዮጵያ የማን ወዳጅ መሆን እንዳለባት ለመወሰን የሌላ ሀገር ፍቃድ አያስፈልጋትም። ሉዓላዊ ሀገር ናት። ስለዚህ አሁንም ቢሆን የፈለገችው ማኅበር ውስጥ ተቀላቅላ አባል ለመሆን የምትወስነው ለራሷ ራሷ ኢትዮጵያ ናት። ኢትዮጵያ ስንል ሕዝቧ ማለት ነው። ሕዝቧ የመረጠው መንግሥት በፈለገው ማኅበር እና ድርጅት አባል መሆን ይችላል። ከላይ እንደገለፅኩት ነው። አሁን ባለው ዓለም ከዚህ ጋር ለምን ወዳጅ ሆንክ? የሚል ኃይል ብዙም ተቀባይነት የለውም። የብሪክስ አባል አሁን ብንሆንም ከአባል ሀገሮቹ ጋር በፊትም ወዳጆች ነን። ከቻይና ጋር በፊትም ሰፊ ወዳጅነት አለን። ትልቅ የኢኮኖሚ ግንኙነት አለን። ከሩሲያ ጋርም የቆየ ወዳጅነት አለን። ከሕንድ ጋርም ያለን ግንኙነት ይታወቃል። ስለዚህ ከእነርሱ ስብስብ ጋር መሆን ምንም ችግር የለውም። ምክንያቱም በግል ደረጃ ጠንካራ ወዳጅነት ካለን ተሰባስበው በማኅበራቸው ውስጥ መገኘቱ ምንም ችግር የለውም። በዚህ መልኩ ማየቱ የተሻለ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ከአንዳንድ ምዕራባውያን ጋር ያለንን ግንኙነት ሊያሳሳው ይችላል የሚል ሃሳብ ይሰነዘራል። ምን ያህል ተጠንቷል ያልነው ለዚሁ ነው። እርስዎ ለዚህ ምላሽዎት ምንድን ነው?

አምባሳደር ዲና፡- ከአንዱ ሀገር ጋር ወይም ከአንድ ተቋም እና ድርጅት ጋር የምንፈጥረው ግንኙነት በሌላው ኪሳራ ማካካስ የለብንም የሚል አቋም አለ። ግንኙነትም ሆነ አባልነት አንዱን በማክሰር ወይም አንዱን በመጫን እና ጥቅሙን በመጋፋት አይደለም። ዞሮ ዞሮ ጥቅም የጋራ ነው። እንዲህ ባለ ጉዳይ ላይ ሁሉም መጠቃቀም ይችላል። ጉዳዩ የጋራ ተጠቃሚነት ነው። የጋራ ተጠቃሚነትን ግምት ውስጥ ያስገባ ስለሆነ ሌሎችም በዚህ ደረጃ ገፍተው የሚቃወሙበት ምክንያት አይኖርም። እነርሱም ቢሆኑ ከእነዚህ ከብሪክስ አባል ሀገሮች ጋር ግንኙነት አላቸው። ሕንድ ከምዕራቡ ዓለም ጋር ጠንካራ ግንኙነት አላት። ብራዚል ከምዕራቡ ዓለም ጋር ጠንካራ ግንኙነት አላት። ታዲያ ኢትዮጵያ ጋር ሲደርስ ለምን የተለየ ይሆናል? ኢትዮጵያ ለምን ትቸገራለች? ለምን አባል ሆና አትጠቀምም?

አዲስ ዘመን፡- ምዕራባውያን የተባበሩት መንግሥታትን የመሳሰሉ ዓለም አቀፍም ሆኑ አህጉራዊ ድርጅቶችን በመጠቀም በሀገራት ላይ ጫና እንደሚያሳድሩ የሚታወቅ ነው። በብሪክስ በኩልስ ተመሳሳይ ጫና ሊፈጠር ስላለመቻሉ ምን ያህል እርግጠኛ መሆን ይቻላል?

አምባሳደር ዲና፡- አሁን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ላይ ለውጥ ለማምጣት ትልቅ የሪፎርም ሥራ እየተሠራ ነው። ይህ ጉዳይ የብዙ ታዳጊ ሀገሮች አጀንዳ ነው። ምክንያቱም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በተለይም የፀጥታው ምክር ቤት ሪፎርም ያስፈልገዋል። እኛ ጋር የተወሰኑ አካባቢዎችን የወከሉ ሀገሮች አሉ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ላይ አፍሪካ አባልነት ይገባታል፤ የላቲን አሜሪካ ሀገሮችም አባልነት መኖር አለበት የሚል የቆየ አጀንዳ አለ። በዚህ ረገድ በተባበሩት መንግሥታት በኩል የሚገፋው ነገር ብዙም ተቀባይነት አይኖርም። ደግነቱ እዚያም በተለይ በፀጥታው ምክር ቤት ውስጥ ድምፅን በድምፅ የመሻር ዕድል አለ። ኢትዮጵያ ደግሞ እዚያ ውስጥም ጠንካራ ወዳጅ ያላት በመሆኑ፤ ከዚህ ቀደምም እንደታየው በወዳጆቻችን አማካኝነት የተጠቀምንበት ሁኔታ አለ።

በዚህ በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ውስጥ እኛ ላይ ሊጫን የነበረውን አንዳንድ አጀንዳዎች ድምፅን በድምፅ በመሻር የመጠቀም መብታቸውን ተጠቅመው ውድቅ ያደረጉበት ሁኔታ አለ። ስለዚህ አሁንም የሚታየው በዚህ ደረጃ ነው። ስለዚህ የብሪክስ አባል ሀገራት የምዕራባውያኑን ስህተት ይደግማሉ የሚል እምነት የለኝም።

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ በሕዳሴው ግድብ ላይ አራተኛ ሙሌት አከናውናለች በዲፕሎማሲው መስክ የሚኖረው ጠቀሜታ ምን ያህል ነው ?

አምባሳደር ዲና፡– አራተኛው የሕዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት ትልቁ የዲፕሎማሲ ሥራ ስኬት ማሳያ ነው። ይህ በጣም ትልቅ ነገር ነው። ይህ በሀገር ደረጃ ኢትዮጵያውያን ከተባበርን ምን ያህል ውጤት ማምጣት እንደምንችል በደንብ ያሳየንበት ነው። ሁለተኛ በግድቡ ላይ እስከ አሁን የነበሩትን የዲፕሎማሲ መስክ ጫናዎችን ተቋቁመን እዚህ የደረሰንበት በመሆኑ፤ ትልቅ ሀገራዊ ስኬት ነው። ከዲፕሎማሲያችን አንፃርም ኢትዮጵያ ልትኮራበት የሚገባ ሲሆን፤ የሕዳሴ ግድቡ ሌሎች ሀገሮችን ለመበደል ሳይሆን ኢትዮጵያን እና አልፎ ተርፎ ሌሎችንም ይጠቅማል ተብሎ የተሠራ መሆኑን ማወቅ አለባቸው።

አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ እጅግ አመሰግናለሁ።

አምባሳደር ዲና፡– እኔም አመሰግናለሁ።

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን  መስከረም 12 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You