ሉሲዎቹ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ዛሬ ቡሩንዲን ለማሸነፍ ተዘጋጅተዋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ የእግር ኳስ ቡድን (ሉሲዎቹ) የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ዛሬ ከብሩንዲ አቻቸው ጋር ያደርጋሉ፡፡ ሞሮኮ አስተናጋጅ በሆነችበት የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ ለመሆን የሚደረገው የደርሶ መልስ ማጣሪያው ጨዋታ በአበበ ቢቂላ ስቴድየም ዘጠኝ ሰዓት ላይ ይካሄዳል፡፡

ጨዋታውንና የቡድኑን ዝግጅት አስመልክቶ የሉሲዎቹ አሠልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ትናንት በሰጡት መግለጫ ለአስራ ሁለት ቀናት ዝግጅት መደረጉን ጠቁመው በነዚህ ቀናት ተጫዋቾች ወደ አቅማቸው እንዲመለሱ መሥራታቸውን ተናግረዋል።፡ አንዳንድ የቡድኑ ተጫዋቾች ከክለቦቻቸው ጋር ስለነበሩ በቶሎ ወደ አቀማቸው የተመለሱ ሲሆን ረፍት ላይ የነበሩት ግን የተወሰነ ጊዜ እንዳስፈለጋቸው አሠልጣኝ ፍሬው አብራርተዋል፡፡

የክረምቱ ሁኔታና የመለማመጃ ሜዳ እጥረት ዝግጅታቸው ላይ ችግር እንደፈጠረባቸው አስረድተዋል፡፡ ሉሲዎቹ ለመጀመሪያው ዙር የማጣሪያ ጨዋታዎች ዝግጅት ለማድረግ አሠልጣኝ ፍሬው ለ26 ተጫዋቾች ጥሪ በማድረግ ወደ ሆቴል የገቡት ጳጉሜን 2/2015 ዓ.ም መሆኑ ይታወሳል። ቡድኑ ዝግጅቱን በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ሲያደርግ የቆየ ሲሆን ዳማ ከተባለ የወንዶች ቡድን ጋር በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የልምምድ ጨዋታ አድርጎ 7 ለ 7 በሆነ ውጤት ነበር የተለያየው፡፡ የማገባደጃ ዝግጅቱንም በአበበ ቢቂላ ስታዲየም አከናውኗል፡፡ ቀደም ሲል ዝግጅት ሲያደርግበት የነበረው የወጣቶች አካዳሚ ሜዳ በአካዳሚው በመፈለጉም ወደ አበበ ቢቂላ ስቴድየም ለመሄድ እንደተገደዱ አሠልጣኙ ገልፀዋል፡፡

አሠልጣኝ ፍሬው በሴካፋ ውድድር ስኬታማ እንደመሆኑ ከበርካቶቹ የሉሲዎቹ ስብስብ ጋር ለአራ ዓመት ቆይቷል፣ ይህም የራሱን ቡድን ለመገንባት የረዳው ሲሆን አሁንም ይህን ለማስቀጠል ከ 18ና ከ 20 ዓመት በታች ቡድን ተጫዋቾችን አሰባስቧል፡፡

‹‹ለአፍሪካ ዋንጫ የሚመጥን ዝግጅት ተደርጓል ብየ አላምንም፣ ምክንያቱም የዝግጅት ጊዜው ከማነሱ ባለፈ ተጫዋቾች ከእረፍት የተመለሱ በመሆናቸው ትንሽ አስቸጋሪ ነበር፣ ያምሆኖ ጥሩ ዝግጅት ለማድረግ ጥረት ተደርጓል›› በማለት አሠልጣኙ በመግለጫቸው ተናግረዋል፡፡

ወደ አፍሪካ ዋንጫው ለማለፍ በቀጣይ በሚኖሩ የማጣሪያ ጨዋታዎች ቡድኑን ለማስተካከል ጥረት እንደሚደረግ የገለፁት አሠልጣኝ ፍሬው፣ ሉሲዎቹ ከአፍሪካ ዋንጫ ከራቁ ረጅም ጊዜ በመሆኑና ተጫዋቾቻቸውም ውጤታማ መሆን ስለሚፈልጉ ትልቅ ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡

ከቡሩንዲ ጋር የሚደረጉት ሁለቱም ጨዋታዎች በኢትዮጵያ መካሄዳቸው ለሉሲዎቹ መልካም አጋጣሚ ሲሆን አሠልጣኝ ፍሬውም በሜዳቸው ባደረጉት ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ብቻ በመሸነፍ ጥሩ አፈፃፀም አላቸው፡፡

ለ15ኛ ጊዜ በመጪው የፈረንጆቹ ዓመት በሚካሄደው የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ላይ ተሳታፊ የሚሆኑ ቡድኖች የሚለዩበት የዚህ የማጣሪያ ውድድር የመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎች በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት በመከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡

የዛሬው ጨዋታ ከአንድ ቀን በፊት ሊካሄድ የነበረ ቢሆንም በመርሃ ግብር ለውጥ የመጀመሪያውን ጨዋታ ዛሬ ቀጣዩን ደግሞ በመጪው ማክሰኞ መስከረም 15/2016 በተመሳሳይ በአበበ ቢቂላ ስቴድየም እንደሚያደርግ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡ ሁለቱም ጨዋታዎች በአዲስ አበባ የመከናወናቸው ምክንያትም ብሩንዲ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር ስምምነት በማድረግና ለካፍ በማሳወቅ ነው፡፡

ከቀናት በፊት አዲስ አበባ የደረሰው የብሩንዲ ብሄራዊ ቡድንም ማረፊያውን በሆሊደይ ሆቴል ያደረገ ሲሆን፤ ልምምዱንም በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ሲያከናውን ቆይቷል፡፡

በደርሶ መልስ ጨዋታውን ያሸነፈው ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎውን የሚለየው በቀጣይ ከሚመደበው ሀገር ጋር በሚኖረው ጨዋታ ላይ የሚመሠረት ይሆናል፡፡ በመሆኑም በመጀመሪያው ዙር የደርሶ መልስ ጨዋታ የተሻለ ሆኖ መገኘት ወደ ውድድሩ አንድ እግርን እንደማስገባት ነው፡፡ በማጣሪያው 40 ሀገራት የሚሳተፉ ሲሆን፤ ሁለት ዙር በሚኖረው የማጣሪያ ውድድር የሚያልፉ ቡድኖች በአፍሪካ ዋንጫው ይካፈላሉ፡፡ በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) መሪነት ከሚካሄዱ ውድድሮች መካከል አንዱና ትልቁ ሲሆን፤ 12 ቡድኖችን በማሳተፍ ይካሄዳል፡፡

 ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን  መስከረም 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You