በድንጋይ ከሰል ምርት ከሚታወቁት አካባቢዎች አንዱ አዲሱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ነው፡፡ ክልሉ ከፍተኛ ኃይል ማመንጨት የሚችሉ የድንጋይ ከሰል ምርቶች የሚገኝበት እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ በተለይ የክልሉ ዳውሮ፣ ኮንታ እንዲሁም ከፋ ዞኖች በድንጋይ ከሰል ምርታቸው ይታወቃሉ፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ማዕድንና ኢነርጂ ልማት ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የማዕድን ዘርፍ ኃላፊ አቶ መንገሻ መዳልቾ በክልሉ ያለውን የድንጋይ ከሰል ክምትች አስመልክቶ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሲገልጹ በክልሉ ያለውን የድንጋይ ከሰል ማዕድን ክምችት ለማወቅ ጥናት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
እሳቸው እንደሚሉት፤ አሁን ባለው ሁኔታ እንደ ክልል የድንጋይ ከሰል ያለባቸው አመልካች ቦታዎች መገኛ ቦታ ተብለው በቦታ ደረጃ የተለዩ ናቸው፡፡ አሁን ላይ የሚሠራው ሥራ ከገጸምድር ላይ ያለና በከፊል ገጸ ምድር ላይ ያለውን ማዕድን የሚመረትበት ነው፡፡
ጥናቶቹ እንደሚያሳዩት፤ የድንጋይ ከሰል ለማግኘት በአንዳንድ ጥናቶች ላይ ከሦስት እስከ አራተኛ ሜትር ጥልቀት ያለው ሲሆን፤ በአንዳንዶች ላይ ደግሞ እስከ 22 ሜትር ጥልቀት ድረስ ሦስት ደረጃ ላይ ክልሉ የድንጋይ ከሰል ክምችት እንዳለ አመላካች ነገሮች ታይተዋል። ከዚያም አልፎ ጥልቀት ላይ ሊኖር እንደሚችል አመላካቾች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ በቀጣይ በግሉ ዘርፍ እንደዚህ ዓይነት አመልካቾቹን ተይዘው ሰፋ ያለ ጥናት ተደርጎ ቦታዎቹ ተለይተው ወደ ሥራ እንዲገቡ እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡
ይህንን ጥናት መሠረት በማድረግ 15 አነስተኛ ደረጃ አምራቾች እና ሦስት በከፍተኛ ደረጃ አምራቾች በአጠቃላይ 18 አምራቾች ፈቃድ ወስደው ድንጋይ ከሰል ለመምረት ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ ከክልሉ በ2015 በጀት ዓመት 748 ሺ24 ቶን ያህል የድንጋይ ከሰል ለማምረት ታቅዶ፤ 209ሺ398 ቶን ለማምረት ተችሏል፡፡
ከእቅዱ አንጻር አፈጻጸሙ ውስን ነው የሚሉት ኃላፊው፤ ለዚህም በርካታ ችግሮች መኖራቸውን በምክንያትነት ይጠቅሳሉ፡፡ ከገቢም አንጻር 30 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማስገባት ታቅዶ፤ 29 ነጥብ3 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘት መቻሉን ይናገራሉ፡፡
በእነዚህ አምራቾች ወደ ሥራ ሲገባ ከሚፈጠር የሥራ ዕድል አንጻር የተያዘው እቅድ በድንጋይ ከሰል ምርት ብቻ ለ600 ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ፣ ለ525 ዜጎች ቋሚና ጊዜያው የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል፡፡
የሥራ ዕድል ፈጠራን አስመልክቶ በክልሉ የማዕድን ዘርፍ መመሪያ ላይ በተቀመጠው አሠራር መሠረት እያንዳንዱ አምራች ከምርት ሽያጭ ገቢ 10 በመቶውን ለሥራ አጥ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ገቢ እንዲያደርጉ የሚያስችል አሠራር መዘርጋቱን ይናገራሉ፡፡ በቀጣይ እነዚህ አምራቾች በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ የሚገቡ ከሆነ ጥሩ ካፒታል የሚያስገኝና ጥሩ ሥራ የሚሠራበት መሆኑን ነው ኃላፊው የሚገልጹት፡፡
የድንጋይ ከሰል ማምረት ሥራ እስካሁን ባለው ሂደት ውጤታማ ነው ማለት አይቻልም የሚሉት ኃላፊው፤ ያለው ፍላጎትና የገበያ ሁኔታ የማይጣጣም መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ዘርፉ ላይ ለመሰማራት የሚፈልጉ ባለሀብቶች እንዳሉም ጠቅሰው፣ ባለሀብቶቹ ወደ ማምረት ሥራው ከገቡ በኋላ ግን ያለው ገበያ አስተማማኝ እንዳልሆነ ነው የተናገሩት፤ ገበያውን ሰብሮ ገብቶ ዘርፉ ላይ ውጤታማ ለመሆን በጣም ከባድ እየሆነባቸው አብዛኛዎቹ እየተቸገሩ መሆኑንም ይገልጸሉ፡፡
በዚህ የተነሳ የአምራቾች ምርት በሜዳ ላይ እየተቃጠለ አመት እስከ አመት ዝናብና ፀሐይ ተፈራርቆበት የሚባክንበት ሁኔታ መኖሩን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አመልክተዋል፡፡ ቢሠራበትና ገበያና አምራቹን የማተሳሰርበት ሁኔታ ቢኖር ከውጭ ሀገር በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚገባውን የድንጋይ ከሰል ማስቀረትና የሀገር ውስጥ ሀብትን በመጠቀም ጥሩ መነቃቃት ይፈጠራል የሚል እሳቤ ይፈጠር እንደነበርም ነው የገለጹት፡፡ አሁን ያለው የገበያ ማነቆ ካልተፈታ አስጊ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
በተለይ አምራቾች ምርታቸውን በቀጥታ ለፋብሪካዎች ለማቅረብ ይቸገራሉ የሚሉት ኃላፊው፤ ለዚህም ችግር በአምራቹና በፋብሪካው መሀል ያሉ ደላሎች መኖር መሆኑን ይጠቁማሉ። አምራቹ ማዕድኑን ለፋብሪካው አቅርቦም የምርቱ ውጤት ዝቅተኛ የሚሆንበት ሁኔታ እንዳለም ተናግረዋል። ምርቱ በፋብሪካው ተቀባይነት አላገኘም እየተባሉ ማዕድኑን መልሰው እንዲወስዱ የሚያደርግበት ሁኔታ እንዳለም ይጠቁማሉ፡፡ የተለየ የጥቅም ግንኙነት በመፍጠር የጥቅም ሽሚያ የሚያደርግበት ሁኔታ መኖሩን ነው የሚያመላክቱት። ይህ የሚያሳየው ጤናማና ፍላጎትን መሠረት ያደረገ አሠራር ዘርፉ ላይ እንደሌለ ነው ይላሉ፡፡
ችግሮቹ በየጊዜው በሚካሄዱ የምክክር መድረኮች በስፋት ይነሳሉ የሚሉት ኃላፊው፤ ይህ ችግር እስኪፈታና አስተማማኝ ገበያ እስከሚፈጠር ድረስ አዲስ ፈቃድ መስጠት መታገዱንም ያስታ ወቁት። አሁን ላይ ቀደምሲል ያሉ አምራቾች ፈቃዳቸውን አሳድሰው እያመረቱ ያለበት ሁኔታ እንዳለም ይጠቁማሉ፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚነሳውን ችግር አስመልክተው ሲናገሩ ምርቱ በስፋት ያለባቸው የዳውሮና የኮንታ ዞኖች መሆናቸውን ጠቅሰው፣ የማምረቱ ሥራ አሁን ላይ እየተስፋፋ መጥቶ በከፋም ዞን የድንጋይ ከሰል ምርት ፍተሻ ሥራ እየተሠራ እንደሆነም አመላክተዋል።
እነዚህ ቦታዎች ላይ እንደ መንገድ መሠረተ ልማት አለመኖር ያሉ የመሠረተ ልማት ችግሮች በስፋት እንደሚታዩም ጠቅሰው፣ ከተርጫ ማዕከል ወደ ሶዶ የሚያሸጋግረው አስፋልት መንገድ በመቆረጡ ምክንያት መንገዱ ዝግ መሆኑንና የጭነት እንቅስቃሴ ለማድረግ አዳጋች እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በተመሳሳይ ከተርጫ ወደ ጅማ የሚወስደው መንገድ በአዲስ የመንገድ ሥራና ከመንገድ ርቀት ጋር ተያይዞ እያሠራ ያለው ድርጅትም ለቆ የወጣበት ሁኔታ እንዳለ ተናግረው፣ የመንገድ ብልሸቶች የድንጋይ ከሰል ጭነው ለሚመጡ ድርጅቶች አስቸጋሪ መሆናቸውን ይገልጻሉ።
እሳቸው እንዳሉት፤ ቀደምሲል ጀምሮ በችግርነት ሲነሳ የነበረው የአካባቢው ማኅበረሰብ ተጠቃሚነት ችግር አንዱ ሲሆን፤ የአካባቢ ተጽእኖዎች በግልጽ ያልተለዩና በሕግም አሳማኝ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ሁኔታ አለመኖር ለተወሰኑ ጊዜያት ሥራዎች ሲያስተጓጉል ቆይቶ ነበር፡፡ በ2015 በጀት ዓመት መስከረም ወር ላይ የክልሉ ደንብ ከወጣ በኋላ የሚነሱ ችግሮችን በመፍታት የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ በአሠራርና በመመሪያ መሠረት ወደ ሥራ ተገብቷል።
በ2016 በጀት ዓመት የድንጋይ ከሰል ምርት ሥራውን አጠናክሮ ማስቀጠል የሚያስችል ሥራ ለመሥራት ታቅዷል የሚሉት ኃላፊው፤ በበጀት ዓመቱ 500ሺ ቶን ምርት ለማምረት የሚያስችል እቅድ መዘጋጀቱንም ይናገራሉ፡፡ የአምራቾች የማምረት ፍላጎት ከተቀመጠው ቁጥር ከፍ ያለ መሆኑን ጠቅሰው፣ ባለፈው ዓመት ካለው አፈጻጸም አንጻር ተነጻጽሮ ዘንድሮ 500ሺ ቶን ምርት ለማግኘት የሚያስችል ሥራ መሥራቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
ኃላፊው፤ በቀጣይ የምርት ፈላጊዎችና አምራቾች ፍላጎትን ባጣጣመ መልኩ ምርቱ እንዲመረት፤ አምራቹም ያለስጋት እንዲያመርት ተረካቢውም በቀጣይ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የሚቀበልበትን አሠራር መዘርጋት እንደሚጠይቅም አስታውቀዋል። ይህንን የማድረጉ ሥራ ደግሞ ኢንዱስትሪውን የሚመሩ አላካትን እና የባለድርሻ አካላትን ትብብር እንደሚጠይቅ ጠቅሰው፣ ይህ ካልሆነ ግን የታቀደውን ለማሳካት አይቻልም ይላሉ።
የድንጋይ ከሰል ምርት የሚመረትበት አካባቢ በአርሶ አደሩ ማሳ እና በሰዎች መኖሪያ አካባቢ መሆኑን ጠቅሰው፣ ከዚህ ጋር በተያያዘ አስተማማኝ ተጠቃሚነትና ገበያ ሳይኖር ተከፋፍተው የሚቀሩ ጉድጓዶችና የተለያዩ አካባቢ ጉዳቶች የመልካም አስተዳደር ችግር እያስከተሉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ችግሩ አስተማማኝ የሆነ የሥራ ቦታ እንዳይፈጠር እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፣ እንደዚህ ዓይነት ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ ታምኖበት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ ነው ብለዋል። እንደዚሁም በመንገድ በኩል የተነሱ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ ሥራዎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደሚሠሩ ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡
በዘርፉ ላይ የተነሱት ችግሮች ከተፈቱ የተሻለ ምርት ማምረት ይቻላል ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ በዋናነት ከገበያ ጋር የተያያዙ ችግሮች ተፈትተው አስተማማኝ ገበያ ሊኖር ይገባል ብለዋል። በዚህ የተነሳ አሁን ላይ ካሉት 15ት አምራቾች ውስጥ ያለውን የገበያ ሁኔታ ተቋቁመው ውጤታማ ሆነው እየሠሩ ያሉት አራት ያህሉ መሆናቸውን ገልጸዋል። እነዚህም ቀጥተኛ የሆነ የገበያ ትስስር ስላላቸው እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡
አሁን ላይ በዓመት ከ20ሺ በላይ ቶን ያመርታሉ ተብለው ፍቃድ ያገኙ ከፍተኛ አምራቾች የሚያመርቱት ምርት ከአንድ ሺ ቶን የማይበልጥ እንደሆነ የሚናገሩት ኃላፊው፤ እነዚህ አምራቾች በሙሉ አቅም እንዲያመርቱ በፌዴራል ማዕድን ሚኒስቴርና በክልሉ ክትትል ተደርጎ ቢሠራ አሁን ካለው የቅንጅትም ሆነ የጥራት ደረጃ የተሻለ ውጤት ማምጣት ይቻላል ብለዋል፡፡
እሳቸው እንደሚሉት፤ በድንጋይ ከሰል ላይ ከተጠቃሚ አንጻር የሚነሱ ችግሮች አሉ፡፡ የኃይል የማመንጨት አቅሙ ከ3ሺ ካሎሪ እስከ 6ሺ ካሎሪ ያለው የድንጋይ ከሰል በተለያየ ፋብሪካዎች ደረጃ ይፈለጋል፡፡ ዝቅ ያሉ እስከ 3ሺ የካሎሪ መጠን ያላቸው የድንጋይ ከሰል ምርቶች ደግሞ በጨርቃጨርቅ፣ በቀለም እና በተለያዩ ፋብሪካዎች ኃይል ለማመንጨት ይፈለጋሉ፤ ከፍ ያሉት 6ሺካሎሪ እና ከዚያ በላይ የሆኑ ካሎሪ ኃይል የማመንጨት አቅም ያላቸው የድንጋይ ከሰሎች በሲሚንቶ ፋብሪካ ሊፈለጉ የሚችሉ ናቸው፡፡
የድንጋይ ከሰል ምርትን መስፈርቱ (ስታንዳርዱን) የጠበቀ ለማድረግ ከምርት ሂደት አንጻርም ዝቅ ሊል እንደሚችል የጠቆሙት ኃላፊው፤ እንደ አመድ፣ ድንጋይ እና ሌሎች የተቀላቀሉ ነገሮች አንድ ላይ ተቀላቅለው እንዲጫኑ መደረጉ በጥራቱ ላይ ጫና ሊፈጥሩ እንደሚችል ይናገራሉ፡፡ ለዚህም መፍትሔ በማፈላለግ ሂደት እንደዚህ ዓይነት ነገሮች የሚለይ ፕሮሰሲንግ ማሽን በዳውሮ ዞን በኢትዮ ማይኒንግ ኮርፖሬሽን የመትከል ሂደት እያለቀ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
ከጥራት ጋር ተያይዞ የሚሠሩ አበረታች ሥራዎች እንዳሉም ነው ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ የገለጹት። በቀጣይ ከገበያው ፍላጎትና ከጥራት ደረጃው ጋር ስታንዳርዱን የጠበቀ የድንጋይ ከሰል ምርት ለውጭና ለሀገር ውስጥ ገበያ የሚቀርበበትን ሁኔታ ለማመቻቻት ያስችል ዘንድ ቀድሞ የተተከለው ማሽን ውጤታማነት እየታየ እንዲሁ በኮንታ አካባቢ ይህንን ፕሮሰሲንግ ማሽን ሥራ እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን የገበያና የጥራት ችግርን ለመቅረፍ ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር የሚሠሩ ሥራዎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት ካለው ሁኔታ ጋር ተያይዞ ለማምረት ፈቃድ አውጥተው ማምረት የቻሉ አምራቾች መኖራቸውን ኃላፊው ጠቁመዋል፤ የድንጋይ ከሰል ምርትን በሀገር ውስጥ የመተካት ሥራው በቅርብ ጊዜ የተጀመረ ቢሆንም አሁን ላይ መነቃቃትን የፈጠረ ነው ብለዋል፡፡ ያለውን ምቹ ሁኔታ ተጠቅሞ ቢሠራ በቀጣይ የተሻለ ውጤት ይመጣል ብለው እንደሚያሰቡ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን መስከረም 11 ቀን 2016 ዓ.ም