ሴትና ሴት

መጀመሪያ ያየኋት ከእናቷ ጋር ነው.. እሷን ከምትመስል መልከኛ እናቷ ጋር፡፡ ከሴት የተወዳጀ ሴትነት መልኩን በእሷ ነው ያየሁት፡፡ ከእናት የተወዳጀ ሴትነት ከአባት እንደተወዳጀ ወንድነት ይሆን? በትልቅነት የእናትን ክንድ ተደግፎ በጠዋት ከእንቅልፍ መንቃት፣ የዓለምን ኑባሬ በሴት ነፍስ በኩል መሻገር እናት የሌለኝ እኔ ባየኋት ቁጥር እንዲህ አስባለው፡፡ በሕይወቴ ትኛንት የማያመኝ ሰው ነኝ፡፡ ትኛንት በእኔ ላይ ጀግና ሆኖ አያውቅም፡፡ ማፈሪያው ነኝ.. ብዙ ትናንትናዎችን እንክትክት አድርጌአለው፡፡ ብዙ ያስለቀሱኝን ትናንቶች እንባዬን አብሼ እንደጣልኩት ምናምንቴ ሶፍት የት ጋ እንደወረወርኳቸው አላስታውሳቸውም፡፡ በእናቴ በኩል የተዋወቅኩት ትናንት ግን ዛሬም ድረስ ያላግጥብኛል፡፡

እናም ይቺን ሴት አያታለው.. ልትወድቅ ያለችውን ዓለም በእናቷ በኩል ስታልፋት፡፡ ለሴትነት የማትመቸውን ጦብያ በእናቷ መሰላልነት ስትረማመዳት፡፡ ከሊስትሮዬ ቀና የምለው እሷን ከእነ እናቷ ለማየት ነው.. እና ልሸኛት፡፡ እየሳቀች ለማንም ግድ በሌለው ሳቅ እና ወሬ በወሬዋ እናቷን እያሳቀች በአጠገቤ ታልፋለች፡፡ የእናቷ ይሆን የእሷ የማላውቀው ውብ ጠረን ጀልጦኝ ያልፋል። አንገቴን ሰብሬ አስተውላቸዋለው፡፡ እናም ሃሳቤ በልጅነቴ እንደወጣች በቀረችው የእናቴ ኮቴ ላይ ተረማምዶ የብዙ ዓመቷን እናቴን ያስታውሰኛል፡፡

ወይ በግንቡ ወይ ደግሞ በሚመጣውና በሚሄደው ሰው ሲከለሉብኝ ከነናፍቆቴ ልጠርገው ወዳሰናዳሁት ጫማ እመለሳለው፡፡ በሄዱበት ተመልሰው አያውቁም፡፡ ይሄን ስለማውቅ እኔም ጠብቄአቸው አላውቅም፡፡ ዛሬ ግን ተስፋ በቆረጥኩበት ሰዓት በሄዱበት መንገድ ሲመለሱ አየኋቸው። ወጣቷ ከነወሬዋ ናት.. ለማንም ግድ በሌለው ወሬዋ እናቷን እያሳቀች፡፡ በልጅ ወሬ የእናት ሳቅ እንደ ማለዳ ጣይ.. በእናት ወሬ የልጅ ፈገግታ እንደ ከሰዓት ጠራራ መሰሉኝ፡፡ በአንድ ሰማይ፣ በአንድ ጀምበር ላይ ተራርቀው የሚያበሩ፡፡ ወዳለሁበት ሲጠጉ ዝግ አሉ ከእርምጃቸው፡፡ የልጅቷ ወሬና የእኗቷ ሳቅ ግን አልተቋረጠም።ሊያልፉኝ ነው ስል ወጣቷ ካንጠለጠለችው ፔስታል ውስጥ ዘለበቱ የለቀቀ ጫማ እያወጣች ‹እንካ ስፋልኝ› ስትል እስክቀበላት ሳትጠብቅ መሬት ላይ ወረወረችው፡፡ ውርወራዋን ከክፉ አልቆጠርኩትም፡፡ ወደእግሯ አይኔን ስሰድ አንድ እግሯ ርቃኑን ነው፡፡ ተበጥሶባት እንደሆነ ገባኝ፡፡

እግሯ ያምራል፡፡ ጥፍሮቿ በቀለም አጊጠው ጉረሱኝ ጉረሱኝ ይላሉ፡፡ እግሯ ላይ አቀርቅሬ ቶሎ ቀና ማለት አልቻልኩም፡፡ የመላዕክት በሚመስል በዛ የተመጠነ ርምጃ እየረገጠች እንዴት ተበጠሰባት? ስል ራሴን ጠየኩ፡፡ እግዜር መናፈቄን አይቶ ከፊቴ ሊያቆማት አስቦ እንጂ በዛ ርምጃ አይደለም ጫማን ያክል ነገር ሊገነጠል ቀርቶ ቁጫጭ እንኳን እንደማይጨፈለቅ እርግጠኛ ሆንኩ፡፡

የምጠርገውን ጫማ ለመጨረስ መፍጠን ጀመርኩ፡፡ ሃሳቤ፣ ቀልቤ ሁሉ መሬት ወደወደቀው ጫማ ነው፡፡ ‹ምን አስቸኮለህ ረጋ በል እንጂ› አሉኝ ሽማግሌው ደንበኛዬ ቁጣና ግሳጼ በቀላቀለ ድምጽ፡፡ በሳምንት ሶስት ቀን ወዳለሁበት መጥተው ጫማቸውን ያስጠርጋሉ፡፡ እንዲህ እንደአሁኑ በሳምንት ሶስት ቀን የማይቀርልኝ ቁጣና ግልምጫ አለኝ፡፡ አንደበታቸው ለመቀየም የቀረበ ነው፡፡ እግዜር ወርዶ በመለኮት እጁ ጫማቸውን ቢጠርግላቸው እንኳን እንከን ከማውጣት ወደኋላ የማይሉ ናቸው፡፡ ሳይቆጡኝ መልካም ቀን ተመኝተውልኝ አያውቁም፡፡ የእሳቸው ጨርሼ መሬት ወዳለው ጫማ እጄን ሰነዘርኩ፡፡

‹ኧረ በደንብ ጥረገው.. ለኮስኮስ አድርገህ ተውከው እሳ? አሉኝ እግራቸውን ከሊስትሮ እቃዬ ላይ ላለማውረድ እያመጹ። በምን ክፉ ቀን ነው እኚህን ሰውዬ ደንበኛ ያደረኩት አልኩ በሆዴ። ሁሌ እንዳጉረመረምኩ ነው፡፡ የከረሙ ደንበኛዬ ናቸው። እንደእሳቸው ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ደንበኛ የለኝም፡፡ ዞረው ይመጡና እዚህ ጋ ቀለም አላጠጣህልኝም› ሲሉ ለዳግም ቡረሻ እግራቸውን ሊስትሮዬ ላይ ያሳርፋሉ፡፡ ለዚህኛው አይከፍሉኝም.. አንድ ጊዜ ከፍለው ቀን ሙሉ እየተመላለሱ ማስጠረግ የሚያምራቸው ናቸው፡፡ ከተገዛ ዘመን ያስቆጠረ ጫማቸው ከነሱ አልፎ ለእኔም መከራ ሆኖኛል፡፡

ቶሎ እንዲሸሹኝ ብዬ በጣቴ ቀለም ቆንጥሬ ያሉኝ ቦታ ላይ ቀባሁላቸው፡፡ አልተዉኝም፡፡ እግራቸውን እያዟዟሩ እዚህ ጋ.. እየህ ጋ እያሉ መከራ ሲያሳዩኝ ሰንብተው ጥርግ አሉልኝ። የእሳቸው መሄድ በእኔ ሕይወት ውስጥ ብዙ ነገር ነው፡፡ መሄዳቸውን ሳውቅ እና እንደማይመለሱ ሳረጋግጥ ወደወደቀው ጫማ እጄን ዘረጋሁ፡፡ አገላብጬ ካየሁት በኋላ ጉልበቴ ላይ የሥራ ጨርቅ አንጥፌ በጥንቃቄ መስፋት ጀመርኩ፡፡ ጫማውን በግራና በቀኝ አንቄ ስሰፋ.. ሴትነቷን ያንደባለልኩት መሰለኝ፡፡ እናት እና ልጅ አጠገቤ ሆነው ያስካካሉ፡፡ የተቀየረ ነገር የለም ልጅ አውሪ እናት ሳቂ ሆነው፡፡ ጆሮዬን ለወሬአቸው ሰጥቼ በግማሽ ልብ ስፌቴን ቀጠልኩ፡፡ ወሬ የማያልቅባት.. የወሬ መጋዘን መሰለችኝ። ትንፋሽ ለመውሰድ ስታርፍ እንኳን አላያትም፡፡ ባልተዛነፈ እና ባልተደነቃቀፈ አንደበት ስታወራ ስሰማት የቬቶቨን ሙዚቃ የማይረባ ነው ስል አሰብኩ፡፡

የእናቷ ጽናት አስቀናኝ፡፡ በልጇ ወሬ ሳትስቅ የቀረችበትን አፍታ አላስተዋልኩም፡፡ ልጅን እንዲህ ማድመጥ ለእናቶች ብቻ የተሰጠ ጸጋ እስኪመስለኝ ድረስ በትልቋ ሴት ተደነቅኩባት። እናትነት ትርጉሙ ልጆቿን ማድመጥ፣ በወሬዎቻቸው መሳቅ ከዛም..ከዛም..ከዛም መሰለኝ፡፡

በወሬዋ ተሰናክዬ ሳላውቅ እጄን ወጋሁት፡፡ ባሰማሁት የስቃይ ድምጽ ሁቱም ተሽቀዳድመው ወደ እኔ ዞሩ፡፡ ትልቋ ሴት እናትነትን በሚያሳብቅ አኳኋን ‹እኔን እኔን› አለችኝ፡፡ ትንሽዋ ሴት ወሬዋን ጋብ ከማድረግ ባለፈ የተናገረችው አልነበረም፡፡ ፊቷ ላይ ግን ብዙ ራሮትን አስተውዬ ነበር፡፡ ደሙ ብዙ ስለነበር ከእኔ አልፎ የምሰፋውን ጫማ በክሎት ነበር፡፡ ደግነቱ ጫማውን ሰፍቼ ስጨርስ ነው የተወጋሁት፡፡ ‹በቃ ተወው! እጅህን እሰረው› አለችኝ ባለጫማዋ ሴት፡፡ ቀና ስል አይን ለአይን ተጋጨን፡፡

‹ይቅርታ ጫማሽን ደም አስነካሁብሽ› አልኩኝ..ደም የነካውን ጫማ እያጸዳዳሁ፡፡

‹ለጫማው ታስባለህ እጅህ ተወግቶ? የሚል ከማን እንደሆነ ያለየሁት ድምጽ ተሰማኝ፡፡

አጠገቤ ሆና እንዲህ የምትራራልኝ ነፍስ እፈልግ ነበር። እናቴ ናፈቀችኝ..፡፡ ወደ ራቀ ትናንት ኮበለልኩ፡፡ በመልክ እኔን የምትመስል ጠይም ጠንበለል ሴት በልጅነቴ የሆነ ቦታ ላይ ብቅ አለች፡፡ ከዚህ ሌላ አላስታውሳትም፡፡ ለአፍታ ትውስ ብላ ጠፋችብኝ፡፡ እናቴን የማስታውሳት.. ረጅም ቀሚስ ለብሳ፣ ባለጥለት ነጠላዋን ግራና ቀኝ ትከሻዋ ላይ ጣል አድርጋ.. እንደመላዕክት የሰፈራችንን ወንድ በሚማርክ ውበት እና ርምጃ ነው፡፡ ከዚህ ሌላ አላስታውሳትም..፡፡ ነፍስ አውቄ ላውቃት ስሞክር ነው እንደወጣች የቀረችው፡፡ ከመዳህ ወደዳዴ ከዛም ወደወፌ ቆመች ተሸጋግሬ..እማይ የሚለውን የልጅነቴን የመጀመሪያ ቃል በተለማመድኩበት አንድ ማታ ላይ ነው እንደወጣች የቀረችው፡፡ ስትወጣ በር ድረስ ተከትያት ነበር..ግን መጣሁ ብላ በምወደው መጫወቻዬ አባብላኝ ወጥታ ቀረች፡፡ ይቺ አፍታ የምቆጭባት ደግሞም የምስቅባት ሁሉንም መሆኛዬ ናት፡፡ እናቴ ወዳለችበት ወደትናንት ስሄድ ከዚህ ቁጭትና ሳቅ ጋር ነው የምላተመው፡፡

ቀና አልኩ ወደ እናትና ልጅ፡፡ እናቷ አጠገቧ የለችም፡፡ ራቅ ብላ ስልክ ስታወራ አየኋት፡፡ ጫማዋን ሰፍቼና በሳሙና ጠርጌ አዲስ አስመስዬ ሰጠኋት፡፡ ‹ሁለት አይነት ጫማማ አላደርግም፣ ይሄንንም ጥረግልኝ› ስትል አውልቃ ሰጠችኝ፡፡ ትዝ ሲላት እጄ ደምቷል…ኦ ይቅርታ..ረስቼው‹ ስትል ያወለቀችውን ጫማ መልሳ አጠለቀችው፡፡ እብድ ነገር ናት..የትኛውንም ሰው የሚያስፈነድቅ እብደት አላት፡፡ ትንሽ እብደት ጣፋጭ ናት ስል እንዳስብ ሆንኩ፡፡

‹ለእኔ አስበሽ ከሆነ መወጋት የለመድኩት ነገር ነው፣ አምጪ ልጥረግልሽ? አልኳት፡፡

‹ኖ..እጅህ እንዲህ ሆኖ እማ አላስጠርግህም› ስትለኝ ። ኪሷን በርብራ አንድ መአት የመሰለኝን ብር ይዛ ተመለሰች፡፡ ‹እና በእኔ ጫማ ጦስ ሥራ ልትፈታ ነው? ስትል ወሬዋንም ብሩንም እኩል አስታቀፈችኝ፡፡

‹ዋጋ ግን አልጠየቅሽኝም? አልኩ የብሩ መብዛት አስደንግጦኝ አንጋጥቼ እያየኋት፡፡

‹መቼም ከዚህ አይበልጥም ብዬ ነው› ስትል ለመፍገግ ሞከረች፡፡

‹ጫማሽን ሰፋሁልሽ እንጂ አልሸጥኩልሽም፡፡ ይሄ ቀን ሙሉ ሰርቼ የማላገኘው ገንዘብ ነው› አልኳት፡፡

እናቷ መጥተው ኖሮ ‹ቢሆንም ያዘው..ደምህ ፈሷል እኮ› አሉኝ፡፡

‹ባይሆን ደንበኛዬ ሁኑ፡፡ እዛ ጋ አንድ ጎበዝ ጫማ ሰፊ አለ እያላችሁ የሰፈራችሁን ሰዎች ወደእኔ ከላካችሁ ይበቃኛል› ስል በእንቢታዬ ጸናሁ፡፡ ሆኖም ግን አልተሸነፉም..ብሩን አጠገቤ አስቀምጠው ወሬና ሳቃቸውን ካቆሙበት በመቀጠል ትተውኝ ሄዱ፡፡ እናቴ ትታኝ እንደሄደችበት እንደዛ ቀን የሆነ ባይተዋርነት ወረረኝ፡፡ እናቴ ወጥታ እንደቀረችበት እንደዛ ማታ የሄዱበትን አስተውል ጀመር፡፡

የእናት ፍቅር..እንደባለወልድ ፍቅር ነው፡፡ ራስን መስቀል ላይ የሚጥል፡፡ ትውልድ በሚመላለስበት እልፍ እግሮች ውስጥ በአንድ ኮቴ ፍቅር መውደቅ፡፡ ውቅያኖስ ውስጥ ሆኖ ውሃ መጠማት፣ ዳቦ ቤት በራፍ ላይ በርሃብ ማዛጋት..በግንቦት ጸሀይ ፊት እትት ማለት የእናት ፍቅር ከሕይወት ተቃርኖ ነው፡፡

በነጋታው ጠዋት ከማለዳዋ ጣይ ውጋግ ጋር የሚወዳደር አንድ ፈገግተኛ ፊት ከርቀት አስተዋልኩ፡፡ የትናንት ማታዋ ሴት አንድ እግር ጫማ አንጠልጥላ ወደእኔ ስትመጣ እናቴ በወጣችበት መንገድ እየተመለሰች ነበር የመሰለኝ፡፡

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን  መስከረም 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You