በንፁህ ልብ ሰብዓዊነትን የማጠንከር በጎ ተግባር

የኢትዮጵያውያን መገለጫ ናቸው የሚባሉ በርካታ መልካም እሴቶች እየተዳከሙ መጥተዋል የሚለው ወቀሳና ስጋት፣ ብዙ ዜጎችን ጉዳዩ እንዲያሳስባቸውና እነዚህን መልካም እሴቶች ለመመለስም ጥረት እንዲያደርጉ ምክንያት ሆኗቸዋል፡፡ ‹‹ልባችን አላስፈላጊና ጎጂ በሆኑ ነገሮች ተሞልቶ ሰብዓዊነት ነጥፏልና በንፁህ ልብ ታግዘን ሰብዓዊነትን ማጠንከር ይገባል›› ያሉ ወገኖች ያቋቋሙትና በዘርፈ ብዙ ምግባረ ሰናይ ተግባራት ላይ የተሰማራው ‹‹ንጹህ ልብ የበጎ አድራጎት ድርጅት››፣ የዚህ ጥረት ማሳያ ተደርጎ ይጠቀሳል፡፡

‹‹ንፁህ ልብ›› የበጎ አድራጎት ድርጅት የተመሠረተውና አገልግሎት መስጠት የጀመረው በ2013 ዓ.ም ሲሆን፣ ከኢፌዴሪ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ፈቃድ ያገኘው ደግሞ በየካቲት ወር 2014 ዓ.ም ነው፡፡ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ታምራት በቀለ የድርጅቱ ምስረታ በሚኖርበት አካባቢ ከነበረው ነባራዊ ሁኔታ ጋር የተሳሰረ እንደሆነ ይገልፃል፡፡ ‹‹ድርጅቱን ያቋቋምነው ሰዎች በምንኖርበት አካባቢ አንዳንድ ማኅበራዊ ችግሮች ነበሩ፡፡ እኛም ችግሮቹን ስለምናውቃቸው እድሜያችን እየጨመረ ሲመጣ የአካባቢውን ችግር እንዴት ማቃለል እንዳለብንና ለዚህም የእኛ አበርክቶ ምን ሊሆን እንደሚገባ ማሰብና መነጋገር ጀመርን›› ሲል ይገልጻል፡፡

እነ ታምራት ሃሳቡን እያጎለበቱ መጥተው እንዴት ወደ ተግባር መቀየር እንዳለባቸው ስምምነት ላይ ይደርሳሉ፡፡ ሰዎችን በማስተባበር ደጋፊ የሌላቸውን አረጋውያን፣ ልጆችንና አካል ጉዳተኞችን ለመርዳት ወስነውም ሥራውን ጀመሩት፡፡ ‹‹የምግብ፣ የአልባሳትና ሌሎች ድጋፎችን በማሰባሰብ ድጋፍ ማድረግ ጀመርን።ሥራው እየተጠናከረና እየሰፋ ሲመጣ ደግሞ ግልጽና ሕጋዊ በሆነ መንገድ መንቀሳቀስ አስፈላጊ እንደሆነ በማመን፣ ለኢፌዴሪ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን የፈቃድና እውቅና ጥያቄ አቀረብን፡፡ ጥያቄያችንም ተቀባይነት አግኝቶ በየካቲት ወር 2014 ዓ.ም ሕጋዊ ፈቃድ አገኘን›› በማለት ስለድርጅቱ አመሠራረት ያወሳል፡፡

‹‹ንፁህ ልብ›› ተብሎ የመሰየሙ ምክንያት ከድርጅቱ አመሠራረትና ዓላማ ጋር የተሳሰረ እንደሆነ አቶ ታምራት ይገልፃል፡፡ ‹‹የበጎ አድራጎት ድርጅቱን ስም ‹ንፁህ ልብ› ብለን የሰየምነው ሰው ሰብዓዊነት የሚሰማው ንፁህ ልብ ሲኖረው ነው፡፡ ቀደም ሲል በሀገራችን የነበሩት ብዙዎቹ በጎ ማኅበራዊ እሴቶች አሁን ተዳክመዋል፡፡ መልካም ጉርብትና፣ መረዳዳት፣ መቻቻልና መተሳሰብ እየተዳከሙ የመጡት በተለያዩ ምክንያቶች ልባችን ርህራሄና ሰብዓዊነት ስለጎደለው እንደሆነ እናምናለን፡፡ ልባችን ለግላችንም ሆነ ለሀገራችን ሊጠቅሙ በማይችሉ በጎ ያልሆኑ ሃሳቦችና ድርጊቶች እየተሞላና እየደፈረሰ በመሆኑ ሰብዓዊነት እየራቀን እንደሆነ እናስባለን፡፡ ስለዚህ አንድ ግለሰብ ሰብዓዊነት የሚሰማው ልቡ ከአላስፈላጊ ነገሮች ሲርቅና ሲፀዳ ነው፡፡ እኛም የድርጅቱን ስም ‹‹ንጹህ ልብ›› ብለን የሰየምነው፣ ከመጥፎና ከአላስፈላጊ ነገሮች የፀዳ ልብ ለሰብዓዊነትና ለበጎነት ወሳኝ ግብዓት መሆኑን በማመን ነው፡፡ ድርጅቱ ያለምንም የዘር፣ የሃይማኖትና የቋንቋ ልዩነት በንጹህ ልብና በሰብዓዊነት ብቻ የተቸገሩ ወገኖችን የሚረዳ ነው›› በማለት ስለድርጅቱ ስያሜ መነሻ ምክንያትም ያስረዳል፡፡

የ‹‹ንፁህ ልብ የበጎ አድራጎት ድርጅት›› ተግባራት በስድስት ዘርፎችና የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ ያተኮሩ እንደሆኑም ሥራ አስኪያጁ አቶ ታምራት ያብራራል። እነዚህም ዘርፎች አረጋውያን፣ ሕፃናት፣ አካል ጉዳተኞች፣ ማማከርና ሥልጠና፣ ሀገራዊ ልማት እና የገቢ ማሰባሰቢያ ናቸው፡፡ ድርጅቱ በእነዚህ የትኩረት ዘርፎቹ አገልግሎት የሚሰጠው በቤት ለቤት ድጋፍና እንክብካቤ እና በድርጅቱ የማገገሚያና የመኖሪያ ማዕከል አማካኝነት ነው፡፡

አቶ ታምራት እንደሚናገረው፣ ድርጅቱ አተኩሮ የሚሰራባቸው ዘርፎች እርስ በእርስ የሚደጋገፉና ለሀገር ልማትና እድገት አስተዋፅኦ ያላቸው ናቸው። ለሀገር ብዙ ውለታ የዋሉ አረጋውያን ያለ ደጋፊ እንዳይቀሩ፣ የነገ የሀገር ተስፋ የሆኑ ህፃናት ተስፋቸው እንዳይጨልም፣ ችሎታ ኖሯቸው በተለያዩ ምክንያቶች ችሎታቸውን እንዳይጠቀሙና አላስፈላጊ ለሆነ የሕይወት ውጣ ውረድ የተዳረጉ ወጣቶች ካሉበት ችግር እንዲላቀቁ እንዲሁም አካል ጉዳተኞች የተሻለ የኑሮ እድል እንዲያገኙ ድርጅቱ አልሞ ይንቀሳቀሳል፡፡

የበጎ አድራጎት ተግባራቱም ሥነልቦናዊ፣ መንፈሳዊ፣ አካላዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥንካሬና ብልጽግናን እውን በማድረግ የተሻለ አካታችና የበለፀገ ማኅበረሰብ ለመፍጠር የሚያግዙ ናቸው። ድርጅቱ ከሚያደርጋቸው የምግብ፣ የአልባሳትና የሌሎች ቁሳቁስ ድጋፍ በተጨማሪ በሀገራዊ ልማት የትኩረት ዘርፉ የንጹህ መጠጥ ውሃ፣ የትምህርትና የጤና ተቋማት ግንባታዎችን የማከናወን እቅዶችም አሉት፡፡

‹‹ንጹህ ልብ›› የበጎ አድራጎት ድርጅት እስካሁን ባከናወናቸው ምግባረ ሰናይ ተግባራት የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ አድርጓል፡፡ ታምራት እንደሚናገረው፣ ድርጅቱ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ በሰራቸው ሥራዎች ለአረጋውያን፣ ለሕፃናት፣ ለሱስ ተጠቂዎች፣ ለሴተኛ አዳሪዎች እና ሥራ ፈላጊ ወጣቶች ድጋፎችን አድርጓል፤ የሥልጠናና ማማከር አገልግሎቶችን ሰጥቷል፡፡ ድርጅቱ የአዲስ አበባ እና የአራት ማዕዘናት የተሰኙ ሁለት የፕሮጀክት ክፍሎች አሉት፡፡ የአራት ማዕዘናት ፕሮጀክት ክፍሉ ድርጅቱ ከአዲስ አበባ ከተማ ውጭ በክልሎች የሚያከናውናቸውን ምግባረ ሰናይ ተግባራትን የሚያስተባብርበት የሥራ ክፍል ነው፡፡

በምዕራፍ አንድ የበጎ አድርጎት ሥራው በአዲስ አበባ፣ የካ ክፍለ ከተማ በ 12 ወረዳዎች ለሚኖሩና በኅብረተሰብ ተሳትፎና በጎ አድራጎት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቶች ለተመረጡ 324 ችግረኛ ወገኖች (108 አረጋውያን፣ 108 ሕፃናት እና 108 አካል ጉዳተኞች) የምግብ፣ የአልባሳትና የሌሎች ቁሳቁሶች ድጋፎችን አድርጓል፡፡ ድጋፍ የተደረገላቸው ወገኖች ምንም ዓይነት ገንዘብና የኑሮ መሠረት ያልነበራቸው በመሆኑ የድርጅቱ ድጋፍ ሕይወታቸውን ታድጓል፡፡ የትምህርት መሣሪያዎች ድጋፍ የተደረገላቸው ልጆችም ትምህርታቸውን ሳያቋርጡ መቀጠል ችለዋል፡፡

የድርጅቱ ድጋፎች አካል ጉዳተኞችም የሕክምና ክትትል እንዲደረግላቸው እንዲሁም አጋዥ እንዲያገኙ አስችሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ድርጅቱ የሚያከናውናቸው የበጎ አድራጎት ተግባራት የከተማ አስተዳደሩ ለሚሠራቸው ችግረኛ ወገኖችን የመደገፍ ሥራዎች ተጨማሪ አቅም የሚፈጥሩ ሆነዋል። ድርጅቱ ከተቋቋመ ገና ሁለት ዓመታትን ብቻ ያስቆጠረ መሆኑን አስታውሶ፣ በቀጣይም የበጎ አድራጎት ሥራውን ወደ ሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች በማስፋት እንደሚሠራ ይገልፃል፡፡

የድርጅቱ የማማከርና ሥልጠና አገልግሎት በተለያየ የኑሮና የጤና ደረጃ ላይ በሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ ያተኩራል፡፡ ሴተኛ አዳሪዎች ካሉበት አስከፊ ሕይወት እንዲወጡ ለማስቻል የሥነ-ልቦና ድጋፍ በመስጠት ራሳቸውን ማቋቋም እንዲችሉ እገዛ ያደርጋል፡፡ በተለያዩ ሱሶች ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ከሱስ እንዲላቀቁ ይደግፋል፡፡ በተጨማሪም አዕምሮ ህሙማን ሕክምና የሚያገኙበትን እድል ያመቻቻል። በሥራ ላይ ላሉ ወጣቶች የሰብዕና ግንባታ ሥልጠናዎችን ሰጥቷል፡፡ ከእነዚህ አገልግሎቶች በተጨማሪ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ ለማድረግ እየሠራም ይገኛል፡፡ በሁለት ዓመታት ውስጥ ከአንድ ሺ ሦስት መቶ በላይ ሰዎች የድርጅቱን የሥልጠናና የማማከር አገልግሎት አግኝተዋል፡፡

‹‹ንፁህ ልብ›› የበጎ አድራጎት ድርጅት ከአዲስ አበባ ከተማ ውጭ በጉራጌ ዞን፣ ማረቆ ወረዳ ለሚገኙ ከ200 በላይ ልጆች በዓመት ለሁለት ጊዜያት ያህል የአልባሳትና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፎችን ያደርጋል፡፡ ይህ ተግባርም በአካባቢው የአልባሳትና የትምህርት ቁሳቁስ እጥረት ያለባቸው ልጆች ችግራቸው እንዲቃለልና ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ አስችሏል፡፡

ከአንድ ሺ 500 በላይ አባላት ያሉት ድርጅቱ፣ የበጎ አድራጎት ተግባራቱን ለማከናወን የሚያስችለውን ገንዘብ የሚያገኘው ከአባላቱ መዋጮ እንደሆነም አቶ ታምራት ይናገራል፡፡ ‹‹ለተረጂዎች የምንሰጠውን ገንዘብና ቁሳቁስ የምናገኘው የድርጅቱ አባላት በሚያደርጉት ድጋፍ ነው፡፡ ሰዎች የድርጅቱ አባላት እንዲሆኑ እንጋብዛለን፤ ፈቃደኛ የሆኑት ቋሚ አባላት ይሆናሉ፡፡ አባላቱ ድጋፍ የሚያደርጉበትን አሠራር በመፍጠርና ከአባላት የሚሰበሰበውን ድጋፍ ለሦስት ወራት በማጠራቀም ድጋፍ ለሚደረግላቸው ወገኖች እናደርሳለን የሚለው የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ ከሀገር ውስጥ ሆነ ከውጭ ከትልልቅ ተቋማት ድጋፍ ለማግኘት አቅደናል፤ የእስካሁኑ ድጋፍ ግን በአባላት መዋጮ ላይ ብቻ የተመሠረተ ነው›› በማለት ስለድርጅቱ የገንዘብ ምንጭ እና የርዳታ አሰባሰብና አቅርቦት ያብራራል፡፡ ‹‹ንፁህ ልብ›› የበጎ አድራጎት ድርጅት ላከናወናቸው የበጎ አድራጎት ተግባራት በየደረጃው ካሉ የመንግሥት ተቋማት የእውቅናና የምስጋና የምስክር ወረቀቶችን አግኝቷል፡፡

በ‹‹ንፁህ ልብ›› የበጎ አድራጎት ድርጅት ተግባራት ላይ ችግር እየፈጠሩ ያሉ በበጎ አድራጎት ሥራ ስም የማጭበርበር ተግባር የሚፈጽሙ አካላት ስለመኖራቸው አቶ ታምራት ይገልጻል። ‹‹የማኅበረሰቡ ግንዛቤ ትልቅ ችግር ሆኖብናል፡፡ ኅብረተሰቡ በበጎ አድራጎት ሥራ ስም በሚከናወኑ የማጭበርበር ተግባራት ተሰላችቷል፡፡ የሃሰተኞቹ አጭበርባሪነት እውነተኛ ዓላማ ይዘው ሃቀኛ የበጎ አድራጎት ተግባራትን ለማከናወን የሚንቀሳቀሱ ወጣቶች ላይ ጫና ይፈጥራል፡፡ ይህም ኅበረተሰቡ በበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ እምነት እንዲያጣና እና ቋሚ ድጋፍ አድራጊዎች እንዳይኖሩ እንቅፋት ይሆናል፡፡›› ነው ያለው፡፡ የበጎ አድራጎት ሥራዎቻችን የፋይናንስና ሌሎች ድጋፎችን የሚፈልጉ ናቸው፤ በበጎ አድራጎት ሥራ ስም በሚከናወኑ ማጭበርበሮች ምክንያት የሚፈጠሩ የታማኝነት ችግሮች እነዚህን ድጋፎች ለማግኘት መሰናክል እየሆኑብን ነው፤ አንዳንድ ሥራዎቻችንም እየተጓተቱብን ነው›› ይላል፡፡

ድርጅቱ በምዕራፍ አንድ መርሃ ግብሩ አገልግሎት ከሰጠባቸው አካባቢዎች በተጨማሪ ዘንድሮ በሌሎች አካባቢዎችም የመድረስ እቅድ አለው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የንጹህ ልብን የማገገሚያና የመኖሪያ ማዕከል በማቋቋም የጎዳና ተዳዳሪዎች፣ የአዕምሮ ህሙማን፣ ሴተኛ አዳሪዎችና አካል ጉዳተኞች ወደ ማዕከሉ እንዲገቡ፣ እንዲያገግሙና የሙያ ሥልጠናዎችን እንዲያገኙ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰም ይገኛል፡፡ በእስካሁኑ የድርጅቱ ጉዞ የመንግሥት ድጋፍ እንዳልተለያቸው በመጥቀስ፣ የድርጅቱ እቅዶች ስኬታማ እንዲሆኑ መንግሥት እገዛ እንደሚያደርግ ተስፋ እንዳላቸው አቶ ታምራት ይናገራል፡፡

 አንተነህ ቸሬ

አዲስ ዘመን መስከረም 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You