‹‹ኢትዮጵያውያን ቦክስ እንችላለን ግን ልምድ ያንሰናል››ቦክሰኛ ፍቅረማርያም ያደሳ ዓለማየሁ ግዛው

በሴኔጋል ዳካር በተካሄደው የአፍሪካ ዞን የኦሊምፒክ ቦክስ ስፖርት ማጣሪያ ውድድር በ57 ኪሎ ግራም የተፋለመው ረዳት ሳጅን ፍቅረማርያም ያደሳ ሁለተኛ በመሆን የብር ሜዳለያ ማጥለቁ ይታወሳል። ውድድሩን በአስደናቂ ብቃት ያጠናቀቀው የቡጢ ተፋላሚ ይህን ውጤት ያስመዘገበው በብዙ ችግሮች ውስጥ አልፎ ነው። ያምሆኖ ፍቅረማርያም በማጣሪያው አራት ተፋላሚዎችን ያሸነፈበት መንገድ አድናቆት ያተረፈለት ሲሆን ለበርካቶችም ተነሳሽነትን የፈጠረ ነው።

ፍቅረማርያም (ጊችሮ ነብሮ) ወደ ቦክሱ ስፖርት እንዲገባ መነሻ የሆነው ተወልዶ ባደገበት አካባቢ ሀገርን መወከል የቻሉ ስመ ጥር ቦክሰኞች በመውጣታቸው ነው። ይህም ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ ትልቅ ሚና እንዳበረከተለት ይናገራል። የአዲስ አበባ ፖሊስ ስፖርት ክለብ ቦክሰኛው በሴኔጋሉ የማጣሪያ ውድድር የገጠማቸው ተፋላሚዎች በልምድ ደረጃ ሁሉም ከኢትዮጵያውያን ቦክሰኞች የላቁ መሆናቸውን ያብራራል። ኢትዮጵያውያን ቦክሰኞች ደግሞ በሀገር ውስጥ ከሚያደርጉት ውድድር ባለፈ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ተሳትፎ ስለሌላቸው የፕሮፌሽናል ልምድ ይጎላቸዋል ይላል ፍቅረማርያም።

ፍቅረማርያምን ጨምሮ በሴኔጋሉ ማጣሪያ የተሳተፈው የኢትዮጵያ ቦክስ ቡድን በበርካታ ችግሮች አልፎ እዚህ ደረጃ መድረሱንም የ57 ኪሎ ግራም ተፋላሚው ይጠቅሳል። እንደ ቡድን ለኦሊምፒክ ማጣሪያ የሚመጥን ዝግጅት ተደርጓል ለማለት ቢያዳግትም ተወዳዳሪዎቹ ቦክሰኞች ተስፋ ሰንቀው በስኬት ታሪካቸውን የመለወጥ ውጥን ይዘው ወደ ውድድር ይገባሉ። በዚህም አዲስ ታሪክ መጻፍ የሚችሉ ብዙዎች እንደሚኖሩ ፍቅረማርያም እምነት አለው።

ውጤት ለማስመዝገብ ቀደም ብሎ በሞሮኮና ሴኔጋል ያደረጋቸው ውድድሮች ጥሩ ልምድ እንደሆኑት ያስታወሰው የሦስት ጊዜ የኢትዮጵያ ቻምፒዮኑ ፍቅረማርያም፣ እሱ በተካፈለበት ኪሎ ግራም በቻምፒዮናው 29 ቦክሰኞች የተፋለሙ ሲሆን፤ እጅግ ጠንካራ የሆነ ፉክክር የተስተናገደበትና ወርቅ አስመዝግቦ የኦሊምፒክ ተሳታፊ ለመሆን እጅግ ፈታኝ እንደነበረ ያስታውሳል። ከተደረገው ዝግጅት በተጨማሪም በውድድሩ እጅግ ፈተኝ ሁኔታዎች መኖራቸውም ለዚህ ምክንያት እንደነበር ይናገራል።

ከጉዞ ጋር በተያያዘ የቀኑ በትክክል አለመታወቁ የቦክስ ቡድኑ ዝግጅቱ ላይ ትኩረት እንደይደረግ ተጽዕኖ ፈጥሮ ነበር። ፍቅረማርያም የነበረውን ሁኔታ ሲያስታውስም ‹‹ለነበሩት ውጣ ውረዶች ኢትዮጵያዊነቴ ጠቅሞኛል፣ ጨከን እንድልም አድርጎኛል›› ይላል። በአጠቃላይ አስቸጋሪና ፈታኝ የሚባሉ ደረጃዎችን በማለፍ የብር ሜዳሊያውን እንዳስመዘገበም ያስረዳል።

በአራቱ ዙሮች ተጋጣሚዎቹን በዝረራ፣ በነጥብና በዳኛ ውሳኔ መርታት የቻለው ፍቅረማርያም፣ የቦክስ ችሎታ ቢኖረውም በልምድ ግን ተጋጣሚዎቹ እንደሚልቁ መታዘቡንም ይናገራል። ‹‹የቦክስ ስፖርት ድብድብ አይደለም፣ ጨዋታው ማሰብን የሚጠይቅ የጭንቅላት ጨዋታ ነው›› የሚለው ፍቅረማርያም፣ ምንም እንኳን ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ ቢችልም በተጋጣሚዎቹና በእሱ መካከል ያለው የልምድ ልዩነት እጅግ ሰፊ መሆኑን እንደተረዳ ይናገራል።

የአራቱን ዙር ውድድሮቹ በፍጹም የበላይነት በማጠናቀቅ በፍጻሜው በሶስት ዙሮች ፍልሚያ በናይጄርያዊው ቦክሰኛ ጆሽዋ ኦላሞ 3-2 በሆነ ጠባብ ውጤት ተሸንፎ ከኦሊምፒክ ተሳትፎ የቀረበትን ሁኔታ ሲያስታውስም ‹‹ኢትዮጵያ ለመጨረሻ ጊዜ በቦክስ ስፖርት ለኦሊምፒክ ተሳትፎ ከበቃች ረጅም ጊዜ በመቆጠሩ እንዲሁም እኔም ሀገርም ተሳትፎውን ስለምንፈልገው ትልቅ ጭንቀት ውስጥ ነበርን›› ብሏል።

እንደ ፍቅረማርያም ገለፃ፣ አፍሪካ ውስጥ ያለው የተሳትፎ እድል ማነሱ በራሱ ጉዳት አለው። በዚህም ከፍተኛ የሆነ ችሎታና ልምድ ካላቸው ስፖርተኞች ጋር ወርቅ ለማምጣት መፋለሙ አስቸጋሪ ሁኔታን ፈጥሮበታል። ተጋጣሚው ጆሽዋ በፕሮፌሽናል ደረጃ የሚጫወት ተወዳዳሪ ነው። እጅግ ጠንካራ፣ ብዙ ዙሮችን መጫወት የሚችልና ጥቂት ሽንፈቶችን ብቻ ያስተናገደም ተፎካካሪ ነው። ፍቅረማርያም ይህን ተጋጣሚ ለማሸነፍ ብዙ ሙከራዎችን በማድረግ በማድረግ ቢታገልም ተጋጣሚው ስህተት የማይሰራና ፍጹም በመሆኑ ሊሸነፍ እንደቻለ ያስረዳል።

ከውድድሩ ብዙ ልምድ በማግኘቱ ቀጣይ ለሚጠብቁት ውድድሮች ብቁ በመሆን እነሱን ማሳካት እንደሚፈልግና ጠንክሮ እንደሚሰራም ገልጿል። በመሆኑም የመጣው ውጤት የቦክስ አፍቃሪውንና ታዳጊዎችን የሚያነሳሳ በመሆኑ በውጪ ውድድሮች ልምድ ቢቀስም ኦሊምፒክን ለመሳተፍ መንገዱን እንደሚያቀለው ጠቅሷል። ብዙ ችሎታ ያለውና ብዙ የቦክስ አፍቃሪ በመኖሩ በቀጣይ ልምዶችን አዳብሮ ከዚህ በኋላ ያሉትን የኦሊምፒክ ማጣሪያዎች ማለፍ እንደሚቻልም ተናግሯል።

አሁን ያለበት ቦታ ላይ መቆም እንደማይፈልግና በኦሊምፒክ መሳተፍ ትልቅ ህልሙ እንደሆነ የሚናገረው ፍቅረማርያም፣ ለዚህም ስፖርቱ እንዲያድግ ክለቦች ቢበራከቱ፣ በባለሀብቶች ቢደግፉ እና ውድድሮች በስፋት ቢደረጉ ትልቅ ሚናን እንደሚያበረክቱ አስረድቷል። ተገቢው ሥራ የሚሠራ ከሆነ ብዙ ትላልቅ ቦክሰኞችን ማፍራት ይቻላል ብሎም ያምናል።

ፍቅረማርያም የመጀመሪያውና የልጅነት ክለቡ የኒያላ ቦክስ ክለብ ሲሆን ለቦክስ እድገቱ ትልቅ አስተዋጽኦ ሊያበረክትለት ችሏል። በኒያላ እራሱን ካጎለበተና ጥሩ እንቅስቃሴ ካደረገ በኋላ የአሁን ክለቡን አዲስ አበባ ፖሊስን ተቀላቅሏል። ክለቡ ድጋፎችን እንደሚያደርግለት አሁን ለደረሰበት ደረጃ ሚና እንዳለውም ያስረዳል። በዚህም በአህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ውድድሮች እንዲሳተፍና ልምድ እንዲያካብት የክለቡ ድርሻ ትልቅ እንደሆነም ተናግሯል።

አዲስ ዘመን  መስከረም 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You