የተስፋ ተቃርኖ

የጠቆረው ሰማይ የተድቦለቦለ የውሃ እንክብል ወደ ምድር እየወረወረ አዲስ አበባን እያጠባት ነው። የዝናቡን ውሃ የጠገበው መንገድም በንፋስ ሃይል ታጥቦ እንደተሰጣ ልብስ ጠፈፍ ማለት ተስኖት በየቦታው ውሃ አቁሯል። ዘውዴ መታፈሪያ ወደ ማምሻ ግሮሰሪ ሲያቀና፤ እግሩ መርገጫ አጥቶ አንዳንዴ እየዘለለ፤ ምቹ መንገድ ሲያገኝ ደግሞ እየተራመደ ነበር።

ገብረየስ ገብረማርያምም በሌላ አቅጣጫ እንዳይወድቅ እና በየመንገዱ የተጠራቀመውን ውሃ የጠገበ አሽከርካሪ በጎማው ረጭቶ እንዳያበሰብሰው በመስጋት ተጠንቅቆ እየተራመደ ማምሻ ግሮሰሪ ደረሰ። ተሰማ መንግሥቴ ግን ለጊዜው ዕድል ከእርሱ ጋር በመሆኗ፤ ዝናብ አልነካውም። በመንግሥት መኪና ተንጠላጥሎ እና ከጭቃው ተከልሎ፤ የመንገዱ መጨቅየት ሳያንገላታው፣ ሳይጎረብጠው እና ሳያሳስበው ማምሻ ግሮሰሪ ደረሰ። ሶስቱም እንደለመዱት በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ሰፍረው የሚጠጡትን አዘው ጨዋታ ጀመሩ።

ገብረየስ፤ ‹‹ሁልጊዜም አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር ተስፋ ይታየኛል፤ በተስፋ 50 ዓመታቶች አለፉ፤ እየመሸብኝ ቢሆንም ዛሬም እንደሕፃን መስከረም ሲመጣ በብዙ ነገር ላይ ተስፋ አደርጋለሁ። አብዝቼ እደሰታለሁ። በተለይ ስለሀገር እያሰብኩ የሚመጣውን ብሩህ ጊዜ ለማየት እመኛለሁ።›› አለ።

ዘውዴ ደግሞ በተቃራኒው፤ ‹‹አንተ ዕድለኛ ነህ። እኔ ግን አዲስ ዓመት ሲመጣ የተደሰትኩት በልጅነቴ ነው። ነፍስ አውቄ ከብት ማገድ ካቆምኩ በኋላ ደስታ ርቆኛል። ቢነጋም ቢመሽም፤ ወርም ሆነ ዓመት ቢቀየር ተስፋ የማደርግበት አጋጣሚ የለም። ሁልጊዜ የሚታየኝ ጨለማ ነው።›› ሲል፤ ገብረየስ ብቻ ሳይሆን ተሰማም በዘውዴ ንግግር በመገረም ግንባራቸውን ቋጠሩ።

ተሰማ፤ ‹‹እንዴት ለዘመናት ተስፋ ታጣለህ? ሰው ደግሞ ምንጊዜም ቢሆን የሚያገኘውም ሆነ የሚኖረው ባሰበው፣ በተመኘው እና በሠራው ልክ ነው። ባታገኝ እንኳ ተመኝተህ በተስፋ እንደመደሰት እንዴት በጨለማ ሕይወትህን ትገፋለህ?›› ሲል ጥያቄ አቀረበ።

ዘውዴ፤ ‹‹ምን ላድርግ የማየው ሰዎች ሲንገላቱ እና አንዳንዴም ሲታመሙ፤ መዳን እየቻሉ ሲሞቱ። አንዳንዶች ደግሞ እንደውም ሳይታመሙ በሰዎች ጥፋት ሕይወታቸው ሲያልፍ፤ አንዱ በሌላው ላይ የጭካኔ አሰቃቂ ተግባርን ሲፈፅም ብቻ ነው። ተስፋ ማድረግ ቀርቶ፤ ለፈጣሪዬ የምፀልየው አደራ ባልተገባ መልኩ በሰው እጅ ላይ ጥለህ እንዳታሰቃየኝ እያልኩ ነው።›› በማለት ምላሽ ሰጠ።

ገብረየስ በበኩሉ ዘውዴን እየተመለከተ፤ ‹‹ዋነኛው ችግርህ ይሔ ነው። ሁልጊዜም ማማረር ይቀናሃል። ታክሞ ከዳነው ይልቅ፤ የሚታይህ ታሞ የሞተው ብቻ ነው። ከተሠራው በጎ ነገር ይልቅ የጠፋውን ነገር ማየት ትወዳለህ። ነገር ግን በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ እያማረሩ በሩቅ አይቶ ከማለፍ ይልቅ ገብቶ ችግር ለማቃለል መሞከር ይሻላል።

አንዳንዱ ሁሉንም ነገር በቸልተኝነት እያየ በራሱ ጉዳይ ላይ ሳይቀር ታዛቢ ለመሆን እየሞከረ፤ ለቤተሰቡ፣ ለዘመዶቹ እና ለሀገሩ ባይተዋር እየሆነ እንደውጪ ሰው አስተያየት ይሰጣል። አስተያየቱ ደግሞ ምሬት አዘል ነው። በዚህም የራሱን ብቻ ሳይሆን የብዙዎችም ተስፋ ያጨልማል።›› አለ።

ዘውዴ ቀዝቀዝ ብሎ ተስፋ በቆረጠ ድምፅ፤ ‹‹ሰው ላይ መፍረድ ቀላል ነው። እኔ በሕፃንነቴ ያየሁት አንዱ የሌላውን ደም እበቀላለሁ ብሎ ሲገድል፤ መገዳደል ጀግንነት ሆኖ ሲነገር ነው። አጎቶቼ ያለ በቂ ምክንያት ሰውን ገድለው ልጆቻቸውን ሜዳ ላይ በትነው በረሃ ሲገቡ ጀግና ተብለዋል። ይህንን እያየሁ አድጌ ምን ተስፋ ላድርግ?›› ሲል የእርሱ በሁሉም ነገር ላይ ተስፋ መቁረጥ ትክክል መሆኑን ለማስረዳት ሞከረ።

ተሰማም ለዘውዴ ‹‹ችግሩ በአስተዳደግህ የመጣብህን ተፅዕኖ ተቋቁመህ ራስህን ለመቀየር አለመሞከርህ ነው። ይህን ተከትሎ ተጨባጭነት የሌለው ስጋት ውስጥ ገብተህ ዘመንህን እያሳለፍክ ነው። ቀድሞም ቢሆን ጥላህንም አታምነውም፤ መጠራጠር መለያህ ነው። ማጥላላትን የምታየው እንደትልቅነት ነው። ይሔ በአንተ ላይ በቅርብ በግልፅ ስላየን ስለአንተ ገለፅን እንጂ፤ ይሔ ችግር በሀገር ደረጃ በብዙ ሰዎች ላይ የሚታይ እና ሀገር ላይም ከባድ ቀውስ እያስከተለ ያለ ጉዳይ ነው። እዚህ ላይ መሠረታዊ ለውጥ ያስፈልገናል።›› አለ።

ገብረየስም፤ ‹‹እኔም እንደማምነው ሰበብ እየፈለጉ ማጥላላት፤ በሌላ በኩል ሰበብ እየፈለጉ የራስ ወገን እንደተጠቃ እየጠቀሱ ማስተጋባት አያዋጣም። እያዳሉ መጥቀምም ሆነ መጉዳት ትርፍ የለውም። እኛ በዓለም ደረጃ መገለጫችን ኢትዮጵያዊነታችን ነው። ስለምን በሀገር ውስጥ በመንደር ደረጃ ስላለው መገለጫችን በመጨነቅ ጊዜያችን ባልተገባ መልኩ እንደምናሳልፈው ግልጽ አይደለም። የሚያዋጣው ከመማረር ይልቅ ተቀላቅሎ መስራት ነው። የሰው ሞት ወይም የሰዎች እኩል ያለመታየት ጉዳይ የሚያበሳጨን ከሆነ፤ ጥረት አድርገን ችግሩን መፍታት እንጂ ተነጥሎ ጨለማ ውስጥ መንከባለል ትርፍ የለውም።›› አለ።

ዘውዴ ‹‹እኔ ሰው ሰው በመሆኑ ብቻ ክብሩ እና ነፃነቱ ሊከበርለት ይገባል የሚል እምነት አለኝ። ይህንን ማለት ደግሞ ወንጀል አይደለም። አንድ ሰው መብቱ ይከበርለት ሲል ከጎሳ ወይም ከብሄር ጋር መወሰድ የለበትም። ስለአንድነት በማሰብ አንድ እንሁን ማለቱን ተከትሎ ጎራ እየለዩ መዋቀስም አይገባም። እያንዳንዱን ሃሳብ ለመግለፅ ሲሞከር እንኳ በራሳቸው ውስጥ ጎጠኝነት አብቦ ቤቱን የሠራባቸው ሰዎች፤ ሁሉንም ሰው እና ሁሉንም ሃሳብ ከጎጥ አንፃር ያቀርቡታል። በእርግጥ ይህንን አስተውዬ በጣም ተከፍቻለሁ። ተስፋ እስከማጣት ደርሻለሁ። በዚህ ምክንያት ምንም ላለመናገር አፌን ዘግቻለሁ።›› አለ።

ገብረየስ ቀበል አድርጎ፤ ‹‹አንተ ብቻ አይደለህም፤ ከአንተ ጋር በተመሳሳይ መልኩ ብዙ ተስፋ የቆረጡ ይኖራሉ። ነገር ግን ችግሩም እኛ እንደምንገልፀው ይህ ብቻ አይደለም። አንዱ ጥግ ይዞ ተጠቅቻለሁ ሲል፤ ሌላኛው ሌላኛውን ጥግ ይዞ እርሱም ተጠቅቻለሁ ይላል። ማን እንዳጠቃ አይታወቅም። አንዱ ጥግ ይዞ የእኔ ሃሳብ ብቻ ይሰማ፤ እኔ ብቻ ትክክል ነኝ ሲል፤ በሌላ ጫፍ ያለውም በተመሳሳይ መልኩ እኔ ብቻ ልሰማ ይላል።

ጎራ ፈጥሮ በቡድን መደበላለቅ ለማንም አይጠቅምም። ጎሳ ውስጥ ከመነከር ወጥቶ እና ልዩነትን እያጠበቡ አንድነትን እያጎሉ በጋራ ለማደግ ማሰብ ይበጃል። እዚህ ላይ መሠራት እንዳለበት አይካድም። ይህ እንዲሆን ደግሞ እኔ እና አንተን ጨምሮ እያንዳንዱ ግለሰብ ከራሱ መነሳት አለበት።›› ሲል ሃሳቡን ገለፀ።

ተሰማም የእነርሱን ሃሳብ የሚያጠናክር በሚመስል መልኩ፤ ‹‹ትክክል ናችሁ። ብዙዎች ውስጣቸው ከእናንተ ሃሳብ ጋር የተስማማ ነው። ነገር ግን ሁሉም በልክ መሆን አለበት። እንደዘውዴ ለዘመናት ተስፋ መቁረጥ አይገባም። ሰዎች ሃሳባቸውን ሲያቀርቡም ሆነ እምነታቸውን ሲያራምዱ ተቀባይነት ሊኖርም ላይኖርም ይችላል። ተቀባይነቱን ለማግኘት ተጨባጭ ማስረጃን ይዞ መቅረብ እና አቀራረቡን የተሻለ ማድረግ ይገባል። ጊዜ እየመረጡ በጊዜ ላይ መሸጎጥ እና ሃሳብን ጊዜ እየመረጡ በማቅረብ ያልተገባ ትርፍ መሰብሰብ ብዙ ርቀት አያስጉዝም።›› አለ።

የገብረየስ ሃሳብ ግን ‹‹በዋናነት በኢትዮጵያ ለዘመናት እየታየ ያለው እና የብዙዎችን ተስፋ ያጨለመው በተናጥል ሽኩቻ ውስጥ ተወትፈው የሚሽከረከሩ በመብዛታቸው ነው። የጋራ ግብ በማስቀመጥ በጋራ ከማደግ ይልቅ፤ አንዱ ሌላውን እየጎተተ ሲቀብር ዘመናቶች ተቆጥረዋል። ይህችን ሀገር የመሩ እና በዚህች ምድር ላይ የኖሩ ሰዎች ቢሰሩም ከሰሩት ይልቅ ያልሰሩትን በማውራት ብዙ ጊዜያቶች አልፈዋል።

የትናንቱን ብቻ እያውጠነጠኑ ማዳመጥ ዛሬን እንደሚያስረሳ ያልተገነዘቡ ሰዎች ተስፋ ማድረግ ተስኗቸዋል። በእርግጥ የትናንቱ መረሳት ባይኖርበትም በልኩ መነሳት አለበት። መቀየር በማይችላው ትናንት ላይ ተጣብቆ ከልክ በላይ ማላዘን ሁሉንም ያከስራል። የዛሬን እየሠሩ ለነገ ተስፋ ማድረግ ጤነኝነትን ያመለክታል። እንደኔ እምነት ፍፁም ተስፋ ማጣት ግን እጅግ ከባድ ነገር ነው›› አለ።

ዘውዴ በበኩሉ፤ ‹‹አዳማጭ መሆን እንችላለን ብላችሁ ካመናችሁ እና እኔን ለማዳመጥ ከፈለጋችሁ በደንብ ብታዳምጡኝ ይሻላል። ሰው ወደደም ጠላ የሆነ ሰው ቤተሰብ ነው። ምርጫ የለውም፤ ያ ቤተሰብ ድሃም ሆነ ሀብታም፤ ባለጌም ሆነ ጨዋ፤ የተዋረደም ሆነ የተከበረ ብቻ ለግለሰቡ ቤተሰቡ የጋራ መገለጫው ነው። በዚህ መገለጫው ላይ አያገባኝም ማለት የራስን ክብር መጠበቅ አለመቻል ነው። ለራስ ክብር ማጣት ደግሞ የህልውና ጉዳይ ነው። ክብር ማጣት ህልውናን ከማጣት ተለይቶ አይታይም። ቢያንስ ሰው ተቀናጥቶ ደስታ ውስጥ መዋኘት ቢያቅተውም ተከብሮ ፤በልቶ ፤ጠጥቶ እና ለብሶ መኖር የሚችልበት ሁኔታ ሊፈጠር ባይችል እንኳ ስለደህንነቱ ማሰብ፣ መጨነቅ እና መጠየቅ ይጠበቅበታል። በዚህ በኩል ማሰብህ፣ መጨነቅህ እና መጠየቅህ ትክክል አይደለም ካላችሁ ለእኔ እናንተ ትክክል አይደላችሁም።›› ሲል አቋሙን ገለፀ።

ገብረየስ በበኩሉ፤ ‹‹በእርግጥ አንተ እንደጠቀስከው ምንም ጥያቄ አታንሳ አላልንም። መጠየቅ ትክክል ነው። ነገር ግን በዚህ ደረጃ ተስፋ መቁረጥ አይገባም። የራስን ክፍተትም በባህል እና በመንግሥት ላይ እያላከኩ መሸፋፈን ጠብ የሚያደርገው ነገር የለም። ምክንያቱም ዓለም የምትሰጠን በሠራነው፤ በለፋነው፤ በከፋነው እና ደግ በሆነው ልክ ነው ይባላል። አውሮፓ እንደምን ሰለጠነች ከተባለ መነሻቸው እና መድረሻቸው ሥራ በመሆኑ ነው። ስለሠሩ ለእነርሱ ዓለም ከፍላቸዋለች፤ በተቃራኒው እኛ ደግሞ በእነርሱ መጠን ስላልሠራን ወይም ዛሬ ላይ ከመሥራት ይልቅ በማይሆን መንገድ ተጉዘን ባለፈው ታሪክ ላይ ቆመን ስለቀረን ወይም ቆመን ባንቀርም ጉዟችን እጅግ አዝጋሚ በመሆኑ ወደ ኋላ ቀርተናል። ስለዚህ አሁን መፍትሔው ላይ በደንብ መሥራት ነው።›› አለ።

ተሰማ በበኩሉ መፍትሔ የሚለውን ሰነዘረ። ‹‹በተቻለ አቅም ለመሥራት፤ ሥራ ሲበላሽም ለመወያየት እና ለመከራከር መሞከር ይሻላል። መመካከር እና መወያየት ክፋት የለውም። በውይይት ብዙ ጥሩ አዳዲስ ሃሳቦች ይገኛሉ። ነገር ግን መከራከርም ሆነ መወያየት ሚዛናቸውን ጠብቀው መከወን አለባቸው። ዋነኛው ጉዳይ በመመካከር በጋራ ዓላማ ፤ ለጋራ ሀገራችን መሥራት ነው። መንግሥትንም ሆነ ማንንም ከማማረር በፊት ሌላውን ለመረዳት እና እዛ ጫማ ውስጥ ሆኖ ለማሰብ መሞከር ያስፈልጋል።

ሃላፊነትን የማይወስዱ የቤተሰባቸው ጉዳይ ላይ ሳይቀር አያገባኝም የሚሉ ዳተኞች በበዙበት ሀገር ውስጥ፤ ሕዝብ ማስተዳደር እና መምራት ከባድ ነው። ብዙዎች ለሙያቸው ተገዢ ሳይሆኑ፤ በተጣለባቸው ሃላፊነት ሕዝብን ማገልገል ሲገባቸው ባልተገባ ቦታ ላይ ተገኝተው ጊዜያቸውን እና ገንዘባቸውን በማማረር ላይ ካሳለፉ ጥፋቱ የማን ነው? ብሎ ሁሉም ራሱን መጠየቅ አለበት። ተስፋ ቆርጦ አሰልቺ ሕይወትን ከመግፋት ይልቅ፤ ሁሉም በየደረጃው ሃላፊነቱን ቢወጣ ብዙ የሚያማርር አይኖርም ነበር።

የመሥሪያ ዕድሉን አግኝተው የሚጠበቅባቸውን ከመሥራት ይልቅ ታዛቢ ሆነው የገዛ ሥራቸውን የሚያጥላሉ ሰዎች ስለመኖራቸው አይካድም። ከሁሉም ነገር ቀድሞ ደህንነት ሊሰማን ይገባል። ማህበራዊ ደህንነት ያስፈልጋል፤ ደህንነት ሳይኖር ስለምግብ፣ ስለትምህርት፣ ስለጤና እና ስለንፁህ መጠጥ ውሃ መናገር ቅንጦት ነው የሚሉ አሉ። በእርግጥ ደህንነት ሳይኖር ስለሙያ ተገዢነት መስበክ የዋህነት ነው የሚሉም አይጠፉም። ነገር ግን በምንም መልኩ ከስጋት ተስፋ ይሻላል፤ እጅግ የተወሳሰበ ችግር መኖሩን በማሰብ አንዱ የሌላውን ሥራ መደገፍ ይኖርበታል።

ሀገር የምታድገው በምሬት እና ተስፋ ቆርጦ በመሸሽ፤ ሃላፊነትን ባለመውሰድ ሳይሆን በሥራ እና በትጋት ነው። የተሠራው ሥራ ትልቅ ውጤት ያስገኛል ብሎ ተስፋ በማድረግ ነው። ሁሉም ከሥራ ይልቅ ወደ ምሬት ራሱን ከመራ ጉዞ ወደ ፊት ሳይሆን ወደ ኋላ ነው። በአዲስ ዓመት ተስፋ እናድርግ፤ እንስራ፤ ከዛም ምናልባትም የአገሪቱ ችግር ከነሰንኮፉ ተነቅሎ ይወጣል።›› ሲል አዲስ ዓመት ተስፋ የሚደረግበት እና ትልቅ ውጤት የሚገኝበት እንጂ፤ ምሬት የሚሰማበት እና ተስፋ የሚቆረጥበት መሆን እንደሌለበት አመልክቶ ሃሳቡን ቋጨ።

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን  መስከረም 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You