መስከረም እና ኪነ ጥበብ

የመስከረም ወር ለየት ይላል። የሬዲዮና ቴሌቪዥን ማስታወቂያዎችን ልብ ብላችሁ ከሆነ የበዓል ይዘት የሚኖራቸው ለእንቁጣጣሽ ወይም መስቀል በዋዜማው ወይም በማግስቱ ብቻ አይደለም። መስከረም ወሩን ሙሉ ደማቅ ነው። የማስታወቂያዎችም ሆነ የፕሮግራሞች ማጀቢያዎች በመስከረም ወር ላይ የሚያተኩሩ የሕዝብ ወይም የታዋቂ ከያኒያን የጥበብ ሥራዎች ናቸው።

መስከረም የተፈጥሮ ጥበብ የሚታይበት ልዩ ወር ነው፤ ይህ የተፈጥሮ ጥበብ ደግሞ ሰዎችም እንዲጠበቡ አደረጋቸው። አዳዲስ ነገሮች የሚታዩበት ስለሆነ አዲስ ፈጠራ ለማሰብ ከያኒያንን ሳያነሳሳ አይቀርም። በተፈጥሮ የክረምት ወራት አልቆ ፀሐይ የሚወጣበት፣ አበቦች በየመስኩ የሚፈኩበት ነው። መስከረም ከክረምቱም ከበጋውም ወቅት የተለየ ነው። በክረምት ‹‹እኝኝኝ…›› ያለ ዝናብ እና ብርድ ነው። መሬቱም ጭቃ ነው። በበጋ ወቅት ደግሞ የነደደ ፀሐይና ሙቀት ነው። መሬቱም አቧራ ነው። መስከረም ግን ከሁለቱም ነፃ የሆነ ነው። የከፋ ጭቃ የለም፤ የከፋ አቧራ የለም። የከፋ ብርድ የለም፤ የከፋ ሙቀት የለም። በእነዚህ ባህሪያቱ ነው የተፈጥሮ ውበት የሆነው። ከወራት ሁሉ ተለይቶ ለሰው ስም እንኳን ይውላል።

የመስከረም ወርን በዚህ ልክ እንዲደጋገም እና እንዲህ ስመ ጥር ያደረገው ተፈጥሯዊ ባህሪውን ምክንያት በማድረግ የኪነ ጥበብ ሥራዎች ናቸው። መስከረም በራሱ ጥበብ የሆነ ወር ነው። ለዚህም ነው በኪነ ጥበብ ሥራዎች ውስጥ ስሙ ተደጋግሞ የሚጠቀሰው። ምንም እንኳን ዘፋኞች ውስጥ ቢበዛም፣ በገጣሚዎች፣ በተዋናዮች፣ በደራሲዎች… ከወራት ሁሉ በበለጠ የተጠቀሰ ነው። የጥበብ ሰዎች አበባ ሲያዩ ሀሳብ ይመጣላቸዋል ማለት ነው። ወደ ግጥሞችና ዘፈኖች ከመሄዳችን በፊት ግን መስከረምን መቼት ያደረጉ የኪነ ጥበብ መጀመሪያ የሆኑትን የስነ ቃል ውጤቶችን እንመልከት።

በምሳሌያዊ ንግግሮች ውስጥ መስከረም ተደጋግሞ ይጠራል። የወሩን ተፈጥሯዊ ባህሪ ከሚገልጸው ምሳሌያዊ ንግግር እንጀምር። ‹‹የመስከረም ዝናብ ከላም ቀንድ ይለያል›› ይባላል። የምሳሌያዊ ንግግሩ ትርጉም የመስከረም ዝናብ ሁሉንም ያማከለ አይደለም ለማለት ነው። የላም ቀንድ በጣም የተጠጋጋ ነው። አንዱ ጋ ዝናብ ዘንቦ አንዱ ጋ ላይዘንብ ይችላል ማለት ነው። ምሳሌያዊ ንግግሩ በጣም የተጋነነ ቢሆንም የመስከረም ዝናብ ግን እንዲህ ነው። በጣም የተቀራረቡ ቦታዎች ላይ (ለምሳሌ አራት ኪሎ ዘንቦ ፒያሳ) ላይዘንብ ይችላል። ይህ አባባል ጥቅል ሁኔታውን ለመግለጽ እንጂ ሁሌም እንዲህ ይሆናል ማለት ግን ላይሆን ይችላል፤ ለምሳሌ ሰሞኑን እንደገና ክረምት መስሏል።

‹‹መስከረም በአበባው ሰርግ በጭብጨባው›› የሚባል ምሳሌያዊ ንግግርም አለ። ጭብጨባ የሰርግ መለያ እንደሆነ ሁሉ የመስከረም መለያውም አበባ ነው። አንድ መንገደኛ እየሄደ የሆነ መንደር ውስጥ ጭብጨባ ከሰማ ‹‹እዚህ ግቢ ሰርግ አለ ማለት ነው›› ብሎ ይገምታል። እርግጥ ነው ነገሩ ሰርግ ብቻም ላይሆን ይችላል፤ በሌላ የድግስ ፕሮግራምም ይጨፈራል። ዋናው ግን ለሰርግ ነው። የመስከረም ወርም እንደዚሁ ነው። ስለመስከረም በተለያየ መረጃ የሚያውቅ አንድ የውጭ አገር ሰው ኢትዮጵያ መጣ እንበል። ኢትዮጵያ ሲገባ ጋራ ሸንተረሩ በአበባ ተንቆጥቁጦ ካየ ‹‹የመስከረም ወር ነው ማለት ነው›› ይላል።

ሌላው ገናና ምሳሌያዊ አነጋገር ደግሞ ‹‹ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም›› የሚባለው ነው። መስከረም አዲስ ዓመት ስለሆነ ባለፈው የተከናወኑ አስገራሚ ነገሮች ይታወሳሉ። የዓመቱ የመጨረሻ ወር ላይ ያሉት የመጨረሻ ሳምንታት የመገናኛ ብዙኃን ሽፋን የሚሰናበተውን ዓመት አስገራሚ ክስተቶችን ይዘግባሉ። ‹‹ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም›› የሚባለው ለዚህ ነው። በዓመቱ ውስጥ የሆነ አስገራሚ ነገር ስለማይጠፋ ማለት ነው። ይህ በውጭው ዓለምም የተለመደ ነው። ‹‹ጉድ ሳይሰማ ጥር አይገባም›› የሚል አባባል ይኑራቸው አይኑራቸው ባላውቅም በታህሳስ ወር መጨረሻ ላይ የተሰናባቹን ዓመት ክስተቶች ያስታውሳሉ።

የሕዝብ የስነ ቃል ጥበብ ከሆኑት ‹‹ለሞኝ ሰኔ በጋው መስከረም ክረምቱ›› የሚባል ምሳሌያዊ ንግግርም አንዱ ነው። በእንዲህ አይነት ጥበባዊ ለዛ መልዕክት ያስተላልፋሉ ማለት ነው። አሁንም ሰኔ እና መስከረምን ልናነፃፅር ነው። ‹‹ለሞኝ ሰኔ በጋው መስከረም ክረምቱ›› የተባለው የሰኔ ወር የክረምት መግቢያ ሲሆን መስከረም ደግሞ የክረምት መውጫ ነው። ሞኝ ወይም ሰነፍ የሆነ ሰው በሰኔ ገበሬው ሁሉ ሲሯሯጥ እሱ ዝም ይላል። መስከረም ላይ ተፍ ተፍ ቢል ከየት ይመጣል! ‹‹ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ›› እንደሚባለው ማለት ነው።

ሌሎች ምሳሌያዊ ንግግሮች ደግሞ በቃል ግጥም የሚባሉ ናቸው። የቃል ግጥም ሆነው እንደ ምሳሌያዊ አነጋገር የሚያገለግሉ አሉ። ያ ማለት ለዘፈንና እንጉርጉሮ ሳይሆን በጨዋታ (በወሬ) መካከል ሀሳቡን ለማዳበርና ግልጽ ለማድረግ ይጠቀሙታል ማለት ነው።

መስከረም ሲጠባ

አደይ ሲፈነዳ

እንኳን ሰው ዘመዱን

ይጠይቃል ባዳ

ይሄን የቃል ግጥም በብዙ የባህል እና የበዓል ዘፈኖች ውስጥ ስለምንሰማው የዘፈን ግጥም ይመስለን ይሆናል። ዳሩ ግን የንግግር ምሳሌያዊ አነጋገር ነው። በወግ መካከል የሚያወሩት ነው። ምናልባትም ዜማ ላይኖረውም ይችላል፤ መድረክ ላይ በሚነበብ ግጥም አይነት በወሬ መሃል ያስገቡታል። የመስከረምን ጸዳልነት ለመግለጽ ነው። በተለይም ገበሬዎች በክረምት ከፍተኛ የሥራ ውጥረት ውስጥ ስለሚሆኑ ዘመድ ከዘመድ እንኳን አይገናኙም። በሌላ በኩል ደግሞ አብዛኛው የገጠሪቱ የአገሪቱ ክፍል (በተለይም ቀደም ባሉት ዘመናት) ድልድይና የመኪና መንገድ ስለሌለ የሚገናኙት የወንዝ ውሃ ሲጎድል ነው። ወንዞች ከመስከረም በኋላ ስለሚጎድሉ ዘመድ ከዘመድ ይገናኛል። እንኳን ዘመድ ባዕዳም ይጠየቃል ያሉት ለዚህ ነው።

ያረሰማ ጎበዝ

እርፍ የነቀነቀ

ወፍጮው እያጓራ

መስከረም ዘለቀ

አዝማሪዎች በሰርግና በሌሎች ዝግጅቶች ላይ ገበሬውን ለማወደስ ይጠቀሙታል። ከአዝማሪዎች በፊት ግን የህዝብ ግጥም ነው። እንደማንኛውም ምሳሌያዊ ንግግር በወግ መካከል ይጠቀሙታል። በነገራችን ላይ ይሄ ምሳሌያዊ ንግግር (የቃል ግጥም ልንለውም እንችላለን) ከመስከረም ወር ይልቅ በሰኔና በሐምሌ ይደጋገማል። ምክንያቱም ሰነፍና ታታሪ ገበሬን ለማነጻጸር የሚያገለግል ነው። ሰነፍ ገበሬ በሰኔ እርሻ ላይ ተፍ ተፍ አይልም፤ ጎበዝ ገበሬ ደግሞ ተፍ ተፍ ይላል። ሰነፉ ገበሬ ጠንክሮ ባለመሥራቱ በሐምሌና ነሐሴ ይቸገራል (የሚበላው ያጣል)። ጎበዝ ገበሬ ግን በክረምት ጠንክሮ ያረሰው ዓመቱን ሙሉ ስለማያልቅ ከመስከረም መስከረም ወፍጮው እያጓራ ይዘልቃል ማለት ነው።

ከቃል ግጥሞችና ምሳሌያዊ ንግግሮች ስንወጣ ደግሞ ደራሲዎችን፣ ገጣሚዎችንና ዘፋኞችን እናገኛለን። ስለመስከረም ብዙ ተዘፍኗል። ምናልባት ግን በዘፈኖች ውስጥ የግጥሞች መደጋገም ይኖር ይሆናል፤ በብዙ የባህል ዘፈኖች ውስጥ የህዝብ ቃል ግጥም ስለሚበዛ መደጋገሙ ያጋጥማል። በሁሉም ውስጥ አበባ ይኖራል፣ ጋራ ሸንተረሩ በአደይ አበባ መድመቁ ይገለጻል።

ወደ ገጣሚዎች ስንሄድ በተደጋጋሚ የሚጠቀሰው እንግዲህ የመንግስቱ ለማ ነው። የመስከረም ወርን ባህሪ የሚገልጽ ነው።

የመስቀል ወፍና

የአደይ አበባ

ቀጠሮ እንዳላቸው

መስከረም ሲጠባ

ማን ያውቃል?

የመስቀል ወፍ እና የአደይ አበባ አንዳች አስማት ያላቸው ነው የሚመስለው። የሚታዩት በመስከረም ወር ብቻ ነው። የመስቀል ወፍ ላይ ግን አንድ ሳይንሳዊ መላ ምት አለ። ወፏ ከየትም የመጣች ወይም አዲስ የተፈጠረች ሳትሆን የነበረች ናት ይባላል። የክረምት ወር አልፎ መስከረም ሲጠባ በሚወጣው ፀሐይ ቀለሟ ይቀየራል የሚል መላ ምት ይጠቀሳል።

የአደይ አበባ ነገር ግን አሁንም ምሥጢሩ አልተገለጸም። መለኮታዊ ምሥጢር ያለው ይመስላል። ቃልኪዳኑን ጠብቆ መስከረም ላይ ነው የሚያብብ። ሌሎች የሳር እና የተክል አይነቶች ዝናብ ወይም የመስኖ ውሃ ካገኙ ይበቅላሉ። በበጋ ወቅት በመስኖ ዳርቻ ይታያሉ። አደይ አበባ ግን ዓመቱን ሙሉ ዝናብ ቢሆን በበጋ ወቅት አይበቅልም፤ በየትኛውም የመስኖ ዳርቻ አደይ አበባ አይታይም፤ ይህ ራሱ ተፈጥሯዊ ጥበብ ነው።

በመስከረም ላይ የተሰሩ በርካታ የኪነ ጥበብ ሥራዎች ናቸው ያሉት። ዘፈኖችንም ግጥሞችንም እንዘርዝር ቢባል ሙሉ ጋዜጣው አይበቃም። ‹‹ደስ ይላል መስከረም›› በሚለው ደስ የሚል የባለቅኔ ሙሉጌታ ተስፋዬ ግጥም እንሰነባበት። ደስ የሚል መስከረም ይሁንላችሁ!

ደስ ይላል መስከረም

በግርሻ ጣይ ሰርዶ ነቅሎ በሚያዚያ ንሽ ተርበጥብጦ

በግንቦት ሐሩር ተቀቅሎ በፀሐይ አብስሎ በዝናብ አብቅሎ

ከወዳጅ ከዘመድ ተቀላቅሎ

ባዝራን ከአህያ አዳቅሎ

በባለ በርሸት ሽልም በቅሎ

ተፈናጦ አብሮ ገስግሶ

ጅራፍ ግርፊያ ሆያ ሆዬ ቡሄ በሉ ተጫውቶ

ኪዳነ ምሕረትን አንግሶ ደግሞ በወሩ ለአስተሮዮው

ግሼን ማሪያም እማአርያም ደጀሰላም ደርሶ ለመሳለም

‹‹እዮሃ አበባዬ መስከረም ጠባዬ

ዐደይ ለምለም ለኔ እንዳንቺ የለም…››

እያሉ ንጥቂያ

ከጀንበር መፍለቂያ እሥከ ጀንበር መጥለቂያ

አለላ ነቅሎ ባሕር እንጉዳይ

ጀግና ሰው ገዳይ

አካል እንጉዳይ

እያሉ ሲያንጎራጉሩ!

ደስ ይላል መስከረም!

ቡቃያው ጣል ከንበል ሲስ

ሹሩባዋ ወርዶ እንዲያ ሲዘናፈል

ልቤ እንደበቆሎ ያድራል ሲ ፈ ለ ፈ ል

በቀጭን ተሰርታ ሥትል ዘንከት ዘንከት

ጃሎ ሲል ሊያነጋ አገር በመለከት

ለመስቀል ጠንስሶ በማድጋ ገንቦ ለእንግዳ ቀንሶ

በሞቴ አፈር ስሆን እያለ ሲያጋፍር

ጥርስ እንጎቻ አስፍቶ አሞጭ በመሰለው እርጎ ፍርፍር

እንኳን ሳቅ ጨዋታው ድብድቡ ልፊያው

ድገሙኝ ያሰኛል ሰፈፍ የለሽ ሞገድ መደዶ ዘር ዜማ ሲቆረቆር ክትፊያው

ደስ ይላል መስከረም!

የሽንብራ እሸት እየጠረጠሩ

የልጅነት ሚዜ ‹‹ኧረ አይዋ ክንዴ›› እያሉ እየጠሩ

አብሮ ወፍ ጥበቃ ማማ ላይ ተሰቅሎ

ካፊያውን በገሳ በአንድ ተጠልሎ

እሳት አቀጣጥሎ በቆሎ ጠባብሶ

አየሁ አላየሁም… ሰማሁ አልሰማሁም

በላልቶ አፍ አብሶ

ለስልሶ አስፈትሎ የእናት ኩታ ለብሶ

ላዋቂ ተልኮ ለልጅ ተጎናብሶ

ደስ ይላል መስከረም!

እንደቢራ ቢሮ አበባ ለአበባ ዐደይ እንቡር እንቡር

በፍቅር ለመክረም

ደስ ይላል መስከረም!

ወፉ ከነ ጎጆው እሥከ መናጆው

ንቡ ከነ ቀፎው መረባ ከነ እርፎው

በዐደይ ለምለም ክብር ለመስከረም ክብር

ቅዱስ! ቅዱስ! ቅዱስ!

የዓመት አሥራት ሊያፈስ

ሊያስገባለት ግብር

በዝማሬ ሲያብር

አንጀት ሲበረብር

ደስ ይላል መስከረም!

ተዋዶ ወዶ ተወሕዶ ያንጀት ተፈቃቅዶ

ባንድ አብሮ ለመክረም

ደስ ይላል መስከረም!

ለቅኔ ዘረፋው ጠፈፍ ሲል ፈፋው

የቆሎ ተማሪ ያ ተመራማሪ

የወላዲት አምላክ የድንግል አዝማሪ

ያ ደበሎ ለባሽ!

በእግዚትነ ማሪያም! እባካችሁ እባሽ እባካችሁ ቁራሽ

እ ያ ለ ሲለምን

ከጥንቅሹ ቅንጥሽ ማሩቴ ባይሰጠው

አይቀር መደንገጡ አራሽ አባ ወራሽ ማብላት ያሰለጠው

የማይለወጠው

በዐይኑ እየመዘነ በልቡ እማይመርጠው

ገሩ ባላገሩ

ያ ባለሞፈሩ ያ ባለዘገሩ

በሞቴ ነው ቋንቋው ስሞት ነው ነገሩ

ደስ ይላል መስከረም!

ወዶ ተወሕዶ ያንጀት ተፈቃቅዶ

አንድ ልብ አቅዶ

አንድ ላይ ለመክረም

ደስ ይላል መስከረም!

ጥቅምትና ኅዳር ቢያዋውል ምንጭ ዳር

ታኅሳስና ጥር ዐውድማ አስለቅልቆ ጥሪት እሚያስቋጥር

የካቲት መጋቢት መኸር አስከትቶ ቢያበስል እንደ ዐቃቢት

ሚያዚያና ግንቦቱ ተርቲበኛው ቀርቦ ወርዶ ረከቦቱ

የላም ልጅ በዋንጫ ቢቀርብ ሥልባቦቱ

ሰኔ ሐምሌ ነሐሴ እንደ ቄስ ምናሴ

እያረበረበ ደግሞ እየወረበ

ሰማይ በበረቀ ታርሶ ርሶ ሲስረቀረቅ

ከራሱ እስኪታረቅ

ሁሉም እንደ ግብሩ

ሁሉም እንደ ሙያው!

አሥራ ሁለቱም ወር

እዮሃ አበባዬ መስከረም ሲጠባ

ያኔ ነው ገቢያ

ያኔ ነው መታያው

ያኔ ነው ማባያው

ደስ ይላል መስከረም

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን  መስከረም 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You