‹‹በተያዘው ዓመት መንግስት በለቀቀልን በጀት ልክ የሚመደቡልንን ተማሪዎች እንደቀደመው ጊዜ ተቀብለን እናስተምራለን›› ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚደንት

 የዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ መሆን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በአጭር ጊዜ ውስጥ መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት እንደሚያስችል የትምህርት ሚኒስቴር በተደጋጋሚ ሲገልጽም ቆይቷል። የዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ መሆን መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣትና ከሚታወቀው በተሻለና በተለየ መልኩ በአጭር ጊዜ ውስጥ መዋቅራዊ ሽግግር እንዲመጣ ወሳኝነት እንዳለውም ይታሰባል።

በዚህም ትምህርት ሚኒስቴር በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ 10 የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ለማድረግ ትልቅ እቅድ ይዟል። በዚህ እቅድ ውስጥ ከተካተቱት መካከልም ፤ ባህርዳር፣ ጎንደር፣ ጅማ፣ ሀዋሳ፣ አርባ ምንጭ እና መቐለ ዩኒቨርስቲዎች ይገኙበታል። ከተቋቋመ ሰባ ሁለተኛ ዓመቱን የያዘው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፤ በተያዘው በጀት ዓመት የ“ራስ ገዝ” አስተዳደርን ተግባራዊ በማድረግ የመጀመሪያው ሆኗል ።

እኛም ይህንኑ በተመለከተ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ ጋር ቆይታን አድርገናል። መልካም ንባብ።

 አዲስ ዘመን – ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ መሆናቸው ያለውን ፋይዳ እንዴት ይገልጹታል?

ዶክተር ሳሙኤል፡- ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ መሆናቸው በርካታ ፋይዳዎች አሉት። ዩኒቨርሲቲዎች ተልዕኮአቸው ላይ ብቻ ትኩረት እንዲያደርጉ፣ ተወዳዳሪና ብቁ ችሎታ ያላቸው ምሩቃንን ለማፍራትና ጥራት ያለው የምርምር ውጤት እንዲሰሩ በማድረጉ በኩልም ራስ ገዝነታቸው ይጠቅማቸዋል ተብሏል።

ዩኒቨርሲቲዎች ችግር የሚያባብሱ ሳይሆን በሰላም መኖርን እና ዴሞክራሲን የሚሰብኩ ተቋማት እንዲሆኑ በተለይ ሀገር በቀል እውቀቶችን በምርምር ማወቅ፣ ለችግሮች የመፍትሄ ሀሳብ ማመንጨት፣ የዓለምንና የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ በመረዳት ቀጣይ አቅጣጫን ለማመላከትም ነጻነትና ራስ ገዝነት እንደሚያስፈልግ ታምኖበታል።

ይህንን ለማረጋገጥ በመንግሥት ቁርጠኝነት ዩኒቨርሲቲዎች ወደ ራስ ገዝነት እንዲሸጋገሩ በተወሰነው መሰረት የተለያዩ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸው ይታወቃል። በዚህም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዩኒቨርሲቲዎችን የራስ ገዝ የማድረግ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ እና አጽድቆ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም አስተላልፏል።

በመሆኑም ዩኒቨርሲቲዎች ራስገዝነት ወይም በሌላ ስሙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተቋማዊ ነጻነት ማለት ተቋማቱ የአስተዳደራዊ፤ የአካዳሚክ፤ የምርመር፤ የሰው ሃብት አስተዳደር፤ የፋይናንስ ጉዳዮቻቸውን ነጻነት ኖሯቸው በዛው ልክ ደግሞ ተጠያቂነትም እንዳለባቸው አውቀው የሚተገብሩበት ስርዓት ነው።

አንድ ተቋም ተቋማዊ ነጻነት ተጎናጽፏል ወይም ራስ ገዝ ሆኗል ብለን ስናስብ በዋናነት ከአካዳሚና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ነጻነት ኖሯቸው ይህንንም ከተጠያቂነት ጋር በመያዝ የተሻለና ውጤታማ ስራን እንዲሰሩ የማስቻል ጅምር ነው።

አስተዳደራዊ ነጻነቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ የራሳቸውን አደረጃጀት እና መዋቅር የመዘርጋት ስልጣን ይሰጣቸዋል፤ በዚህ መሰረት ዩኒቨርሲቲዎቹ ከፍተኛ አመራሮቻቸውን ጨምሮ በመዋቅራቸው ውስጥ የሚያስፈልጓቸውን የአመራር እና የአስተዳደር አካላትን በራሳቸው መመደብ እንዲችሉ መንገድ ይከፍትላቸዋል።

በሌላ በኩልም ፋይናንሻል አቅማቸውን በጀታቸውን በአግባቡ የመጠቀም እድል ይፈጥርላቸዋል። ዩኒቨርሲቲዎች አመራሮችን የመሻር፤ የመሾም፤ ሀብት የመፍጠር፤ የውስጥ መመሪያዎችንና አስተዳደራዊ ስርዓቶችን የመዘርጋት ነጻነት ይኖራቸዋል። ከሁሉም በላይ ደግሞ የሰው ኃብታቸውን በአግባቡ ከመጠቀም ብሎም ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎች የመቅጠርና ስርዓቱን እንዲሁም ደመወዝና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን የመወሰን አቅም ይፈጥርላቸዋል። በተለይም ለዩኒቨርሲቲው ብሎም ለአገር ይጠቅማል፤ ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎችን ይሰራል ብለው ያመኑበትን ባለሙያ በድርድር እስከመቅጠር ድረስ የሚደርስ ነጻነት እንዲኖራቸው ያስችላቸዋል።

ከተማሪዎች ቅበላ ጀምሮ አስመርቆ እስከማውጣት ድረስ ያለው ሂደት ጤናማ ብሎም በእውቀት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ለማድረግ ተማሪዎችን አወዳድሮ እስከመቀበል ድረስ ያለውን ውሳኔ የማንንም ድጋፍ ሳይጠይቁ የመወሰን አቅም ይፈጥርላቸዋል።

ተቋማት ራስ ገዝ በሆኑ ቁጥር ለሚያስተምሯቸው ተማሪዎች ምን ዓይነት የትምህርት ስርዓት መከተል እንዳለባቸው ገበያውም በሚፈልገው ልክ የመወሰን ከዛም አልፎ የሚያስትምሩበትን ቋንቋም እስከመወሰን ድረስ እድል ይኖራቸዋል።

በነገራችን ላይ ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ የማድረግ ጅምሩ ቀደም ባለው ጊዜ በእኛም አገር የነበረ ነው። አሁን ባለንበት ዘመን በጣም ትልልቅና ብዙ የምርምር የቴክኖሎጂ ሽግግርን እያደረጉ ያሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ የሆኑ ናቸው። ምክንያቱ ደግሞ የትምህርት ስራ በራሱ ከፍ ያለ ነጻነትን የሚፈልግ ነው። ለምሳሌ ምርምር ሲካሄድ የተለያዩ ግብዓቶች ያስፈልጋሉ፤ ግብዓቶቹ ደግሞ በአስቸኳይ የግዢ ስርዓት መፈጸም ሊኖርባቸው ይችላል። ነገር ግን አሁን ያለው የፋይናንስና የግዢ ስርዓት ይህንን የሚፈቅድ አይደለም ።

በመሆኑም እነዚህ ችግሮች ተቀርፈው ዩኒቨርሲቲዎች ችግር ፈቺ ሊሆኑ የሚችሉት ራሳቸውን ማስተዳደር ሲችሉ ብቻነው። ዛሬ ላይ ቆመን በዓለም አቀፍ ደረጃ ልንጠራቸው የምንችላቸው ስመ ጥር ዩኒቨርሲቲዎችም ራስ ገዝ ናቸው። የውጤታማነታቸው ምስጢርም ይኸው ነው።

ለምሳሌ እነ ሀርቫርድን ጨምሮ የስቴት ዩኒቨርሲቲዎች የመንግስት ናቸው። ግን ደግሞ ራስ ገዝ አስተዳደርን ስለሚከተሉ በዩኒቨርሲቲዎች ደረጃ ላይ ሁሌም ከላይ የሚታዩ ናቸው። በመሆኑም ራስ ገዝ ማድረግ የዓለም ተሞክሮም እንደሚያሳየው በትምህርት ጥራት፣ በምርምር ስራዎች ላይ የራሱ የሆነ አወንታዊ ሚና እንዳለው ነው።

በኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት አስርተ ዓመታት በትምህርት ተደራሽነት ላይ ከፍ ያለ ስራ ተሰርቷል፤ አሁን በመንግስት ደረጃ 51 እና በግል 5 ዩኒቨርስቲዎች አሉ። እንዲሁም 325 አካባቢ የግል ኮሌጆችም ይገኛሉ። በመሆኑም ይህ ተደራሽነት ጥሩ ቢሆንም የዛሬ አምስት ዓመት የትምህርት ፍኖተ ካርታ ጥናት ሲካሄድ የተገኘው ውጤት የሚያሳየው ተደራሽነቱ አበረታች ቢሆንም የትምህርት ጥራቱ ላይ ግን ችግር እንዳለ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘም ምን መሰራት አለበት ለሚለው ፍኖተ ካርታው ካስቀመጠው ምክረ ሃሳብ አንዱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ራስ ገዝ ማድረግ ነው።

በመሆኑም የዚህን የጥናት ውጤት በመያዝ ዩኒቨርሲቲዎቹ ራስ ገዝ የሚሆኑበትን አሰራር የማመቻቸት ሂደት ነው የተጀመረው። ራስ ገዝ የመሆን ጉዳይም ከጥናቱ ጋር አብሮ የመጣ ጉዳይ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።

የዓለም ተሞክሮ የሚያሳየንም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ነጻነት ለአካዳሚክ ውጤታማነት ጉልህ ሚና እንዳለው ነው። ሌላውና የሚገርመው ነገር ራስ ገዝ በአገራችን ዛሬ የተጀመረ አሰራር አይደለም፤ በንጉሱ ጊዜ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩኒቨርሲቲ ሲቋቋም ራስ ገዝ ሆኖ ነው የተቋቋመው፤ በዛን ወቅት የነበረውን ተሞክሮም መለስ ብለን ስናየው በትምህርት ጥራት ላይ የነበረው ሚና ቀላል የሚባል አልነበረም፤ ሆኖም ከመንግስት ለውጥ ጋር በተያያዘ በዛ መልኩ መቀጠል ባለመቻሉ አሁን የደረስንበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። በጠቅላላው ግን ራስ ገዝ አንዱ የትምህርት ሚኒስቴር የሪፎርም ስራ አካል ነው።

ከራስ ገዝነት በተጓዳኝ ጥናቱን መሰረት በማድረግ ዩኒቨርሲቲዎችን በሚና የመከፋፈል ስራ ይሰራል። አሁን ላይ ዩኒቨርሲቲዎቻችን በሙሉ የሚሰጡት ትምህርትም ሆነ ደረጃቸው ተመሳሳይ ነው ነገር ግን አንድ ዓይነት መሆን አይጠበቅባቸውም። ስለዚህ ዩኒቨርሲቲዎቹ በትኩረትና በተልዕኮ ሊለያዩ ይገባል ይህም ሲባል የተወሰኑት ምርምር ሌሎቹ አፕላይድ ሳይንስ የተቀሩት ሕክምና ከዚህ የሚተርፉት ደግሞ የመማር ማስተማር ስራውን ከምርምሩ ጋር አዋህደው ይቀጥሉ ተብሎ ዩኒቨርሲቲዎቹን የመለየት እንዲሁም ካላቸው አካባቢያዊ ሁኔታና ጸጋ እንዲሁም ከኋላ ታሪካቸው በመነሳት ትኩረት እንዲያገኙ ሆኗል። በዚህ መነሻነትም ከዚህ በኋላ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ተመሳሳይ ስራን አይሰሩም።

አዲስ ዘመን፦ ትምህርት ሚኒስቴር በተለይም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ የጀመረው የሪፎረም ስራ ምን ዓይነት ውጤቶች የሚጠበቁበት ነው?

ዶክተር ሳሙኤል ፦ ትምህርት ሚኒስቴር በተለይም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ የጀመረው ሪፎርም በደንብ ተጠንቶ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብም ባለቤት ሆኖበት የተሰራ ነው። በተለይም አሁን ላይ የሪፎርም ስራውን ጨርሶ ራስ ገዝ የሆነው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንደ አነሳሱ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ እስከ መጨረሻው ተሳትፎውን ካደረገበት ተቋሙ ብቁ ሆኖ የማይወጣበት አንዳችም ምክንያት አይታየኝም።

ይህም ማለት ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም የነበረውንም ተሞክሮ ቀምሮ ሪፎርሙንና ራስገዝ የመሆን እድሉን ተጠቅሞ ብቁ ተማሪዎችን ማፍራት የሚችል፣ የተሻሉና የአገርን የህዝብን ችግር ሊፈቱ የሚችሉ ምርምሮችን ማካሄድ የሚችል፣ ለአገር መፍትሔ ማምጣት የሚችሉ ሀሳቦች የሚፈልቁበት ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ ለአገራችን የዲፕሎማሲ አቅም ሊሆን የሚችል ተቋም ይሆናል። በሌላ በኩልም በሀብት አጠቃቀም ማመንጨትና አያያዝ በኩልም ለሌሎች መሰል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አርዓያ መሆን የሚችል ተቋም እንዲሆን ያስችለዋል። ሪፎርሙም በዋናነት የሚያሳካው ይህንን ነው።

ብቁ ተቋማት አገር ያስቀጥላሉ እንዲሁም የወደፊቱን ጊዜ መሸከም ይችላሉ፤ በመሆኑም ትምህርት ሚኒስቴር በዩኒቨርሲቲው ላይ ሲሰራ የቆየውም ሪፎርም ይህንን የሚያመጣ ነው።

አዲስ ዘመን፦ አንድ ተቋም ተቋማዊ ነጻነት ተጎናጽፏል ወይም ራስ ገዝ ሆኗል ብለን ስናስብ በዋናነት ከአካዳሚና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ነጻነት ኖረው ማለት እንደሆነ እንረዳለን አሁን ደግሞ ቻንስለሩን ጨምሮ እርሶም ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት የሆኑት በሹመት ነውና እነዚህ ሀሳቦች አይጣረሱም?

ዶክተር ሳሙኤል፦ ዩኒቨርሲቲዎቹ የህዝብ ናቸው፤ ሕዝብ ደግሞ እንዲያስተዳድረው የወከለው መንግስት አለ፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ ዩኒቨርሲቲዎቹ እንዴት መመራት አለባቸው የሚለውን የሚገዛ የወጣ ሕግም አለ።

በሌላ በኩል ደግሞ ዩኒቨርሲቲው ራስገዝ ሲሆን ቻንስለር ይኖረዋል ይላል ሕጉ በሌሎች አገራት ያለው ተሞክሮ እንደውም ዩኒቨርሲቲው ያለበት ከተማ ከንቲባ ወይም የክልሉ ገዥ ነው ቻንስለር የሚሆነው፤ እኛም የሄድነው በዚሁ መሰረት ነው። ዞሮ ዞሮ ራስ ገዝ ሆነው በራሳቸው የሚንቀሳቀሱ ዩኒቨርሲቲዎች በየትኛውም ዓለም የሚሰራው በዚህ መሰረት ነው።

ተጠባባቂ ፕሬዚዳንትነትንም በተመለከተ መጀመሪያም ቢሆን ተጠባባቂ ያስፈለገበትም ሆነ፤ ለሆነ አካል ተጠባባቂነት የተሰጠበትም የራሱ ምክንያቶች አሉት፤ ሪፎርሙ ሁለት ዓመቱን ያሳለፈው እንደ ሽግግር ጊዜ ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ ራስ ገዝ ሆኖ ለተቋቋመው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትም ሆነ ቻንስለር መሾም አስፈላጊ በመሆኑ ብዙ አውጥተን ሰዎችን ሾመናል። ሹመቱም ከውጭ አዲስ ሰው ቢመጣ ይሻላል አይሻልም፤ ያሉት ሰዎች ቢቀጥሉ ይሻላል ወይስ ስራውን በቅርበት እንደ እኔ ሲከታተሉ የነበሩ ሰዎችን ቢመደቡ ይሻላል የሚለው ሁሉ ታይቶ ነው የተወሰነው።

ሪፎርሙን መሬት አስነክቶ ራስ ገዙ የመፍጠር ሁኔታ መስመር ይዞ በውድድር ፕሬዚዳንቶችና ምክትል ፕሬዚዳንቶች ተመርጠው በአዲሱ መዋቅር ዩኒቨርሲቲው ስራውን እንዲቀጥል ያደርጋል አያደርግም የሚለው ሁሉ ታይቶ ነው ወደ ውሳኔ የተገባው።

እኔ በበኩሌ ሪፎርሙ እንዴት መሬት መያዝ እንዳለበት የሚሰራውን ስራና የሽግግሩን ጊዜ እንድመራ እንጂ በቋሚነት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት እንድሆን አይደለም። ይህንን ስናደርግ ዩኒቨርሲቲው ራስገዝነቱን የሚሸራርፍ ነገር በተለየ ሁኔታ እንዲታይ የሚያደርገውን ነገር ለማስቀረት ካለን ፍላጎት የተነሳ ነው ይህንን ያደረግነው።

በዚህ መልኩ ከሄድን በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ሪፎርሙ የሚፈልጋቸውን ርምጃዎች (ሂደቶች ) ሄደን አዲስ አመራር አስመርጠን ዩኒቨርሲቲው ራሱን የቻለ ገለልተኛ ራስገዝ ዩኒቨርሲቲ አስደርገን ኃላፊነታችንን እንጨርሳለን።

አዲስ ዘመን፦ ተማሪዎች ተወዳድረውና ከፍለው ይማሩ መባሉ የትምህርት አቅሙ ቢኖራቸውም ከፍለው ለመማር ግን አቅም የሌላቸውን የሕብረተሰብ ክፍሎች ይጎዳል እንደውም ፍትሃዊነትም ላይ ከፍ ያለ ችግር ያስከትላል እየተባለ ነውና እርስዎ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?

ዶክተር ሳሙኤል፦ ይህ ነገሩን በትክክል ከማስረዳትና ከመረዳት ማነስ የመጣ ውዥንብር አድርጌ ነው የምወስደው:: ነገር ግን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም ይሁን ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች በአጠቃላይ ያለፈን ተማሪ በሙሉ ሲቀበሉ አልኖሩም:: ሁሌም ቢሆን ተማሪዎች በየዩኒቨርሲቲው የሚመደቡት በውድድር ነው። መንግስት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስገዝ ሲያደርግ ደግሞ አሰራሩ ሁለት መልክ ይኖረዋል፤ በዚህም መንግስት በጀት መድቦላቸው የሚማሩ ተማሪዎች አሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ዩኒቨርሲቲው የሚጠይቀውን ክፍያ አሟልተው የሚማሩ ይኖራሉ፤ ተማሪዎችን ከትምህርት ሚኒስቴር (መንግስት) አልቀበልም ማለት በጀትም አልፈልግም እንደማለት ነው፤ በመሆኑም በአንድ በኩል ለመደበኛ ስራ ማስኬጂያችን በጀት እየጠየቅን በሌላ ጎን ደግሞ ተማሪ አትመድቡብን ማለት አንችልም።

ነገር ግን ይህም ቢሆን ዩኒቨርሲቲው ራስገዝ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በተሰጠው ነጻነት መሰረት የመክፈል አቅም ያላቸውን ተማሪዎች አወዳድሮ መቀበል ይችላል። በያዝነው 2016 ዓ.ም ተማሪዎች ከትምህርት ሚኒስቴር (ከመንግስት) ይመደባሉ፤ ምናልባትም አሁን በጀመርነው ፍጥነት ስራው በትክክል የሚሄድ ከሆነ በሁለተኛው መንፈቅ ዓመት ከፍለው መማር የሚችሉ የተወሰኑ ተማሪዎችን በጥቂት ፕሮግራሞች ላይ ለመቀበል እንሞክራለን።

እዚህ ላይ ሁሉም ሊያውቀው የሚገባው ነገር በተያዘው ዓመት መንግስት በለቀቀልን በጀት ልክ የሚመደቡልንን ተማሪዎች እንደቀደመው ጊዜ ተቀብለን እናስተምራለን።

ወደፊት ግን የአገሪቱን የማለፊያ ነጥብ ያመጡትን ተማሪዎች እናወዳድራለን፤ ተወዳድረው ካለፉት ውስጥ ደግሞ መክፈል የማይችሉትን መንግስት እንዲከፍልላቸው የምንለይበት አሰራርም እንዘረጋለን። ነገር ግን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን አይቀበልም የሚለው ነገር የማስረዳትና የመረዳት ችግር እንጂ እንዲህ የሚባል አሰራር የለም። ራስገዝ በሚል እሳቤ ፍትሃዊነትንም ማዛባት አይቻልም። የመንግስት ተቋም መሆኑም አይቀርም። እዚህ ላይ ግን የመንግስት ተቋም ሆኖ ጠንካራ ተወዳዳሪ ብቁ ባለሙያዎችን የሚያስመርቅ ተቋም እንዲሆን እንፈልጋለንም፤ እንሰራለንም። የተማሪዎችን አቀባበልና ወጪ አሸፋፈን በተመለከተም ከምንፈልገው ጉዳይ ውስጥ አንዲት ነጠላ ጉዳይ ከመሆኗም በላይ የሪፎርሙ ስራ ወይም የሚጠበቀውም ውጤት ይኸው ብቻ አይደለም።

አዲስ ዘመን፦ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራስገዝ ከመሆኑ ጋር በተገናኘ ከሌሎች ዓለም አቀፍ ራስገዝ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የሚኖረው ግንኙነት ምን ዓይነት መልክ እንዲኖረው ነው የሚፈለገው?

ዶክተር ሳሙኤል፦ በነባሩም የከፍተኛ ትምህርት አዋጅ የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከውጭ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የመስራት ነጻነት አላቸው። ይህ ራስገዝነታቸው የሚሰጣቸው ሳይሆን ተፈጥሯዊ የአሰራር ሂደታቸው ነው። በዓለም ዙሪያ ካሉ ተመሳሳይ የትምህርት ተቋማት ጋር የመግባቢያ ሰነድ የመፈራረም፤ ውል የመዋዋል፤ በጋራ ተማሪ የማስተማርና ምርምሮችን የመስራት በጋራ መምህራንን የማልማት ጉዳይ ላይ ይሰራሉ።

ይህ የቆየው የአሰራር ሂደታቸው ደግሞ ራስገዝ በመሆን በሚጎናጸፉት ነጻነት ይበልጥ ይጠናከራል እንጂ እንደ አዲስ የሚሰራ ወይም የሚኬድበት ጉዳይ አይሆንም። ጠንካራ ዓለም አቀፍ ግንኙነት እንዲኖረን ደግሞ እስከ አሁን ያልሰራንበት ከእኛ የጎደለ ነገር ካለ ፈትሸን የምናጠናክረው ይሆናል።

አዲስ ዘመን፦ ዪኒቨርሲቲው ራስገዝ በመሆኑ በተለይም የተማረ የሰው ኃይል ፍልሰትን ሊያስቀረው፤ ማስቀረት እንኳን ባይችል ይቀንሰዋል ብለው ያስባሉ?

ዶክተር ሳሙኤል፦ ሰዎች ተምረው በእውቀታቸው አገራቸውን ማገልገል ሲገባቸው ለምን አገር ጥለው ይሄዳሉ የሚለው ነገር ኢኮኖሚያዊ አልያም ፖለቲካዊ ችግር ብቻ አድርገን መውሰድ ይከብዳል፤ በርካታ ጉዳዮችም አሉ፤ ዋናው ግን የግል ውሳኔ ነው። እንደ እኛ ግን በዓለም ዙሪያ ያሉ ኢትዮጵያውያን ለሳምንትም ለአንድ መንፈቅም መጥተው ዜጎቻቸውን በአንድ ወይም በሌላ መንገድ የተማሩባቸውን የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎችን ቢደግፉ ደስታችን ነው። ለዚህ ሊያበቁ የሚችሉ በእኛ በኩል መሰራት ያለባቸውን ስራዎች እንሰራለን።

በሌላ በኩል ደግሞ እጃችን ላይ ያሉ ምሁራኖቻችን የተሻለና ምቹ የስራ አካባቢ እንዲፈጠርላቸው በዚህ ሪፎርም ውስጥ ሆነን እንሰራለን። የስራ ቦታቸው፤ የሚያገኙት ክፍያ፤ በየጊዜው ሊኖራቸው የሚገባው የስራ እድገት፤ ሊያገኙት የሚገባውን ያህል እውቅና ከሰጠናቸውና እነዚህን ነገሮች ካስተካከልንላቸው በአገራቸው ላይ ለመኖር፤ ለመስራት፤ አገራቸውንም ራሳቸውንም ለመለወጥ ሌላ ምክንያት አይፈልጉም ብዬ አምናለሁ፤ በመሆኑም አሁን የምንከተለው አቅጣጫ እጃችን ላይ ያሉትን ማቆየት ነው።

በዓለም ዙሪያ ያሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሆኑ ምሁራንን ደግሞ ወደአገራቸው ወደመሰረታቸው ተመልሰው አገር እንዲያገለግሉ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲንም እንዲያገለግሉ በዛ ውስጥ ደግሞ ለአገርና ለህዝብ አስተዋጽዖ እንዲያደርጉ የበኩላችንን እናደርጋለን።

አዲስ ዘመን፦ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንደ ማሳያም የራስ ገዝነት ጉዞውን አንድ ብሎ ጀምሯልና ይህ አካሄድ እንደው ከጊዜ ወደጊዜ እየወደቀ መጣ ለሚባለው የትምህርት ጥራት የሚኖረው አስተዋጽኦ እንዴት ይገለጻል?

ዶክተር ሳሙኤል፦ የተማሪ ቅበላ ስርዓቱ በውድድርና ጠንካራ ይሆናል፤ የመግቢያ መስፈርቱም ብቃትን መሰረት ያደረገ ይሆናል። ከአመራር ጀምሮ እስከ ተማሪዎች ድረስም ብቃት ይታያል ማለት ነው። ማንኛውም መምህር በሂደት ራሱን ካላበቃና ካላሳደገ ዘላለሙን መምህር ሆኖ የሚቆይበት እድል የጠበበ ነው የሚሆነው።

በሁለትና በሶስት ዓመት ውለታው ሲታደስ ብቃትን መሰረት አድርጎ ከመሆኑም በላይ ይህ መምህር ባለፈው ኮንትራቱ ከታደሰለት በኋላ በመማር ማስተማር ሂደቱ ላይ ምን አስተዋጽዖ አበርክቷል?፤ ምርምር ላይ የነበረው ስራ ምን ይመስላል? ምን ያህል ጥናቶችን ለህትመት አብቅቷል ? ሀብት በማምጣት በኩልስ ሚናው ምን ነበር? ለማህበረሰቡ የሚጠቅም ነገር ላይ ምን አድርጓል? ተቋምን በመደገፍና በመምራት በኩል አስተዋጽዖው እንዴት ይለካል ? ውለታውን ማደስ ይገባል አይገባም የሚል ታይቶ የሚወሰን ይሆናል።

ይህ አሰራር ደግሞ ሌላው ዓለምም የሚጠቀምበት ነው። ወደእኛ አገርም አምጥተን ከነባራዊ ሁኔታዎቻችን አንጻር ቃኝተነው የምንተገብረው ይሆናል።

ውድድር ሲመጣም ብቃትን መሰረት ያደርጋል። ብቃት የሌላቸውንም ቀስ እያልን ከስርዓቱ የምናስወጣበትና በብቃትና በፍትህ ላይ የተመሰረተ የእውቅና ስርዓት እንዲዘረጋ ደግሞ እናደርጋለን።

አዲስ ዘመን፦ እንደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በትምህርት ክፍሎችስ ላይ ለውጦች ይኖሩ ይሆን?

ዶክተር ሳሙኤል፦ እስከ አሁን በዚህ ዙሪያ የሰራነው ስራም የለም፤ ውይይትም አልጀመርንም። ወደፊት ግን በዝርዝር ፈትሸነው ለውጥ የሚኖር ከሆነ ለውጡም ለዩኒቨርሲቲው ጠቃሚ መስሎ ከታየን እንሄድበታለን። ነገር ግን ለውጥ መጣ ለማስባል ብቻ የሆኑ የትምህርት ክፍሎችን በማጠፍና በመዝጋት አላምንም።

አዲስ ዘመን፦ ስለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።

ዶክተር ሳሙኤል፦ እኔም አመሰግናለሁ

 እፀገነት አክሊሉ

አዲስ ዘመን  መስከረም 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You