መድረክ ላይ የሚታዩና የሚሰሙ ሰዎች አሉ። መልክ ያላቸው የአይን ምግቦች አሉ፤ ተናጋሪ የሆኑ የጆሮ ምግቦች አሉ። ሁለቱንም ያሟሉ ደግሞ ሊኖሩ ይችላሉ። እኔ ግን መሰማት ነው ዕድሌ መሰለኝ፤ ወይም እዚህ አካባቢ ነው እንጀራዬ።
ጥሩ ሕዝብ ስላለ ነው እንጂ ጥሩ ተናጋሪ ስለሆንን አይደለም። ለስላሳ ህዝብ ነው፤ የዋህ ህዝብ ነው፤ ማንም እንደ ህዳር አህያ ሊጭነው ይችላል።
የህዳር አህያ ብዙዎቻችሁ ስለማታ ውቁት ላብራራው። በገጠር አካባቢ የጭነት መሳሪያ አህያ ነው። በነገራችን ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎቻችን አዲስ አበባ ቁጭ ብለው ውስኪ እየጠጡ የሚደራደሩት በአህያ ለሚጭን ገበሬ ነው። እነርሱ የቱርክ ጫማ አድርገው ስብሰባ ተቀምጠው የሚወራጩት በባዶ እግሩ ለሚሄድ ገበሬ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲ መሪ ከመሆን በላይ አሳፋሪ ነገር የለም።
አንድ ደስ ያለኝን ነገር ልናገር፤ ም/ርዕስ መስተዳድሩ አቶ ሙስጠፌ ይመጣሉ ተብሎ ነበር። አንዱ ደስ ያለኝ ይመጣሉ በመባሉ ነው፤ ሁለተኛው ግን አሁን ባለመኖራቸው ነው፤ ምክንያቱም እንደልባችን እናወራለን። እስኪ እንዲህ አይነት ቦታ እንኳን እንሳቅ!
የህዳር አህያን ላብራራና ወደ ሀሳቤ ልግባ።
ህዳር፣ ታህሳስና ጥር ማለት በገጠር የአዝመራ ወቅት ነው። እና በዚህ ወቅት እኔ አህያ ቢኖረኝ ማንም አይጠይቀኝም። በሌላ ጊዜ ‹‹እባክህ አህያህን›› ተብሎ ተለምኖ ነው። በህዳር ግን ማህበረሰቡ ተስማምቶ ያገኘው ሰው መጫን ይችላል። እናም እባካችሁ እንደ ህዳር አህያ ማንም ዝም ብሎ አይጫነን።
ክቡር ም/ርዕሰ መስተዳድሩ እንዲህ አይነት መድረክ ላይ እመጣለሁ ማለታቸው ደስ ይላል። አንደኛ ባለሥልጣናት እንደኛው ከሰው መሃል ሲገኙና ሲናገሩ ደስ ይላል። ሁለተኛ ደግሞ ለምርጫ ቅስቀሳ ያገለግላል። ብሩክ የሺጥላ ፕሮግራም ላይ አንድ ሚኒስትር ተገኝተው ተናግሬ ነበር። ነገ ‹‹ማናችሁ›› ከምንላቸው እንዲህ እየመጡ አብረውን ሻይ ቢጠጡ። ስናለቅስም ስንስቅም ቢያዩን። የምናስተላልፋቸውን መልዕክቶችም ቢሰሙ።
የገጠር እናቶች የልጆቻቸው አንገት ላይ የሚያስሩት ክታብ የሚባል ነገር አለ፤ ከውስጡ ያለው የእግዚአብሔር ስም ነው። እኔ ደግሞ የምለው እንደዚህ አይነት የመድረክ ንግግሮች በክታብ መልክ ተዘጋጅተው የፖለቲከኞች አንገት ላይ ቢታሰርላቸው።
አገሪቱን ምጣድ፣ ህዝቡን እንጨት ስሜታቸውን እሳት አድርገው ዳቦ ሊጋግሩ፤ ያለፈውን ቂምና በቀል እርሾ፣ ጊዜያዊ
ፍላጎታቸውን ዱቄት አድርገው እያቦኩ ያሉ ሰዎች አሉ። ምጣዱን አንሰብርም አገራችን ናት፣ ህዝቡን አንማግድም ንብረታችን ነው፤ እኛ ግን እባካችሁ እኛ ላይ አትጋግሩ ማለት እንችላለን። እንድንረዳቸው ከተፈ ለገም ከልጆቻችን አፍ እየነጠቅን ገንዘብ ብናዋጣላቸው ይሻለናል። እነዚህን ሰዎች ማበልጸግ ካለብን፣ መርዳት ካለብን
ሰው ከምንማግድ ገንዘብ ብናዋጣላቸው ይሻለናል።
የፖለቲካ ፓርቲዎቻችን 108 ደርሰዋል፤ ታላቋ አሜሪካ ግዙፍ ፓርቲዎች ሁለት ብቻ ናቸው ያሏት። አሜሪካን አገር 107 እና 108 ምናልባትም የመኪና ፋብሪካ ነው ሊኖር የሚችለው። እነዚህን 108 ፓርቲዎች እንዲያው ፈጣሪ በሚጨፈልቅበት ጨፍልቆ ቢያዋህድልን። እነርሱ ሊዋሃዱ አይችሉም፤ ምክንያቱም የፖ ለቲካ ፓርቲን በማቋቋም ኑሮን መደጎም ይቻላል። ስለዚህ ይህን ፓርቲ አፍርስ ማለት የሚበላበትን ትሪ እንደ መንጠቅ ማለት ነው። እኔ ታዲያ ምን አሰብኩ! እንደዚህ አይነት ሰዎችን ማህበረሰቡ የመረዳጃ ዕድር ቢኖረው።
መርስ ኤኃዘን ወልደቂርቆስ የ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መባቻ የተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ እንዳሰፈሩት በእቴጌ ጣይቱና በእነ ቢትወደድ ተሰማ በእነ ፊትአውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ መካከል መገፋፋት ነበር። ይሄ እንግዲህ የተለመደ ነው፤ ሥልጣን እስካለ ድረስ ጠብ አለ፤ ጠብ እስካለ ድረስም መገፋፋት አለ። የሰው ልጅ ለሥልጣን ለገንዘብ ይገፋፋል። እንዲያውም በዕ ውቀቱ ሥዩም ከአሜን ባሻገር መጽሐፉ ላይ የጻፈው ሦስቱ ኤልሻዳዮች የሚል ጽሑፍ አለ። ሥልጣን፣ ገንዘብ እና ጠመንጃ ከተገናኙ በጣም አደገኛ ነው። በነገራችን ላይ ብዙዎቻችን ጥሩ ሰው የመሰልነው ሥልጣን ስላጣን ነው። ብዙ ሰው ሀብት ሲያገኝ ፀባዩ ይቀይራል ይባላል፤ እየተቀየረ አይደለም። በፊት ሀብት በማጣቱ የጠወለገ፣ የተቀበረ ስሜት አለ፤ ክፋቱ አልታወቀም ነበር። በኋላ ሲታወቅ ግን እገሌ ክፉ ሰው ነው ይባላል፤ አዲስ ክፋት ፈጥሮ አይደለም፤ የነበረው አቅም መገለጫ ስላገኘ ነው።
ትዕንቢት ሚኪያል ምዕራፍ ሁለት ላይ ‹‹ሌሊት በመኝታቸው ላይ ክፋት ያስባሉ›› ይላል። ኃይል በእጃቸው ከሆነ ሲነጋ ይፈጽሙታል ይላል። አንዳንድ ጊዜ አልጋችን ላይ ተኝተን ‹‹የእገሌ ፎቅ የእኔ ቢሆን›› እንላለን። ጠዋት ስንነሳ ሥልጣን
ቢኖረን ያንን ፎቅ እንወስደዋለን። ደግነቱ ግን ብዙዎቻችን ምኞት እንጂ ሥልጣን የለንም።
እና እዚያ መርስኤኃዘን ወልደቂርቆስ መጽሐፍ ላይ እንደሚለው እቴጌ ጣይቱን በቤተ መንግሥት ውስጥ ያሉ ሰዎች ሰድበዋቸው ነበር አሉ። ‹‹ስድቡን ግን አልጽፈውም›› ነው ያሉት መርስኤኃዘን ወልደቂርቆስ። እብድና ጤነኛ የሚለየው ያሰበውን ሁሉ በመናገርና አለመናገር ነው፤ የሚጠቅምና የሚጎዳን በመለየት ነው። ለምሳሌ እኔና አንድ የአዕምሮ ህመምተኛ አንድ ቤት ብንሄድና ሁለታችንም ርቦን ጠረጴዛ ላይ የተቀመጠ ዳቦ ብናገኝ፤ እኔ ‹‹እነዚህ ሰዎች ይህን ዳቦ ቆርሰው አይሰጡንም እንዴ! ምን ስግብግቦች ናቸው!›› እያልኩ አስባለሁ። የአዕምሮ ህመምተኛው ግን ዳቦውን ቆርሶ፤ የእኔንም የውስጥ እብደት አጋልጦ እኔን ጭምር ያበላኛል። በውስጣችን ግን ሁላችንም እብዶች ነን።
ያሰብነውን ሁሉ ባንናገር፤ ያሰብነውን ሁሉ ባንጽፈው። በተለይ በተለይ በተለይ መገናኛ ብዙኃን ላይ የምትሰሩ እንዲያው በየፈጣሪያችሁ ስም ያሰባችሁትን ሁሉ አትናገሩ! ቡና ተፈልቶ የሚወራውን መገናኛ ብዙኃን ላይ ያወሩታል። ያሰብነውን ሁሉ ብናወራ እኮ ተፋጅተን ነበር። ስንት ነገር እያመረን ቀርቷል።
የዚች አገር ሰላም እንዲቀጥል ከተፈለገ፤ በዶክተር ዐብይ፣ በአቶ ለማ፣ በዶክተር ደብረጽዮን ወይም በዶክተር አምባቸው እጅ አይመስለኝም። እያንገሸገሸንም ቢሆን መጠጣት ያለብን ሀቅ የዚች አገር ሰላም በእያንዳንዳችን ምላስ እና እጅ ላይ ነው። ፌስቡክ ላይ የምትጽፉ ሰዎች፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአማራው መብት፣ የኦሮሞው መብት፣ የትግሬው መብት… ብለው የሚናገሩ ሰዎች አሉ፤ ‹‹ወክለናቸዋል›› የሚል ሰው ግን እስካሁን አልመጣም። እኔ አሁን በብሄሬ ወክየሃለሁ ያልኩት የፌስቡክ ጸሐፊ የለኝም። እያሰብን የምንተወው ነገር ይኑር።
አንገረ ፈላስፋ የሚል አንድ በግዕዝ የተጻፈ መጽሐፍ አለ። እዚያ መጽሐፍ ላይ ‹‹ክፉ ነገር ብትሰማና ብታስብ እዚያው ውስጥ ተወውና ፈርሶ በስብሶ እንደ ሽንት ከሰውነትህ ተኖ ይወጣል›› ይላል። ያሰብነውን ሁሉ ካወራን፣ ያየነውን ሁሉ ከበላን እናብዳለን።
ሌላው መናገር እንደምንፈልግ ሁሉ መስማትም እንልመድ፤ ትዳርና ሥልጣን የሚታጣው ምላስ እየረዘመ ጆሮ እየጠበበ ሲመጣ ነው። አባወራ እንወያይ ብሎ ከሚስቱ ጋር ይቀመጣል። ይናገር ይናገር እና ‹‹ጨርሻለሁ ደህና ዋይ›› ይላል።
አንድ መሥሪያ ቤት ‹‹ከሰረ›› የሚባለው ወጪና ገቢው ካልተመጣጠነ ነው። አንድ ሰው ጥቂት እየሰማ ብዙ ከተናገረ እንደ ኢትዮጵያ የወቺ ንግድ ነው የሚሆነው። የአፋችንና የጆሯችን ወጪ ይመጣጠን።
አዲስ ዘመን ግንቦት 10/2011